Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በኦሮሚያ የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ ለላቀ ፍሬ እንዲበቃ ህዝቡ ከጎኑ ተሰልፎ የድርሻውን እንዲወጣ ኦህዴድ ጥሪ አቀረበ

0 560

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በኦሮሚያ ክልል የተጀመረው የለውጥና የመታደስ እንቅስቃሴ ለላቀ ፍሬ እንዲበቃ ህዝቡ ከጎኑ ተሰልፎ የድርሻውን  እንዲወጣ የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) ጥሪ አቀረበ። የኦህዴድ 27ኛው የምስረታ በዓል ዛሬ በአዳማ ገልመ አባገዳ አዳራሽ በድምቀት ተከብሯል።

የኦህዴድ ሊቀመንበር አቶ ለማ መገርሳ በበዓሉ ላይ እንደገለጹት  ድርጅቱ ከህዝብ አብራክ ተወልዶ ያደገ በመሆኑ የኦሮሞ ሕዝብን መብትና ተጠቃሚነትን ለማጎልበት ቅድሚያ ሰጥቶ ሰፊ ርብርብ ማድረጉን ይቀጥላል።

“ወቅቱ በየደረጃው ጥልቅ ተሀድሶ የተካሄደበት አዲስ ምዕራፍ ላይ የምንገኝበት ስለሆነ በቀጣይ በሁሉም መስክ ውጤታማ ተግባራትን ለማከናወን በጋራ መነሳት ያስፈልጋል “ብለዋል።

“በተሀድሶ ውስጥ ሆነን በዓሉን ስናከበር ህዝቡ ከኛ ብዙ እንደሚጠብቅ በመገንዘብ  ነው ” ያሉት ሊቀመንበሩ ህዝቡን ለመካስ ድርጅቱ ጠንክሮ የሚሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

በተሀድሶው በየደረጃው የሚገኘው መዋቅር በአዲስ መልክ የተደራጀ መሆኑን አመልክተው ህዝቡንም በተቀናጀ አግባብ በማንቀሳቀስ የህዳሴውን ጉዞ የሚያደናቅፉ  የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባራትን ለመዋጋት ርብርብ እንደሚደረግም ተናግረዋል።

ባለፉት ዓመታት የተገኙትን ድሎች በመገምገም ጠንካራ ጎኖችን ለማስቀጠል እንዲሁም በሂደቱ ያጋጠሙ እጥረቶችን ለማስወገድ በሚደረገው እንቅስቃሴ ህዝቡ ከድርጅቱ ጎን ተሰልፎ የድርሻውን እንዲወጣ  ሊቀመንበሩ ጥሪ አቅርበዋል።

በክልሉ የሚኖሩ ብሔር ብሔረሰቦችም በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ኋላ ሳይሉ ለክልሉ ሰላምና ልማት መረጋገጥ በቅርበት ሆነው የድርሻቸውን  እንዲወጡም ጠይቀዋል።

የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ በከር ሻሌ በበኩላቸው ድርጅቱ 27ኛ ዓመቱን ሲያከብር እድሜ ለማስቆጠር ሳይሆን ከየት ተነስቶ ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ  ራሱን ፈትሾ በቀጣይ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የሚነሳሳበት መሆኑን ተናግረዋል።

አቶ በከር የክልሉን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ የሚያመላክት ጽሁፍ አቅርበው በመድረኩ ተሳታፊዎች  ውይይት ተደርጎበታል።

የበዓሉ ታዳሚና የአሰላ ከተማ የአገር ሽማግሌ አቶ ደበሌ ዋሚ ከለቻ በሰጡት አስተያየት “መንግስት ኪራይ ሰብሳቢነት፣ ሙስናንና አድሎአዊ አሰራር ለማስወገድ የተነሳሳበት ወቅት በመሆኑ ከድርጅቱ ጎን እንቆማለን” ብለዋል።

ሌላዋ የበዓሉ ታዳሚ የጦር ኃይሎች ሆስፒታል ነርስ ሻለቃ አበራሽ ደረሰ በበኩላቸው ድርጅቱ ህዝብ እንዲያስተካክል ያቀረበለትን ጥያቄ ተቀብሎና አርሞ  በዓሉን ለማክበር በመብቃቱ የሚያስደሰት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

“በቀጣይ ለክልሉ ሰላም፣ልማትና እድገት መረጋገጥ ሁላችንም ከድርጅቱ ጋር ሆነን በቁርጠኝነት ልንሰራ ይገባል “ብለዋል።

በበዓሉ ላይ አባገዳዎች፣የሀይማኖት አባቶች፣ከክልሉ ሁሉም ዞኖች የተውጣጡ ጥሪ የተደረገላቸው አካላት፣የአዳማ ከተማ ነዋሪዎች፣የድርጅቱ አባላትና ደጋፊዎች ተሳትፈዋል፡፡

ትናንት ምሽት በገልመ አባገዳ አዳራሽ አቅራቢያ በሚገኘው የሰማዕታት ሐውልት ስር በትግሉ ለተሰው ሰማዕታት የህሊና ጸሎትና የሻማ መብራት ሥነ ሥርዓት ተካሂዷል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy