Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ዕድሜ የማይወስነው የኩላሊት ሕመም

0 1,539

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ሐሙስ የካቲት 30 ቀን 2009 ዓ.ም. ጠዋት ብሔራዊ ቲያትር መግቢያ በር ላይ ‹‹የዓለም የኩላሊት ቀን›› የሚል ጽሑፍ ያለበትና የሁለት ኩላሊቶች ምስል የታከለበት ባነር ተለጥፏል፡፡ ወደ ውስጥ ዘለቅ ሲባል ደግሞ ከወትሮው ለየት ባለ መልኩ ብዙ ሰዎች በሁለት ረድፍ ተሰልፈዋል፡፡ ከሰልፈኞቹም መካከል ግማሹ ይመዘገባል፣ ሌላው ይመዘናል፣ እኩሉ ደግሞ  የደም ግፊቱን ይለካል፡፡ ከተለያዩ ሕክምና ተቋማት የተውጣጡ ባለሙያዎችም ታዳሚውን በማስተናገድ ሥራ ተወጥረው ይስተዋላሉ፡፡የኩላሊት በሽታን ለማወቅ የሚያስችል ነፃ ምርመራ እየተካሄደም ነበር፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕፃናትና የሕፃናት ኩላሊት  ሕክምና ስፔሻሊስት፣ ረዳት ፕሮፌሰርና የኢትዮጵያ የኩላሊት ሕመም ማኅበር የቦርድ አባል ዶ/ር ቤዛዬ አበበ እንደምትለው፡ የዓለም የኩላሊት ቀንን ምክንያት በማድረግ ስለኩላሊት ሥራና የሕመም ሁኔታ፣ መከላከያ መንገድም የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራምም ነው፡፡እንደ ማኅበር ማስተላለፍ የሚፈልጉትም ያለሐኪም ትዕዛዝ ለሕመም ማስታገሻ እየተባለ በተደጋጋሚና በብዛት የሚወስዱት ልዩ ልዩ መድኃኒቶች በኩላሊት ላይ ጫና የሚፈጥሩ መሆናቸውን ነው፡፡ የበሽታው መንስዔ በሕክምና ምርመራ ሳይረጋገጥ ሰው መድኃኒት መውሰድ እንደሌለበትም አክለዋል፡፡የኩላሊት በሽታ ከአፈጣጠር ወይም ሕፃን ከተወለደበት ጊዜ ጀምሮ በሁሉም የዕድሜ ክልል ባሉ ሰዎች ላይ ይከሰታል፡፡ በተለይ በሕፃናት ላይ የሽንት ቧንቧ ችግር በተደጋጋሚ ጊዜ ሲኖር ኩላሊት ላይ ጠባሳ ይተዋል፡፡ ይህም ለኩላሊት ድክመት ይዳርጋል፡፡በአዋቂዎች ላይ የደም ግፊትና ስኳር በሽታ ለኩላሊት ችግር ሌላው መንስዔ ናቸው፡፡ ተቅማጥና ትውከት መጠማትን የሚፈጥር መሆኑም በሰውነት ለኩላሊት ችግር መንስኤ ሊሆን ይችላል፡፡ ሰማንያ በመቶ የሚሆኑት የኩላሊት ታማሚዎች በከፍተኛ የደም ግፊት ሕመም ይያዛሉ፡ሁለቱም ኩላሊቶች እያንዳንዳቸው 50 በመቶ ያህል የሰውነትን የጨውና የውኃ መጠን ይቆጣጠራሉ፡፡ ኩላሊቶቹ ለመቆጣጠርና ለማስወገድ ከሚችሉት አቅም በላይ ጨው በብዛት መመገብ ጨው በሰውነት እንዲከማች ያደርጋል፡፡ የተከማቸውም ጨው የደም ግፊትን ይጨምራል፡፡ ከፍተኛ የደም ግፊት ደግሞ የኩላሊትን የደም ስር በመጉዳት ለኩላሊት የሚደርሰውን የደም መጠን ይቀንሳል፡፡በዚህም የተነሳ እያንዳንዱ ኩላሊት የማጣራትና የመቆጣጠር አቅሙ ወደ 15 በመቶ ዝቅ ይላል፡፡ ይህም ለኩላሊት እጥበት (ዲያሌሲስ) እንደሚደረግ ዶ/ር ቤዛዬ ተናግረዋል፡፡የኩላሊት በሽታ ምልክቶች በርካታና የተለያዩ ናቸው፡፡ ከእነዚህም መካከል ከፍተኛ የደም ግፊት፣ የሽንት መጠን መቀነስና ከውኃማ ቀለም ወደ ሻይ ቀለም መቀየር፣ ሽንት ላይ አረፋ መብዛት፣ ጠዋት ከአልጋ ሲነሱ ዓይን አካባቢ እብጠት መታየት፣ የመሳሰሉ እንደሚገኙና አንዳንዴም ምንም ዓይነት ምልክት አይታይበትም፡፡እንደ ዶ/ር ቤዛዬ ማኅበሩ የዓለም የኩላሊት ቀንን አስመልክቶ ‹‹ጤናማ አኗኗር ለጤናማ ኩላሊት›› በሚል ርዕስ በብሔራዊ ቲያትር አዳራሽ ያካሄደው የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራም የተከናወነው ትምህርታዊ ውይይት በማካሄድና ለኅብረተሰቡ ነፃ የኩላሊት ምርመራ በማድረግ ነው፡፡በትምህርታዊው ውይይት ላይ ጤናማ አመጋገብና ጨው መቀነስ የደም ግፊትን ለመቀነስ እንደሚረዳ፣ በተጓዳኝም የታዘዙ መድኃኒቶችን በአግባቡ በመውሰድና የደም ግፊት በየጊዜው በመለካት የኩላሊት ጉዳትን ለመከላከል እንደሚቻል ተገልጿል፡፡የደም ግፊትን መቀነስ የሚቻለው የአኗኗር ዘይቤን በመለወጥ ሲሆን፣ ይህም አዘውትሮ ስፖርት መሥራትን፣ ጨውና ክብደት መቀነስን፣ ከአልኮል መጠጥ መታቀብንና ሲጋራ አለማጨስን ያካትታል፡፡ከማኅበሩ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ከፍተኛ ውፍረት የኩላሊትን የሥራ ጫና በማብዛት ለኩላሊት ጉዳት ያጋልጣል፡፡ ይሁን እንጂ ውፍረትንና የኩላሊት ሕመምን በአብዛኛው መከላከል ይቻላል፡፡ የኩላሊት ሕመም በተለይ በወፍራም ሰዎችና ከዚሁ ጋር ተያይዞ የስኳርና የደም ግፊት ታማሚዎች ላይ በብዛት ይታያል፡፡ በዓለም ውስጥ ውፍረት በወንዶች 18 በመቶ በሴቶች ላይ ደግሞ 21 በመቶ ይከሰታል፡፡በአንዳንድ አገሮች አንድ ሦስተኛውና ከዚያም በላይ የውፍረት ችግር በኅብረተሰቡ ይገኛል፡፡ ከፍተኛ ውፍረት ለልብ፣ ለስኳር፣ ለደም ግፊት፣ ለካንሰር፣ ለኮሊስትሮ፣ ለአተነፋፈስ ሕመም፣ ለሐሞት ጠጠር፣ ለአጥንትና መገጣጠሚያ (የጉልበት) ሕመም፣ ለሥነ አዕምሮና ብሎም ለሞት ያጋልጣል፡፡የሕፃናት ውፍረት ደግሞ ለአስም፣ ለትንፋሽ ማጠር፣ ለመገጣጠሚያ ሕመም፣ ለስኳርና ለልብ ሕመም እንደሚዳርጋቸው፣ በጓደኞቻቸው ለዘለፋና ለመሳሰሉት ጥቃት ስለሚጋለጡም ድብርትና በራስ የመተማመን ጉድለት እንደሚታይባቸው መረጃው አክሏል፡፡የኩላሊት ሕመም በአብዛኛው ሳይታወቅ የሚጎዳ ሕመም ነው፡፡ ሕሙማኑ አዘውትረው ስፖርት በመሥራት፣ የደም ግፊትን በማስተካከል፣ የስኳር ሕመምን፣ ክብደትን በመቆጣጠር፣ በቂ ፈሳሽ በመውሰድ፣ ሲጋራ ባለማጨስ፣ በሐኪም ያልታዘዙ መድኃኒቶችን ባለመውሰድ፣ ለሕመሙ የተጋለጡ ከሆነ የኩላሊት ምርመራ በማድረግ መከላከል ይችላሉ፡፡reporter

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy