Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ኢትዮዽያ የሰሜን አሜሪካ ጎብኚዎችን ለመሳብ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ነው

0 494

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በአለም አቀፉ የቱሪዝም ተቋም ‘ሎንሊ ፕላኔት’ በአለም ሊጎበኙ ከሚገባቸው አስር ሃገራት አንዷ በመሆን የተመረጠችው ኢትዮዽያ የሰሜን አሜሪካ ጎብኚዎችን ለመሳብ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች መሆኗን ትራቭል ፐልስ ድረ ገፅ ዘገበ።

የኢትዮዽያ ቱሪዝም ድርጅት መሰረቱን በኒውዮርክ ካደረገውና በአሜሪካና ካናዳ ከጉዞ ጋር የተያያዙ የንግድና የሚዲያ ስራዎችን ከሚሰራው ኮርነር ሰን ከተሰኘው ተቋም ጋር ስምምነት መፈፀሙን ነው ዘገባው ያመለከተው።

ሃገሪቷ ዘርፈ ብዙ ታሪክና ባህሏን ለማስተዋወቅ በቅርቡ ያስተዋወቀችው “ምድረ ቀደምት” ወይም በእንግሊዝኛው “The Land of Origins,” የሚል የብራንድ ስያሜ የሰሜን አሜሪካ ቱሪስቶችን ለመሳብ እንደሚያግዛትም መረጃው ጠቁሟል። የአፍሪካ ቀደምትና ጥንታዊቷ ሀገር የሆነችው ኢትዮዽያ የሰው ዘር መገኛነቷ ምስክር የሆነችው የሉሲ አፅምን ጨምሮ የአባይ ወንዝ ምንጭና የቡና መፈጠሪያ ሃገር ናት ሲል ገልጿታል ድረ ገፁ።

እኤአ በ2015 ከ800ሺ በላይ ጎብኚዎችን ያስተናገደችው ኢትዮዽያ በዚህም ካለፉት 10 አመታት በ12 በመቶ ብልጫ ያለው የጎብኚዎች ቁጥርን አስመዝግባለች። በ2016 የጎብኚዎቹን ቁጥር ወደ ዘጠኝ መቶ ሺ ለማሳደግ ያለሙት የቱሪዝም ሃላፊዎች ይህንኑ ቁጥር ወደ ሚሊዮን ጎብኚዎች ለማሳደግ ውጥን መያዛቸውን ጠቅሷል።

ከአዲስ አበባ ሎስ አንጀለስ የቀጥታ በረራን በ2015 የጀመረው የኢትዮዽያ አየር መንገድ ሀገሪቷ የሰሜን አሜሪካ ቱሪስቶችን ለመሳብ የምታደርገውን ጥረት እንደሚደግፍ የገለፀው ድረ ገፁ አየር መንገዱ በአሜሪካም ከኒውዮርክ፣ዋሺንግተን ዲሲና ካናዳ ቶሮንቶ በመነሳት የበረራ አገልግሎት እየሰጠ እንደሆነም አስነብቧል።

አየር መንገዱ በአፍሪካም የሃገር ውስጥ በረራን ጨምሮ 55 ሃገራትን ያገናኛል፤በዚህ ወር መጀመሪያም በአህጉሪቱ የመጀመሪያ የሚያደርገውን የኤር ባስ ኤ350 በረራውን ጀምሯል።

በአፍሪካ በቅኝ ግዛት ያልተገዛች ብቸኛዋ ሃገር የሆነችው ኢትዮዽያ የአፍሪካ ማዕከልና ከ80 በላይ ባህልና ማንነትን የያዙ ብሄር ብሄረሰቦች ሃገርና ከአለም ከፍተኛ የዲፕሎማቲክ ተቋማት ከሚገኙባቸው ሃገራት አንዷ መሆኗንም ዘገባው አመላክቷል። ENA

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy