Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በኢትዮጵያ በትራፊክ አደጋ የሚሞተው በበሽታ ከሚሞተው 7 እጥፍ የበለጠ ነው!

0 4,396

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በኢትዮጵያ ባለፉት 5 ዓመታት ብቻ 16 ሺህ ዜጎች በትራፊክ አደጋ ህይወታቸውን አጥተዋል፤ ከ50 ሺህ ያላነሱ ዜጎች ደግሞ ለቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት ተዳርገዋል፡፡ በ 2008 . ም ብቻ እንኳ 4351 ሞት፣ 12 ሺህ ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት መመዝገቡንና ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት መውደሙን የኢፌዴሪ ትራንስፖርት ሚኒስቴር የትራንስፖርት ባለስልጣን መረጃ ያመላክታል፡፡

አደጋውን ልዩ የሚያደርገው አነስተኛ የተሽከርካሪ ቁጥር ባለባት አገር ላይ የሚመዘገበው የትራፊክ አደጋ ከፍተኛ መሆኑና ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ መምጣቱ እንደሆነ የዘርፉ ምሁራን ያስረዳሉ፡፡

በፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን በመንገድ ትራፊክ ደህንነት ትምህርትና ግንዛቤ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዮሐንስ ለማ እንደሚሉት፤ አገሪቱ ያላት የተሽከርካሪ ብዛት ዝቅተኛና 8 ተሽከርካሪ ለ100 ሺህ ሰው ንጽጽር የሚደርስ ቢሆንም አነስተኛ መጠን ባለው ተሽከርካሪ የሚደርሰው አደጋ ግን በተቃራኒው ከፍተኛ ነው፡፡ በአደጋው ከሚሞቱ ሰዎች መካከል 48 በመቶ ከ 15 እስከ 44 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ወጣቶች በመሆናቸው፤ በትራፊክ አደጋ ምክንያት አገሪቱ ሊሠራ የሚችል አምራች ኃይል በየቀኑ እያጣች እንደምትገኝ አመላካች ነው፡፡

በዓለም በትራፊክ አደጋ ምክንያት በዓመት 1 ነጥብ 24 ሚሊዮን ሞት እንደሚከሰትና ከሚሞቱት አራት ሰዎች መካከል ሦስቱ ወንዶች መሆናቸውን ነው የሚገልጹት፡፡

አቶ ዮሐንስ ለማ እንደሚሉት፤ በአገሪቱ 95 በመቶ ወጪና ገቢ ምርቱ እንዲሁም 90 በመቶ የሰዎች እንቅስቃሴ በየብስ ትራንስፖርት መሆኑም ለአደጋው መበራከት አስተዋፅኦ ያለው ሲሆን፤ የአሽከረካሪው ስህተት፣ የእግረኞች የመንገድ አጠቃቀም ልምድ ያለመዳበር፣ የተሽከርካሪው የቴክኒክ ብቃት መጓደልና የመንገዱ ሁኔታ ምቹ አለመሆን ለአደጋዎች መከሰት ምክንያት ቢሆኑም፤ 85 ነጥብ 9 በመቶ ለሚሆነው አደጋ የአሽከርካሪው ስህተት ምክንያት በመሆኑ በአሽከርካሪው ህብረተሰብ ላይ ብዙ ሥራዎችን መሥራት ያስፈልጋል፡፡

ለእግረኛና ለተሽከርካሪ ቅድሚያ አለመስጠት፣ ርቀትን ጠብቆ አለማሽከርከርና በሕግ ከተፈቀደው ፍጥነት በላይ ማሽከርከር በግንባር ቀደምነት የሚጠቀሱ የአሽከርካሪው ስህተቶች ሲሆኑ፤ ከሚደርሰው አደጋም 60 ነጥብ 3 ይሸፍናሉ፡፡ በተመሳሳይ እግረኛው በጥንቃቄ አለመጓዝ፣ ማቋረጫዎችን በአግባቡ አለመጠቀም፣ መስመሩን አለመያዝ፣ ተሽከርካሪን አቅልሎ መመልከት፣ ግራና ቀኙን ሳያስተውል ማቋረጥ ለችግሩ መባባስ ምክንያት ናቸው የሚሉት አቶ ዮሐንስ፤ በእግረኛ መንገድ ላይ ከተሽከርካሪ በተቃራኒው መጓዝ፣ የማቋረጫ ድልድዮችን መጠቀም፣ ዜብራ የተሰመረባቸውና የትራፊክ መብራቶች ያሉበትን አካባቢ መጠቀም እንዲሁም ቀጥተኛ፣ ግልጽ ሁሉንም ሊያሳይ የሚችል መንገድ መምረጥ ከአደጋው ህይወትንና ንብረትን ለመታደግ ይረዳል ባይ ናቸው፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ረዳት ኢንስፔክተር አሰፋ መዝገቡ ስለ ትራፊክ አደጋ ብዙ እየተባለና የግንዛቤ ሥራዎችም እየተሰሩ ባለበት ሁኔታ አደጋው ሊቀንስ ያልቻለውና በከፍተኛ ሁኔታ እየተባባሰ የመጣው ህግ የማወቅና ያለማወቅ ችግር ሳይሆን የስነምግባር ጉድለት መሆኑን ገልፀው፤አደጋው ሲደርስ የደረሰባቸውም ሆኑ አደጋውን አድራሹ ሰው የማዘን ስሜታ ቢታይባቸውም ቀደመው ሲጠነቀቁ ግን አይስተዋልም ብለዋል፡፡

አደጋውን አስመልክቶ የሚከናወኑ የግንዛቤ ፈጠራ ስራዎች በአንድ አቅጣጫ ማለትም አጋር አካላት ላይ ብቻ ትኩረት አድርገው መሰራታቸው ህዝቡ ጉዳዩን በመገንዘብ በባለቤትነት እንዲይዘው አላደረገም የሚሉት ኢንስፔክተሩ፤ በጉዳዩ ዙሪያ በሚዘጋጁ መድረኮች ላይ መሳተፍ ያለበት ከአጋር አካላት ባሻገር የችግሩ ሰለባ እየሆነ ያለው የህብረተሰብ ክፍል ሊሆን እንደሚገባና መረጃው ከመንግስት ወደ ህዝብ በቀጥታ የሚተላለፍበት ሁኔታ ሊፈጠር ይገባል ባይ ናቸው፡፡

እንደ ኢንስፔክተሩ ገለጻ፤ አደጋው ከሰው ህይወት ማጥፋት ባሻገር የሚፈጥረው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ከፍተኛ ሲሆን፤ አንድ ሹፌር አደጋ ሲያደርስ በእርሱ ላይ ከሚፈጠሩ ችግሮች ባሻገር በስሩ የሚተዳደሩ ቤተሰቦችና የእርሱን ድጋፍ የሚሹ አካላት ጭምር ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ይዳረጋሉ፡፡ በመሆኑም ጉዳዩን በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው የሃይማኖትና የትምህርት ተቋማት ጭምር ትኩረት ሰጥተው የችግሩን አስከፊነትና የሚያመጣውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ በስፋት ሊያስተምሩ ይገባል፡፡

የፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ካሳሁን ኃይለማርያም፤ አደጋው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ በመምጣቱ የህይወት መጥፋት ከማስተከሉ ባሻገር በአገሪቱ ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖም እየፈጠረ ነው፡፡ በፍጥነት በማደግ ላይ ከሚገኘው ኢኮኖሚ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተሽከርካሪ ወደ አገር ውስጥ እየገባ በመሆኑና ይህም ለትራፊክ አደጋ ተጋላጭነት ስለሚጨምር ህብረተሰቡ ተገቢውን ግንዛቤ ካላገኘና አደጋውን መቀነስ ካልተቻለ አገሪቱ የምታጣው ሀብት ከፍተኛ ይሆናል፡፡ በተለይ የችግሩ ሰለባ የሆነው ከ15 እስከ 29 ዓመት ዕድሜ ያለው ወጣት መሆኑ አገሪቱ ትምህርታቸውን አጠናቀው የተመረቁና ብዙ መሥራት የሚችሉ ኃይሎችን እንድታጣ እያደረገ ይገኛል፡፡

ወጣትነት ከሚፈጥረው የችኩልነት ስሜትና ካለመረጋጋት ባሻገር ተሽከርካሪው የሚሰጠውን ተጨማሪ ኃይል ለመቆጣጠር አለመቻል ለአደጋ ተጋላጭነቱን እያባባሰው እንደሚገኝ የሚናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ፤ የወጣትና የሴቶች እንዲሁም የአካል ጉዳተኞችን የሚመለከቱ ተቋማት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው መሥራት ይጠበቅባቸዋል፤ የመንገድ ትራፊክ አደጋ የትራንስፖርት ባለስልጣኑ፣ የትራፊክ ፖሊስ ድርሻ ተደርጎ ከተወሰደ ችግሩ ሊቀንስ አይችልም፤ በመሆኑም የሃይማኖት አባቶች፣ ወጣቱ፣ሕፃናትና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ጉዳዩን በባለቤትነት ሊሠሩት እንደሚገባና በተለያዩ ቦታዎች የትራፊክ ፍሰቱን ለማገዝና እግረኞችን ለማስተማር የሚሠሩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጭ ወጣቶች ሊበራከቱ ይገባል ባይ ናቸው፡፡

የአዲስ አበባ አሽከርካሪ ተሽከርካሪ ፍቃድ እና ቁጥጥር ባለስልጣን ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ታምሩ ፉፋ እንደሚያስረዱት፤ በአገሪቱ የሚገኙ ተሽከርካሪዎች ህጋዊ በሆነ መልኩ መንጃ ፈቃድ ያላቸው እንዳሉ ሁሉ ህገወጥ በሆነ መልኩ ሀሰተኛ ሰነድ የያዙና መንጃ ፈቃዱም የሌላቸው የሚገኙ በመሆኑ አደጋዎች ተበራክተው ይስተዋላል፤ ሆኖም የትምህርት አሰጣጡ ጥራቱን የጠበቀ እንዲሆን ፤ በአግባቡ በማይሠሩ ላይ ደግሞ አስተማሪ ዕርምጃዎችን በመውሰድ ችግሩን ለማቃለል ጥረት እየተደረገ ነው፡፡

የመድን ፈንድ አስተዳደር ኤጀንሲ የህግ ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሐሰን ሙሐመድ፤ በአገሪቱ የተሽከርካሪ አደጋ ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ በተሽከርካሪ ባለቤት፣ በተጎጂ፣ በሟች ቤተሰብና በአገር ኢኮኖሚ ላይ ተፅዕኖ እየፈጠረ ሲሆን፤ ከአደጋ በኋላ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎችም አስፈላጊውን የአስቸኳይ ህክምና ዕርዳታ ባለማግኘታቸው በቀላሉ ሊድኑ የሚችሉት ህይወታቸውን ሲያጡ ይስተዋላል ይላሉ፡፡

እንደ አቶ ሐሰን ገለጻ፤ የሦስተኛ ወገን የመድን ሽፋን በተጎጂዎች ላይ የሚደርስን መጉላላት ለማስቀረት ካሳና ህክምና የማግኘት መብት ቢያጎናጽፍም በግንዛቤ እጥረት ምክንያት አደጋ ደርሶበት የተሽከርካሪውን ሰሌዳ ቁጥር ባለመያዙ ወይም ማንነቱ ባለመታወቁ ምክንያት ተገቢውን ካሳና ህክምና ሳያገኙ የቀሩ በርካቶች ናቸው፡፡ ስለዚህም ህብረተሰቡ ጥንቃቄ በማድረግ እንዲንቀሳቀስና ከአደጋ ራሱን እንዲጠብቅ፤ እንዲሁም አደጋ ሲከሰት መረጃ የመያዝና ለሚመለከተው አካል በመግለጽ ትብብር የማድረግ ባህል እንዲያዳብር መክረዋል፡፡ዑመር እንድሪስ

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy