የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) 27ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን የክልሉን ህዝብ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚያስችሉ ስራዎች በመስራትና የገባውን ቃል በማደስ እንደሚያከብር አስታውቋል።
የኦህዴድ ሊቀመንበር እና የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ መጋቢት 17 2009 ዓ.ም የሚከበረውን 27ኛ የድርጅቱን የምስረታ በዓል አስመልክቶ በዛሬው እለት መግለጫ ሰጥተዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በመግለጫቸው የኦህዴድን የምስረታ በዓል የሚከበረው በጥልቅ ተሃድሶ እንቅስቃሴ ወቅት የተለዩ ችግሮችን መነሻ በማድረግ ለኦሮሞ ህዝብ ተጠቃሚነት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ለመስራት ቃል በመግባት ነው ብለዋል።ለህዝቡ ቃል የተገባውን ስራ ከግብ ለማድረስም የድርጅቱ አባላት፣ የስራ አመራሮች እና የክልሉ ህዝብ ተቀናጅቶ መስራት አለባቸው ነው ያሉት አቶ ለማ።
የዘንድሮው የምስረታ በዓል የሚከበረው ለህዝቡ የተገባውን ቃል በማስታወስ እና ወደ ተጨባጭ ስራ በመቀየር የኦሮሞ ህዝብ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ በሚያስችል ደረጃ በመስራት ነው ማለታቸውን የኦሮሚያ ራዲዮና ቴሌቭዥን ድርጅት ዘገባ ያመለክታል።
በተያያዘ ዜና የኦህዴድ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ በከር ሻሌ 27ኛ የኦህዴድ ምስረታ በዓልን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ፥ “የዘንድሮውን የምስረታ በዓል የምናከብረው የጥልቅ ተሃድሶ እንቅስቃሴን መነሻ በማድረግ ህብረተሰቡ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች ለመመለስ በመስራት ነው” ብለዋል።
አቶ በከር በመግለጫቸው፥ ኦህዴድ ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ ባካሄደው ትግል በፖለቲካ፣ በማህበራዊ እና በኢኮኖሚው ዘርፍ በርካታ ድሎችን አስመዝግቧል፤ የኦሮሞ ህዝብንም ተጠቃሚ ማድረግ ችሏል ሲሉም ተናግረዋል።
በዚህ የትግል ወቅት ከህብረተሰቡ የተነሱበትን ትችቶች በማዳመጥ የተስተዋሉ ክፍተቶችን ከመሰረታቸው ለመቅረፍ ድርጅቱ ወደ አዲስ ምእራፍ ተሸጋግሯል ነው ያሉት አቶ በከር።
ህብረተሰቡ ለጠየቀው ጥያቄ ምላሽ የመስጠት ሂደቱም ለህዝቡ በመወገን የሚካሄድ ሲሆን፥ እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልፀዋል።
“በዓሉ በጥልቅ የመታደስ እንቅስቃሴን በማጠናቀቅ ከህዝቡ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ እየሰጠን ባለንበት ወቅት የሚከበር በመሆኑ የድርጅቱ አባላት እና ደጋፊዎች የድርጅቱ ትግል ከግብ እንዲደርስ የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል”ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የዘንድሮውን ኦህዴድ 27ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በተለያዩ የፓናል ውይይቶች ለማክበር ዝግጅት መጠናቀቁ ተነግሯል።
በዓሉ የፊታችን እሁድ በጭሮ ከተማ በክልል ደረጃ እንደሚከበር ከኦሮሚያ ክልል መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።