የዙና ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ስራ አስኪያጅና ባለቤት አቶ ዘሪሁን ጌታሰው በተጠረጠረባቸው የወንጀል ክሶች ዙሪያ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ምስክሮቹን ማሰማት ጀመረ።
የአቃቤ ህግ ምስክሮች ግለሰቡ የተለያዩ ተሽከርካሪዎችን ከ60 እስከ 70 ቀናት በግማሽ ክፍያ አስመጣለሁ በማለት 119 ግለሰቦችን ላይ ከባድ የማታለል ወንጀሎችን መፈጸሙን የሚያሰረዱ ናቸው።
ተከሳሹ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 04 22 ማዞሪያ ጎላጎል ታወር ላይ ቢሮ በመክፈት ለጊዜው ካልተያዘው ወንድሙ ልዑልሰገድ ጌታሰው ጋር በመሆን በተለያዩ ሚዲያዎች በመጠቀም ከቻይና ከ60 እስከ 75 በሚሆኑ ቀናት ውስጥ ሲኖትራኮችን እና የተለያዩ ተሽከርካሪዎችን ከውጭ ሀገር እናስመጣለን በሚል ሲያስተዋውቅ መቆየቱን አቃቤ ህግ በክሱ ገልጿል።
ግማሹን ክፍያ በቅድሚያ እንዲከፈሉ በማድረግ ቀሪውን ደግሞ ምንም አይነት የባንክ ብድር ውል ስምምነት ሳይኖረው እንዳለው በማስመሰል የግል ተበዳዮች እምነት እንዲጥሉበት አድርጓል ይላል ክሱ።
ከ337 ሺህ እስከ 3 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር ከግል ተባዳዮቹ ጋር ውል በመፈፀም መቀበሉን የሚገልጸው የአቃቤ ህግ ክስ፥ በአጠቃላይም በሚሊየን የሚቆጠር ብር ከ119 ግለሰቦች በተመሳሳይ መንገድ መውሰዱን ያመለክታል ።
ተከሳሹ ይህን ተግባር ፈፀሞ ከሃገር በመውጣቱ በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ በኩል በኢንተር ፖል አማካይነት ሲፈለግ ቆይቶ በዱባይ የተያዘ ሲሆን፥ ፖሊስ ባደረገው ምርመራም 9 ሚሊየን ብር እና 269 ሺህ 200 የአሜሪካ ዶላር በኤግዚቢትነት እንደተያዘ ተጠቁሟል።
ተከሳሹ በቀረበበት 119 ክሶች ላይ ˝በፍትሀብሄር እንጂ በወንጀል ልጠየቅ አይገባም፣ ሁለተኛ የቀረበብኝ ክስ ወንጀል የሚያቋቁም ፍሬ ነገሮችን የሚያሟላ አይደለም˝ የሚለውን ጨምሮ አራት የክስ መቃወሚያዎችን አቅርቧል።
አቃቤ ህግ በተከሳሹ የቀረቡትን መቃወሚያዎች ተቀባይነት እንዳያገኙ በጽሁፍ ለፍርድ ቤቱ ባቀረበው መቃወሚያ መሰረት ውድቅ ሆነዋል።
ተከሳሹ በቀረቡበት ክሶች ላይ በሰጠው የእምነት ክህደት ቃል የወንጀል ድርጊቱን አልፈፀምኩም በማለቱ ፍርድ ቤቱ የጠቅላይ አቃቤ ህግ ምስክሮች ማድመጥ ጀምሯል።
ጠቅላይ አቃቤ ህግ ያቀረባቸው የስው ማስረጃዎችም በክሱ ላይ በተገለፀው መልኩ ተከሳሹ የወንጀል ድርጊቱን ስለመፈፀሙ ለፍርድ ቤቱ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።
ቀሪ ምስክሮችንም ለማድመጥ ፍርድ ቤቱ ለመጋቢት 11 2009 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ይዟል። FBC