Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ተቋርጦ የነበረው ኤታኖልን ከቤንዚን ጋር የመቀላቀል ሥራ ተጀመረ

0 537

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

አሽከርካሪዎች በነዳጅ ማደያ ወረፋ መጉላላት ገጥሟቸዋል ካለፈው ዓመት ጀምሮ ተቋርጦ የነበረው ኤታኖልን ከቤንዚን ጋር የመቀላቀል ሥራ ከመጋቢት 7 ቀን 2009 .ም ጀምሮ መቀጠሉን የማዕድን ነዳጅና ተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር አስታወቀ። ሂደቱም በነዳጅ ማደያ አካባቢዎች ወረፋ እንዲፈጠርና አሽከርካሪዎች እንዲጉላሉ ምክንያት መሆኑ ተገለጸ።

በማዕድን ነዳጅና ተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር የባዮፊዩል ልማት ማስተባበሪያ ዳይሬክቶሬት ተወካይ አቶ ሚካኤል ገሰሰ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳመለከቱት፣ አቅርቦቱ የቀጠለው የፍንጫአ ስኳር ፋብሪካ ኤታኖል ማምረት በመጀመሩ ነው። የመተሃራ ስኳር ፋብሪካ ማሽን ቢበላሽም በቅርቡ ተጠግኖ አገልግሎት እንደሚሰጥ ታሳቢ መደረጉም ምርቱን በቀጣይነት ለማቅረብ ያስችላል።

እንደ እርሳቸው ገለፃ፤ የፍንጫአ ስኳር ፋብሪካ የሚያመርተው ኤታኖል ችግሩን በዘላቂነት ሊቀርፍ ስለማይችል የመተሃራ ስኳር ፋብሪካ ማሽን በአጭር ጊዜ ውስጥ ተስተካክሎ ሥራ ይጀምራል፡፡ ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ የስኳር ፋብሪካዎች የኤታኖል ማምረቻ ፋብሪካ እንዲኖራቸው ከስኳር ኮርፖሬሽን ጋር እየተሰራ ነው።

በሌላም በኩል በአዲስ አበባ በነዳጅ ማደያዎች በተፈጠረው የወረፋ መብዛት አሽከርካሪዎች መጉላላት እንዳጋጠማቸውም አዲስ ዘመን ጋዜጣ ያነጋገራቸው አሽከርካሪዎች ገልጸዋል፡፡ የታክሲ አሽከርካሪ የሆነው ወጣት መኳንንት መኩሪያ እንደሚለው፣ በአንዳንድ የነዳጅ ማደያዎች ጭራሹንም ነዳጅ የለም። ረጅም ርቀት ተጉዞ ነዳጅ ወደሚገኝባቸው ማደያዎች ከተሄደ በኋላም ረጃጅም ሰልፍ ያጋጥማል፡፡

ወጣት መኳንንት እንደገለጸው፣ ችግሩ ይህን ሰሞን ይባባስ እንጂ ማደያዎች ብዙ ጊዜ ‹‹ነዳጅ የለም›› እያሉ ይመልሳሉ» የወረፋ መብዛትም ያጋጥማል፡፡ ‹‹ከመገናኛ አራት ኪሎ ድረስ የመጣሁት እዚያ አጥቼ ነው፡፡ አሁንም እዚህ ከመጣሁ በኋላ ወረፋ ይዤ ቆሚያለሁ፣ ላግኝ አላግኝ እንኳን አላወቅኩትም›› የሚለው መኳንንት የተፈጠረው ችግር የገንዘብም የጊዜም ብክነት እንዳደረሰበት ይናገራል፡፡

ሌላኛው አሽከርካሪ አቶ ሙሉጌታ ገብረመድህን በበኩላቸው፣ እንዲህ ዓይነት ወረፋ ሲያጋጥም ምክንያቱ ምን እንደሆነና መቼ እንደሚፈታ በግልጽ የማይታወቅ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ‹‹ችግሩ ምን እንደሆነ አናውቅም፣ ከማደያዎች ግን ነዳጅ የለም እንባላለን›› በማለት በተፈጠረው ወረፋ ሥራ እንደፈቱም አመልክተዋል።

በነዳጅ ማደያዎች ወረፋ የበዛው ቤንዚንን ከኤታኖል በመቀላቀሉ ሂደት እንደሆነ የሚናገሩት ደግሞ በኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት የነዳጅ አቅርቦትና ሽያጭ መምሪያ ሥራ አስኪያጅ አቶ አባይነህ አወል ናቸው፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት በአቅርቦት በኩል ያጋጠመ ችግር የለም፡፡ የወረፋ ችግሩ የተፈጠረው ከመጋቢት 7 ቀን 2009 .ም ጀምሮ የነዳጅ አከፋፋይ ኩባንያዎች ቤንዚን ከኤታኖል ጋር ለመቀላቀል በሚያከናውኑት የሥራ ሂደት ነው፡፡

በሌላ በኩል አሽከርካሪዎች ረጅም ሰልፍ ሲያዩ የነዳጅ እጥረት ያለ እየመሰላቸው ለሌላ ቀን ለማስቀመጥ እንደገና ሲሰለፉ ወረፋውን እንደሚያባብሱት አቶ አባይነህ ገልጸዋል፡፡ የቤንዚንና ኤታኖል መቀላቀል ሥራው ቀልጣፋ እንደሚሆንና ችግሩ በአጭር ጊዜ እንደሚቀረፍም አመልክተዋል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy