Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ወጣቱ በሁሉም ስራዎች ላይ እጁን ያስገባ!

0 327

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ወጣቱ በሁሉም ስራዎች ላይ እጁን ያስገባ! (ዳዊት ምትኩ)

በየትኛውም ሀገር ውስጥ ወጣት የልማት ሃይል አንቀሳቃሽ ሞተር ነው። በሀገራችን ከግማሽ በላይ የሚሆነው የህብረተሰብ ክፍል ወጣት እንደሆነው ሁሉ፤ በሌሎች ሀገሮችም አብዛኛው አሃዝ ከዚህ የተለየ የሚሆን አይመስለኝም። እናም ይህን ትኩስ ሃይል በልማቱ ዘርፍ ለመጠቀም መንግስት የተመቻቹ ሁኔታዎችን ሊፈጥርለት ይገባል።

የሀገራችን ወጣት በቀጥተኛም ይሁን ቀጥተኛ ባልሆኑ የትምህርትና የመገናኛ ብዙሃን አውታሮች በዴሞክራሲያዊ አስተሳሰቦች ዙሪያ ጥልቅና ግንዛቤ አለው። ከዚህ ዕውቀቱ በመነሳትም የሚጠቅመውንና የሚጎዳውን ጠንቅቆ ያውቃል። በአንድ ወገን ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ፣ በሌላ ወገን ደግሞ ፀረ ልማትና ፀረ – ዴሞክራሲን የሚያቀነቅኑ ወገኖች መኖራቸውን ተረድቷል። እነዚህን ሁለት የሚቃረኑ እሳቤዎችን ከራሱ ተጠቃሚነት አንፃርም መዝኗቸዋል።

በመሆኑም ‘የየትኛው ፓርቲ ደጋፊ ብሆን እኔም ተጠቅሜ ነገር የምረከባትን ሀገር በማሳደግ ዴሞክራሲዬንና ሰላሜን አረጋግጣለሁ?’ በሚልም እውነታዎችን ፈትሿቸዋል። በተለይም በቅርቡ በሀገራችን አንዳንድ አካባቢዎች በተከሰተው ሁከት ሳቢያ ዋነኛ ተዋናይ የነበረው ወጣቱ፤ ባገኘው ትምህርት እነዚህን እሳቤዎች አጥብቆ ይዟል ማለት ይቻላል።

ካሳለፋቸው የራሱ ጥቂት የድምዳሜ እውነታዎች ተነስቶም ከማደናገር ውጪ  ይህ ነው የሚባል የፖለቲካ መርህ የሌለውን የፅንፈኛውን ጎራ የሚመርጥበት ምንም ዓይነት ምክንያት ሊኖረው እንደማይችል መገንዘቡን የተሃድሶ ትምህርት የወሰዱት ወጣቶች ሲናገሩ አድምጠናል። በዚህም በእነርሱ የጥፋት መንገድ በመታለል በፀረ ልማትና ፀረ ዴሞክራሲ እምነታቸው ተባባሪ ሊሆን እንደማይፈልግ በግልፅ ገልጿል። ህገ መንግስተየን በሚገባ በማወቁም ችግሮች ካሉም በሰላማዊ መንገድ እንዴት መፍታት እንደሚችል ተገንዝቧል።

ይህን ለልማት ምቹ የሆነን ወጣት በአግባቡ ይዞ መጠቀሙ ደግሞ ከመንግስት የሚጠበቅ ነው። እርግጥ መንግስት ለወጣቱ 10 ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ፈንድ መድቦ እስከ ሰኔ ድረስ ያለውን በጀት በየክልሉ መላኩ ይታወቃል። ክልሎችም የፌዴራል መንግስት ከመደበው ከዚህ ገንዘብ በተጨማሪ የራሳቸውን በማከል ወጣቶች እንዲጠቀሙ ስራውን እያሰፉት ነው።

ወጣቶችም ከዚህ ፈንድ ተጠቃ መሆን ጀምረዋል። እርግጥ ገንዘቡን በተገቢው ቦታ ማዋልና ስራን ሳይንቁ በማናቸውም ስራዎች ውስጥ ሊያንቀሳቅሱት ይገባል። አንድ ኚህ ኪሎ ሜትር በአንድ እርምጃ ይጀመራል እንደሚባለው፤ ወጣቶች ማንኛውንም ስራ ከታች መጀመር ይኖርባቸዋል። የስራ ክቡርነት መታወቅ አለበት። በማንኛውም ስራ ላይ እጃቸውን ማስገባት አለባቸው።

ወጣቱ የመንግስትን ትኩረትና የተመደበለትን ተንቀሳቃሽ ፈንድ በአግባቡ ለመጠቀም ራሱን ለስራ ዝግጁ ማድረግ ይኖርበታል። በእኔ እምነት ራስን ለስራ ማዘጋጀት አንድን ችግር ለመፍታት ግማሽ መንገድ እንደመሄድ ያህል ይቆጠራል። እናም ወጣቱ አስቀድሞ ራሱን ለማንኛውም ስራ ማዘጋጀት አለበት። ማንኛውም ስራ ከችግር መውጫ ቀዳዳ መሆኑን ማመን ይኖርበታል።

ይህ ሃይል ስራን ሳይንቅና ምናልባትም በስደት ቢሄድ ለባዕድ ሀገራት ሊያበረክተው የሚችለውን የጉልበት ስራ ዓይነት ጭምር ስራዎችን አክብሮ በመስራት የመንግስትን ትኩረት አሟጦ ሊጠቀምበት ይገባል። “ስራ ክቡር ነው” የሚለውን አርማ ከፍ አድርጎ ማውለብለብ ይጠበቅበታል። ያኔ ራሱን፣ ቤተሰቡንና ከምንም በላይ እያሰበችለት ያለችውን ሀገሩን መጥቀሙ አጠያያቂ አይሆንም።

ከዚህ በተጨማሪም ወጣቱ ስራ ፈጣሪ እንጂ ስራ ጠባቂ ሊሆን አይገባም። ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደሞከርኩት የፌዴራል መንግስትና ክልሎች ወጣቱ በስራ ውስጥ እንዲያልፍ ተንቀሳቃሽ ፈንድ አዘጋጅተዋል። ወጣቱ በዚህ ፈንድ እንደምን ራሱን ለስራ ዝግጁ ማድረግ እንደሚችል ማሰብ ይኖርበታል። በአሁኑ ወቅት ሀገራችን ውስጥ የተመቻቸ የስራ ምህዳር አለ። ዋናው ነገር ይህን ምቹ የስራ ድባብ በፈጠራ ክህሎት አጅቦ እንዴት ውጤታማ ማድረግ እንደሚቻል ማወቁ ላይ ነው።

እርግጥ ወጣቶች የዚህች ሀገር ገንቢዎች ናቸው። ሀገራችንን ከድህነት ለማውጣት በሚደረገው ትግል ፋና ወጊዎች ሆነው መንቀሳቀስ ይገባቸዋል። በወጣቶች ላይ ኢንቨስት ማድረግ ሀገርን ማበልፀግ መሆኑን ሁሉም ሊገነዘበው ይገባል። በእኔ እምነት እንደ ኢትዮጵያ ያለ በርካታ ቁጥር ወጣት ያለው ሀገር በወጣቱ ላይ ኢንቨስት አድርጎ ከወጣቱ አፍላ ጉልበት የሚያገኘውን ልማታዊ ፋይዳ ማረጋገጥ ካልቻለ ሁለት ችግሮች ሊያጋጥሙት ይችላሉ።

አንደኛው በርካታ ቁጥር ያለው ስራ አጥ ወጣት ይፈጠርና ይህ ስራ አጥ ኃይልም የራሳቸው አጀንዳ ያላቸው የውስጥና የውጭ ሃይሎች መጠቀሚያ ሆኖ ለሁከትና ብጥብጥ በር የሚከፍት ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ሀገራት ከወጣቱ ማግኘት የሚገባቸውን የልማት ተጠቃሚነት ዕውን ማድረግ አይችሉም።

እርግጥ ስራ የሌለው ወጣት ማናቸውንም ጉዳዮች እንደ ስራ ሊመለከት ይችላል—የሁከት ተግባርንም ቢሆን። ይህ ደግሞ የተረጋጋ ሰላምና የልማት ስራ የሚከናወንበትን ሀገር ሊረብሽና ወደአልተፈለገ አቅጣጫ ሊወስድ ይችላል። ለዚህ አባባሌ በቅርቡ በሀገራችን አንዳንድ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረው የሁከት ተግባር ሁነኛ አስረጅ ይመስለኛል። ወጣቶች በየአካባቢያቸው ካለው የመልካም አስተዳደር ችግር በተጨማሪ በሚፈለገው መጠን ስራ ሳይፈጠርላቸው በመቆየቱ፤ ለሀገራችን የውጭ ጠላቶች ለሚላላኩ የጥፋት ሃይሎች ፀረ-ኢትዮጵያ አጀንዳ ሰለባ ሆነው ነበር።

ይህ ሁኔታም በሰው ህይወትና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማስከተሉ የሚዘነጋ አይደለም። እናም አስቀድሞ ወጣቱን በሚፈለገው መጠን በስራ እንዲታቀፍ ማድረግ ቢቻል ኖሮ፤ የተከሰተው ጥፋት ዕውን አይሆንም ነበር—ከሀገራዊ ልማት ተጠቃሚ የሆነ ወጣት በምንም መልኩ የሀገሩን ጥቅም በመፃረር የሌሎች ባዕዳን ሃይሎች መጠቀሚያ ሊሆን ስለማይችል ነው። እናም የኢፌዴሪ መንግስት ከዚህ ዓመት ጀምሮ ወጣቱን አቅም በፈቀደ መልኩ አደራጅቶ ከልማቱ ተጠቃሚ እንዲሆን ፕሮግራም ቀርፆ ወደ ስራ መግባቱ ይበል የሚያሰኝ ተግባር ይመስለኛል።

ወጣቱ ኃይል አፍላ ጉልበት ያለው በመሆኑ፤ ሀገራት ይህን ለስራ ዝግጁ የሆነ ጉልበት በሚገባ መንገድ መጠቀም ይኖርባቸዋል። ይህን ጉልበት አጣጥሞ በተገቢው መንገድ መጠቀምም ለሀገራዊ ዕድገት ያለው ፋይዳ ግልፅ ነው። ወጣቶች በተፈጥሯቸው ሁሉንም ነገር የመስራት ስሜት የታደሉ ናቸው። እነርሱን በማናቸውም ሀገራዊ የልማት ትልሞች ውስጥ በማስገባት ማሳተፍ ስራዎችን በአፍላ ጉልበት እንዲሁም በፈቃደኝነትና በፍላጎት ስሜት ሊተገብሩት ይችላሉ። ይህም የተያዙ ዕቅዶችን ለመፈፀምና የሚፈለገውን ሀገራዊ ዕድገት ለማምጣት ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል። ስለሆነም በወጣቶች ላይ መዋዕለ ንዋይን ማፍሰስ ውጤቱ መልሶ የሚከፍለው ሀገርን መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። ያም ሆኖ ወጣቱ መንግስት ያዘጋጀለትን ፈንድ በመጠቀም ራሱ ጠቅሞ አገሩንም ሊጠቅም ይገባል። ይህም ከድህነት መውጫው አንድ መንገድ መሆኑን ማወቅ ያስፈልጋል።

                                   

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy