Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ተዳፍኖ የነበረውን እሳት የጫረው ደብዳቤ

0 456

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ብሪታንያውያን ከአውሮፓ ኅብረት ለመውጣት በአብላጫ ድምፅ መወሰናቸውን ተከትሎ የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ትሬዛ ሜይ ብሪታንያ ከአውሮፓ ኅብረት ለመውጣት ይፋዊ ጥያቄ ያቀረበችበትን ደብዳቤ ለአውሮፓ ካውንስል ፕሬዚዳንት ዶናልድ ተስክ ልከዋል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትሯ ተፅፎ በአውሮፓ ኅብረት የብሪታንያ አምባሳደር በሆኑት ሰር ቲም ባሮው በኩል ዶናልድ ተስክ እጅ የገባው የባለ ስድስት ገፁ ደብዳቤ መላክም የህዝበ ውሳኔው ተግባራዊነት የመጀመሪያ እርምጃ ተደርጎ ተወስዷል፡፡ ደብዳቤው የአውሮፓ ኅብረት አባል አገራት ከኅብረቱ ለመውጣት የሚያስችላቸውን ድንጋጌ የያዘውን የሊዝበን ስምምነት አንቀፅ 50ን ለመተግበር የሚያስችል እርምጃ ነው፡፡

ለወትሮውም ቢሆን ለበርካታ ወሳኝ ጥቄዎች በቂና አሳማኝ ምላሽ ያልሰጠ ውሳኔ ነው ተብሎ የተተቸው የብሪታንያውያን ህዝበ ውሳኔ አሁን ደግሞ ሌሎች ግዙፍ መዘዞችን ይዞ ብቅ ብሏል፡፡ በተለይ እ..አ በ2014 ከብሪታኒያ ለመነጠል ህዝበ ውሳኔ አካሂዳ የታላቋ ብሪታንያ ኅብረትን ከመበታተን ለጥቂት ያየተረፈችው ስኮትላንድ ዳግም ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ የአገሪቱ ፖለቲከኞች በአብላጫ ድምፅ መወሰናቸው ከይፋዊ ጥያቄው መዘዞች ግንባር ቀደሙ ተብሏል፡፡

የስኮትላንድ ቀዳማዊት ሚኒስትር ኒኮላ ስተርጀን ያቀረቡትን ጥሪ ተከትሎ የአገሪቱ የተወካዮች ምክር ቤት አባላት ብሪታኒያ ከአውሮፓ ኅብረት ጠቅልላ እስከምትወጣበት ቀነ ገደብ ባሉት ሁለት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ በአብላጫ ድምፅ ወስነዋል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ትሬዛ ሜይ ደብዳቤ ብራሰልስ ከመድረሱ አንድ ቀን ቀደም ብሎ የተከናወነውና 69 59 በሆነ ድምፅ የተላለፈው ይህ ውሳኔ በስኮትላንድና በብሪታኒያ መንግሥት መካከል ውይይት እንዲደረግ ምክንያት እንደሚሆንም ተገልጿል፡፡

የአልጀዚራው ዘጋቢ ኒቭ ባርከር ከለንደን ባሰራጨው ዘገባ፣ የተወካዮች ምክር ቤት ውሳኔው እ..አ በ2014 የስኮትላንድን ከብሪታኒያ መነጠል ደግፈው ሃሳባቸው በአብላጫ የህዝበ ውሳኔ ድምፅ ውድቅ የሆነባቸው አካላት “መልካም አጋጣሚ” ሲሆን የብሪታኒያን ከአውሮፓ ኅብረት መውጣት ለሚፈልጉ ወገኖች ደግሞ “ትልቅ ራስ ምታት” ነው ብሏል፡፡

የስኮቲሽ ብሔራዊ ፓርቲ መሪ ቀዳማዊት ሚኒስትር ኒኮላ ስተርጀን ብሪታኒያ ከአውሮፓ ኅብረት የመውጣቷን ሃሳብ አስመልክቶ ላሰሙት ተደጋጋሚ ተቃውሞ ወግ አጥባቂው የጠቅላይ ሚኒስትር ትሬዛ ሜይ መንግሥት ያሳየውን “ግትር” አቋምም በፅኑ አውግዘውታል፡፡

የስኮትላንድ መፃዒ እድል በስኮትላንዳውያን ሊወሰን ይገባል” በማለት ፈርጠም ብለው የተናገሩት ቀዳማዊት ሚኒስትር ኒኮላ ስተርጀን፣ ከብሪታኒያ መንግሥት ጋር መደራደር ለስኮትላንድ ዕጣ ፋንታ አስፈላጊ እርምጃ እንደሆነም ለተወካዮች ምክር ቤት አባላት ነግረዋቸዋል፡፡ የምክር ቤቱ ቀጣይ እርምጃ ምን መሆን እንደሚገባው በቀጣዩ ወር እንደሚያሳውቁም ቃል ገብተዋል፡፡

ይሁን እንጂ የስኮትላንድ ምክር ቤት አባላት ውሳኔውን ማፅደቃቸውን ተከትሎ ወዲያውኑ መግለጫ ያወጣው የጠቅላይ ሚኒስትር ትሬዛ ሜይ መንግሥት ይደረግ የተባለውን ህዝበ ውሳኔ አስመልክቶ ከስኮትላንድ ጋር ድርድር ለማድረግ ፈቃደኛ እንዳልሆነ አስታውቋል፡፡

ብሪታኒያ ከአውሮፓ ኅብረት ጋር የሚኖራት ቀጣይ ግንኙነት እንዲሁም ከብሪታንያ የተነጠለች ስኮትላንድ ምን እንደምትመስል በግልፅ ባልታወቀበት በአሁኑ ወቅት ስኮትላንዳውያን ህዝበ ውሳኔ እንዲያደርጉ መፍቀድ ተገቢ ያልሆነ አካሄድ ነው በማለት ለንደን ኤደንብራን ወቅሳለች፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ትሬዛ ሜይ በበኩላቸው ለአውሮፓ ካውንስል ፕሬዚዳንት የተላከውንና የህዝበ ውሳኔው ተግባራዊነት የመጀመሪያ እርምጃ ተደርጎ የተቆጠረውን ደብዳቤ አስመልክቶ ባሰሙት ንግግር፣ “እርምጃው ሊቀለበስ የማይችል ታሪካዊ አጋጣሚ ነው” በማለት ከስኮትላንድ የቀረበባቸውን ተቃውሞ በተቃውሞ መልሰውታል፡፡ ይልቁንም “የብሪታንያ መንግሥት የብሪታኒያን ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ፍላጎት እውን ለማድረግ የጀመረው ተግባርና ለብሪታንያ ብሩህ መፃኢ ጊዜ መሰረት የሚሆን ልዩ አጋጣሚ” ሲሉ ያንቆለጳጰሱት ይህ እርምጃ፣ ለአገሪቱ አንድነት የሚበጅ መልካም እድል እንደሆነም በልበሙሉነት ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡

በተጨማሪም፣ ምንም እንከን የማይወጣለት ፍፁም እርምጃ አድርገው ያቀረቡትን የአንቀፅ 50 ትግበራ ጅማሬውን “ጠንካራና ፍትሐዊ የሆነች እንዲሁም ልጆቻችንና የልጅ ልጆቻችን የሚኮሩባት ብሪታንያን ለመገንባት የሚያስችል ልዩ እድል” በማለትም የምስጋና ብዛት አዝንበውበታል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትሯ፣ “ህዝበ ውሳኔውን ተግባራዊ ለማድረግ ከፊት ለፊታችን ያሉብንን ትልልቅ ስራዎች በማሰብ ወደኋላ ልንመለከት እንችላለን፤ አልያም የመጪውን ጊዜ ብሩህነት አስበን በብሪታንያዊነት መንፈስ ጉዟችንን ወደፊት ለማድረግ እናስብ ይሆናል፤ እኔ በበኩሌ በብሪታንያ በማመን ወደፊት ስለሚጠብቁን ብሩህ ጊዜያት ማሰብንና መጓዝን መርጫለሁ” በማለት አገሪቱ ከኅብረቱ ለመነጠል የጀመረችውን እንቅስቃሴ እውን ለማድረግ እየሰሩ ስለመሆናቸው ተናግረዋል፡፡

ከኤደንብራ ሆኖ ለአልጀዚራ የሚዘግበው ናዲም ባባ ስኮትላንዳውያን በለንደንና ኤደንብራ እሰጥ አገባ ግራ መጋባታቸውን ገልጿል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ስኮትላንዳውያን በዚህ ወቅት አጥብቀው የሚሿቸው ነገሮች፣ ብሪታንያ ወደፊት ከአውሮፓ ኅብረት ጋር ስለሚኖራት ግንኙነትና ከሌሎቹ የብሪታንያ ኅብረት አባላት (እንግሊዝ፣ ዌልስና ሰሜን አየርላንድ) ጋር በአውሮፓ ኅብረት የንግድ ኅብረት ጥላ ስር መቆየት ስለሚኖረው ፋይዳ በግልፅ ማወቅ እንደሆነም ዘግቧል፡፡

የአውሮፓ ካውንስል ፕሬዚዳንት ዶናልድ ተስክ የጠቅላይ ሚኒስትሯን ደብዳቤ ከተቀበሉ በኋላ ዕለቱ ለእርሳቸውም ሆነ ለአውሮፓ ኅብረት አስደሳች ቀን እንዳልሆነ በመግለፅ አገሪቱ ከኅብረቱ ለመውጣት የሚያስችላትን ድርድር ኅብረቱ እንደሚጀምር ቃል ከገቡ በኋላ “ትናፍቁናላችሁ፤ እናመሰግናለን፤ ደህና ሁኑ” በማለት የብሪታንያን ከአውሮፓ ኅብረት መውጣት የሚቃወሙ አካላትን ሆድ የሚያባባ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሯ እንከን የማይወጣለትና ፍፁም አስመስለው ያቀረቡት የህዝበ ውሳኔው ትግበራ የመጀመሪያ እርምጃን ያብጠለጠሉት ፖለቲከኞች ደግሞ ቁጥራቸው ቀላል የሚባል አይደለም፡፡

የሌበር ፓርቲ መሪ ጀርሚ ኮርቢን ብሪታንያ ከአውሮፓ ኅብረት ጋር በምታደርገው ድርድር አገሪቱ በኅብረቱ ገበያዎች ተጠቃሚ እንድትሆንና የሰራተኞች መብቶች እንዲከበሩ የጠቅላይ ሚኒስትር ትሬዛ ሜይ መንግሥት የመጨረሻ አቅሙን አሟጦ ለመጠቀም ዝግጁ ከሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሯን እንደሚደግፏቸው በቅድመ ሁኔታ የታጀበ ቃል ገብተዋል፡፡

ብሪታንያ ከመቸውም ጊዜ በበለጠ ለጥቂቶች ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ዜጎች መብትና ጥቅም መከበር የቆመ መንግሥት ያስፈልጋታል” ያሉት የፓርቲው መሪ፣ ፓርቲያቸው ለጠቅላይ ሚኒስትሯና ለመንግሥታቸው የሚያቀርበው ትልቅ ቅድመ ሁኔታም ይኸው እንደሆነ ለምክር ቤት አባላት ነግረዋቸዋል፡፡

የብሪታንያን ከአውሮፓ ኅብረት መውጣት የሚቃወሙትና የሊበራል ዴሞክራቲክ ፓርቲ መሪ ሆኑት ቲም ፋረን በበኩላቸው፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ትሬዛ ሜይ የአገሪቱን ዕጣ ፋንታ በሚገባ ሳያመዛዝኑ እተራመዱ እንደሆነ የሚገልፅ አስተያየት ሰንዝረዋል፡፡

ብሪታንያውያን ኪሳራ የሚያመጣባቸውን ስምምነት ብቻ ሳይሆን ከኅብረቱ የመውጣትን ውሳኔ ከነአካቴው የመቀልበስ መብት እንዳላቸው የተናገሩት የፓርቲው መሪ ትሬዛ ሜይ ወግ አጥባቂ ፓርቲ ይህን አገር አጥፊ የሆነ ውሳኔ ለመተግበር ሲሯሯጥ የሌበር ፓርቲ የሚቸራቸው ድጋፍ አሳዛኝ እንደሆነም በምሬት ተናግረዋል፡፡

..አ በ2014 ስኮትላንድን ከብሪታንያ የመነጠል ህዝበ ውሳኔ በተደረገበት ወቅት የመነጠሉን ጎራ እየመሩ ሽንፈት የተጎነጩት የስኮቲሽ ብሔራዊ ፓርቲ የውጭ ጉዳዮች ቃል አቀባይ አሌክስ ሳልመንድ ብሪታንያን ከአውሮፓ ኅብረት ለማስወጣት ሽር ጉድ ሲሉ በእንግሊዝ፣ በሰሜን አየርላንድ፣ በዌልስና በስኮትላንድ ያሉ ፖለቲካዊ ሁኔታዎችን ግን አለማጤናቸው እንዳስገረማቸው ተናግረዋል፡፡

ከብሪታንያ ኅብረት አባላት መካከል የብሪታንያ ከአውሮፓ ኅብረት የመውጣት ሃሳብን በደገፉት እንግሊዝና ዌልስ የህዝበ ውሳኔውን ውጤት በተቃወሙት ሰሜን አየርላንድና ስኮትላንድ መካከል ያለው ግንኙነትም ብዙዎችን ስጋት ላይ ጥሏል፡፡

ብሪታንያ ከአውሮፓ ኅብረት ለመውጣት በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ከኅብረቱ ጋር ዘርፈ ብዙ ድርድሮችን ታደርጋለች፡፡ ይሁን እንጂ ከስኮትላንድ ጉዳይ ባሻገር ህዝበ ውሳኔውም ይሁን ውሳኔውን ለመተግበር የመጀመሪያ ደረጃ እርምጃ ተደርጎ የተቆጠረው የጠቅላይ ሚኒስትር ትሬዛ ሜይ ደብዳቤ ያልመለሷቸው በርካታ ጥያቄዎች ስለመኖራቸው የሚናገሩ ፖለቲከኞችና ልዩ ልዩ አካላት ቁጥራቸው የበዛ ነው፡፡

ንግድ፣ የሌሎች አገራት ዜጎች፣ የሰሜን አየርላንድ ድንበር፣ ፀጥታና የሽግግር መዋቅር አገሪቱና ኅብረቱ ከሚደራደሩባቸው ጉዳዮች መካከል በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡ ትሬዛ ሜይ ከኅብረቱ ጋር በሚደረጉ ድርድሮች መንግሥታቸው ለእያንዳንዱ ዜጋ ፍላጎትና ጥቅም እንደሚቆም ቃል ገብተዋል፡፡

ይሁን እንጂ የብሪታንያን ከአውሮፓ ኅብረት የመውጣት እቅድን ገና ከጅምሩ በጥብቅ የተቃወሙ አካላት በብሪታንያውያን ህዝበ ውሳኔ ላይ ብሎም በብሪታኒያ መፃኢ እድል ላይ ትልቅ ተፅዕኖ እንደሚኖረው እየተገለፀ ይገኛል፡፡

በሊዝበን ስምምነት አንቀፅ 50 ድንጋጌ መሰረት ብሪታንያና ሌሎቹ የኅብረቱ አባል አገራት የድርድሩን ጊዜ ካላራዘሙት በስተቀር እ..አ መጋቢት 29 ቀን 2019 አገሪቱ ጓዟን ጠቅልላ ከአውሮፓ ኅብረት የምትወጣበት የመጨረሻው ቀን ይሆናል፡፡

– See more at: http://ethpress.gov.et/addiszemen/index.php/news/herald-guest/item/11981-2017-03-31-18-34-48#sthash.S3dHgKF6.dpuf

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy