Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የቀድሞዋ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ሽኝት ተደረገላቸው

0 355

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ተሰናባቿ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ዶክተር ንኮሳዛና ዲላሚኒ ዙማ አህጉሪቱን ለማስተሳሰር ያደረጉት ጥረት የሚበረታታ እንደነበር ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ተናገሩ።የስራ ዘመናቸው በስኬት ይጠናቀቅ ዘንድ በየደረጃው የሚገኙ የኢትዮጵያ የስራ ኃላፊዎች ድጋፍ እንዳልተለያቸው ደግሞ ዲላሚኒ ዙማ ገልፀዋል።

ፕሬዝዳንት ሙላቱ ዛሬ በጽሕፈት ቤታቸው የቀድሞ የሕብረቱን ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ዶክተር ንኮሳዛና ዲላሚኒ ዙማን ሽኝት አድርገውላቸዋል።ሽኝቱን የተከታተሉት በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽንና በአፍሪካ ሕብረት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ዋህደ በላይ እንደተናገሩት ፕሬዝዳንቱ ”ሊቀ-መንበሯ በቆይታቸው የአህጉሪቱን ችግሮች በመፍታት ረገድ ትልቅ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል” ብለዋል።

ለሕብረቱ መጠናከርና ሰላም የሰፈነባትና የበለፀገች አህጉር ለመፍጠር ያበረከቱት አስተዋጽኦ በአባል አገራቱ ዘንድ የሚያስመሰግናቸው መሆኑንም ነው የተናገሩት።በአህጉሪቱ ለመልካም አስተዳደር እንዲሁም ዴሞክራሲያዊ አስተዳደርና የህግ የበላይነትን ለማስፈንም የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ሲያበረክቱ ቆይተዋል ሲሉ ገልጸዋል።

አህጉሪቱን በስኬት ሲመሩ መቆየታቸው በተለይም ‘አይችሉም’ ተብለው ለሚፈረጁት ሴቶች አርአያ እንደሚያደርጋቸው ፕሬዝዳንቱ መናገራቸውን አስረድተዋል።የሴቶችን ተሳትፎ እና አቅም በማሳደግ በኩልም ዙማ በሊቀ-መንበርነታቸው ዘመን ጉልህ ድርሻ ሲያበረክቱ መቆየታቸውንም ገልጸዋል።በተለይም አጀንዳ 2063ን በማስፈፀም ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ነው የተናገሩት።

ደቡብ አፍሪካና ኢትዮጵያ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን በሚያጠናክሩበት መስክ ላይ የነበራቸው ሚና ከፍተኛ እንደነበርም ነው የገለጹት።ተሰናባቿ የሕብረቱ ሊቀ-መንበር ዶክተር ንኮሳዛና ዲላሚኒ ዙማ በበኩላቸው ”ኢትዮጵያ በቆየሁባቸው አራት ዓመታት ተኩል ከአገሪቱ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ጋር የነበረኝ ትብብር ስኬታማ እንድሆን አድርጎኛል” ነው ያሉት፡ኢትዮጵያን ተማሪ ከነበሩበት ከ1976 ዓ.ም ጀምሮ እንደሚያውቋት የተናገሩት ዙማ አገሪቱ በአሁኑ ወቅት ያሳየችው ለውጥ “የተለየ ነው” ብለዋል።ይኸም ለሌሎች የአፍሪካ አገራት በአርዓያነት የሚጠቀስ እንደሆነ ተናግረዋል።

”እንደ አገር በተለይም በአዲስ አበባ ያለው ምግብ፣ ሙዚቃውና አየሩ በጣም የሚያስደስት ነው፣ በቆይታዬም ስኬታማ ነበርኩ፤ ነገር ግን አሁንም ለአህጉሪቷ ዕድገት ብዙ መስራት ይጠበቅብኛል” ብለዋል።ዶክተር ንኮሳዛና ዲላሚኒ ዙማ የአራት ዓመት ተኩል የሕብረቱ ሊቀ-መንበርነታቸውን አጠናቀው ባለፈው ጥር ወር በትረ-ስልጣኑን ለቻዳዊው ሙሳ ፋቂ መሃማት ማስረከባቸው ይታወሳል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy