Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በአገራችን የዕዳ ጫና ወደ መካከለኛ ደረጃ ደርሷል» – ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ

0 1,112

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ከአምና ጀምሮ በአምስት ዓመቱ የመካከለኛ ጊዜ ውስጥ በማጠናቀቅ ለሀገሪቱ ራዕይ መሳካት ወሳኙን ድርሻ እንዲይዝ ተደርጐ የተቀረፀ ነው፡፡ በተያዘው ዓመትም የተከናወኑ ተግባራት በልማት ዕቅዱ አተገባበር ምዕራፍ በዚህ ዓመት ለማሳካት የተያዙትን ግቦች ከዳር በማድረስ የታጠሩ ብቻ ሳይሆን ባለፈው ዓመት አጋጥመውን በነበሩ ልዩ ልዩ ተግዳሮቶች ምክንያት የተጓደሉ ጉዳዮች ለማካካስ ተብሎ የተቀመጠውንም አቅጣጫ ታሳቢ አድርጓል፡፡ ከዚህ አኳያ አጠቃላይ የኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግና በሌሎችም የኢኮኖሚና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረውን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ሪፖርት እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡

አጠቃላይ እይታ

ሀገራችን በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን በአማካይ 10 ነጥብ 1 በመቶ ዓመታዊ የኢኮኖሚ ዕድገት ያስመዘገበች መሆኑ ይታወቃል፡፡ የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን መጀመሪያ በሆነው 2008 .ም ኢኮኖሚው በአማካይ 11 በመቶ እንደሚያድግ የተተነበየ ቢሆንም በተግባር የተመዘገበው የ8 በመቶ አማካይ ዓመታዊ ዕድገት ነበር፡፡ ይህ ዕድገት በራሱ ሲታይ በዓለማችን ትልቁ ተብሎ የተወሰደ ቢሆንም ካስቀመጥነው ትንበያ ጋር የሚጣጣም አልነበረም፡፡ ለኢኮኖሚው በትንበያው መሠረት አለማደግ ግልጽ የሆኑ ምክንያቶች ነበሩ፡፡ አንደኛውና ዋነኛው ምክንያት በዓለም አቀፍ ደረጃ በኤልኝኖ ምክንያት የተከሰተው የአየር ንብረት ለውጥ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በአገራችን ባለፉት ሃምሳ ዓመታት ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ ከባድ ድርቅ ተከስቷል፡፡ ድርቁም የዕድገታችን ዋነኛ ሞተር ተደርጎ በተወሰደው የግብርናው ዘርፍ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ በማሳረፉ የምርት መቀነስ አጋጥሟል፡፡

ግብርና እና የድርቅ ተጽዕኖው

ግብርናችን ወትሮ በአማካይ ወደ ሰባት በመቶ ያድግ የነበረ ቢሆንም በድርቁ ምክንያት ወደ 2 ነጥብ 3 በመቶ ሊያሽቆለቁል ችሏል፡፡ እዚህ ላይ ሊሠመርባቸው የሚገቡ የተለያዩ ቁም ነገሮች እንዳሉ ግን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ በአንድ በኩል የ2007/2008 የመኸር ምርት ዕድገቱ ከዜሮ በታች ወደ 2 በመቶ የወረደ መሆኑ እና ይህ ቅናሽ ወትሮ ድርቅ በሚያጋጥምባቸው ሁሉም ዓመታት ካለው ከፍተኛ ቅናሽ ያነሠ መሆኑ በሌላ በኩል ደግሞ ከሌሎች የድርቅ ዓመታት በተለየ ሁኔታ የመስኖና የበልግ ምርት ተሽሎ በመገኘቱ አጠቃላይ የግብርና ዕድገት ወትሮ ከዜሮ በታች ይሆን የነበረው ወደ 2 ነጥብ 3 በመቶ የተጠጋ ከዜሮ በላይ ዕድገት ማስመዝገቡ ነው፡፡

ለዚህ አወንታዊ የግብርና አማካይ ዕድገት መነሻውም ለበርካታ ዓመታት በግብርናና ገጠር ትራንስፎርሜሽን ሥራ በተለይም የተፈጥሮ ሃብታችንን በተቀናጀ የተፋሰስ ልማት አማካይነት ለማሻሻል የሠራነው የተከማቸ የሥራ ውጤት ተደርጐ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ይህ ሥራችን ከሌሎች የግብርና ምርታማነት ማሳደጊያ ሥራዎቻችን ጋር ተቀናጅቶ ከተሠራ ድርቅን የመቋቋም አቅማችን በከፍተኛ ደረጃ የተሻሻለና አስተማማኝ ደረጃ ማድረስ እንደምንችል አመላካች ሆኗል፡፡ የምግብ ዋስትናችንንም በአስተማማኝ ሁኔታ በማረጋገጥ ለገበያ የሚሆን ትርፍ ምርት በከፍተኛ ደረጃ በማምረት የግብርና ኮሜርሻይዜሽን ስትራቴጅያችንም የተሳካ እንደሚሆን ያረጋገጠ ነው፡፡

ለአጠቃላይ የ2008 .ም ኢኮኖሚያዊ ዕድገታችን ከግብርና ውጭ የኢንዱስትሪ ዘርፉም በከፍተኛ ፍጥነት በማደግ የራሱን የማይተካ ሚና ተጫውቷል፡፡ አይ.ኤም.ኤፍ በሠራው ትንበያ እንኳ ሲታይ የኢንዱስትሪና የአገልግሎት ዘርፎች በድምር የኢኮኖሚ ዕድገቱ 7 በመቶ በእሴት ደረጃ ጭማሪ እንደሚያመጡ አመላክቶ ነበር፡፡ በተጨባጭም የሆነው ከዚሁ ጋር የተቀራረበ ነበር ማለት ይቻላል፡፡

በአጠቃላይ ወትሮም እንደሚታወቀው በእንደዚህ ዓይነት ከባድ ድርቅ ባጋጠመ ማግስት በአብዛኛዎቹ ትርፍ አምራች አካባቢዎች የተመጣጠነ ዝናብ እንደሚኖር ታሳቢ ያደረገ የ2008/2009 የመኸር ወቅት ዝግጅት ተደርጐ ወደ ሥራ ተገብቶ ነበር፡፡ እንደተተነበየው የመኸሩ ወቅት ግብርና በተለይም የዕድገቱ መሠረት የሆኑ የዋና ዋና የግብርና ምርቶች ግመታ በማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ተሠርቶ ይፋ ሆኗል፡፡ በዚህም መሠረት የዚህ ዓመት የመኸር ግብርና ምርት ዕድገት በአማካይ ወደ 9 በመቶ ያህል ዕድገት ያስመዘግባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ይህ አሃዝ እንደአምናው ሁሉ በመስኖ ሥራና በበልግ ግብርና በርትተን ከሠራን ወደ 12 በመቶ አጠቃላይ የግብርና ዕድገት ሊኖር ይችላል ተብሎ ይገመታል፡፡ ይህም የግብርና ዕድገት ከፍተኛው ተብሎ ሊወሰድ የሚችል ነው፡፡ በመሆኑም በዘንድሮው ዓመት አጠቃላይ የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ያለው አወንታዊ ተጽእኖ ትልቅ ይሆናል፡፡

በሁለተኛው የዕድገትና ሽግግር ዘመን የግብርናው ሚና

በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመንም ግብርና የኢኮኖሚ ዕድገታችን ዋነኛ ምንጭ ሆኖ እንደሚቀጥል ማስቀመጣችን ይታወቃል፡፡ በመሆኑም አነስተኛ አርሶ አደርና አርብቶ አደሮች የሚያከናወኑት የግብርና ሥራ የግብርና ኮሜርሻላይዜሽን ክላስተርን በመምረጥ በዚሁ ላይ ርብርብ በማድረግ የግብርናን ትራንፎርሜሽን ማፋጠን እንዳለብንም አቅጣጫ ተቀምጦ ተሠርቷል፡፡ ከዚህ አኳያ የልማት ቀጠናዎችን መሠረት በማድረግ የማስፋት ስትራቴጅያችንን አሟልቶ ለመተግበር የሚያስፈልጉ የግብርና ግብአቶችንና የአርሶና አርብቶ አደሩ የቴክኖሎጅ አጠቃቀም ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ በዘርፉ የሚታዩትን አሳሪ ማነቆዎችን ለመፍታት ጥረት ሲደረግ ቆይቷል፡፡

የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃን በማጎልበት አስተማማኝ የግብርና ልማትን ለማረጋገጥ እንዲሁም የግብርና ልማታችን በይዘትም በትግበራም ከአረንጓዴ ልማት ስትራቴጅያችን ጋር የተጣጣመ እንዲሆን ለማድረግም ሆነ ዘመናዊ ውሃን ማዕከል ያደረገ የመስኖ ግብርና ልማትን ለማስፋፋት በተመሳሳይ መልኩ ትኩረት ተሰጥቶ ርብርብ ሲደረግ ቆይቷል፡፡

የአርሶና አርብቶ አደሮቻችንን ገቢ በፍጥነት ለማሳደግ የላቀ ዋጋ ወደሚያስገኙ የሰብልም ሆነ የእንስሳት ምርቶች ማምረት እንዲሸጋገር ማድረግና ከዚሁ ጋር በማያያዝም የግብርና ግብይትን በተቀላጠፈና ዘመናዊ በሆነ መንገድ ተግባራዊ ለማድረግ ከዚሁም ፈጣን ለውጥ ጋር ተያይዞ የሚመጣውን ዕድል የገጠር ወጣቶችና ሴቶች በሰፊው እንዲጠቀሙ ለማድረግ ሥራዎች በትኩረት ሲተገበሩ ነበር፡፡ እነዚህን መሠረት በማድረግ በዕቅድ ዘመኑ አጋማሽ ላይ ሆነን ያስቀመጥናቸው ግቦች በምንመለከትበት ጊዜ በአብዛኛው በተሻለ ደረጃ የተፈፀሙ ነበር ማለት ይቻላል፡፡

ዳግም የድርቅ ክስተትና የመቋቋም ሂደቱ

በአገራችን ደቡብና ደቡብ ምሥራቅ ክፍል ከመስከረም አጋማሽ እስከ ህዳር ወር መጨረሻ የሚዘንበው ዝናብ በአገባብ፣ በመጠንና በስርጭት ያልተስተካከለ በመሆኑ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል 9 ዞኖች፣ በኦሮሚያ ክልል በቦረናና ጉጂ ዞኖች፣ በባሌና ምሥራቅ ሐረርጌና ምዕራብ ጉጂ ቆላማ ወረዳዎች፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል በደቡብ ኦሞና በሰገን ህዝቦች አካባቢ ዞኖች፣ በጋሞጐፋ ዞን ቆላማ ወረዳዎች አዲስ ድርቅ ተከስቷል፡፡

የዕለት ደራሽ ዕርዳታ ፈላጊ ቁጥር ለመለየት እንዲቻል የ2008/2009 የምርት ዘመን የመኸር ቅድመ አዝመራ ጥናት በሰብል አብቃይና አርብቶ አደር አካባቢዎች ተካሂዷል፡፡ በዚሁ መሠረት 5 ነጥብ 6 ሚሊየን ህዝብ የዕለት ደራሽ ዕርዳታ እንደሚያስፈልገው የተለየ ሲሆን ይህም አምና ከነበረው የ10 ነጥብ 2 ሚሊየን ዕርዳታ ፈላጊ ቁጥር ጋር ሲነፃፀር በ44 በመቶ ቀንሶ ይታያል፡፡

ድርቁ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያሳደረባቸውና በአስቸኳይ ጊዜ ምላሽ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገባቸው ወረዳዎች ቁጥር በመጋቢት ወር 2008 .219 ከነበረበት በታህሣሥ ወር 2009 .192 ወይም 12 በመቶ ቀንሷል፡፡ ይሁንና ባለፈው ዓመት የደረሰው የድርቅ አደጋ ተሻጋሪ ተፅዕኖ በመኖሩና በአርብቶ አደር አካባቢዎች አዲስ ድርቅ በመከሰቱ በዓመቱ ሊኖር ከሚችለው የተረጂ ቁጥር አኳያ ሲታይ ያሳየው ቅናሽ አነስተኛ ነው፡፡

2009 የዕለት ደራሽ ዕርዳታ እንደተለመደው በምግብና ምግብነክ ያልሆነ አቅርቦት አግባብ የሚፈጸም ሲሆን ለምግብ 598 ሚሊየን እና ምግብ ነክ ላልሆነ አቅርቦት 350 ሚሊየን በድምሩ 948 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር እንደሚያስፈልግ ተለይቷል፡፡ ለዓመቱ የሚያስፈልገው የምግብና ምግብነክ ያልሆነ አቅርቦት በፌዴራልና የክልል መንግሥታት፣ በአጋር አካላት፣ በህብረተሰቡና በግል ባለሀብቱ የሚሸፈን ሲሆን እስካሁን ባለው ጊዜ የፌዴራል መንግሥት የመሪነት ሚናውን በመውሰድ 1 ቢሊየን ብር በመመደብ የምላሽ ሥራ እየተሰራ ሲሆን የክልል መንግሥታትም በራሳቸው በጀት በመመደብ የምላሽ ሥራውን እያከናወኑ ይገኛሉ፡፡

የዕርዳታ አቅርቦቱ ከባለፈው ዓመት የዞረና በዚህ ዓመትም የተመደበውን ሀብት በመጠቀም ለአርብቶ አደርና ቆላማ ወረዳዎች ቅድሚያ በመስጠት የቀረበ በመሆኑ በሰው ህይወት ላይ ጉዳት እንዳይደርስና ከድርቁ ጥንካሬ አኳያ በእንስሳት ሀብቱ ላይ ሊደርስ የሚችለውን ከፍተኛ ጉዳት ማቅለል ተችሏል፡፡ ይሁንና እስካሁን ድረስ እየተደረገ ያለው ጥረት በአርብቶ አደሩ አካባቢ ያለውን የድርቅ አደጋ የሚመጥን እንዲሆን ለማድረግ ከፍተኛ ክትትል እየተደረገ ይገኛል፡፡

የእንስሳት ጉዳትን መቀነስና ትርጉም ባለው አግባብ መቀልበስ የሚቻለው ለርቢ እንስሳት መኖ በማቅረብና የተቀሩትን እንስሳት ለገበያ ማቅረብ ሲቻል ነው፡፡ ሆኖም ግን እንስሳትን ለገበያ ለማውጣት የተሰራው ሥራ ከችግሩ ስፋት አኳያ ሲታይ አነስተኛ ሆኖ ይገኛል፡፡ ስለዚህ የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ ከፍተኛ ርብርብ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በአጋር አካላት በኩል እስካሁን ድረስ ያለው እንቅስቃሴ ቀዝቃዛና ትኩረቱ በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በምዕራብ አፍሪካና በጐረቤት አገሮች ላይ ያነጣጠረ ነው፡፡ በመሆኑም በአገራችን የተከሰተውን የድርቅ አደጋ በመመከት ረገድ የመንግሥት፣ የህብረተሰቡና የግል ባለሀብቱ ድርሻ እጅግ የጐላ መሆን ስላለበት አገራዊ አቅምን አሟጦ ለመጠቀም ቅንጅታዊ አሠራርን ማጠናከር ይገባናል፡፡

ኢኮኖሚውና የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ

የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ከነባር ኢንዱስትሪዎች አቅም አጠቃቀም መሻሻል እና ወደማምረት መሸጋገር እንዲሁም አዳዲስ የኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንቶች በ2008 ዓመት ወደ ሥራ በመግባታቸው የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ንዑስ ዘርፍ የ18 ነጥብ 4 በመቶ ዕድገት በማስመዝገብ ከመቼውም ጊዜ በላቀ በኢንዱስትሪው ዘርፍ ለተመዘገበው ፈጣን ዕድገት ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ በተመሳሳይ ከኢንዱስትሪው ዘርፍ ውስጥ የሚመደበው የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ንዑስ ዘርፍ የ25 በመቶ ዕድገት በማስመዝገብ ለኢንዱስትሪው ዘርፍ ዕድገት አሁንም ትልቁን ሚና በመጫወት ላይ ይገኛል፡፡

ከአጠቃላይ ዕድገቱ አኳያ ከፍላጐት አንፃር በ2008 በጀት ዓመት የግልና የመንግሥት ኢንቨስትመንቶች ተጠናክረው በመቀጠላቸውና የመንግሥት ፍጆታም ከዕቅድ በላይ መፈፀሙ በዓመቱ ለተመዘገበው የኢኮኖሚ ዕድገት በጎ አስተዋጽኦ ነበራቸው፡፡ በተለይም በፈታኝ ሁኔታዎች ውስጥ ሆነንም የግልና የመንግሥት ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች እምብዛም ሳይስተጓጐሉ ለማስፋፋት የተደረገው እንቅስቃሴ አገራዊ የምርት ዕድገቱ በፈጣን ሁኔታ እንዲቀጥል አስችሏል፡፡ በአንፃሩ ደግሞ በሚቀጥሉት ክፍሎች እንደምናየው በ2008 ዓመት የታየው የሸቀጦች የወጪ ንግድ አፈፃፀም ከዕቅድም ሆነ ከባለፈው ዓመት አፈፃፀም አኳያ ደካማ መሆን ከድርቁ ባሻገር ለጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ዕድገት ተፈላጊ የሆነውን የውጭ ምንዛሬ በማቅረብ ደረጃ የራሱን ተጽእኖ በማድረግ የምርት ዕድገቱ ቅናሽ ውስጥ የራሱን አሻራ አሳርፏል፡፡

በዘንድሮ ዓመት አጠቃላይ የኢኮኖሚ ዕድገት ምጣኔን ለማወቅ የዓመቱን ማጠቃለያ መጠበቅ ያለብን ቢሆንም ከወዲሁ መናገር የሚቻለው ግን ዋናውን የዕድገት ምንጭ የሆነውን የመኸር ግብርና ውጤት ግምቱን በማወቃችንና በኢንዱስትሪና በአገልግሎት ዘርፍም ያለው ሁኔታ ዕድገቱ እንደሚቀጥል ያሉን አመልካቾች የሚያሳዩን በመሆኑ የአምናውንም ጉድለት በመጠኑም ቢሆን ለማካካስ የሚያግዝ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በመሆኑም ከግብርና ዘርፍ በተጨማሪም የኢንዱስትሪውና የአገልግሎት ዘርፎችም የተቀመጠላቸውን የ20 ነጥብ 6 እና የ10 ነጥብ 2 በመቶ የተጨማሪ ዕሴት ዕድገቶች በቅደም ተከተል ሊያሳኩ እንደሚችሉ ይጠበቃል፡፡

ከኢኮኖሚ ዕድገት አኳያ ልንደርስበት የምንችለው ድምዳሜ ሀገራችን ካጋጠማት ከፍተኛ ድርቅ እና በዓለም የኢኮኖሚ ዕድገትና የሸቀጦች ዋጋ መቀዛቀዝ የተነሣ መጠነኛ ቅናሽ የታየበት ቢሆንም የዓለም ኢኮኖሚ በዚሁ ወቅት 3 ነጥብ 1 በመቶ እንደሚያድግ ከተደረገው ግመታ፣ ከሁሉም በላይ እኛ የምንገኝበት የሰሀራበታች ኢኮኖሚ ዕድገት ወትሮ ከሚታወቅበት የ5 በመቶ አማካይ ዕድገት አሽቆልቁሎ ወደ 1ነጥብ4 በመቶ እንደሚያድግ ከተደረገው ግመታ ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ መሆኑ እንዲሁም የዘንድሮ ዓመት የማገገም ሂደቱም በአበረታች ሁኔታ እየቀጠለ በመሆኑ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በርግጥም በጠንካራ መሠረት ላይ እየተገነባ የመጣ መሆኑን፣ ያልተጠበቁ ተግዳሮቶችንም ጭምር የመቋቋም አቅሙ እየተጠናከረ የመጣ መሆኑን እንድናምን ያደርገናል፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮችና ቀላል የማምረቻ ኢንዱስትሪዎች ግንባታ

በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመንም ሆነ በመካከለኛ ጊዜ ራዕያችን እንዳስቀመጥነው በዚህ ዕቅድ ዘመን የሰው ጉልበት በስፋት የሚጠቀሙ በዓለም አቀፍ ደረጃ በምርታማነት፣ በጥራትና በዋጋ ተወዳዳሪ የሆኑ ቀላል የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎችን ለመገንባት ለዘርፉ የተለየ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል፡፡ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ንዑስ ዘርፍ በተለይም የከፍተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው አስተማማኝ የውጭ ምንዛሪ ምንጭ እንዲሆን የተጀመረው ሥራ ገና ወደሚፈለገው ደረጃ ያልደረሰ መሆኑ በውል እየታየ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ የነባር ኢንዱትሪዎችን አቅም ለማሳደግ፣ ለአዳዲስ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች መስፋፋት የአገር ውስጥና የውጭ ኢንቨስትመንቶችን በብዛትና በጥራት ለመሳብ፣ ከፍተኛ ተክኖሎጂ የሚጠቀሙ ኢንዱስትሪዎችን ልማት መሰረት ከወዲሁ ለመጣልና ከቀላል ኢንዱስትሪዎች ጋር ለማስተሳሰር፣ ከባድ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ፣ የኬሚካልና የፋርማሲቲካል ኢንዱስትሪዎችን ለማስፋፋትና ኤክስፖርትና ስትራቴጂክ ገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርቶች ለመተካትና ተመጋጋቢ ሆነው እንዲፈጸሙ ለማድረገ ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮችንና ክላስተሮችን በማልማት ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ በመፍጠር የሀገር ውስጥና የውጭ ኢንቨስተሮችን በስፋት መሳብ፣ ዘመናዊ የሥራ አመራር ልምድ በአገር ውስጥ አንዲጎለብት በማድረግና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ በማድረግ በዋነኛነት የውጭ ንግድን በማስፋፋትና ከውጭ የሚገቡ የኢንዱስትሪ ምርቶችን በአገር ውስጥ ምርቶች በመተካት፣ የውጭ ምንዛሪ ገቢያችንን ለማሳደግ እና የኢኮኖሚና ማህበራዊ እድገታችንን ለማፋጠን እየተሠራ ይገኛል፡፡ በክልሎች የተጀመሩ አራቱ የተቀናጁ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ፓይለት ፕሮጀክቶችን በማልማት በሚሊዮን የሚቆጠሩ አርሶ አደሮች ምርት ከኢንዱስትሪ ጋር ትስስር ኢንዲፈጥሩ በማድረግ በግብርና ምርቶች ላይ እሴት በመጨመር የገጠር ትራንስፎርሜሽንና የግብርና ኢንዱስትሪ ትስስር ማጠናከር፣ በክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ከአነስተኛ ወደ መካከለኛ ኢንዱስትሪ ለሚሸጋገሩ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ባለሐብቶች ደረጃቸውን የተጠበቁ ኢንዱስትሪ ክላስተሮችና ፓርኮች እንዲያለሙ ሊያደርጉ የሚችሉ ሥራዎች ተጀምረዋል።

የኢንዱስትሪውን ዘርፍ በማስፋፋት የመዋቅራዊ ሽግግሩን ለማፋጠንና ሰፊ የሥራ እድል ለመፍጠር እንዲሁም የኤክስፖርት አቅምን ለማሳደግና የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማፋጠን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት የተሻለ አማራጭ ሆኖ በመገኘቱ በተለያዩ ከተሞች በፌዴራል መንግሥት አማካይነት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ እየተከናወነ የሚገኝ ሲሆን የተወሰኑት ኢንዱስትሪ ፓርኮች ወደ ምርት ሂደት ሊሸጋገሩ ችለዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በዕቅድ ከተያዙ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ውስጥ ሁለቱ ምርት የጀመሩ ሲሆን ሰባቱ በግንባታ ሂደት ላይ ይገኛሉ፡፡ ቀሪዎቹ አራት ኢንዱስትሪ ፖርኮች በጨረታ ሂደት ላይ ናቸው፡፡ የፓርኮቹ ግንባታ እንዲፋጠንና የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ ባለሃብቶች ገብተውባቸው ወደ ማምረት እንዲሸጋገሩ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ይደረጋል፡፡

ከላይ የተጠቀሱት 13 ኢንዱስትሪ ፓርኮችና በግል ባለሃብቶች እየለሙ ያሉ ሦስት ኢንዱስትሪ ፓርኮች ተጨምሮባቸው በክልሎች ከሚለሙ መለስተኛ ፓርኮች ጋር ተደምረው በተናጠል ኢንዱስትሪያቸውን ካቋቋሙ የግል ባለሃብቶች ጋር ተቀናጅቶ ሲታይ በሀገራችን የኢኮኖሚውን መዋቅራዊ ሽግግር ለማምጣት የሚያስችል መሠረት እየተጣለ መሆኑን አመላካች ነው፡፡ ሥራው እጅግ ከባድና ውስብስብ በመሆኑ የሀገራዊ ባለሃብቶችን በተለያዩ ማበረታቻዎች በመደገፍ ወደ ማኑፋክቸሪንግ እንዲገቡ እየተደረገ ያለው ጥረት መጠናከር ያለበት ይሆናል፡፡ የሆነ ሆኖ የተያዘው አቅጣጫ በትኩረትና በጥራት ከተመራ እያጋጠመን ያለውን የውጭ ምንዛሬ እጥረት የመቅረፍና የዘላቂ ኤክስፖርት መሠረት የመጣል አቅም ያለው በመሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላት አሁን እየታየ ካለው አበረታች ድጋፍ በላይ ሄደው መደገፍና ማጠናከር ይገባቸዋል፡፡

የወጪ ንግድ እና የውጭ ምንዛሬ ግኝት

በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የኢኮኖሚውን መዋቅራዊ ሽግግር ከማረጋገጥ አኳያ ትልቅ ድርሻ ያለው የወጪ ንግዳችንን ማስፋፋትና አስተማማኝ የውጭ ምንዛሬ ምንጮች እንዲኖሩ በማድረግ የሀገሪቱ የውጭ ክፍያ ሚዛንን የተረጋጋና ቀጣይነት ያለው እንዲሆን ማድረግ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የዓመቱ አጋማሽ አፈፃፀማችን በሚታይበት ጊዜ ከሸቀጦች የወጪ ንግድ ማለትም ከግብርና ምርቶች የወጪ ንግድ፣ ከማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እና ከማዕድናት ዘርፍ የተገኘው ገቢ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ4 ነጥብ 2 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል፡፡ ይህ ሂደት ለተከታታይ ሦስት ዓመታት የቀጠለ በመሆኑና ይህንኑ ለመቀየር የተደረጉ ጥረቶች በተለያዩ ምክንያቶች ስኬታማ ባለመሆናቸው ሁኔታውን በዝርዝርና ከተለመደው ወጣ ባለ የአፈፃፀም መሻሻል ለመቀልበስ ጥረት ማድረግ የሚገባን ይሆናል፡፡

በዚህም መሠረት ለሁሉም ዓይነት የኤክስፖርት ሸቀጦች የኤክስፖርት ግኝት መቀነስ ጥቅልና ተመሳሳይነት ያላቸው ምክንያቶች እንደሌላቸው ታሳቢ ያደረገና በመንግሥት መዋቅሩ ከታጠረ ግምገማ በመውጣት ከዘርፉ የሚመለከታቸው ተዋኒያን ባለሃብቶችና ማህበሮቻቸው ጋር ጥልቀት ያለው ግምገማና አሳሪ ማነቆዎችን የመፍታት ጥረት ተጀምሯል፡፡ በቅርቡ ከጨርቃ ጨርቅና አልባሳት እንዲሁም ከቆዳና ቆዳ ውጤቶች፣ ከሥጋና ቁም እንስሳት አምራቾችና ኤክስፖርተሮች ጋር ውጤታማ ውይይቶች ተካሂደዋል፡፡ ሥራው በትኩረት ከተያዘም ለውጥ ሊመጣ እንደሚችል ለማየት ተችሏል፡፡ በእነዚህ ዘርፎች አብዛኛዎቹ ነባር ፋብሪካዎች በተሻለ የሚያመርቱም ቢሆን ምርታቸውን በአገር ውስጥ እንዲሸጡ የሚያስገድዳቸውን ምክንያቶች በመፍታት ላይ ያነጣጠረ እንዲሆን የማድረግ የጋራ መግባባት ተፈጥሯል፡፡ ጥረቱም ወደ ማምረት እየተሸጋገሩ ያሉ በርካታ አዳዲስ ፋብሪካዎችም ወደ ዚህ ወጥመድ እንዳይገቡ ሁኔታዎችን ያመቻቻል ተብሎ ተወስዷል፡፡ ነባር ፋብሪካዎች በሙሉ አቅምና በኤክስፖርት ጥራት እንዲያመርቱ ከማድረግ ባሻገር መሠረቱን ለማስፋት አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች በስፋት እየገቡ መሆናቸው ሁኔታውን ከመሠረቱ ለመቀየር የሚያስችለን መሆኑን ታሳቢ ያደረገ ድጋፍና ክትትል እየተደረገ ይገኛል፡፡ ከዚህ አኳያ የፌዴራልና የክልሎች የኢንዱስትሪ ፓርክ ልማት አፋፃፀማችንን ውጤታማ ማድረግ አስተዋጽኦ ትልቅ ይሆናል፡፡

የሀገራችን ኤክስፖርት ግኝት አሁን ባለንበት የኢኮኖሚ አወቃቀር ምክንያት ከግብርና ምርቶች ኤክስፖርት ከ70 በመቶ በላይ የምናገኝ መሆኑ ይታወቃል፡፡ የዚህ ዘርፍ ኤክስፖርት መውደቅ ዋነኛው ምክንያት በተከታታይ እንደታየው ኤክስፖርት ሊደረግ የሚችል ምርት ያለ እና የምርት ጭማሪ ያሳየ እንኳ ቢሆንም በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ የታየው የፍላጐት መቀነስና ያስከተለው የዋጋ መውረድ ነው፡፡ ይህ ክስተት በግብርና ዘርፍ ብቻ ሳይወሰን በኮሞዲቲዎች ኤክስፖርት ላይ ሁሉ ተጽእኖን አሳርፏል፡፡ በዚህም ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን በግብርናና ማዕድናት ሸቀጦች ወጪ ንግድ ላይ በሰፊው በተሰማሩ ሌሎች ሀገራትም የችግሩ ገፈት ቀማሽ ያደረገ በመሆኑ በመካከለኛና በረጅም ጊዜ በኢኮኖሚው ውስጥ መዋቅራዊ ሽግግር በማካሄድ በምርቶቹ ላይ እሴት በመጨመር ኤክስፖርት ማድረግ ብቸኛው አማራጭ መንገድ መሆኑ ይበልጥ እንድናሰምርበት ያደርገናል፡፡ እስከዚያ ድረስ ግን ከአጭር ጊዜ አኳያ አሁንም በኤክስፖርት ገበያ ሰንሰለት የሚታየውን የተወሳሰበ የኮንትሮባንድ ንግድ በጋራ ጥረት በማስቆም ኤክስፖርት የሚደረገውን መጠን በከፍተኛ ደረጃ ከፍ ማድረግ ብቸኛው አማራጭ ሆኗል፡፡

ከዚህ አኳያ የቡናና የቁም እንስሳት እንዲሁም ከማዕድናትም በባህላዊና በዘመናዊ መንገድ የሚመረተው የወርቅ ማዕድን አቅርቦትን ለማሳደግ በኮንትሮባንድ ንግድ ላይ ሰፊ ዘመቻ መክፈት ያለብን ይሆናል፡፡

በአንፃሩ ደግሞ በዚሁ የአመቱ አጋማሽ ነዳጅን ጨምሮ ለገቢ ዕቃዎች የተደረገው የውጭ ምንዛሬ ወጪ ካለፈው ዓመት ተመሣሣይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ4 ነጥብ 1 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል፡፡ ይህም በመሆኑ የግማሽ ዓመቱ የሀገሪቱ የውጭ ንግድ ሚዛን ጉድለት አምና በተመሳሳይ ወቅት ከነበረበት የ7 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በመጠኑ ተሻሽሎ ወደ 6 ነጥብ 72 ቢሊዮን ዶላር ሆኗል፡፡ ሆኖም የንግድ ሚዛን ጉድለቱ አሁንም ቢሆን እጅግ ከፍተኛ መሆኑ ሊሠመርበት ይገባል፡፡ የሸቀጦች የወጪ ንግድ ገቢ የሸፈነው የገቢ ንግድ ወጪ 15 ነጥብ 5 በመቶ ብቻ መሆኑ ይህንን የሚያመለክት ነው፡፡

የክፍያ ሚዛኑ ያለበትን ሁኔታ ለመረዳት አገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ከምታገኝባቸው መንገዶች መካከል ከኤክስፖርት ግኝቱ በተጨማሪ የሐዋላ፣ የውጭ ብድርና እርዳታ ፍሰት እንዲሁም ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት ይገኙባቸዋል፡፡ በዚህ መሠረት ከግል ሃዋላ በተለይም ግለሰቦች ከሚልኩት ሃዋላ የተገኘው ገቢ ከአምና ጋር ሲነፃፀር በ10 ነጥብ 3 በመቶ ብልጫ አለው፡፡ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሃዋላ ግን አምና በድርቁ ምክንያት በስፋት የገባ በመሆኑና ዘንድሮ ይኼው በመቀነሱ ተፈጥሯዊ ቅናሽ አሳይቷል፡፡ ከዚህ ሌላ የተጣራ መንግሥታዊ የውጭ ሃዋላ በ55 ነጥብ 3 በመቶ ብልጫ አሳይቷል፡፡ በአንፃሩ የዕዳ ጫናችን ከፍ እያለ በመሄዱና የረጅም ጊዜ ብድር አወሳሰድ እየቀነስን በመምጣታችን ይኸው የውጭ ምንዛሬ ግኝት ከአምናው ጋር ሲነፃፀር በ14 ነጥብ 5 በመቶ ቢቀነስም በአንፃሩ ደግሞ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት በ101ነጥብ 3 በመቶ በማሻቀቡ የካፒታል ሂሣብ /Capital account / በዚህ ወቅት የ27ነጥብ 3 በመቶ እድገት አሳይቷል፡፡

በአጠቃላይ የውጭ ምንዛሪ ግኝት በማሳደግ የክፍያ ሚዛን እንዳይሻሻል ተግዳሮት ሆነው የቆዩት ዋና ዋና ምክንያቶች ሲታዩ በዓለም አቀፍ ገበያ እኛ የምንልካቸው አብዛኛዎቹ ምርቶች ዋጋ መቀነስ፣ በመጠኑም ቢሆን የብር የውጭ ምንዛሪ ተመን ከእውነተኛ ዋጋው አንፃር ጠንካራ መሆን እና በቻይናና በአንዳንድ ዋና ዋና የንግድ ሸሪኮቻችን የታየው የመግዛት ፍላጎት መቀዛቀዝ ሲሆኑ በአገር ውስጥ ደግሞ የኤክስፖርት ዘርፍ አመራራችን በዘርፉ የሚታዩ አሳሪ ማነቆዎችን ከመፍታት አኳያ የሚፈለገው ደረጃ ላይ አለመድረሱ ናቸው፡፡ እነዚህን የአጭርና የረጅም ጊዜ ባህሪ ያላቸውን ተግዳሮቶችን ደረጃ በደረጃ ለመቅረፍ የሚያስችል አመራር በመስጠትም ሆነ በአፈፃፀም የተሻሻሉ እንዲሆኑ ለማድረግና ወሳኝ የሆነውን የኢኮኖሚው መዋቅራዊ ትራንስፎርሜሽን ላይ ልዩ ትኩረት በማድረግ ማፋጠን ያስፈልገናል፡፡

የፊስካል ፖሊሲው፣ የገቢ አሰባሰብ ሥራው እና የዕዳ ጫና

የፊስካል ፖሊሲ መንግሥት ከሚያከናውናቸው ገቢ የማሰባሰብና ወጪን የመደልደል ተግባራት ባለፈ ልማታዊ መንግሥት እንደመሆናችን መጠን የኢኮኖሚ እድገትን፣ ፍትሃዊ የሃብት ድልድልን፣ የዋጋ ንረትን፣ የኢንቨስትመንት መጠንና የዘርፍ ስብጥርን፣ የመዋቅራዊ ሽግግር አቅጣጫን፣ የሥራ መስኮችና የሥራ አጥነት ምጣኔን፣ አገራዊ የፋይናንስ አቅምና የተዓማኒነት ደረጃ እንዲሁም የንግድ ፍሰትና ስብጥርን የመሳሰሉ ቁልፍ የኢኮኖሚ ክስተቶች ከገንዘብ ፖሊሲ በተጓዳኝ የሚቃኙበት አንዱ መሣሪያ ነው፡፡

ከዚህ አኳያ በ2009 የመጀመሪያው አጋማሽ የፌዴራል መንግሥት ገቢ አሰባሰብ ከዕቅድ አንፃር የ90 በመቶ አፈፃፀም ተመዝግቧል፡፡ ይህ አፈፃፀም ካለፈው ተመሣሣይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ12 ነጥብ 26 በመቶ ዕድገት አስመዝግቧል፡፡

የፌዴራል መንግሥት ገቢን በዝርዝር በምናይበት ጊዜ ከቀጥታ ታክሶች የዕቅዱን 102 ነጥብ 3በመቶ የተሰበሰበ በመሆኑ የዕቅዱን ያህል የተከናወነ ነበር ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡ ነገር ግን አጠቃላይ የፌዴራል መንግሥት ገቢ ከእቅዱ አንሶ እንዲገኝ ዋናው ምክንያት ቀጥታ ያልሆኑ ታክሶች የዕቅድ አፈፃፀም ወደ 23 በመቶ የሚሆን ጉድለት ያሳዩ በመሆኑ ነው፡፡ ከቀጥታ ያልሆኑ ታክሶችም ውስጥ ትልቁን ጉድለት የተሸከመው የተጨማሪ ዕሴት ታክስ ሲሆን ጉድለቱም ወደ 25 በመቶ አካባቢ ነዉ፡፡ በመሆኑም በዚህ ዙሪያ ትኩረት አድርጎ መስራት ለዚሁም የተጀመረው የታክስ ሪፎርም ሥራዎችን አጠናክሮ በጥራት መፈፀም ወሳኝ ሆኖ ይገኛል፡፡ ከዚህ አኳያ አሁን የሚታየውን የታክስ ህግ ማስከበር ሥራዎቻችን ደካማ መሆንን በመቀየር የታክስ ኦዲት ላይ፣ የድህረዕቃ አወጣጥ ኦዲት፣ የታክስ ኢንተልጀንስ ሥራዎችና የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ ቁጥጥር ክፍተት፣ ሽያጭንና ግዥን ያለደረሰኝ ግብይት የመፈፀም ህገወጥነት፣ ግብር ከፋዮች የክፍያ የውል ስምምነት ግዴታዎችን እንዲያከብሩ እንዲሁም ውዝፍ ግብርና ታክስ ዕዳዎችን ተከታትሎ የመሰብሰብ ውስንነቶችን በመሠረቱ መቅረፍ የሚገባን ይሆናል፡፡ ይህ የተጨማሪ እሴት ታክስ ማጭበርበር ጉዳይ ኢኮኖሚያችንን ክፉኛ የሚጎዳ በመሆኑ የተጠናከረ እርምጃ መውሰድ የምንጀምር ይሆናል፡፡

ከእነዚህ የዕለት ተዕለት ተግባራት ባሻገር በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን መጨረሻ የታክስ ገቢ ከአጠቃላይ የሃገሪቱ ምርት አኳያ ወደ 17 በመቶ እንዲደርስ ለማድረግ የተያዘው ዕቅድ የክልሎችንም የታክስ ገቢ እድገት ታሳቢ ያደረገም ቢሆንም ዋናው ወይም እስከ 15 በመቶ ድርሻ የያዘው የፌዴራል መንግሥት ገቢ በመሆኑ ይህንኑ በማሳካት ለክልሎችም መልካም ተሞክሮ እንዲሆን የታክስ ሥርዓት ማሻሻያ ፕሮጀክት ተቀርፆ ዓለም አቀፍ የሙያ ድጋፍም ታክሎበት እየተከናወነ ይገኛል፡፡ የጉምሩክ ሥርዓቱንም ዘመናዊና ቀልጣፋ እንዲሁም ውጤታማ ለማድረግ የተቀረፀው የአንድ መስኮት /Single window/ ፕሮጀክትም ወደ ትግበራ ሂደት እየተሸጋገረ ይገኛል፡፡ የፌዴራልና የክልል መንግሥታት የታክስ አስተዳደር ሥርዓት የማጣጣም፣ የጋራ ገቢዎችን በወቅቱ ሰብስቦ በየድርሻቸው የማስተላለፍ እንዲሁም የሰው ሃይል አቅም ግንባታ ላይ ድጋፍ የመስጠት ሥራም ተቀናጅቶ እየተሠራ ይገኛል፡፡ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የገቢ ማሰባሰብ አኳያ ትኩረት የተሰጠበት የመርካቶ አካባቢ የታክስ ህግ ተገዥነት ፕሮጀክት ተተግብሮ ውጤቶች መመዝገብ የጀመሩ በመሆናቸው ይህንኑ አጠናክረን የምንቀጥል ይሆናል፡፡

የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዳችን ከአገር ውስጥ ከሚሰበሰብ የታክስና ታክስ ያልሆኑ ገቢዎች እንዲሁም ከሀገር ውስጥ ቁጠባ በተጨማሪ ከውጭ ከሚገኝ ብድር በተለይም ዋና ዋና ሜጋ ፕሮጀክቶቻችን ፋይናንስ እንደሚደረጉ ይታወቃል፡፡ ከዚህ አኳያ ባለፈው ዓመት የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ባደረጉት የዕዳ ጫና ትንተና መሠረት በሀገራችን ዕዳ ጫና ወደ መካከለኛው /moderate/ ደረጃ ደርሷል፡፡ ለዚህም ዋናው ምክንያት በባለፉት ክፍሎች እንደተገለፀው ከኤክስፖርት የምናገኘው ገቢ ከአጠቃላይ የሀገሪቱ ምርት ጋር ሲነፃፀር እዚህ ግባ የሚባል አለመሆኑና የኤክስፖርት ግኝትን በየዓመቱ ቢያንስ በ20 በመቶ አካባቢ እናሳድጋለን ብለን የያዝነው ዕቅድ ባለመሳካቱ ነው፡፡ ይህን ሁኔታ በመሠረታዊነትና በዘላቂነት መፍታት ፈጣንና ፍትሃዊ እድገታችንን ለማስቀጠል ወሳኝ ይሆናል፡፡

የዋጋ ግሽበትን ለማረጋጋት ምን ተሰራ?

ዋጋን ማረጋጋትና የዋጋ ንረትን በነጠላ አሃዝ ገድቦ ማቆየት ከዕድገትና ትራንስፎርሜሽኑ ግቦች መካከል አንዱ ነው፡፡ ይህ ስትራቴጅክ ግብ እንዲሳካና የብርን የመግዛት አቅም ጠብቆ ለማቆየት፣ ቁጠባንና ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት፣ የገቢ ክፍፍልንና ሀብት ድልድልን ሚዛናዊ ለማድረግና የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ቀጣይነትን ለማረጋገጥ ሲሠራ ቆይቷል፡፡

እስከያዝነው ወር ድረስም ይህ የነጠላ አሃዝ ግብ ከተቀመጠው አማካይ 8 በመቶ ተገድቦ እንዲቆይ ለማድረግ ልዩ ልዩ የገንዘብ ፖሊሲ እርምጃዎች መውሰዳችን፣ ጥብቅ የፊሲካል ፖሊሲ መከተላችን፣ እንዲሁም የሀገር ውስጥ ገበያን ለማረጋጋት አንዳንድ መሠረታዊ ሸቀጦችን ከውጭ አገር ገዝቶ በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ በመቻላችን እና የዓለም ገበያ የሸቀጦች ዋጋ መረጋጋት በተለይም ከእኛ ኢኮኖሚ አኳያ የነዳጅና የብረት ዋጋ ተረጋግቶ የቆየ በመሆኑ በአጠቃላይ ዓመታዊ የዋጋ ንረቱ ካስቀመጥነው የ8 በመቶ ዕድገት በታች ሆኖ እንዲፈፀም አስችሏል፡፡

የገንዘብ ፖሊሲው አካል የሆነው የወለድ ተመን የተረጋጋ መሆን የማክሮ ኢኮኖሚውን ከማረጋጋትና ተገማች እንዲሆን ከማድረግ ረገድ ትልቅ ሚና ያለው ነው፡፡ ከዚህ አኳያ የሀገሪቱን ተጨባጭ ማክሮ ኢኮኖሚያዊ አመላካቾችን ያገናዘበ፣ የተረጋጋ፣ አስቀማጮችንም ሆነ ተበዳሪዎችን የማይጐዳና የሥራ ዕድልን የሚያሰፋ እንዲሁም የፋይናንስ ተደራሽነትን የሚያስፋፋና የመንግሥትን የልማት ፖሊሲ የሚደገፍ እንዲሆን ትኩረት ተሰጥቶ እንቅስቃሴ ተደርጓል፡፡ በዚሁ መሠረት በተቀማጭ ገንዘብ ላይ የሚከፈለው ዝቅተኛ የወለድ ምጣኔ 5 በመቶ ሆኖ እንዲቀጥል ሲደረግ የማበደሪያ ወለድ ምጣኔን ግን ባንኮች ራሳቸው የሚወስኑት እንዲሆን ተደርጓል፡፡

የተረጋጋ የማክሮኢኮኖሚ ሁኔታ እንዲኖርና የዋጋ ንረቱም በተቀመጠው ገደብ አካባቢ እንዲጫወት ለማድረግ ጥቅም ላይ ከሚውሉ የፊሲካል ፖሊሲ ስልቶች አንዱ መንግሥት ለበጀት ጉድለት መሸፈኛ ከብሔራዊ ባንክ የሚወስደው ቀጥታ ብድር በበጀቱ መፅደቅ ወቅት በተቀመጠው መሠረት መሆኑንና ከዋጋ ንረት ግቡ ጋር የተጣጣመ መሆኑን ጥብቅ ክትትል ማድረግ ነው፡፡ በዚህ መሠረት እስከ ዓመቱ አጋማሽ ድረስ መንግሥት ከብሔራዊ ባንክ የወሰደው ቀጥታ ብድር ወደ ብር 12 ቢሊዮን የደረሰ ሲሆን ይህም በዕቅድ ከተያዘው መጠን ጋር የተጣጣመ ነው፡፡

እንደዚሁም የዋጋ መረጋጋትን ለማስፈን የግምጃ ቤት ሠነድን እንደከፊል የገንዘብ ፖሊሲ መሣሪያ መጠቀሙ የቀጠለ ሲሆን እስከ ዓመቱ አጋማሽ ድረስ በተካሄዱ ሳምንታዊ የግምጃ ቤት ሠነድ ጨረታዎች አማካይነት ወደ 107 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ሽያጭ ተካሂዷል፡፡ በመጠኑም ከዕቅድ በላይ ሽያጭ የተካሄደ ሲሆን ይህም ሽያጭ ከአምና ተመሳሳይ ወቅት የ38 ነጥብ 8 በመቶ እና የሠነዶች አቅርቦትም የ38 ነጥብ 2 በመቶ ዓመታዊ ዕድገት አስመዝግቧል፡፡ ለዚህም ዋነኛ ምክንያት ባንክ ያልሆኑ ድርጅቶች የግምጃ ቤት ሰነድ ጨረታ ላይ ያላቸው ተሳትፎ በመጨመሩ ነው፡፡ ይህም ጤናማ አካሄድ ለማክሮኢኮኖሚ መረጋጋትና ለዋጋ ንረት ካለው ፋይዳ አኳያ ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ነው፡፡

የተረጋጋ የውጭ ምንዛሬ ተመን ፖሊሲ የአገሪቱን የወጪ ንግድ ተወዳዳሪነት ለማጠናከር፣ የንግድ ሚዛን ለማሻሻል እንዲሁም የውጭ ምንዛሬ ግኝቱን ለማዳበር የሚረዳ የገንዘብ ፖሊሲ አካል እንደመሆኑ መጠን የሀገሪቱን ተጨባጭ የዕድገት ደረጃ ያገናዘበ ከፊል አስተዳደራዊና ከፊል ገበያ መር የሆነ የውጭ ምንዛሬ ተመን ፖሊሲ በጥብቅ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል፡፡

በዚህም መሠረት የዓመቱ የመጀመሪያ አጋማሽ አፈፃፀም ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የብር ዋጋ ከአሜሪካን ዶላር አኳያ በ6 በመቶ አካባቢ እንደወደቀ (depreciate) ያሳያል፡፡ ይህም ከተቀመጠው ግብ ጋር የተጣጣመ መሆኑን ያመለክታል፡፡ ይህ የብር የውጭ ምንዛሬ ዋጋ የተረጋጋና ከተቀመጠው ግብ ጋር ተጣጥሞ የተፈፀመው አንደኛ ብሔራዊ ባንክ በቀጥታ የውጭ ምንዛሬ ገበያ ላይ ተሳታፊ በመሆኑ እና ሁለተኛው ደግሞ ከውጭ የሚገቡ መሠረታዊ ሸቀጦች በተለይም የነዳጅ፣ የማዳበሪያና ለዋና ዋና ሜጋ ፕሮጀክቶቻችን ግንባታና ማስፋፊያ ለሚውሉ ዕቃዎችና መሣሪያዎች ግዥ በድምሩ እስከ 1 ነጥብ 10 ቢሊዮን ዶላር በባንኩ በኩል በቀጥታ በመስጠቱ ነው፡፡ ይህም ሆኖ በአገራችን በቅርቡ ተከስቶ የነበረውን አለመረጋጋት በማስታከክ በኦፊሴላዊ የውጭ ምንዛሬ ተመንና በጥቁር ገብያው ተመን መካከል መጠነኛ ልዩነት ያለ በመሆኑ በምንወስዳቸው ማክሮኢኮኖሚና አስተዳደራዊ እርምጃዎች የጥቁር ገበያው እየተስተካከለ የሚሄድ ይሆናል፡፡

የኢኮኖሚ መሰረተ ልማት (ትምህርትና ጤና)

የኢኮኖሚ መሠረተልማቶች አቅርቦት ማሻሻል የኢኮኖሚውን ፈጣን መዋቅራዊ ሽግግር የሚደግፍና ሰፊ የሥራ ዕድል የመፍጠር አቅም ያለው በመሆኑ በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት እስከ ዓመቱ አጋማሽም ትኩረት ተሰጥቶት እየተተገበረ ይገኛል፡፡ ከዚህ አኳያ ግዙፍ የሆነውን የዘርፉን እቅድና አገልግሎት የማቅረብ ችሎታ ያላቸውን ተቋማትን ለመገንባት ትኩረት ተሰጥቷል፡፡ አፈፃፀሙ በሚታይበት ጊዜ ከመካከለኛ እስከ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ያለ መሆኑን ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ በመካከለኛ ደረጃ ላይ ያሉ አፈፃፀሞችን ለማሻሻል ከፍተኛ ጥረት ይደረጋል፡፡

የትምህርትና ስልጠና ዘርፍ ውጤታማነትን ለማሳደግና የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ ሀገሪቱ የምትፈልገውን ብቁና ተወዳዳሪ የሰው ሀይል አቅርቦትን በቀጣይነት በጥራት ለማፋጠን የሚያስችሉ መሰረታዊ ሥራዎችን እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡ በዚህም መሰረት ለትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ ትግበራ የወደፊት የ15 ዓመት አቅጣጫ ጠቋሚ ፍኖተ ካርታ የማዘጋጀት ሥራ በመሰራት ላይ ይገኛል፡፡ በዘርፉ የተያዘው እቅድ አፈጻጸምና ሽፋኖቹ የሚያሳዩት በቅድመ መደበኛ እና በ2ኛ ደረጃ የትምህርት ተሳትፎ ላይ ከፍተኛ የሆነ ርብርብ ማድረግ እንደሚጠይቅ ነው፡፡ የሁለተኛ ደረጃ የትምህርት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ባለፈው ዓመት የተጀመረው የማስፋፋትና ተጨማሪ ግንባታዎች የማካሄድ ሰራ ተጠናክሮ ሊሰራ ይገባል፡፡

የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ዘርፍ በሙያ ደረጃ ምደባና ብቃት ምዘና፣ በአሰልጣኞች ልማትና ተቋማት አቅም ግንባታ እንደዚሁም ኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዙሪያ የተለዩ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡

የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት ተደራሽነትን ለማሳደግ በሀገሪቱ ያሉ ዜጎች እኩል የሥራ እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ እና ለኢኮኖሚው እድገት አስተዋጽኦ ማድረግ እንዲችሉ ተቋማትን በዋና ዋና ወረዳዎች ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል፡፡

በከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ተደራሽነትን ለማሳደግ በመደበኛ ፕሮግራም በነባር ተቋማት 136 ሺ ተማሪዎች የተመደቡ ሲሆን የተቋማቱን የመቀበል አቅም ከማሳደግ ጎን ለጎን የ11ዱ አዲስ ዩኒቨርሲቲዎች ግንባታ ሂደት በአማካኝ 60% ለማድረስ ታቅዶ እስከ አሁን ድረስ 42 በመቶ ማድረስ ተችሏል፡፡ በዘንድሮ ትምህርት ዘመን ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከገቡ ተማሪዎች ውስጥ 42 በመቶ ሴቶች ሲሆኑ በቅድመ ምረቃ ፕሮግራሞች ላይ የሴቶች ተሳትፎ 40 በመቶ መድረስ ችሏል፡፡ የሴት መምህራንን የአመራርነት ቁጥርና ድርሻ ለማሳደግ የተለያዩ የማሳኪያ ስልቶች ተነድፈው እየተተገበሩ ይገኛሉ፡፡

በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተገቢውን የመምህራን ምጥጥን ለማረጋገጥ በዚህ ዓመት ከደረስንበት 24 ሺ አካባቢ መምህራን በ2012 ሊደረስ ከሚገባው 33ሺ መምህራን ውስጥ 30 በመቶ የሶስተኛ ዲግሪ የቀሩት ደግሞ የሁለተኛ ዲግሪ እንዲኖራቸው ታቅዶ ሥልጠናዎች እየተካሄዱ ይገኛል፡፡

የእናቶችን ጤና አገልግሎት የማሻሻል ሥራ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት መስጠትን፣ የቅድመ ወሊድ አገልግሎትንና በሰለጠነ ጤና ባለሙያ የሚሰጥ የወሊድ አገልግሎትን ያካተተ ነው፡፡ በዚህ መሠረት የዕቅዶቹ አፈፃፀም በሁሉም ከ75 በመቶ በላይ በመሆኑ ጉድለት የታየባቸውን ይበልጥ ለማሻሻል መትጋት ያለብን ይሆናል፡፡

የህጻናት ጤና ማሻሻልን በተመለከተም የክትባት መርሃ ግብር አፈጻጸም ሲታይ ዕድሜያቸው ከአንድ ዓመት በታች ለሆኑና የፀረ አምስት ሶስት ጊዜ ክትባት 95 በመቶ ማድረስ ተችሏል፡፡ በተመሳሳይ የኩፍኝ መከላከያ ክትባትን ከሚገባቸው ወደ 90 በመቶ ህፃናትን መከተብ ተችሏል:: በሌላ በኩል ሁሉንም ዓይነት ክትባት የወሰዱ ህፃናት ወደ 88 በመቶ ያህሉን አገልግሎቱን ማድረስ ተችሏል።

የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ማሻሻል ሥራ በትኩረት የተሰራ ሲሆን ከዚህ አኳያ የኤች አይቪ ኤድስ ስርጭት መቀነስና መግታት አፈጻጸም ሲታይ ባለፈው ሰባት ወር ውስጥ አገልግሎቱን ያገኛሉ ተብለው ከሚጠበቁት ውስጥ ግማሽ ያህሉ ሰዎች የምክርና ምርመራ አገልግሎት መስጠት የተቻለ ሲሆን ወደ 70 በመቶ የሚሆኑ የፀረኤች አይ ቪ መድሃኒት በመውሰድ ላይ ይገኛሉ።

የቲቢ በሽታ መከላከልና ቁጥጥር እንዲሁም የወባ በሽታን መከላከልና መቆጣጠር አፈጻጸም በሚታይበት ጊዜ አበረታች ውጤቶች የተመዘገቡበትና በአፍሪካ ደረጃም በተደረገ ውድድር ሀገራችን የተሻለ አፈፃፀም በማስመዝገብ ግንባር ቀደም ሆና የተመረጠችበት ነው፡፡ ስለሆነም ይህንኑ አስጠብቀን ለመዝለቅ መትጋት ያለብን ይሆናል፡፡

ለሴቶችና ወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ

መንግሥታችን የሴቶችና የወጣቶችን እኩል ተሳትፎና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ይረዳ ዘንድ የዕውቀትና የክህሎት አቅማቸውን የሚያጎለብት ሰፊ የትምህርትና ሥልጠና ሥርዓት በመዘርጋት እንዲሁም መልዓተህዝቡን በማሳተፍ ተንቀሳቅሷል፡፡ እስካሁን በሠራናቸው ሥራዎችም አስደናቂ ውጤቶችን አስመዝግበናል፡፡ በዚህም ከአንደኛ ደረጃ ጀምሮ እስከ ዩኒቨርሲቲ ትምህርትና ሥልጠና ያገኙ ዜጎቸ ቁጥር በእጅጉ የጨመረ ቢሆንም እነዚህን ዜጎች በኢኮኖሚው ውስጥ በሚፈጠር የሥራ ዕድል የማሰማራት ሂደት አዝጋሚ በመሆኑ የሥራ ፈላጊ ቁጥር በተደረገው ልየታ እስከ 5 ሚሊዮን አካባቢ እንደሚጠጋ ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡

ለእነዚህ ዜጎች የሥራ እድል በዋናነት በግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ እንዲፈጠርላቸው ተግተን ከምንሰራው ሥራ ባሻገር በአነስተኛና ጥቃቅን ዘርፍ ተደራጅተው ሥራ እንዲፈጥሩ የሚደረግ የድጋፍ ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ በዚህም መሠረት ምንም እንኳን ሥራው በተመኘነው ፍጥነት የተጓዘ ባይሆንም አሁን በደረስንበት ደረጃ መሠረት ተጥሏለታል፡፡ በቀጣይም የወጣቶቹን የቢዝነስ ፕላን መሠረት በማድረግ የሥልጠናና የማማከር፣ የብድር ፋይናንስና የመስሪያ ቦታዎች ዝግጅትና ከገቢያ ጋር የማስተሳሰር ዝግጅት ከወዲሁ እየተከናወነ ይገኛል፡፡ ሥራውን ለማፋጠን ይቻል ዘንድ ከልምድ ማነስ የተነሳ በጅምር አካባቢ የተፈጠረውን የመደነጋገር ሁኔታ በመቅረፍ ወደ ተግባር የምንገባበት ምዕራፍ ላይ ደርሰናል፡፡ ጉዳዩ የሚመለከተን ሁላችንም በወጣቶችና ሴቶች ዙሪያ ተከልሰው በተዘጋጁት የልማትና የእድገት ፓኬጆች መሠረት ይበልጥ በትኩረት መረባረብ ያለብን ይሆናል፡፡

 ወንድወሰን ሽመልስ

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy