Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የብሄራዊ መግባባት አለ እና የለም «እሰጥ አገባ»

0 732

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ በተደጋጋሚ ከሚሰሙ ጉዳዮች መካከል ብሄራዊ መግባባት የሚለው ሚዛኑን ይደፋል፡፡ እንደየአገሩ ትርጓሜ የሚለያይ ቢሆንም፤ ብሄራዊ መግባባት ዋና ዋና አገራዊ በሆኑ ታሪካዊ፣ ፖለቲካዊና በልማት አጀንዳዎች ላይ ተመሳሳይ አመለካከት መያዝ እንደሆነ የድረ ገጽ መረጃዎች ያብራራሉ።

ይህ አመለካከትም በአብዛኛው የአገሪቱ ህዝብ ዘንድ ሲንፀባረቅ ብሄራዊ መግባባት ተፈጥሯል ማለት ይቻላል የሚሉት በዲላ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና የዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህሩ አቶ ሙኸዲን አማን ናቸው።

ብሄራዊ መግባባት በአገር ደረጃ ለማምጣት በመሰረታዊነት የመንግስት የፖለቲካ ውሳኔና መልካም ፈቃድ ያስፈልጋል። ኢትዮጵያ ውስጥ በፖለቲካው መስክ ሁለት ጫፎች አሉ። እነዚህን የተለያዩ አመለካከቶች ወደ አንድ ለማምጣት (ብሄራዊ መግባባት ለመፍጠር) መንግስት ቀዳሚ ሚና መጫወት ይኖርበታል። ምክንያቱም መንግስት ስልጣን አለው። አስፈፃሚ አካል ነው። ስለዚህ የሚታዩትን ጫፍ የወጡ ልዩነቶች ለማጥበብና ወደ አንድ ለማምጣት የአንበሳውን ድርሻ መውሰድ አለበት የሚል እምነት አላቸው፤ አቶ ሙኸዲን።

ብሄራዊ መግባባት በመፍጠሩ ሂደት ውስጥ ምሁሩንና ተፅእኖ ፈጣሪ ሰዎችን ማሳተፍ ይገባል ይላሉ መምህሩ። በአገሪቱ ፖለቲካ ስርዓትና ታሪክ የተለያዩ ሀሳቦችን የሚያራምዱ ሰዎችን ሁሉ ማካተት ያስፈልጋል። በአገሪቱ በተፈጠሩ ቅራኔዎችና አለመግባባቶች ዙሪያ ሁሉም ይመለከተናል ከሚሉ ወገኖች ጋር ግልፅ ውይይት በማድረግ ወደ አንድ ድምዳሜ በመድረስ የጋራ አመለካከት መያዝ ብሄራዊ መግባባት ለመፍጠር ያስችላል ሲሉም ምክረ ሀሳብ ይሰጣሉ።

መምህሩ እንደሚሉትም፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ብሄራዊ መግባባት አለ ለማለት አስቸጋሪ ነው። ምክንያቱም አሁንም ድረስ በሁለት ጫፍ ላይ ያሉ ፖለቲከኞችንም ሆነ ግለሰቦችን የማያስማሙ ጉዳዮች አሉና ነው፡፡ ያም ሆኖ ግን መንግስት እንደሚለው እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አይነት ሜጋ ፕሮጀክቶች ዙሪያ፣ ከሌላው አገር በተለየም መልኩ ኢትዮጵያዊነት ስሜት ላይ ህዝቡ ተመሳሳይ አቋም አለው። ይህ አቋምና አመለካከት በኳስ፣ በሩጫና በጦርነት ጎልቶ ይታያል። አደጋ ሲመጣ ኢትዮጵያዊያንን አንድ የሚያደርጓቸው ነገሮች ብዙ ናቸው። ለምሳሌ የኢትዮኤርትራን ጦርነት መጥቀስ ይቻላል። እነዚህ ነገሮች ብሄራዊ መግባባት መኖሩን የሚያስረዱ ክስተቶች ናቸው።

ብሄራዊ መግባባትን ማየት የሚስፈልገው በአገራዊ አንኳር አጃንዳዎች ላይ አጠቃላይ ህዝቡ ያለውን አመለካከት በመመዘን እንጂ ከመንግስት አቅጣጫ ብቻ መሆን የለበትም። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከኢትዮጵያዊነት ስሜት ይልቅ ለብሄር ትኩረት መስጠት እየታየ ነው፡፡ እኔ ብቻ የሚል ስሜቶች በተለያዩ ክልሎች እየተስተዋሉ ናቸው። እነዚህ ነገሮች ላይ የተማሩ ሰዎችም የየራሳቸው ጫፍ የወጣ ሀሳብ ያራምዳሉ። በዚህ የተነሳ ብሄራዊ መግባባቱ ካለበትም ደረጃ እንዳይቀንስ ስጋት አለኝ፡፡ ስለዚህ የመንግስት ስራ መሆን ያለበት የፌዴራል ስርዓቱ በብሄር የተቃኘ መሆኑ ለመጠላላት ወይም ለመቃረን አለመሆኑን ሳይታክት ማስረዳት ነው፡፡ ብለዋልምሁሩ።

ይህ ሲባል ግን ስራው የመንግስት ጉዳይ ብቻ ነው ማለት እንዳልሆነ ለምሳሌ ሲቪክ ማህበራትም የራሳቸወ ድረሻ እንዳላቸው ነው አቶ ሙኸዲን የሚገልጹት። ማህበራቱም የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ የመጫወቻ ሜዳውን ማስተካከል ያስፈልጋል። የተለያዩ የተገለሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን ጭምር ስለብሄራዊ መግባባቱ ሲባል የውይይት መድረክ በመፍጠር ማሳተፍም ይገባል። ስለዚህ መንግስት ብቻ ሳይሆን ሁሉም ወገን ብሄራዊ መግባባት እንዲፈጠር መስራት ይኖርበታል የአቶ ሙኸዲን ምከረ ሀሳብ ነው።

የሃረሪ ወጣቶች ፊዴሬሽን ፕሬዚዳንትና የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሪሽን ስራ አስፈፃሚ አባል ወጣት ሙክታር ሳሊም በአቶ ሙኸዲን ሀሳብ ላይ በከፊል ይስማማል። ብሄራዊ መግባባት ሲባል አብዛኛው የአገሪቱ ህዝብ ከህገ መንግስቱ ጀምሮ አገሪቷ በምታወጣቸው ህጎች፣ ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎችና ዕቅዶችና ስራዎች ላይ የጋራ አመለካከት መያዝና በሙሉ መንፈስ ተግባራዊ ማድረግን የሚጠይቅ ነው ይላል ወጣቱ። ከዚህ አኳያ እንደ አገራችን ተጨባጭ ሁኔታ በሁሉም ጉዳዮች ላይ ብሄራዊ መግባባት አለ ብዬ አላምንምሲልም ነው የሚናገረው።

ወጣቱ ለዚህ ድምዳሜው ማሳያውም በአገሪቱ ወቅታዊ ችግር ሊፈጠር የቻለው ብሄራዊ መግባባቱ የሚፈለገው ደረጃ ባለመድረሱ ነው የሚል ነው። በአንፃሩ ደግሞ ብሄራዊ መግባባት የተደረሰባቸው በርካታ ጉዳዮች መኖራቸውን ያነሳል። ለአብነት ያህል በልማት ጉዳይ ላይ በተለይ ደግሞ ከህዳሴው ግድብ ግንባታ ላይ ብሄራዊ መግባባት ተፈጥሯል ሲል አስተያየቱን ያጠናክራ።

በየክልሉ ያሉ የወጣት ማህበራት አደረጃጀቶች በጋራ ሆነው የኢትዮጵያ ወጣቶች ፊዴሬሽንን እንደመሰረቱ የሚናገረው ወጣት ሙክታር፤ በዚህ አደረጃጀት አማካኝነት አገሪቷ ባወጣቻቸው ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎችና ህግ መንግስቱ ላይ ወጣቱ ዘንድ ብሄራዊ መግባባት እንዲፈጠር ፌዴሬሽኑ የበኩሉን ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን ነው የገለጸው፡፡

በአገር አቀፍ ደረጃ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ያንቀሳቀሰው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴው ግድብ ብሄራዊ መግባባት ለመኖሩ አንዱ ማሳያ ነው። ወጣቱም በፌዴሪሽኑ አማካኝነት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ 100 ሚሊዮን ብር በማበርከት የበኩሉን ድርሻ ተወጥቷል። ከዚህ በተጨማሪም በጉልበቱና በእውቀቱም ግንባር ቀደም ሚና እየተጫወተ ይገኛል። የህዳሴው ዋንጫ በየክልሎቹ ሲዞርም ህዝቡን በመቀስቅስ ረገድ ግንባር ቀደም ተሳታፊው ወጣቱ ነው። ፊዴሬሽኑ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚፈለገውን ያህል ባይሆንም በአገሪቱ ብሄራዊ መግባባት እንዲፈጠር የበኩሉን ድርሻ አበርክቷል የሚል እምነት አለው።

ፌዴሬሽኑ በሚፈለገው ደረጃ ብሄራዊ መግባባት እንዲኖር ከማድርግ አኳያ ውስንነቶች እንዳሉበት ወጣቱ ይጠቅሳል። ብሄራዊ መግባባት ለመፍጠር ዋናው አመለካከትን መቀየር ነው። የወጣቱን አመለካከት መቀየር የሚቻለው ደግሞ በተለያዩ ጊዜዎች በሚዘጋጁ መድረኮች ጥልቅ ውይይት በማድረግ ነው። በተጨማሪም ለብሄራዊ መግባባት እንደ ክፍተት በሚታዩ ጉዳዮች ላይ ያለውን አደረጃጃት ተጠቅሞ መታገልም የግድ ይላል ባይ ነው።

ወጣት ሙክታር እንደሚለው ከሆነ ፌዴሬሽኑ ብሄራዊ መግባባት የሚፈለግበት ደረጃ ለማምጣት ያልተቻለበት ምክንያት አንዱ የአቅም ውስንነት ነው። ምክንያቱም የሚፈለገውን ብሄራዊ መግባባት ለማምጣት በመላ አገሪቱ ተንቀሳቅሶ መስራት ይጠይቃልና ነው። በተመሳሳይ ደግሞ ወጣቱ በፌዴሬሽኑ ውስጥ የሚንቀሳቀሰው ከራሱ የግል ስራ ጎን ለጎን በመሆኑ የብሄራዊ መግባባት ስራን ትኩረት ሰጥቶ እንዳይሰራ አድርጎታል፡፡ ፊዴሬሽኑ ውስጥ የሚሰሩ አመራሮች ይሁኑ አባላት ስራውን የሚያከናውኑት ደመወዝ ተከፍሏቸው ሳይሆን በበጎ ፈቃድ ነው። ከዚህ አኳያ ያሉ ችገሮች ሊቀረፉ ይገባል።

«ፈተናውን ለማለፍ በአሁኑ ጊዜ ከመንግስት ጋር እየተነጋገርን ነው ያለው። ችግሩ የሚፈታ ከሆነ በቋሚነት ይንንን አደረጃጀት በመጠቀም ብሄራዊ መግባባት መደረስ ባሉባቸው ጉዳዮች ላይ መድረክ በመፍጠር አመለካከት የመቀየር ስራ ይሰራል። በሌላ በኩል ደግሞ ፌዴሬሽኑ ብሄራዊ መግባባት ሊፈጠርባቸው በሚገቡ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ መንግስት አቅጣጫ መስያዝ ይጠበቅበታል» ሲልም ያስገንዝባል ።

አደራጃጀታቸውን በማጠናከር ዙሪያ ከመንግስት ጋር እየተነጋገሩ እንደሆነም ወጣቱ ተናግሯል። በአገሪቷ አጠቃላይ ህዝብ ከ30 በመቶ በላይ የሚሆነው ወጣት ኃይል ነው። በተለይ ወጣቱን ኃይል በበጎ መልኩ መጠቀም የሚቻለው በአግባቡ መምራት ሲቻል ነው። ይህን ወጣት ለመምራት ደግሞ መዋቅር ያስፈልጋል። በፌዴሬሽን ደረጃ የተቋቋመውን በፋይናንስ ጭምርም በመደገፍ እንደ አገር ብሄራዊ መግባባት በሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ላይ ለመስራት ዕቅዳቸው መሆኑንም ጠቁሟል።

ብሄራዊ መግባባት በዋና ዋና አገራዊ ጉዳዮች ላይ ህዝቡ ተመሳሳይ አቋም መያዝ ማለት ነውየሚሉት በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት የዲሞክራሲ ተቋማት ማስተባበሪያ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሲቪል ማህበራት አስተባባሪ ሚኒስትር አቶ አብዱልአዚዝ መሀመድ ናቸው። ይህ ማለት ግን መላው ህዝብ መቶ በመቶ አንድ አቋም ይይዛል ማለት አይደለም። ለምሳሌ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ከሞላ ጎደል መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በግንባታው እየተሳተፈበት፤ በሞራልም እየደገፈ ያለበት ሁኔታ ስላለ ብሄራዊ መግባባት በዚህ ዙሪያ አለ ማለት ይቻላል፡፡ ነገር ግን ጥቂት የሚባሉ ግለሰቦችና የፖለቲካ ፓርቲዎች የህዳሴ ግድቡን ላይደግፉት ይችላሉ። ይህ ግን ብሄራዊ መግባባት አልመጣም ማለት አይደለም። አንድን የአገር አጀንዳ ወይም ፕሮጀክት 90 በመቶና ከዚያ በላይ ህዝብ ከደገፈው ብሄራዊ መግባባት ተፈጥሯል ማለት ይቻላልሲሉም ነው ብሄራዊ መግባባት በእረሳቸው ዘንድ ያለውን ትርጓሚ የሚያብራሩት።

እንደ አቶ አብዱልአዚዝ ገለፃ፤ በመንግስት እምነት የብሄራዊ መግባባት መገለጫ ከሆኑት ጉዳዮች መካከል የህዳሴ ግድብና ታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ በተሰው ማግስት ህዝብ ስሜቱን የገለፀበት አግባብ ይገኙበታል። ለአብነት ያህል ታላቁ መሪ በተሰው ማግስት ህዝቡ የእሳቸውን ራዕይ ከዳር ማድረስ አለብን ብሎ ከጫፍ ጫፍ በልማት ስራ ላይ ሲረባረብ ታይቷል። በቀጣይ መንግስት እነዚህ የማጠናከርና የማጎልበት ስራ ነው የሚሰራው።

አቶ አብዱልአዚዝ በኢትዮጵያ ውስጥ ብሄራዊ መግባባት አለ ቢሉም የፖለቲካ ምሁሩ አቶ ሙኸዲን ግን በሚኒስትሩ ሀሳብ አይስማሙም። በኢትዮጵያ ውስጥ ብሄራዊ መግባባት የለም የሚያስብል ደረጃ ላይ ነው ሲሉ ይሞግታሉ። ምክንያታቸውም «በአገሪቱ ታሪክ፣ ፖለቲካና ልማት ጉዳዮች ላይ ብዙ የልዩነት አመለካከቶች አሉ። በክልሎች መካከል እንኳ ብዙ ልዩነቶች ጎልተው ይታያሉ። በቅርቡ በአገሪቱ የተከሰቱት ችግሮች ብሄራዊ መግባባት እንደሌለ ማሳያዎች ናቸው። ከዚህ አኳያ እኔ ሙሉ በሙሉ ብሄራዊ መግባባት አለ ብዬ ለመናገር እቸገራለሁ» ብለዋል።

ከወራት በፊት ከአዲስ ዘመን ጋር ቃለ መጠይቅ አድርገው የነበሩት የኢህአዴግ መስራችና ነባር ታጋይ አቶ ስብሀት ነጋም፤ ብሔራዊ መግባባት የሚባለው ቃሉም ብዙ አይገባኝምበሚል ድምዳሜ ላይ ተንተርሰው መሬት ላይ ያሉ እውነታዎች ሲፈተሹ ብሄራዊ መግባባት ተፈጥሯል ማለት አይቻልም ነው ያሉት።

ህገመንግስቱ በየብሄራችን ሆነን አንድ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ማህበረሰብ እንፈጥራለን ነው የሚለው፡፡ ይሔ ደግሞ የሚፈጠረው እያንዳንዱ ብሄር ሌላውን ብሄር በመሬቱ የሚያስተናግድ ከሆነ ነው፡፡ የሶማሌ ሀብታም፣ የአማራ ሀብታም፣ የኦሮሞ ሀብታም፣ የትግራይ ሀብታም ሌሎቹም ሀብታሞች ወደሌላው ክልል ቢሄዱ ወገኖቼ ናቸው ብሎ መቀበልና እኩል ማየት አለ ወይ? እኔ አይመስለኝም። ካለ ግን ብሄራዊ መግባባቱ ተፈጥሯል ማለት ነው። በፕሮግራም ደረጃ ግን አለ። መግባባት በአየር ላይ የሚፈፀም አይደለም፡፡ ለእኔ ብሄራዊ መግባባት ያለ አይመስለኝም። አሁን ያለው ትምክህት፣ ጠባብነትና እና አክራሪነት ነውሲሉም ነው አቶ ስብሀት የተናገሩት።

እርሳቸው እንደሚሉትም፤ ብሔራዊ መግባባት የሚተገበረው በሁለት ነገሮች ነው፡፡ አንዱ በፖለቲካ ነው፡፡ ሁለተኛው ግን ነፃ የካፒታልና የሰራተኛ እንቅስቃሴ ሲኖር ነው፡፡ ለምሳሌ ትግሬው የኦሮሞ ሌባንና የትግራይ ሌባን አንድ አድርጐ ያያቸዋል? የኦሮሞ ልማታዊ ባለሃብትና የትግራይ ባለሃብትስ አንድ አድርጐ ያያቸዋል? ሌላውም ሌላውም እንደዚህ ተብሎ ሊፈተሽ ይገባል፡፡ ያኔ ብሄራዊ መግባባት አለ ማለት ይቻላል፡፡

በቅርቡ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ መግባባት ሳይሆን እርቅ ያስፈልጋል ሲሉ ለመንግስት ምክር ሀሳብ ሰጥተዋል። መንግስት ምክረ ሀሳቡን እንዴት ያየዋል? የሚል ጥያቄ ለሚኒስትሩ አቶ አብዱልአዚዝ ቀርቦላቸው በምላሻቸው፤ በተደጋጋሚ በፖለቲካ ፓርቲዎችም ጭምር ብሄራዊ እርቅ ያስፈልጋል ሲባል ይደመጣል። በመንግስት እምነት የሚስፈልገው ብሄራዊ መግባባት እንጂ እርቅ አይደለም። እርቅ የሚባለው በሁለት ወገን መህል ጥልና አለመግባባ ሲኖር ለማስታረቅ የሚደረግ ነው ብለዋል።

ኢህአዴግ ወደ መንግስት ስልጣን የመጣው በህዝቡ ምርጫ ነው። በየአምስት ዓመቱ የሚካሄደው ምርጫ ህዝቡ ኢህአዴግ አያስፈልገኝም ካለ ድምፁን ነፍጎ ሊያነሳው ይችላል። ስልጣን የሚሰጠውም ሆነ የሚነፈገው በምርጫ ህግ ነው። ስለዚህ በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ነው መታየት ያለበት እንጂ በአንዳንድ ፓርቲዎች እርቅ ስለተባለ ብሄራዊ መግባባት የለም ወደሚል ድምዳሜ ሊወሰድ አይገባምየአቶ አብዱልአዚዝ መቋጫ ነው።

 ጌትነት ምህረቴ

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy