Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ከጥልቅ ኃዘናችን ባሻገር

0 528

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ሰሞኑን እኛ ኢትዮጵያውያን ጥልቅ ሀዘን ተሰምቶናል። ወዲህ በአዲስ አበባ ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ቆሼ እየተባለ ከሚጠራው አካባቢ ልብ የሚሰብር አስደንጋጭ መርዶ ሰምተናል። እስከ ትናንት ማምሻ ድረስ ያለው መረጃ እንደሚያመለክተው በአካባቢው የሚጠራቀመው የቆሻሻ ክምር መናድ 113 ዜጎቻችንን ቀጥፎብናል። መሰንበቻውን ደግሞ በጋምቤላ ክልል የደቡብ ሱዳን የሙርሌ ጎሳ አባላት ዳግም ድንበር ጥሰው በመግባት 18 ዜጎችን ገድለዋል፤ 30 ህጻናትን አፍነው በመውሰድ ጎጆዎችን አቃጥለዋል የሚል መረጃ እየወጣ ነው ። ይህም ይበልጥ ሀዘንና ትካዜ እንዲሰማን አድርጓል።

መንግሥት በአዲስ አበባ በተለምዶ ቆሼ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የደረሰውን አደጋ ተከትሎ ከትናንት ጀምሮ ለሦስት ቀናት የሚቆይ ብሔራዊ ሀዘን አውጇል። ለተጎጂዎችም ድጋፍ እያደረገ ይገኛል። በጋምቤላ አካባቢም ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች ከመደገፍ ባሻገር፤ ታፍነው የተወሰዱትን ህጻናት የማስመለስ ጥረት እየተከናወነ ነው። እነዚህ ልባችንን በጥልቅ ሀዘን የሞሉትን ክስተቶች ለመወጣት እየተደረገ ከአለው ጥረት ባሻገር፤ በምን ጉዳይ ላይ አተኩረን መሥራት ነበረብን? ወደፊትስ ምን መከናወን አለበት ? የሚሉት ጥያቄዎች ግን የሁሉም ዜጋ ስለሆኑ በደንብ ሊጤኑ ይገባል። ለዘላቂው መፍትሄም መትጋት ያስፈልጋል፡፡

በቅድሚያ በተለምዶ ቆሼ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ከተከሰተው አደጋ ጋር ተያይዞ የሚነሱትን ጉዳዮች እንመልከት። የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 44 የአካባቢ ደህንነት መብት በሚለው ንኡስ ርእስ ስር «ሁሉም ሰዎች ንፁህና ጤናማ በሆነ አካባቢ የመኖር መብት አላቸው» በማለት ይደነግጋል። ይሁንና በተጠቀሰው ቦታ የደረሰው አደጋ ይህንን በሚፃረር መልኩ ዜጎች ከጤናቸው አልፎ ለደህንነታቸው አስጊ በሆነ ሥፍራ ሲኖሩ እንደነበር ያመለክታል። ከቆሻሻው የሚወጣው ሽታ በጤና ላይ የሚያስከትለው እክል ከፍተኛ መሆኑ ሳይዘነጋ፤ የመናድ ዕድል በአለውና አደጋ እንደሚያስከትል በሚገመት ከፍተኛ የቆሻሻ ክምር የሚገኝበት አካባቢ የመኖሪያ ሥፍራ መሆኑ አቢይ ማስረጃ ነው።

ሕገ መንግሥቱ ለዜጎች የሰጠውን መብት የማስከበር ኃላፊነት የከተማው አስተዳደር አለፍ ሲልም በየደረጃው የሚገኙ የሥራ ኃላፊዎች ነው። ይሁንና በቸልታ የታየው ጉዳይ የዜጎችን ህይወት አስከፍሏል፡፡ ተጎጂዎች በህገወጥ መንገድ የሠፈሩ ናቸው ቢባሉ እንኳን ፈጣን እርምጃ ባለመወሰዱ የመጣ አደጋ መሆኑ ዕሙን ነው፡፡ ለወደፊቱም ትልቅ የማንቂያ ደውል ይሆናል።

በመሰረቱ ምንም ያህል የአቅም ውስንነት ቢኖር የደህንነት ሥጋት በአለበት አካባቢ ላስቲክና ሸራ ወጥረው የሚኖሩ ዜጎች ጉዳይ ቀድሞውንም ቢሆን ተገቢነት እንደሌለው በመፈተሽ አስፈላጊው እርምጃ ሊወሰድ ይገባው ነበር። በከተማዋ በሕገ ወጥ መንገድ የሚካሄዱ ግንባታዎችን ለመከላከል የሚተጋው አካልም ጥቃቅን ነገሮች ላይ ከማተኮር ይልቅ፤ እንደዚህ አይነት እክሎችን ቀድሞ ቢከላከል አደጋውን የማስቀረት ዕድል እንደነበር ሊገነዘብ ይገባል። ስለሆነም ዘላቂ መፍትሄ ከማበጀት ጎን ለጎን ለእዚህ ተወቃሽም ተጠያቂም የሆኑ አካለትን መለየትና አስተማሪ እርምጃ መውሰድ አስፈላጊ ነው።

በአዲስ አበባም ሆነ በሌሎቹ የአገሪቱ አካባቢዎች አሁንም ለአደጋ በሚያጋልጥ መልኩ ህይወታቸውን የሚገፉ ዜጎች መኖራቸውን ግምት ውስጥ በማስገባት ስለ ዘላቂ መፍትሄ ከወዲሁ መታሰብ አለበት። በሥፍራው በደረሰው አደጋ የተፈናቀሉት ዜጎች በትክክል ተለይተው፣ ዳግም አደገኛ ሥፍራ ለመኖር ተጋልጠው ለሌላ ቀውስ እንዳይዳረጉ የማያዳግም መፍትሄ ሊበጅላቸው ይገባል። ህዝብን ማዳን ከሁሉም ተግባር በላይ ነውና።

በጋምቤላ የፈተፈጸመውም ጥቃት አሁን ችግሩን ለመፍታት ከሚደረገው ጥረት ባሻገር ቀድም ብለን ምን መሥራት ነበረብን የሚለውን ጥያቄ የሚያስነሳ ነው። በ2008 .ም ከደቡብ ሱዳን ዘልቀው ወደ ክልሉ በመግባት ጥቃት የፈጸሙት የሙርሌ ጎሳ አባላት እያሰለሱ ተመሳሳይ ድርጊት ሲፈጽሙ ቆይተዋል። የመሰንበቻው ግድያና ዘረፋም የተከታታይ ጥቃታቸው ማሳያ ነው። የፌዴራልና የክልሉ መንግሥት ጉዳዩን ግምት ውስጥ በማስገባት የአካባቢውን ደህንነትና ፀጥታ ለማረጋገጥ ቢጥሩም፤ የአሁኑ ጥቃት ውስንነት እንዳለ ይጠቁማል። ይህም ቀዳዳዎቹን በአግባቡ ፈትሾ ዜጎች ሳይሳቀቁ የሚኖሩበትን መንገድ ለመፍጠር ይከናወን የነበረው ተግባር ይበልጥ ሊጠናከር ይገባ እንደነበር አመላካች ነው።

በሰሞኑ ጥቃት የተጎዱትን ዜጎች ለመደገፍና ታፍነው የተወሰዱትን ለማስመለስ ከሚደረገው ጥረት ጎን ለጎን ከደቡብ ሱዳን እየመጡ በጋምቤላ አካባቢ ጥቃት የሚፈጽሙት የሙርሌ ጎሳዎችን ለመግታት ዘላቂ መፍትሄዎች ላይ ሊተኮር ይገባል። የተጀመረው የድንበር አካባቢን ጥበቃ የማጠናከር ተግባር የማይገመቱ መግቢያ ቀዳዳዎችን ትኩረት አድርጎ ቢቀጥል አደጋውን መቀነስ ይቻላል። ከደቡብ ሱዳን መንግሥት ጋር የሚደረገው የሁለትዮሽ ውይይትም ለመፍትሄው አቢይ ጉልበት ስለሚሆን ተጠናክሮ መቀጠል አለበት።

በአጠቃላይ በአዲስ አበባም ሆነ በጋምቤላ ህይወታቸውን የአጡት ዜጎቻችን ሁላችንንም ለከፍተኛ ሀዘን ዳርገዋል። ለቤተሰቦቻቸው መጽናናትን እንመኛለን። በከፍተኛ ደረጃ እየተሻሻለ የመጣው አደጋን የመከላከል አቅም ብዙ ትሩፋቶችን ቢያቋድሰንም አስቀድሞ የመተንበዩና ጥንቃቄ የማድረጉ ጉዳይ ጎልብቶ ዳግም ለሀዘን የማንዳረግበትን ጊዜን ግን ለማየት እንጓጓለን። addiszemen

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy