Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ኢትዮጵያ ከውሃ ማማነት ወደ ሃይል ማመንጫ ማማነት እየተሸጋገረች ነው–አፍሪካን ሜትሮ

0 1,265

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ኢትዮጵያ ከውሃ ማማነት ወደ ሃይል ማመንጫ ማማነት እየተሸጋገረች መሆኑን አፍሪካን ሜትሮ ድረ-ገፅ ዘገበ፡፡

ዓለም በካርቦን ልቀት እየተጨነቀች ባለችበት በዚህ ወቅት ከታዳሽ ሐይል የሚገኘው የሃይል አማራጭ መተኪያ እንደሌለው ዘገባው ያብራራል፡፡

በቅርቡ የተደረጉ ጥናቶች ከሰሐራ በታች የሚኖሩ 600 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች የኤሌክትሪክ አቅርቦት እንደማያገኙ አሳይተዋል፡፡

በዚሁ አካባቢ ከሚከናወኑ ንግዶች ግማሽ ያህሉ ዋነኛ ችግራቸው አስተማማኝ የሃይል አቅርቦት አለመኖር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የሃይል መቆራረጥ ደግሞ የአፍሪካ አገራትን ከ 1 እስከ 2 በመቶ የሚጠጋ ዓመታዊ የምርት ምጣኔያቸውን እንደሚያሳጣቸው ድረ-ገጹ ጠቅሷል፡፡

እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገራት ደግሞ ኢንዱስትሪውን ለማስፋፋት መሰረት የሆነውን አስተማማኝ የሃይል አቅርቦት ለማግኘት ከፍተኛ ፍለጋ እያደረጉ መሆናቸው ተገልጿል፡፡ ኢትዮጵያ ከአካባቢ ብክለት የፀዳ የሃይል አቅርቦት በማመንጨት  ኢኮኖሚዋን ለማሳደግና ድህነትን ለማስወገድ እየተጋች ነው፡፡

አገሪቱ ለተያያዘችው የእድገት ጉዞ የሃይል አቅርቦቱ መተኪያ የሌለው ሐብት መሆኑ ይታወቃል፡፡ ለዚህም የምትከተለው የኢነርጂ ስትራቴጂ ከአካባቢ ብክለት እና ከካርቦን ልቀት ነፃ የሆነ የሃይል አቅርቦትን እውን ማድረግ ነው፡፡

በ 1980ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ በአገሪቱ የነበረው አጠቃላይ የሃይል አቅርቦት ከ380 ሜጋ ዋት የማይበልጥ ነበር፡፡

ባለፉት አምስት አመታት አሉ የተባሉ የሐይል አቅርቦት አማራጮችን በመጠቀም የሐይል ማመንጫ  ግንባታ መከናወኑን የኢትዮጵያ ኤሌከትሪክ ሐይል አቅርቦት የውጭ ግንኙነት ዳይሬክተር ለኢትዮጵያ ሔራልድ ጋዜጣ መናገራቸውን ድረ ገፁ ገልጿል፡፡

ከውሃ የሚገኘው የሃይል አቅርቦት የአገሪቱ ዋነኛ ሐብት ሆኖ የተዘገበ ሲሆን ከጢስ አባይ 75 ፣ከግልገል ጊቤ አንድ  184፣ ከተከዜ 300 ፣ከግልገል ጊቤ ሁለት 420 ፣ከጣና በለስ 460 ፣ከፊንጫ አመርቲ ነሽ 97 ፣ከግልገል ጊቤ ሶስት 1 ሺ 870 በድምሩ 3 ሺ 404 ሜጋ ዋት ሃይል እያመነጨች መሆኗን ድረ ገፁ ጠቅሷል፡፡

በተመሳሳይ የሃይል አቅርቦቱ በሌሎች የሐይል አማራጮች እየተደገፈ ሲሆን ከአዳማ አንድ የንፋስ ሐይል ማመንጫ  51 ሜጋ ዋት፣ ከአሽጎዳ የንፋስ ሐይል ማመንጫ  120 ሜጋ ዋት፣ ከአዳማ ሁለት የንፋስ ሐይል ማመንጫ  153 ሜጋ ዋት ማመንጨት ተችሏል፡፡ከእንፋሎት ሐይል የሚመነጨውን 8 ሜጋ ዋት ጨምሮ በአገሪቱ  በድምሩ  4260 ሜጋዋት ሐይል እየተመረተ ነው፡፡

በተለያዩ ጊዜያት የተደረጉ ጥናቶች አገሪቱ ከውሃና ከሌሎች የተፈጥሮ ሃብቶች 60 ሺ ሜጋዋት ሐይል ማመንጨት እንደምትችል አሳይተዋል፡፡ አገሪቱ በተመሳሳይ  ከንፋስ፣ ከእንፋሎትና ከጸሐይ  ሐይል ለማመንጨት የታደለች መሆኗን ጸሐፊው ገልጿል፡፡የተያዙት ፕሮጀክቶች በጠቅላላ ከአካባቢ ጋር ተስማሚ በመሆናቸው አገሪቱ የያዘችውን የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ያሳልጣሉ፡፡

ኢትዮጵያ በአፍሪካም ሆነ በአለም  ደረጃ ከታዳሽ ሐይል እና ከአካባቢ ጋር ተስማሚ የሆነ የሐይል አቅርቦትን እውን ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኗን አቶ ምስክር መናገራቸውን አንብበናል፡፡ አገሪቱ የአለም ስጋት የሆነውን የካርቦን ልቀት ለመቀነስ የያዘችውን ዘመቻ እውን ለማድረግ ተግታ እንደምትሰራም  ተጠቁሟል፡፡

በግንባታ ላይ ያለው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሲጠናቀቅ 6 ሺ 450 ሜጋዋት ሃይል የሚያመነጭ ሲሆን በግዙፍነቱ ከአፍሪካ አንደኛ ከአለም ስምንተኛ መሆኑንም አፍሪካ ሜትሮ ድር ገፅ አስነብቧል፡፡

ከዚሁ ጎን ለጎን  254  ሜጋዋት ሃይል እንደሚያመነጭ የሚጠበቀው የገናሌ ዳዋ ሶስት ፕሮጀክት ግንባታ 83 በመቶ መጠናቀቁን ጸሐፊው ጠቅሷል፡፡ ባልተለመደ መልኩ በአዲስ አበባ እየተከናወነ የሚገኘው የረጺ የሃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ከቆሻሻ 50 ሜጋ ዋት ሃይል እንደሚያመነጭ አቶ ምስክር መናገራቸው ተገልጿል፡፡

በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን ማብቂያ ከሁሉም አማራጮች 17 ሺ ሜጋዋት የማመንጨት ግብ ተቀምጦ እየተሰራ መሆኑ ተብራርቷል፡፡

ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ እያደገ የመጣውን ኢኮኖሚ ተከትሎ የሃይል ፍላጎቱ በከፍተኛ መጠን አሻቅቧል፡፡

ከሚመነጨው ሐይል ውስጥ 40 በመቶ የሚጠጋው ለኢንዱስትሪ አገልግሎት የሚውል ሲሆን የተቀረው ለአገልግሎቱ ዘርፍና ለቤት ውስጥ አገልግሎት የሚከፋፈል ነው፡፡

የኤሌክትሪክ ሃይል ለውጭ ገበያ ማቅረብን በተመለከተ የአገር ውስጥ ፍላጎቱን በበቂ ደረጃ መመለስ ከተቻለ በሗላ ለጎረቤት አገራት በሽያጭ እንደሚቀርብ አቶ ምስክር መናገራቸው ተጠቅሷል፡፡ አገሪቱ በአሁኑ ወቅት  60 ሜጋ ዋት ሐይል ለጅቡቲ እያቀረበች መሆኗን ጸሐፊው ተናግሯል፡፡ በተጨማሪ ለሱዳን ከ 50 እስከ 100 ሜጋ ዋት ለማቅረብ ስምምነት መታሰሩ ተጠቁሟል፡፡ ነገር ግን ይህ ሁሉ የሚከናወነው የአገር ውስጥ ፍላጎቱን በማይጎዳ መልኩ ነው ሲሉ አቶ ምስክር መናገራቸውም ተዘግቧል፡፡

የሃይል አቅርቦቱን ለጎረቤት አገራት ማስተላለፍ ከገንዘብ በላቀ እርስ በእርስ በመደጋገፍ ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ እድገትን እውን በማድረግ አሀጉራዊ ትስስሩን ጥልቅ ለማድረግ እንደሚያስችል ተገልጿል፡፡ ለውጭ ገበያ የሚቀርበው ሐይል በአገሪቱ የሚታየውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመቀነስ  እና ለልማቱ ቅልጥፍና  የማይናቅ እገዛ ያበረክታል፡፡

አካባቢውን በሐይል አቅርቦት፣በባቡር መስመር ፣ በአውራ ጎዳናና በአየር ትራንስፖርት ማስተሳሰር ከተቻለ በቀጠናው ሰላምንና መረጋጋትን ለማስፈን አዳጋች አይሆንም፡፡ ይህም ብልጽግናንና እድገትን ያረጋግጣል፡፡

ባለፉት አስራ አምስት አመታት ብቻ 19 ሺ ሜትር ርዝመት ያላቸው ከፍተኛ ሐይል ተሸካሚ ምሰሶዎችን መገንባት ተችሏል፡፡ በ1980 ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ በአገሪቱ የነበረው 8 በመቶ የሐይል አቅርቦት በአሁኑ ወቅት 56 በመቶ እንደደረሰ  አቶ ምስክር መናገራቸውን ድረ ገፁ ጠቁሟል፡፡

ኢትዮጵያ በአህጉሪቱ ተጠቃሽ የሆነና ከካርቦን ልቀት ነጻ የሆነ  የአረንጓዴ ኢኮኖሚ  ልማትን እውን ከማድረግ ጎን ለጎን የአፍሪካ የሐይል ማማ ለመሆን እየተጋች ትገኛለች በማለት ዘጋቢው ሐተታውን ደምድሟል፡፡ ENG

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy