Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የቀጣናው የወደብ ቅርምትና የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ

0 1,087

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስና ሳውዲአረቢያ የአሰብን ወደብ ለ30 ዓመታት ተከራይተው የጦር ሠፈር ገንብተዋል፡፡ በጅቡቲ ወደብ ደግሞ አሜሪካ፣ ፈረንሳይ፣ እንግሊዝ፣ ቻይናና ሌሎች የጦር ሰፈር የገነቡ ሲሆን፤ ግብፅና ቱርክም ፈቃድ እንዳገኙ ይፋ የሆነ ነገር ባይኖርም «የእንግባ» ጥያቄ አቅርበዋል። በቅርቡም የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ ከግብፅ ጋር በጋራ በመሆን በበርበራ ወደብ ዙሪያ የጦር ሠፈር ለመገንባት ፈቃድ አግኝታለች፡፡

የሱዳን ወደብን በተመለከተ እስካሁን ይፋ የሆነ ነገር ባይኖርም ከሳውዲአረቢያ በተለይም ከኳታርና ጋር የጠበቀ የኢንቨስትመንት ግንኙነት ያላት መሆኑ ሲታሰብ ጥያቄው ቢቀርብ የሱዳን እንቢተኝነት አጠራጣሪ ነው፤ የሶማሊያም አዲሱ መንግሥት ለአረብ አገራት ያደላ በመሆኑ ወደቡን የሚጠይቀው ካገኘ ዓይኑን ሊያሽ እንደማይችል አካባቢውን ጠንቅቀው የሚያወቁ ሁሉ ይገልጻሉ። ይህ የጎረቤት አገራትን ወደብ መቀራመት «ለኢትዮጵያ ስጋት ነው» ብለው የሚከራከራከሩ በአንድ ወገን፤ «እንቅስቃሴውን በአግባቡ መያዝ ከተቻለ ቱሩፋቱ ያመዝናል» የሚሉ በሌላ ወገን እየተከራከሩ ናቸው፡፡

ለምሥራቅ አፍሪካና መካከለኛው ምሥራቅ ፖለቲካ ቅርበት ያላቸውና በግጭትና ግጭት አፈታት ዙሪያ የሚሰሩት አቶ ካህሳይ ገብረእየሱስ የአገራቱ ወደቦቹን የመቀራመት አንዱ ምክንያት ከቀይ ባህር ወደ ሕንድ ውቂያኖስ የሚወስደው መስመር በቀን የአንድ ቢሊዮን ዶላር ንግድ የሚተላለፍበት በመሆኑ መስመሩን በመቆጣጠር የንግድ እንቅስቃሴያቸው እንዳይገታ በማድረግ የበላይነትን ለመያዝ የፈጠረው ሽኩቻ መሆኑን ይናገራሉ። ሳውዲአረቢያ የባህር ኃይሏን በዓለም ኃያል የማድረግና እስልምና ባለባቸው አገራት የማስገባት፤ ግብፅ ደግሞ የቀጣናውን ፖለቲካ ለመቆጣጠር ያላት ፍላጎት ተጨማሪ ምክንያቶች መሆናቸውን ነው አቶ ካህሳይ የሚያነሱት።

ለፖለቲካል ሣይንስ ምሁሩ ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርኸተስፋ ለአገራቱ የወደብ ቅርምት ውስጥ መግባት መሠረታዊ ሰበቡ የየመን ጦርነት ነው፡፡ በሳውዲአረቢያና በኢራን የሚመራው የሱኒና የሽያት የሃይማኖት ቅራኔና ፉክክርም ሌላው ምክንያት ነው፡፡ ይህ ወደቦችን የመቆጣጠር እንቅስቃሴ በቀጣናው የጦር መሣሪያ እንዲረጭ በማድረግ አካባቢውን ለጦርነትና ትርምስ የሚያመቻች መሆኑ ሲታሰብ ስጋቱ ቀላል እንዳልሆነ ሊጤን ይገባልም ባይ ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ስትራቴጂካዊ ጥናት ኢንስቲትዩት የዓለም አቀፍ ሕግና ግንኙነት ምሁሩ አቶ መላኩ ሙሉዓለም የሁለቱ ምሁራንን ሃሳብ ይጋራሉ። ቀጣናው ካለው ከፍተኛ ጥቅም አንጻር፤ አገራቱ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ በዲፕሎማሲ ሳይሆን በኃይል ለማስከበር እሽቅድድም ውስጥ መግባታቸውን ነው አቶ መላኩ የሚናገሩት።

አቶ ካህሳይ እንደሚሉት፤ የጅቡቲና የኤርትራ ወደቦች በሦስተኛ ወገን መያዛቸው በኢትዮጵያ ላይ የሚያመጣው የጎላ ጉዳት የለም። የጅቡቲን ወደብ ከኢትዮጵያ ውጪ የሚጠቀም አገር አለመኖሩና አገሪቱ ብዙም በሀብት የታደለች አለመሆኗ ጅቡቲ ከኢትዮጵያ ጉያ እንዳትወጣ ያደርጋታል፡፡ የኤርትራ መንግሥትም ሆነ መሪ ድርጅቱ እየሞቱ በመሆኑ የአሰብ ወደብ ኪራይ ስጋት የለውም፡፡ ጉዳት ከተባለ ግን መንግሥቱ መሞቱ ስለማይቀር ቆላማው የቀይ ባህር አካባቢ የአሸባሪዎች መፈልፈያ ሊሆን መቻሉ ነው፡፡

በአቶ ካህሳይ አተያይ፤ ለኢትዮጵያ አስቸጋሪ የሚሆነው ሶማሊያ ወደቧን ብታከራይ ነው። ምክንያቱም አገሪቷ በጎሳ የተከፋፈለችና እርስ በርሳቸው የሚቆራቆሱባት አገር መሆኗ፤ አሁን ሥልጣን የጨበጠው መንግሥትም ከአፍሪካ ይልቅ ለአረብ አገራት ልቡ ያደላ መሆኑ ነው፡፡ በዚህ እውነታ ላይ ሶማሊያ ወደቧን ለሦስተኛ አገር አሳልፋ የምትሰጥ ከሆነ ለኢትዮጵያ አስቸጋሪ ይሆናል፡፡

ይሄኛው የአቶ ካህሳይ ሃሳብ ለአቶ መላኩ ትክክል አይደለም፡፡ «ጎረቤቶቻችን ወደቦቻቸውን ለሦስተኛ ወገን አሳልፈው መሰጠታቸው ለኢትዮጵያ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል» ይሉና፤ በጎረቤት አገራት የጦር ሰፈር ሲመሰረት አገራቱ የጦር መሣሪያ ስለሚያገኙ በኢትዮጵያና በእነርሱ መካከል የኃይል ሚዛን ልዩነት ይፈጠራል። አገራቱ አካባቢውን ለቀው ሲወጡም መሣሪያቸውን ለማጓጓዝ ከፍተኛ ወጪ ስለሚጠይቃቸው ትተውት ይሄዳሉ፡፡ ይሄ ደግሞ እንደ ኤርትራ ያሉ ተንኳሽና ሰላማዊ የመንግሥት ሽግግር ለማድረግ ዝግጅት የሌላቸው አገሮች የልብ ልብ ተሰምቶቸው ወደ ጦርነት ሊገቡ ይችላሉ፤ የእርስ በእርስ ጦርነትም ማስከተሉ አይቀርም፡፡

ኢትዮጵያ ከጎረቤትና ከአፍሪካ አገራት ጋር ባላትን ግንኙነት ላይ ምርምር የሚያደርጉትና «ጅቡቲ የጥገኝነታችን መስፈሪያ» እና «ብላክ ኢትዮጵያ» የተባሉ መጽሐፎች ደራሲ አቶ በለጠ በላቸው፤ የጎረቤት አገራት ወደቦች በሦስተኛ ወገን መያዛቸው መሠረተ ልማትን ለማስፋፋትና አሸባሪዎችን ለመዋጋት ከሆነ ኢትዮጵያ ተጠቃሚ ልትሆን የምትችልበት ዕድሉ አለ ይላሉ፡፡ ነገር ግን የወደብ ዋጋ ጭማሪን ሊያመጣ መቻሉ፤ የግብፅ በእነዚህ አገራት ወደቦች ላይ ፍላጎት ማሳደሯ ለኢትዮጵያ አደገኛ ነው ይላሉ። ሁለቱም አጋጣሚ የሚወሰነው ግን ከአገራቱ ጋር በሚኖር ግንኙነት ይሆናል ሲሉም ይናገራሉ።

ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፤ «ጎረቤቶቻችን ወደቦቻቸውን አሳልፈው መስጠታቸው በኢትዮጵያ ላይ ጫናም ሆነ ጉዳት አያመጣም። የኢትዮጵያ መከላከያ በጦር ሜዳ በተግባር የተፈተነ ነው። አካራዮቹም ሆነ ተከራዮቹ ይህን ጠንቅቀው ስለሚያውቁ ጦርነት ለመለኮስ አይደፍሩም። ከዚያ ይልቅ ጎረቤቶቻችን በኪራይም ይሁን በእርዳታ በሚያገኙት ድጋፍ መሠረተ ልማት ስለሚያስፋፉ ኢትዮጵያ ተጠቃሚ ትሆናለች። ለዚህ ግን ጠንካራ ሥራ መሰራት አለበት» ሲሉ ይመክራሉ።

አቶ በለጠ በበኩላቸው፤ ከጎረቤት አገራት ጋር በማህበራዊ፣ በኢከኖሚ፣ በፖለቲካም ይሁን በሌላ ያለውን ትስስር ወደብ ከሚከራዩ አገራት የበለጠ ማጠናከር ያስፈልጋል ይላሉ። ከዚህም ጎን ለጎን የመደራደር አቅምን ማሳደግ፤ ጎረቤቶቻችን ለምን ወደ ሌላ አገር ማማተር እንደጀመሩ መገምገምና ማስተካከያ ማድረግ አሰፈላጊ መሆኑንም መክረዋል።

አቶ መላኩ፤ ደግሞ ኢትዮጵያ ጥቅሟን የሚጉዱትን አካላት በጸጥታው ምክር ቤት ጫና በማሳደር እንዲለወጥ ማድረግ እንዳለባት፤ የወደቦቹ ኪራይ አሁን ጉዳት ባያደርስም በቀጣይ የሚኖራቸው ተፅዕኖ በጥልቀት ተመርምሮ አማራጮችን በማስቀመጥ መስራትና በጥንቃቄ መያዝ እንዳበት ነው የሚመክሩት።

አቶ ካህሳይም፤ ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በቀጣናው በኢኮኖሚና በፖለቲካ አመርቂ ሥራ በመስራቷ የአካባቢውን መልከዓ ምድራዊ ፖለቲካ በላቀ መልኩ ለመቆጣጠር እንዳስቻላት ይገልጹና በቀጣይም የውስጥ ችግርን ከመፍታት በተጨማሪ ከጎረቤት አገራት ጋር የበለጠ ለመቀራረብ ጠንካራ የዲፕሎማሲ ሥራ መስራት፣ የአገሪቱ ምሁራንንም በማሳተፍ ጥናት በማድረግ በቀጣናው የሚፈጠሩ ችግሮችን የሚፈታ አካሄድ ማፍለቅ ያስፈልጋል። ይህ ከሆነ ምንም እንኳ በቀጣናው ያለው ችግር ፈታኝ ቢሆንም ኢትዮጵያ አሸናፊ ሆና መውጣቷ አይቀርም ብለዋል፡፡ አጎናፍር ገዛኸኝ

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy