Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በአዲስ አበባ የነዳጅ ማደያዎችን ለማቃጠል ተንቀሳቅሰዋል የተባሉ 9 ተጠርጣሪዎች ክስ ተመሰረተባቸው

0 547

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች ላይ የሚገኙ ከሰባት በላይ የነዳጅ ማደያዎችን ለማቃጠል ተንቀሳቅሰዋል የተባሉ ዘጠኝ ተጠርጣሪዎች ክስ ተመሰረተባቸው።ተጠርጣሪዎቹ በውጪ ከሚገኙ የሽብር ድርጅቶች በተለያዩ ማህበራዊ መገናኛዎች ተልዕኮ በመውሰድ ነው ድርጊቱን ሊፈፅሙ የነበረው ብሏል ጠቅላይ አቃቤ ህግ በክሱ።

ተጠርጣሪዎቹ 1ኛ ክንፉ መሀመድ፣ 2ኛ መሀመድ ካሳ፣ 3ኛ ደረጀ አያሌው እና ሌሎች ስድስት ግለሰቦችን ጨምሮ ዘጠኝ ተጠርጣሪዎች ናቸው ክስ የተመሰረተባቸው።በክሱ እንደተጠቀሰው ተከሳሾቹ በአዲስ አበባ መካኒስ ጀርመን አደባባይ፣ ጭላሎ ሆቴል አካባቢ፣ ቦሌ አርፖርት አካባቢ፣ ቃሊቲ እና አየር ጤና አካባቢዎች የሚገኙ የነዳጅ ማደያዎችን ነው ለማቃጠል ተንቀሳቅሰዋል የተባለው።

እነዚህ ተጠርጣሪዎች ማደያዎችን ለማቃጠል የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት ማድረጋቸው የተጠቀሰ ሲሆን፥ 1ኛ ተከሳሽ ቀደም ብሎ በውጭ በሚገኝ የሽብር ቡድን በአባልነት ተመልምሎ የሽብር ተልዕኮ የሚፈፅሙ ሌሎች አባላትን እንዲመለምል መደረጉ በክሱ ተብራርቷል።

ከተመለመለ በኋላም በውጭ ሀገር ከሚገኙት የሽብር ቡድኑ አመራሮች ጋር በዋትስአፕ እና ሌሎች መሰል ማህበራዊ መገናኛዎች ተልዕኮዎችን በተደራጀ መንገድ ሲቀበል እንደነበር ነው ክሱ የሚያስረዳው።

ተከሳሹ ሌሎች በክሱ የተጠቀሱ የሽብር ቡድን አባላትን መልምሎ አቅጣጫ ይሰጣል፤ የተቀሩት ተጠርጣሪዎችንም በተለያዩ ጊዜያት ድርጊቱ የሚፈፀምባቸውን ቦታዎች እንዲለዩ አቅጣጫ ሰጥቷል ይላል ክሱ።

ተጠርጣሪዎቹም ወደተለያዩ ማደያዎች በማምራት የጥበቃውን ሁኔታ እና ቃጠሎውን ለመፈፀም አመቺውን ጊዜ ሲያጠኑ ቆይተዋል ነው የተባለው።በዚህም መሰረት መስከረም 26 ቀን 2009 ከሌሊቱ 8 እስከ 9 ስአት ድርጊቱን ለመፈፀም አመቺ ጊዜ ተደርጎ ተለይቷል።

በአንድ ጊዜ ሁሉንም ጠርሙስ ውስጥ ቤንዚን በመሙላትና ጨርቅ በማስገባት በጠርሙስ ውስጥ የገባውን የጨርቁን ጫፍ በክብሪት ለኩሶ ወደ በመወርወር ነው ነዳጅ ማደያዎቹን ለማቃጠል ታስቦ የነበረው።

ይሁንና በተባለው ቦታና ስአት ተጠርጣሪዎቹ ጥቃቱን ለመፈፀም ቢያመሩም ሁሉም ማደያዎች ውስጥ የነበረው ጥበቃና የአካባቢው ሁኔታ ድርጊቱን መፈፀም ስላላስቻላቸው መመለሳቸውን ነው ክሱ የሚያስረዳው።

ከዚህ በተጨማሪ ኮልፌ አጣና ተራ እና ባምቢስ አካባቢ ያሉ ማደያዎች ላይም ቀኑ ባልታወቀ መስከረም 2009 ዓ.ም በተመሳሳይ የማቃጠል ድርጊቱን ለመፈፀም ታስቦ የፀጥታ ሁኔታን ጥናት የማድረግ ዝግጅት ላይ እንደነበሩም ተጠቅሷል።

ጠቅላይ አቃቤ ህግ ከ1ኛ እስከ 7ኛ ያሉ ተከሳሾች ድርጊቱን ለመፈፀም ያቀዱ፣ የተዘጋጁ፣ ያሴሩ፣ ያነሳሱና የሞከሩ በመሆኑ በፈፀሙት የሽብርተኝነት ድርጊትን ለመፈፀም ማቀድ፣ መዘጋጀት፣ ማሴር፣ ማነሳሳት እና ሙከራ ወንጀል ክስ መስርቶባቸዋል።

8ኛ እና 9ኛ ተከሳሾችም የሽብር ድርጅት ውስጥ አባል በመሆን የድርጅቱን ተልዕኮ ለማሳካት ሲንቀሳቀሱ የነበሩ በመሆኑ በፈሙት የሽብርተኛ ድርጅት ውስጥ መሳተፍ ወንጀል ተከሰዋል።

ተጠርጣሪዎቹ ክሱ የተመሰረተባቸው በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ የወንጀል ችሎት ሲሆን፥ ክሱን በችሎት ለማንበብ ለመጋቢት 21 ቀን 2009 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy