Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በ15 ሲኖትራኮች የ40/60 ቤቶችን ብረት መዝረፉን አምኗል የተባለ ሠራተኛ የ11 ዓመት ጽኑ እስራት ተወሰነበት

0 613

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ለ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ የሚውሉ የተለያየ መጠን ያላቸውን ብረቶች በ15 ሲኖትራኮች ጭኖ መዝረፉን (መውሰዱን) አምኗል የተባለ የአዲስ አበባ ከተማ ሠራተኛ፣ በ11 ዓመታት ጽኑ እስራትና በ7,000 ብር እንዲቀጣ ውሳኔ ተሰጠ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ የግብዓት፣ ክምችትና ሥርጭት ኦፊሰር የነበረው አቶ ተስፋለኝ በቀለ ድርጊቱን መፈጸሙን በፍርድ ቤት ሙሉ በሙሉ በማመኑ፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት የቅጣት ውሳኔውን እንዳስተላለፈበት ገልጿል፡፡

ከተስፋለኝ ጋር የወንጀል ድርጊቱን ፈጽመዋል በማለት የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ክስ የመሠረተባቸው ዳርሰማ ዳኦ፣ ስንታየሁ ተስፋዬ፣ አበበ ተስፋዬ፣ ልዑል ፈቃዱ፣ አሸናፊ ረታና ኢዮስያስ ዓለሙ ናቸው፡፡ ድርጊቱን እንዳልፈጸሙ ክደው በመከራከራቸው ዓቃቤ ሕግ የሰነድና የሰው ምስክሮቹን አቅርቦ እንዲያሰማ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ታኅሳስ 10 ቀን 2009 ዓ.ም. ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 15ኛ ወንጀል ችሎት ያቀረበው ክስ እንደሚያስረዳው፣ ተከሳሾቹ የዝርፊያ ወንጀሉን የፈጸሙት ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ መጋዘን ነው፡፡ መጋዘኑ የሚገኘው በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስድስት ውስጥ ሲሆን፣ ተከሳሾቹ ድርጊቱን የፈጸሙት ኅዳር 10 ቀን 2009 ዓ.ም. ከቀኑ ሰባት ሰዓት እስከ 10 ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ መሆኑንና የብረቱም ግምት ከ6.4 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡

ኦፊሰሩ ጥቅም ለማግኘትና ለሌሎቹም ለማስገኘት በማሰብ ግምቱ 6,407,229 ብር የሆነ ባለ ስድስት ዲያሜትር 55 ጥቅልና ባለ ስምንት ዲያሜትር 73 ጥቅል የመንግሥት ብረት፣ በ15 ሲኖትራኮች በማስጫን እንዲዘረፍ ማድረጉ በክሱ ተገልጿል፡፡

ዳርሰማና ስንታየሁ በ15 ሲኖትራኮች የተጫነውን ብረት ሞጆ ሳይት ፉሪ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኘው ዳርሰማ በተባለው ተከሳሽ መጋዘን ውስጥ እንዲራገፍ ማድረጋቸውም ተጠቁሟል፡፡ ብረቱን ከኢንተርፕራይዙ መጋዘን ያወጡት በሐሰተኛ ሰነድ ተጠቅመው መሆኑም ተገልጿል፡፡

ተከሳሾቹ የብረቱን ምንጭና የባለቤትነት መብት እንዳይታወቅ ከማድረጋቸውም በተጨማሪ፣ ዳርሰማ ከሕግ ተጠያቂነት እንዲያመልጥ ስንታየሁ ሞጆ ሳይት ከሚገኘው መጋዘን የተራገፈውን ብረት በ11 ሲኖትራኮች በማስጫን ሰበታ የሚገኘው የግሉ ፕላስቲክ ፋብሪካ መጋዘን ማስተላለፉን ክሱ ያብራራል፡፡

አበበ ተስፋዬ የወንጀሉ ድርጊት እንዲፈጸም ሲያመቻች፣ አሸናፊ ደግሞ በሁለት ሲኖትራኮች የቀረበለትን ብረት በመግዛት አዳማ በሚገኘው የግል የንግድ ድርጅቱ ውስጥ ማስቀመጡን ክሱ ይጠቁማል፡፡ ኢዮስያስ ደግሞ የተሸጠለትን 1,932 ኩንታል ብረት በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ‹‹ጭድ ተራ›› በሚገኘው ንግድ ድርጅቱ ውስጥ ማስቀመጡን ክሱ ያብራራል፡፡

በአጠቃላይ ተከሳሾቹ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 (1ሀ እና ለ)ን፣ 33 እና የሙስና ወንጀሎች አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 31(2)ን፣ ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 780/2005 እና አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 23(2ሀ) ላይ የተደነገገውን ተላልፈው በመገኘታቸው በፈጸሙት ከባድ የእምነት ማጉደል ሙስና ወንጀል፣ በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ (ንብረት) ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ የሙስና ወንጀልና መንግሥታዊ ሰነዶችን አስመስሎ ማዘጋጀትና መገልገል የሙስና ወንጀል ክስ እንደተመሠረተባቸው መዘገባችን ይታወሳል፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy