Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የሰላም መግቢያ በር

0 404

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የሰላም መግቢያ በር  (ዳዊት ምትኩ)

ፌዴራሊዝም በህዝቦች መካከል ያልተማከለ የፖለቲካ ስርዓት የመንግስት ስልጣንና ተግባራት በፌዴራል የመንግስት መስተዳድር እና በክልል መንግስታት መካከል በሕገ መንግስት በግልፅ የሚከፋፈልበት ስርዓት ነው። በዚህ ስርዓት የመንግስት ስልጣን፣ ኃላፊነት፣ አስተዳደር፣ ግብር የመሰብሰብና የፋይናንስ ሃብት የውሳኔ አሰጣጥ ሂደት በአንድ ማዕከል ወይም ቦታ ብቻ የተጠራቀሙና የተከማቹ እንዲሆኑ አይደረጉም—በተለያዩ ቦታ የስልጣን ማዕከላት ወይም ቦታዎች ይከፋፈላሉ እንጂ። ይህም የፌዴራል ስርዓት ዋነኛ መገለጫ ያልተማከለ የመንግስት ስልጣን፣ ኃላፊነት፣ አስተዳደር እና የውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ያለው መሆኑን ያሳየናል።

የፌዴራላዊ ስርዓት በአንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ ውስጥ ሁለት ወይም ከሁለት በላይ የሆኑ የመንግስት መስተዳድሮችን ያዋቀረ፣ ለተወሰኑ ጉዳዮች በጋራ መስተዳድር አማካኝነት መስተዳድሮች ተቋማት የራስ አስተዳደርን የሚያቋቁም የስርዓት ዓይነት ነው። በዚህ ዓይነት የስርዓት አወቃቀር የፌዴራሉ መስተዳድር እና የክልል መስተዳድሮች የበላይና የበታች ግንኙነት የላቸውም።

ምንም እንኳን በህገ መንግስቱ ተለይተው ለየራሳቸው በተሰጣቸው ጉዳዮች እያንዳንዳቸው ያላቸው ስልጣን የተለያየና የየራሳቸውም ነፃነት የተጠበቀ ቢሆንም፣ የመንግስት አስተዳደር ስራና ሂደት በሁለቱ መስተዳድሮች መካከል የመደጋገፍና የመቆራኘት ስራን የግድ ማለቱ አይቀሬ ነው። በመሆኑም በሁለቱ መስተዳድሮች የተወሰነ የኃላፊነት መደራረቦች እና መደጋገፍ ይኖራል። ይህም ሁሉም የፌዴራል ስርዓቶች የሚጋሩት የወል ባህሪ ነው ማለት ይቻላል።

የፌዴራል የፖለቲካ ስርዓትን የሚከተሉ ሀገሮች የተፃፈ ሕገ መንግስት ያላቸው ናቸው። ከዚህ በተጨማሪም የዚሁ ስርዓት ተከታይ ሀገሮች በተለያየ ሁኔታ ለሕገ-መንግስት የበላይነት መረጋገጥ ልዩ ትኩረት ይሰጣሉ። ይህም የሆነበት ዋነኛ ምክንያት የፌዴራል ሕገ-መንግስት፣ የፌዴራል የፖለቲካ ማህበረሰብ ከመገንባት፣ ከሕዝቦች ሉዓላዊነት የስልጣን ባለቤት መሆናቸውን መሰረት በማድረግ የመንግስትን ስልጣን በሁለት ወይም ከዚያም በላይ ባሉ የመንግስት አስተዳደር ማዕከላት መካከል ያከፋፈሉበት፣ ስላላቸው ስልጣንና ተግባር የወሰኑበት፣ ጥቅሞችን ማቻቻል መደራደርና ስልጣንን ያከፋፈሉበት፣ የፌዴራል ስርዓታቸውን ያዋቀሩበት፣ ያደራጁበትና ስለ አሰራሩ የደነገጉበት የበላይ ህግ መሆኑ ብቻ አይደለም። የሀገራቸው አጠቃላይ የማህበራዊ፣ የኢኮኖሚያዊ የፖለቲካዊና የሕግ ስርዓት የሚመረኮዝበትና የሚገነባበት ዋና የሕግ ማዕቀፍ በመሆኑም ጭምር ነው።

ህገ-መንግስት በአንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ ውስጥ በጋራ ጉዳዮቻቸው የጋራ የመንግስት መስተዳድር ተቋማትን ለማቋቋም፣ ለየራሳቸው ለሆኑ ጉዳዮች ደግሞ ከሌላው የራስ መንግስት መስተዳድሮን ለማቋቋም ፈቃድና ፍላጎታቸውን የገለፁበት ከፍተኛ የህግና የፖለቲካ ቃልኪዳን ሰነድ ነው። በዚህም ስርዓቱ እያንዳንዱ መስተዳድር ለህገ-መንግስቱ ተገዥ የመሆን ግዴታ እንዳለበት ይደነግጋል።

በዚህ ስርዓት ውስጥ ከህገ-መንግስቱ ጋር የሚቃረን ወይም የሚጋጭ ተግባር በህግ ተቀባይነት አይኖረውም። ስለዚህ የህገ- መንግስት የበላይነትን መቀበል ለፌዴራል ስርዓት መተግበርና ስኬታማነት ቁልፉና ወሳኙ ጉዳይ ነው ማለት ይቻላል። በፌዴራል ሀገሮች ህገ-መንግስትን የማክበርና የማስከበር ኃላፊነትን በተግባር የማዋሉን ሁኔታ እጅግ አስፈላጊ የሚያደርገው፤ የፌዴራሉን መስተዳድር እና በእርሱ ስር የታቀፉ አባል ክልላዊ መስተዳድሮች ማንነትና ህልውና የሚመነጨው እንዲሁም የሚመረኮዘው በህገ መንግስቱ በመሆኑ ምክንያት ነው።

ምንም እንኳ በፌዴሬሽኖች መካከል እንደ ምሳሌነት ከላይ የተጠቀሱት የጋራ ባህሪያት የሚታዩ ቢሆንም፤ ሁሉም ፌዴሬሽኖች አንድ ዓይነት አወቃቀርን ሊከተሉ አይችሉም። እርግጥም ፌዴሬሽኖች ግዙፍ ልዩነቶች ሊኖራቸው የግድ ነው። ምክንያቱም ፌዴሬሽኖቹ ስርዓቱን እንዲያቋቁሙ ያስገደዷቸው የየራሳቸው የታሪክ፣ የፖለቲካ፣ የማህበራዊና የኢኮኖሚያዊ ነባራዊ ሁኔታዎች የሚለያዩ በመሆናቸው ነው። ከእነዚህ ልዩነቶች ውስጥ ፌዴራላዊ ስርዓቱ በውስጡ የሚያቅፋቸው የብዝሃነት አስተሳሰቦች ናቸው።

እነዚህ ነባራዊ ሁኔታዎች ፌዴራሊዝም በልዩነት ውስጥ ያለን አንድነት የሚያከብር የሰላም በር እንጂ የግጭቶች መግቢያ እንዲሆን የሚያደርጉት አይደሉም። የአገራችን ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ህገ- መንግሥቱን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በገዛ ፈቃዳቸው ተስማምተው እና ተማምነው እንዲያፀድቁት የተጫውተው ሚና የላቀ መሆኑ በተግባር ታይቷል። እርግጥ የኢትዮጵያ ባህል፣ ቋንቋ እና ታሪክ ማለት የኢትዮጵያ ህዝቦች ባህሎች፣ ቋንቋዎች እና ታሪኮች ተደምረው የሚፈጥሩት ውህደት ነው። ይህ የሀገራችን ነባራዊ ክስተትን በልዩነት ውስጥ ባለ አንድነት ሊያስተናግድ የሚችለው በፌዴራሊዝም ሥርዓት ውስጥ ነው። ለኢትዮጵያ ብቸኛው አማራጭ ፌዴራላዊ ሥርዓትን መከተል መሆኑን የሥርዓቱ ባለቤቶች የሆኑት የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በፅናት አምነውበት እንዲተገበር የወሰኑትም ለዚሁ ነው።

ይህ ውሳኔያቸውም ለዛሬው እነርሱነታቸው ያበቃቸው ከመሆኑም በላይ፤ የፌዴራል ሥርዓቱ አንዳንድ ወገኖችና ፅንፈኞች ሃቁን ካለመገንዘብ አሊያም ለመረዳት ካለመፈለግ ካላቸው ፍላጎት በመነሳት እንደሚሉት ዓይነት በድንቡሽት ላይ የተገነባ ቤት አለመሆኑንም አሳይተዋል። ምክንያቱም ሥርዓቱ በህዝቦች ፈቃድ ተረጋግጦ በጠንካራ መሠረት ላይ የተገነባ መሆኑን ከ25 ዓመታት በኋላም ቢሆን በሚገባ ማረጋገጥ ስለቻሉ ነው።

እርግጥ የእነዚህ ወገኖች የማምታታትና የማደናገር ሙከራ ምንም ውጤት የሚያስገኝላቸው አይመስለኝም። ምክንያቱም መላው የሀገሪቱ ህዝቦች በደማቸው የፃፉት ህገ መንግሥት ፀድቆ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦችም በአንድነት ተሳስረው የእድገት ጉዟቸውን ስለተያያዙት ነው።

ለነገሩ አንዳንዶቹ ይህን ሃቅ እያዩ እንኳን በማንኛው በማደግ ላይ በሚገኝ ሀገር ውሰጥ እንደሚፈጠረው በግጦሽ ቦታና በውኃ ምክንያት በአንዳንድ የሀገራችን ብሔረሰቦች መካከል የሚከሰቱ ነባራዊ ክሰተቶችን እንዲሁም አማርኛ ተናጋሪዎች ከአንዳንድ አካባቢዎች ተባረሩ በሚሉ የፌዴራል ሥርዓቱ በእነዚህ ጉዳዮች ምክንያት ከሽፏል እስከማለት ደርሰዋል። ይህ ግን ፈፅሞ ውሸት ነው።

እርግጥ ግጭቶች የትም ይከሰታሉ። መነሻቸው ግን ፌዴራላዊ ስርዓቱ አይደለም። እርግጥ ከሰው ልጅ ግጭቶች አኳያ በዓለማችን ላይ የተፈጥሮ ሀብት እጥረት መኖሩ እንደ መንስኤ የሚታይ ነው። ሀገራችንም ከዚህ የተፈጥሮ ዕውነታ ልትርቅ አትችልም። እንደ ማንኛውም የዓለማችን ክፍል የተፈጥሮ ሀብት እጥረት ያለባት ስለሆነች። እናም ግጭት ትናንትም ይሁን ዛሬ እንዲሁም ነገ መኖሩ ያለና የሚኖር ጉዳይ መሆኑን ግንዛቤ መያዝ ተገቢ ይመስለኛል።

ያም ሆኖ ግን ፌዴራላዊ ሥርዓቱ ካለፉት ጊዜያት ጋር ፈፅሞ በማይገናኝ መልኩ ለዚህ ነባራዊ ችግር ትኩረት ሰጥቶ በመስራቱ ሁኔታውን በመለወጥ ላይ ይገኛል። የሀገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ያላቸውን የተፈጥሮ ሀብት በአግባቡ እንዲጠቀሙና ከሌሎች ህዝቦች ጋር በመተሳሰብ የጋራ ሀብታቸው እንዲሆን ማድረግ ችሏል። ዳሩ ግን ያለፉት ሥርዓቶች በሀገሪቱ ህዝቦች ውስጥ ፈጥረውት ያለፉት የተዛቡ አመለካከቶች እንዲህ በቀላሉ በጥቂት ዓመታት በቀላሉ የሚቀየሩ አይደሉም— ሂደትን፣ ጊዜንና የአስተሳሰብ ለውጥን ይጠይቃሉ። ይህን ዕውን ለማድረግም ሥርዓቱ አንድነትን በሚያጠናክሩና በሚያፀኑ መሰረቶች ላይ በመመርኮዝ እየሰራ ይገኛል።

በሀገራችን በመገንባት ላይ ያለው ፌዴራላዊ ሥርዓት ለሚፈጠሩ ሁነቶች ወቅታዊና አስተማማኝ ምላሽ እየሰጠ ዛሬ ላይ ደርሷል። በዚህም ሊፈጠሩ የሚችሉ አነስተኛ ኑባሬያዊ ተግዳሮቶችን በመፍታት ሁሉም የሀገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በጋራ ተሳስበውና ተፈቃቅደው በአንድነት የሚኖሩበትን አስተማማኝና ህዝቦችን ተጠቃሚ ያደረገ ሥርዓት መፍጠርም ተችሏል። ይህ ሁኔታም ፌዴራላዊ ስርዓቱ የሰላም በር መሆኑንና ግጭቶችን እንደ ማንኛውም አገር የመፍታት ብቃት ያለው መሆኑን ያረጋግጣል።

                                           

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy