Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

አስተማማኝ ሰላምና መስተንግዶው ቱሪስቶችን መሳቡን ቀጥሏል

0 524

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ኢትዮጵያን ሲጎበኙ ለሦስተኛ ጊዜ ነው፡፡ በመጀመሪያው ጉብኝታቸው እንደ እአአ በ2003 የላሊበላ ውቅር አቢያተ ክርስቲያናትን፣ የአክሱም ሐውልቶችን እና የአክሱም ጽዮን ቤተክርስቲያን፣ የጎንደር ቤተ መንግሥት እንዲሁም ሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክን ጎብኝተዋል፡፡

እንግሊዛዊው ዶክተር አለን ግሪጎር ኑሯቸው በለንደን ነው ፤ የተለያዩ የዓለም አገራትን ጎብኝተዋል፡፡ ከአስራ አራት ዓመታት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ሰሞኑን የአክሱም ሐውልቶችን እና የአክሱም ማርያም ጽዮን ቤተክርስትያንን ሲጎበኙ አገኘኋቸው፡፡

በአገሪቱ የቱሪስት መዳረሻ አካባቢዎች ላይ መሠረታዊ ለውጦች ማየታቸውን የሚናገሩት ዶክተር አለን፣ ለዚህም በአክሱም ሐውልቶች ዙሪያ የተመለከቱትን ለውጥ ይጠቁማሉ፡፡ አካባቢው የዛሬ አስራ ሦስት ዓመት ገደማ ለጉብኝት ምቹ እንዳልነበር አስታውሰው፣ አሁን ግን መንገዱ በኮብል ስቶን መነጠፉ ለጎብኚዎች ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ይጠቁማሉ፡፡

ዶክተር አለን ኢትዮጵያ የተለየች አገር ነች ይላሉ፡፡ የኢትዮጵያ ሰው ሠራሽ ቅርሶች እና ውብ መልከአ ምድሮች ሀገሪቱን ተመላልሰው እንዲጎበኙ አድርጓቸዋል፡፡

ዶክተር አለን ዘንድሮ ኢትዮጵያን ለመጎብኘት ያላቸው እቅድ ከወራት በፊት በአገሪቷ በተከሰተው ሁከት ሳቢያ ይደናቀፋል የሚል ስጋት ነበራቸው፡፡ ይሁንና በሀገሪቱ ምንም የጸጥታ ችግር እንዳላጋጠ ማቸው ይጠቅሳሉ፡፡

በብሄራዊ ሙዚየም ጉብኝት ሲያደርጉ ያገኘኋቸው ቻይናዊው ሚስተር ሱን ተንጀ ኢትዮጵያን ለመጎብኘት ሲመጡ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው ፡፡ በዚህ ጉብኝታቸው ብቻ በአዲስ አበባ የተለያዩ የቱሪስት መዳረሻዎችን፣ ድሬ ዳዋን፣ ሀረርን እንዲሁም በደቡብ ክልል የተለያዩ አካባቢዎችን ጎብኝተዋል፡፡

አገሪቷ ከጥቂት ወራት በፊት አለመረጋጋት ውስጥ እንደነበረች ያስታወሱት ሚስተር ሱን ተንጆ፣ ከፀጥታ ጋር በተያያዘ ምንም ዓይነት ችግር እንዳላጋጠማቸው ነው የተናገሩት፡፡ በበርካታ የአፍሪካ አገራት ካሉ የቱሪስት መዳረሻዎች ይልቅ በኢትዮጵያ የተሻለ ቆይታ ማድረጋቸውን ይገልጻሉ፡፡

ሚስተር ሱን በቅርቡ ወደ አገራቸው ሲመለሱ ለጓዳኞቻቸው እና ለሥራ ባልደረቦቻቸው በኢትዮጵያ ስላለው ጸጥታ አስተማማኝነትና ስለ ማራኪ የቱሪስት መዳረሻዎቿ እንደሚያሳውቁም ተናግረዋል፡፡

ከጀርመን ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውን የገለጹት ሚስተር ሊዮን ጆናስ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ አስተማማኝ ሰላም ስለመኖሩ ሚስተር ሱን እና ዶክተር አለን ባነሱት ሃሳብ ይስማማሉ፡፡

የዛሬ ሦስት ዓመት ገደማ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የተለያዩ አካባቢዎችን የጎበኙት ሚስተር ሊዮን፣ ሰሞኑን በአማራ፣ በትግራይ፣ በኦሮሚያ እና በደቡብ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ጉብኝት አድርገዋል፡፡ አገሪቱ ካላት በርካታ ሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ ቅርሶች በተጨማሪ የህዝቡ እንግዳ ተቀባይነት፣ የጸጥታ አስተማማኝነት እና የአየር ጸባይ ምቹነት ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ እንዳደረጋቸው ይናገራሉ፡፡

በአሁኑ ጉብኝታቸው ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ አገሪቱ አለመረጋጋት ውስጥ እንደሆነች በተለያዩ መንገዶች ቢከታተሉም፣ ለመጎብኘት ካላቸው ከፍተኛ ፍላጎት የተነሳ ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣት አልታቀቡም፡፡ በአገራቸው ሆነው ሲወራ የሰሙት አስጊ ነገር እንዳላጋጠማቸውም ነው የሚገልጹት፡፡

በኢትዮጵያ የአንድ ወር ከአስራ አምስት ቀናት ጉብኝት ያደረጉት ሚስተር ሊዮን፣ ቆይታቸው በጣም አስደሳች እንደነበርም ይናገራሉ፡፡ እንደ ሚስተር ሊዮን ገለጻ ፤ በኢትዮጵያ የዛሬ ሦስት ዓመት የነበረው አስተማማኝ ሰላምና የህዝቡ የእንግዳ ተቀባይነት ዘንድሮም አልተለወጠም፡፡

የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጌትነት ይግዛው እንደሚሉት፤ ከወራት በፊት በአገሪቱ ተፈጥሮ የነበረው አለመረጋጋት ሁከቱ በተነሳበት በመጀመሪያዎቹ ወራት በቱሪዝም ዘርፉ ላይ መጠነኛ አሉታዊ ተጽዕኖ ፈጥሮ ነበር፡፡

አንዳንድ አገራት ዜጎቻቸው ወደ ኢትዮጵያ እንዳይጓዙ ማስጠንቀቂያ ሰጥተው እንደነበር የሚናገሩት አቶ ጌትነት፣ በዚህም ምክንያት ወደ አትዮጵያ ሊመጣ ካሰበው ቱሪስት 0 ነጥብ 82 በመቶ እንዳልመጣ ይገልጻሉ፡፡ ይህም በጣም አነስተኛ አኀዝ መሆኑን ኃላፊው ይናገራሉ፡፡

አቶ ጌትነት እንደሚሉት፤ አገራቱ በሰጡት ማስጠንቀቂያ የተወሰኑት ጉዟቸውን የሰረዙ ቢሆንም፣ ማስጠንቀቂያ እየተሰጣቸውም የኢትዮ ጵያ መንግሥትን በመተማመን የተለያዩ መዳረሻዎ ችን የጎበኙ ቱሪስቶች ጥቂት የሚባሉ አይደሉም፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁን ተከትሎ አገራቱ ማስጠንቀቂያውን ማንሳታቸውን የገለጹት አቶ ጌትነት፣ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በኋላ የቱሪስት ፍሰቱ ወደ ነበረበት መመለሱን ይገልጻሉ፡፡

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ የዛሬ አስራ ሦስት ዓመታት ገደማ በዓመት 200 ሺ ጎብኝዎች ኢትዮጵያን ይጎበኙ ነበር፡፡ በ2008 ይህ አኀዝ በብዙ እጥፍ በማደግ 910 ሺህ መድረሱን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡ ዘንድሮ ይህን አኀዝ ወደ አንድ ሚሊዮን ለማድረስ እቅድ ተይዞ እየተሠራ ነው፡፡ ethpress.

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy