Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ትግራይ ክልል ችግር የታየባቸው 444 የሚሆኑት ከጽሁፍ ማስጠንቀቂያ እስከ ማሸግ የደረሰ እርምጃ መወሰዱን ገልጸዋል ፡፡

0 1,634

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የትግራይ ክልል ጤና ቢሮ የህብረተሰቡን ጤና በሚጎዳ መልኩ ጤናና ጤና ነክ አገልግሎት ሲሰጡ አግኝቻቸዋለሁ ባላቸው ተቋማት ላይ እርምጃን መውሰዱን አስታወቀ፡፡

በትግራይ ጤና ቢሮ የምግብ፣ የመድሀኒትና የጤና እንክብካቤ ቁጥጥር የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ባህረ ተካ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት፤ በክልሉ የሚገኙ 3 ሺህ 999 ሆቴሎች ፣ ምግብ ቤቶች ፣ሬስቶራንትና ካፍቴሪያዎች ላይ የቁጥጥር ስራ ተካሂዷል፡፡

በቁጥጥር ሂደቱ ችግር የታየባቸው 444 የሚሆኑት ከጽሁፍ ማስጠንቀቂያ እስከ ማሸግ የደረሰ እርምጃ መወሰዱን ገልጸዋል ፡፡ከዚህ ቀደም የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸውም ማረም ባልቻሉ 14 ጤና ነክ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ደግሞ ፈቃዳቸው እንዲነጠቅ መደረጉን አቶ ባህረ ተናግረዋል፡;

የአገልግሎት ጊዜያቸው ያለፈባቸው መድሀኒቶችንም ሲሸጡ እና ከተሰጣቸው ሀላፊነት ውጭ መርፌ የመውጋት አገልግሎት ሲሰጡ የተገኙ የመድሀኒት መደብሮችም እርምጃ ከተወሰደባቸው ውስጥ እንደሚገኙ የጠቀሱት አቶ ባህረ፤ ተቋማቱ ላይ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችሉ 4 መመዘኛ መስፈርቶችን በመያዝ ቢሮው ወደ እርምጃ መግባቱን ጠቅሰዋል፡፡

የልዩ ክሊኒክ ፈቃድ በተሰጣቸውና የመጀመሪያ ደረጃ ባላቸው ክሊኒኮች እንዲሁም በመድሀኒት ቸርቻሪ መደብሮች ላይም ተመሳሳይ እርምጃ ተወስዷል ብለዋል።
መድሀኒት የመሸጥ ፍቃድን ወስደው ሀላፊነት በጎደለው መልኩ መርፌ የመውጋት አገልግሎትን ሲሰጡ ሁለት መድሀኒት መሸጫ መደብሮች ተገኝተው እስከ ሁለት አመት የታገዱ ሲሆን፤እነዚህ መደብሮች ከዚህም በላይ ጊዜው ያለፈበት መድሀኒትን ለገበያ ሲያቀርቡም በመያዛቸው መሆኑን የስራ ሂደት አስተባባሪው ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል 23 የመጀመሪያ ክሊኒኮች የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው ሲሆን የገንዘብና አስተዳደራዊ እርምጃዎችም ተወስዶባቸዋል ።

ክሊኒኮቹ እርምጃው የተወሰደባቸው አንድ ክሊኒክ ማሟላት ባለበት መስፈርት ተለክተው ያሉት አስተባባሪው ፤ ክሊኒኮቹ በአገልግሎት መስጫ ህንጻቸው ፣በሰው ሀይላቸው እና በተቀመጠላቸው የአገልግሎት አሰጣጥ መስፈርት እንዲሁም በተግባራዊ እንቅስቃሴያቸው አፈጻጸማቸው ዝቅ ያለ በመሆኑ ነው ብለዋል።እነዚህ ተቋማት በተሰጣቸው ማስጠንቀቂያ መሰረት አሰራራቸውን ካላስተካከሉ ተከታይ እርምጃ የሚወሰድባቸው መሆኑን ጠቁመዋል ።

አስተያየታቸውን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የሰጡ የክልሉ ነዋሪዎች በበኩላቸው የተወሰደውን እርምጃ አድንቀው ሆኖም እርምጃው የዘመቻ ስራ መሆኑ ግን ውጤታማ እንደማያደርገው ነው የተናገሩት።

የጤና ጉዳይ ከምንም በላይ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ በመሆኑም የቁጥጥር ስራው ቋሚ ጊዜ ተመድቦለት ለውጥ በሚያመጣ መልኩ የክትትል ስራዎች ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።

በተለይም በሆቴልና በሬስቶራንት መስተንግዶዎች ላይ ሰፊ ከንጽህና ጉድለት የሚመነጩ ከፍተኛ የጤና እክሎችን ሊፈጥሩ የሚችሉ ችግሮች በተጨባጭ እንዳሉም ነዋሪዎቹ ያነሱ ሲሆን፤በምግብ ዝግጅት ወቅት ከማብሰያ ስፍራ ጀምሮ እስከ መጸዳጃ ቤት ድረስ ያሉ ችግሮች በቀጣይ ሊታሰብባቸው ይገባል ብለዋል።የትግራይ ክልል ጤና ቢሮ የክትትልና ድጋፍ እንዲሁም የቁጥጥር ተግባሩ በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ስራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቋል፡፡ FBC

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy