Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የላይቤሪያ ፕሬዚዳንት ጉብኝት የሀገራቱን ግንኙነት የበለጠ ያሚያጠናክር መሆኑ ተገለጸ

0 414

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የላይቤሪያዋ ፕሬዚዳንት አሌን ጆንሰን ሰርሊፍ ጉብኝት የኢትዮጵያና ላይቤሪያን ግንኙነት ወደ ተሻለ ምዕራፍ ማሸጋገር የሚያስችል መሰረት የተጣለበት መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።የሚስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ ተወልደ ሙሉጌታ በሳምንቱ በዲፕሎማሲው መስክ የተከናወኑ ተግባራትን አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።ፕሬዚዳንት አሌን ጆንሰን ሰርሊፍ የሁለቱን አገራት ግንኙነት ለማሳደግ ያለመ የሦስት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት አድርገው ዛሬ ወደ አገራቸው ተመልሰዋል።ፕሬዚዳንቷ በቆይታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝና ከፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ ጋር የተወያዩ ሲሆን በአምስት ዘርፎች በትብብር መስራት የሚያስችል ስምምነትም ተፈርሟል።የኢንዱስትሪና የዓሣ ሃብት ልማት እንዲሁም ትምህርት ስምምነት ከተደረሰባቸው መስኮች መካከል እንደሆኑ አቶ ተወልደ ጠቅሰዋል።ፕሬዚዳንት ሰርሊፍ የሀዋሳና ዱከም ኢንዱስትሪ ፓርኮችን መጎብኘታቸውንና አገራቸው በዘርፉ የኢትዮጵያን ልምድ መቅሰም እንደምትሻ መናገራቸውንም ገልጸዋል አቶ ተወልደ።በላይቤሪያ የተከሰተውን ግጭት ለማረጋጋትና የኢቦላ ወረርሽኝ ለመከላከል ኢትዮጵያ ላደረገችው ድጋፍ ፕሬዚዳንቷ ምስጋና ማቅረባቸውንም ተናግረዋል። የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫኬር ማያርዲት ጉብኝት ሌላው የሳምንቱ አበይት ጉዳይ መሆኑንም አቶ ተወልደ አንስተዋል። በኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን መካከል ከተፈረሙ ስምንት ስምምነቶች መካከል ንግድ፣ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ የመንገድ ልማትና ትምህርትን ጠቅሰዋል። “በደቡብ ሱዳን ዘላቂ ሠላም እንዲሰፍን ኢትዮጵያ በኢጋድ በኩል ያላሰለሰ ጥረት ስታደርግ ቆይታለች” ያሉት አቶ ተወልደ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የተፈረሙ ስምምነቶች ወደ ተግባር እንዲቀየሩ ሚናዋን መወጣቷን እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል። በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሂሩት ዘመነ የተመራ የልዑካን ቡድን በጄኔቭ ስዊዘርላንድ የሰብዓዊ መብት ምክር ቤት ስብሰባ ለመታደም ወደ ስፍራው ማቅናቱም ሌላው የሳምንቱ ክስተት መሆኑን ተናግረዋል። ሚኒስትር ዴኤታዋ በስብሰባው ላይ በኢትዮጵያ ስላለው የሰብዓዊ መብት አያያዝ ማብራሪያ መስጠታቸውንም ገልጸዋል።በተለይም በአገሪቷ ተከስቶ በነበረው ግጭት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተፈጥረው ከሆነ የሚያጣራ ቡድን መቋቋሙንና በወቅቱ የነበረውን የሰብዓዊ መብት አያያዝ ሁኔታ የሚዳስስ ሪፖርት ለተወካዮች ምክር ቤት መቅረቡን መናገራቸውንም አክለዋል። የግለሰብና የቡድን መብቶችን ለማስከበር አገሪቷ እየተከተለችው ባለው አሰራርና በተገኙ ውጤቶች ዙሪያ ማብራሪያ መስጠታቸውንም እንዲሁ። በህዳሴው ግድብ ላይ ጥቃት ለማድረስ 20 የሚደርሱ ጸረ ሠላም ኃይሎች ያደረጉት ሙከራ መክሸፉም ሌላው የሳምንቱ መነጋገሪያ ጉዳይ እንደነበር አስታውሰዋል። መንግሥት በወሰደው እርምጃ 13ቱ ሲገደሉ ሰባቱ በቁጥጥር ስር እንደዋሉ መዘገቡ ይታወሳል።አቶ ተወልደ ስለ ጉዳዩ በሰጡት ማብራሪያ “ጥቃቱ ከመድረሱ በፊት ድርጊቱ መክሸፉ ኢትዮጵያ ሁሌም ዝግጁ መሆኗን ያመላከተ ነው” ብለዋል። የጸረ ሠላም ኃይሎቹ ድርጊት መክሸፍ አገሪቷ ሠላምና መረጋጋቷን ለማስቀጠሏ ማሳያ መሆኑን የተናገሩት ቃል አቀባዩ ይኸው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል። ዜጎች ከጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የአገሪቷ ሠላም እንዳይደፈርስ የጀመሩት ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚኖርበትም አስገንዝበዋል።

ምንጭ ፦ኢዜአ

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy