ኢትዮጵያና ኢጣሊያ በሶማሊያ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ውይይት አካሄዱ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሂሩት ዘመነ በአፍሪካ ቀንድ አገራት የኢጣሊያ ልዩ ልዑክ ሚስተር ሉቺያኖ ፔዞቲ የተመራውን የልዑካን ቡድን ትናንት በፅህፈት ቤታቸው አነጋግረዋል።
ሚኒስትር ዴኤታዋ በሶማሊያ በተለያዩ ዘርፎች እየተከናወኑ ባሉ ስራዎች ተጨባጭ ለውጥ እየታየ መሆኑን ገልጸዋል።
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለአገሪቷ ተቋማት አቅም ግንባታ፣ ብሔራዊ ወታደራዊ ኃይል ማጠናከርና ኢኮኖሚዋን ለማረጋጋት ለሚደረገው ጥረት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አመልክተዋል።
በተጨማሪም በአገሪቷ ለተከሰተው ድርቅ ድጋፍ ለማድረግ የተገባውን ቃል ወደ ተግባር መለወጥ እንደሚገባም አሳስበዋል።
በተለያዩ ጉዳዮች በአገራቱ መካከል የሚካሄዱ መደበኛ የሃሳብ ልውውጦች ትልቅ ዋጋ እንዳላቸው ነው ሚኒስትር ዴኤታዋ የገለጹት።
በአፍሪካ ቀንድ አገራት የኢጣሊያ ልዩ ልዑክ ሚስተር ሉቺያኖ ፔዞቲ በበኩላቸው “የውድቀት አገር ተብላ ትጠራ የነበራችው ሶማሊያ ችግሯቿን በመፍታት ወደ ትክክለኛው ጎዳና እያመራች ነው” ብለዋል።
ለውጡ የመጣው የሶማሊያ መንግስት፣ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ) እና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ባሳዩት ቁርጠኝነት መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ኢጣሊያ የኢጋድ አጋር አካላት ፎረም የጋራ ሊቀመንበር መሆኗን አስታውሰው በፎረሙ ለሚከናወኑ ፕሮግራሞችና ፕሮጀክቶች ተፈጻሚነት ድጋፍ እያደረገች መሆኑን መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ድረ-ገጽ መረጃ ያሳያል።
የኢትዮጵያና ኢጣሊያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የተጀመረው እንደ አውሮፓዊያኑ ዘመን አቆጣጠር 1889 ነው።
የአገራቱ የንግድ ልውውጥ መጠን በ300 እና 400 ሚሊዮን ዩሮ መካከል እንደሚገኝ መረጃዎች ያመላክታሉ።
የኢንቨስትመንት ጥበቃ ስምምነትና የተደራራቢ ታክስና ቀረጥ ማስቀረት ስምምነቶች መፈራረማቸውም ይታወቃል።