Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የህዳሴ ግድብ አሳታፊ ያልሆኑ የቅኝ አገዛዝ ዘመን ስምምነቶችን የሻረ ነው – ምሁራን

0 531

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አሳታፊ ያልሆኑ የቅኝ አገዛዝ ዘመን ስምምነቶችን የሻረ እና በአባይ ተፋሰስ ሀገራት የይቻላልን መንፈስ ያሳደገ ታላቅ ፕሮጀክት መሆኑን ምሁራን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ቀድሞውንም ቢሆን በአባይ ወንዝ ላይ የተፈረሙ ስምምነቶችን ስትቃወም የነበረ ቢሆንም የግድቡ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ መቀመጥ ግን በተግባር አቋሟን ያረጋገጠችበት ነው ብለዋል አስተያየታቸውን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የሰጡ ምሁራን።

ግድቡ አሁን ላይ 24 ሰዓት ያለማቋረጥ እየተሰራ መሆኑ ለላይኛው የተፋሰሱ ሀገራት የይቻላል መንፈስን የፈጠረ፤ ለታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት ደግሞ የቅኝ ግዛት ዘመን ስምምነቶችን ትተው ወደ ድርድር እንዲመጡ ያደረገ መሆኑንም ገልፀዋል።

ኢፍትሃዊ ስምምነት

በ18ኛው ክፍለዘመን መጨረሻ በ19ኛው መጀመሪያ አካባቢ አፍሪካዊያንን በቅኝ ግዛት የተቀራመቱት ምእራባዊያን ሀገራት በርካታ አፍራሽ ስምምነቶችን ተፈራርመዋል።

ከእነዚህ ኢፍትሃዊ እና ሀገራትን ለአለመተማመን ከሚዳጉ በርካታ ስምምነቶች መካከል ብሪታኒያ በአባይ ወንዝ ላይ ያደረገቻቸው ስምምነቶች ይገኙበታል።

በዚያ የቅርምት ዘመን በተለይም በ1929 በወቅቱ የሱዳን ቅኝ ገዥ የነበረቸው ብሪታንያ ከግብፅ ጋር ኢትዮጵያን ያገለለ የውሃ ስምምነት አድርጋለች።

በዚህ ስምምነት የላይኛው ተፋሰስ ሀገራት የወንዙን የውሃ ፍሰት መጠን የሚቀንስ አንዳች እንቀስቃሴ እንዳያደርጉ ይከልክላል።

ይህ ስምምነት ተፈርሞ ሳለ ሱዳን ከብሪታንያ ቅኝ ግዛት ነፃ መውጣቷን ተከትሎ በ1956 ዳግም የ1929ኙ ስምምነት በ1959 በካርቱም እና ካይሮ መካከል ታድሶ ተፈረመ።

ይህ ሁሉ ሲሆን ኢትዮጵያ በአደባባይ ስምምነቱን እየተቃወመች ድምፅ ታሰማ ነበር።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና የአለም አቀፍ ግንኙነት ተባባሪ ፕሮፌሰሩ ዶክተር ያዕቆብ አርሳኖ፥ ስምምነቱ በኢፍታሃዊነት እና በማንአለብኝነት መንፈስ የተፈረመ ይሉታል።

ይህን ስምምነት ከጅምሩ በከፍተኛ ደረጃ ስትቃወም የነበረችው ኢትዮጵያ ብቻ ናት።

የተወሰኑ የላይኛው ተፋሰስ ሀገራት ስምምነቱን መጋፋት ያን ያህል ውጤት ያመጣል የሚል እምነት አልነበራቸውም ይላሉ በጉዳዩ ዙሪያ ጥናት ያደረጉ ምሁራን።

የኢትዮጵያ አቋም እና አለም አቀፉ ህግ…

የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የአሁኑ የአፍሪካ ህብረት በይፋ ሲቋቋም በ1963 የድንበር ስምምነቶችን አይነኬ አድርጎ ተመልክቷቸዋል።

የናይል የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ደግሞ በወንዙ ላይ የተፈረሙ ስምምነቶችንም ከደንበር ጋር አስተሳስረው ባልሆነ አቅጣጫ ጉዳዩን ሲያጦዙት ተስተውሏል።

በአለም አቀፍ ህግ ሲታይ ግን የኢትዮጵያ አቋም ትክክል እና የህግ መሰረት ያለው ነው፤ ምክንያቱም ባልፈረሙት ስምምነት ተገዥ መሆን አይቻልምና።

ይህ የዘመናት አቋም ከመርህ እና ከቃላት ባለፈ ወደ ተግባር የተሸጋገረው መጋቢት 24 2003 ዓ.ም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመሰረት ድንጋይ ሲቀመጥ ነው።

የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የዲፕሎማሲ እና የአለም አቀፍ ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰሩ ዶክተር ሙሃሙዱ አብዱላሂ ሁሴን፥ የግድቡ የመሰረት ድንጋይ የተጣለባት ቀን በወንዙ ላይ ፍትሃዊነት የጎደላቸውን የቅኝ ግዛት ስምምነቶች መቃብር የከተተች ናት ይላሉ።

ከዚያ በፊት በርካታ የተፋሰሱ ሀገራት የኢትዮጵያን አቋም ይጠራጠሩ እንደነበር ያስታወሱት ዶክተር ሙሃሙድ፥ ሀገሪቱ እንዴት ባለ አቅም ይህን የረጅም ጊዜ ስምምነት በመጣል ታላቁን ፕሮጀክት እውን ታደርጋለች የሚል ጥርጣሬ እንደነበራቸው አመላክተዋል።

የግድቡ ግንባታ መጋመስ እና ፋይዳው…

በሃይድሮ ዲፕሎማሲ ላይ ከመመረቂያ ፅሁፍ እስከ አለም አቀፍ ጥናቶች የሰሩት ዶክተር ያዕቆብ፥ ይህ ፕሮጀክት መጋመሱና
አሁን ላይ የተወሰኑ ተርባይኖቹ ወደ ሃይል ማመንጨት ተግባራቸው ለመግባት እየተዘጋጁ መሆኑ ብዙ ነገሮችን ቀይሯል ይላሉ።

ምሁሩ ግብፅ በየጊዜው የቅኝ ግዛት ስምምነቶችን ታሪካዊ እና የራሷን መብት ብቻ የሚያስጠብቁ አድርጋ በማንሳት ታደርጋቸው የነበሩ አፍራሽ አካሄዶችን መቀነሷን በማሳያነት ይጠቅሳሉ።

ይህም የሆነው ኢትዮጵያ የግድቡን ግንባት ግልፅ ማድረጓና የትኛውንም ወገን የማይግዳ ነው በሚል የምታራምደው አቋም አሸናፊ እየሆነ በመምጣቱ ነው ብለዋል።

አሁን ላይ የግብፅ አቋም ከዛሬ ስድስት ዓመት በፊት እንደነበረው አለመሆኑንም ነው ዶክተር ያእቆብ ያነሱት።

የዲፕሎማሲ እና የአለም አቀፍ ግንኙነት ረዳት ፕሮፌሰሩ ዶክተር ሙሃሙድ በበኩላቸው የታላቁ የህዳሴ ግደብ ተጠናክሮ መቀጠሉ ለኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳይሆን ለላይኛው ተፋሰስ ሀገራትም ትልቅ የመነቃቃት መንፈስ የፈጠረ መሆኑን ጠቁመዋል።

ምሁራኑ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አሳታፊ ያልሆኑ የቅኝ አገዛዝ ዘመን ስምምነቶችን ከመሻርና በአባይ ተፋሰስ ሀገራት የይቻላልን መንፈስ ከማሳደጉም በላይ መላ ኢትዮጵያዊያን በራሳቸው አቅም ይህን ታላቅ ፕሮጀክት እውን ማድረግ እንደሚችሉ ለአለም ያሳየም ጭምር ነው። FBC

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy