Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የቱሪዝም አባት አቶ ሀብተሥላሴ ታፈሰ የሚታወሱበት የ13 ወር ፀጋ መለያ

0 1,128

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

‹‹እኔ ያደግሁት ውጭ አገር ነው፡፡ የትም ዓለም ላይ 13 ወር የለም፡፡ ፒራሚድ ሲታይ ግብፅ ነው፡፡ አይፈልታወር ሲታይ ፈረንሣይ ነው፡፡ የነፃነት ሐውልት ሲታይ አሜሪካ አለ፡፡ እኛ የምንታወቅበት የለንም ነበር፡፡ ሁሉ ነገር ከዘር፣ ከሃይማኖት ጋር የተያያዘ ነበር፡፡ ሳላውቀው አንድ ወቅት ላይ የ13 ወር ደመወዝ ይሰጠን ብዬ ጠየቅሁ፡፡ ወዲያው ይህንን ሐሳብ ወደ ቱሪስት መሳቢያነት መቀየር እንደሚቻል አሰብኩ፡፡ ሌላው ሁሉ ከዘር ከሃይማኖት ጋር የሚያያዝ ነበር፡፡ ላሊበላን ባደርግ ኢትዮጵያ በሙሉ ክርስቲያን ባለመሆኑ ችግር ነበረበት፡፡ የአሥራ ሦስት ወር ፀሐይ ግን ከምንም ነገር ጋር አይገናኝም፡፡ ምንም የፖለቲካና የሃይማኖት ንክኪ የለውም፡፡ አሁን ከዚያ የበለጠ ከተገኘ ደግሞ ቶሎ መተካት ነው፡፡ ምንም ችግር የለበትም፡፡›› በማለት በአንድ ወቅት ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የተናገሩት አቶ ሀብተሥላሴ ታፈሰ በኢትዮጵያ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ መሥራች፣ የአሥራ ሦስት ወራት ፀጋ (13 Months of Sunshine) በሚል መጠሪያ የአገሪቱ ቱሪዝም ለዘመናት ሲያስተዋውቅ የኖረውን መለያ የፈጠሩና በዘርፉ በርካታ ሥራዎችን ያስተዋወቁ፣ የተገበሩ የቱሪዝም አባት ናቸው፡፡ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ይህንን ውለታቸውን ቆጥሮ ዕውቅና በመስጠት ለመጀመሪያ ጊዜ ሽልማት አበርክቶላቸዋል፡፡ ሰሞኑንም ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ እጅ ለሁለተኛ ጊዜ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡ በቱሪዝም መስክና በተያያዥ ጉዳዮች ላይ ሔኖክ ያሬድና ብርሃኑ ፈቃደ ከጥቂት ዓመታት በፊት አነጋግረዋቸው ነበር፡፡ ይኸው ቃለ ምልልስ ለትውስታ ይሆን ዘንድ እንዲህ ቀርቧል፡፡  

ሪፖርተር፡- በዘርፉ በጠቅላላው ኢትዮጵያን ለምን ያህል ጊዜ አገልግለዋል?

አቶ ሀብተሥላሴ፡- ከመጀመሪያው እ.ኤ.አ. ከ1954 ጀምሮ አገልግያለሁ፡፡ ያኔ ከውጭ አገር ወደ ኢትዮጵያ እንደመጣሁ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ እሠራ ነበር፡፡ ከዚያ በግድ ይህንን ሥራ [ቱሪዝምን] እንድሠራ አዘዙኝ፡፡ ገባሁበት፡፡ ከባድ ሥራ ነው፡፡ ያን ጊዜ ካሜራ ወደ ኢትዮጵያ አይገባም ነበር፡፡ ሲገባም ጉምሩክ ይይዘዋል፡፡ ፈቃድ ከማስታወቂያ ሚኒስቴር ማውጣትም ያስፈልግ ነበር፡፡ በዚህ ሰበብ ሁለት ጊዜ ታስሬያለሁ፡፡ ፎቶግራፍ ለምን ታነሳለህ ብለው ነው ያሰሩኝ፡፡ ያን ጊዜ ፎቶግራፍ የሚያነሳ ሰው ሰላይ ተደርጐ ይታሰብ ስለነበር ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በቱሪዝም ሙያዎ ኢትዮጵያን ምን ያህል ያውቋታል?

አቶ ሀብተሥላሴ፡- ያልደረስኩበት ቦታ የለም፡፡ በእግር፣ በፈረስ፣ በግመል፣ በሄሊኮፕተር፣ በአውሮፕላን ሁሉ ተዘዋውሬ ከ100 በላይ ሰው ያልረገጣቸው የኤርትራ ደሴቶችን አይቻለሁ፡፡ ትልቅ ሀብት ናቸው፡፡ ቢያውቁበት በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ መሰብሰብ ይችሉ ነበር፡፡ በጋምቤላ በኩል ጂካው ድረስ ሄጃለሁ፡፡ የደቡብ ሱዳን ጠረፍ ነው፡፡ በኤርትራ በኩል ቤንአመር ድረስ ወዳለው የጠረፍ ቦታ ደርሻለሁ፡፡ ቤንሻንጉልን በሙሉ እስከ ሱዳን ድረስ አዳርሻለሁ፡፡ መሥራት ካስፈለገ ማየት፣ ማወቅ ግድ ይሆናል፡፡ ካየን፣ ካወቅን በኋላ ማውራት ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- በእነዚህ ሁሉ ጊዜያት እርስዎ ብዙ ሠርተዋል፡፡ ከሠሯቸው መካከል አሁንም ድረስ የሚታወቀው ኢትዮጵያ የአሥራ ሦስት ወር ፀጋ የሚለው አገሪቱ መጠሪያ ነው፡፡ ይህ የኢትዮጵያ መለያ ለብዙ ጊዜ ያገለገለ ነው፡፡ አሁን መቀየር አለበት የሚሉ አሉ፡፡ ይቀየር ቢባል ምን ይሰማዎታል?

አቶ ሀብተሥላሴ፡- ሁልጊዜ አንድ ነገር ሲፈጠርና የሚበልጠው ሲገኝ ያንን ማየቱ ተገቢ ነው፡፡ በአንድ ወቅት ምክትል አፈንጉሥ ገብረ ወልድ ፎቅ ቤት ሠርተው ነበር፡፡ ያን ጊዜ በንጉሡ ዘመን የመንግሥት ግልበጣ ሙከራ ነበር፡፡ መንግሥቱ ንዋይ ደግሞ ጠንሳሽና የእኛም ዘመድ ነበር፡፡ ሰውየው ሰማይ ጠቀስ ፎቅ ሠርተሃል ተብለው ታሰሩ፡፡ ይህ ከሆነማ አፍርሱት ሲሏቸው የለም አንተን ነው የምናፈርሰው ብለው ገደሏዋቸው፡፡ አሁን ደግሞ በተገላቢጦሽ ሰማይ ጠቀስ ፎቅ እንዲሠራ ነው የሚፈለገው፡፡

ሪፖርተር፡- የአሥራ ሦስት ወር የፀሐይ ፀጋን እንዴት መረጡት?

አቶ ሀብተሥላሴ፡- እኔ ያደግሁት ውጭ አገር ነው፡፡ የትም ዓለም ላይ 13 ወር የለም፡፡ ፒራሚድ ሲታይ ግብፅ ነው፡፡ አይፈልታወር ሲታይ ፈረንሣይ ነው፡፡ የነፃነት ሐውልት ሲታይ አሜሪካ አለ፡፡ እኛ የምንታወቅበት የለንም ነበር፡፡ ሁሉ ነገር ከዘር፣ ከሃይማኖት ጋር የተያያዘ ነበር፡፡ ሳላውቀው አንድ ወቅት ላይ የ13 ወር ደመወዝ ይሰጠን ብዬ ጠየቅሁ፡፡ ወዲያው ይህንን ሐሳብ ወደ ቱሪስት መሳቢያነት መቀየር እንደሚቻል አሰብኩ፡፡ ሌላው ሁሉ ከዘር ከሃይማኖት ጋር የሚያያዝ ነበር፡፡ ላሊበላን ባደርግ ኢትዮጵያ በሙሉ ክርስቲያን ባለመሆኑ ችግር ነበረበት፡፡ የአሥራ ሦስት ወር ፀሐይ ግን ከምንም ነገር ጋር አይገናኝም፡፡ ምንም የፖለቲካና የሃይማኖት ንክኪ የለውም፡፡ አሁን ከዚያ የበለጠ ከተገኘ ደግሞ ቶሎ መተካት ነው፡፡ ምንም ችግር የለበትም፡፡

ሪፖርተር፡- ዛሬም ድረስ መሥራት የሚፈልጓቸው ብዙ ጉዳዮች አሉ፡፡

አቶ ሀብተሥላሴ፡- መርዳት ነው የምፈልገው፡፡ መሥራት ያለባቸው የተመደቡት ሰዎች ናቸው፡፡ እነርሱን ለመርዳት ዝግጁ ነኝ፡፡ አምስት ያህል ፕሮጀክቶች አሉኝ፡፡ ፍልውኃን በአግባቡ አልተጠቀምንበትም፡፡ ወንዶገነትና ሶደሬ አካባቢ ጥቅም ላይ ውሏል፡፡ ነገር ግን ከ3,000 በላይ ፍልውኃ በየቦታው አለን፡፡ ያ የማያልቅ፣ ከወርቅና ከከበረ ድንጋይ ሁሉ የበለጠ ሀብት ነው፡፡ ነገር ግን አልተሠራበትም፡፡ እኔጋ ጥናቱ አለ፡፡ ዩኔስኮ ውኃውን ጨምሮ ያገኘው ጉዳይ አለ፡፡ ጥናቱ በእጄ ስላለ ለመንግሥት እሰጣለሁ፡፡ ይሠሩበታል ብዬ አስባለሁ፡፡ አሁን ቱሪስቶች ያሉት እዚሁ ከጐናችን ነው፡፡ ዱባይ፣ ኤምሬቶች አሉ፡፡ ድሮ ዓረብ ድሃ ነው፡፡ አሁን ዓለምን የያዙ እነሱ ናቸው፡፡ ፍልውኃ አረንጓዴያማ መስክ ይወዳሉና አቅሙ ላላቸው ባለሀብቶች መስጠት ከተቻለ ሰው ይመጣል፡፡ ከዱባይ አዲስ አበባ የሦስት ሰዓት በረራ ብቻ ነው የሚያስፈልገው፡፡ ከአውሮፓና ከአሜሪካ ሰው ይመጣል ብሎ መጠበቅ ከባድ እየሆነ ነው፡፡ ቀውስ ላይ ናቸው፡፡ የቅርብ አገሮች ግን መምጣት የሚችሉበት አቅም አላቸው፡፡ በግብፅ ለሁለት ዓመት ቆይቻለሁ፡፡ አባቴ አምባሳደር ነበሩና በዚያ ኖረናል፡፡ በጣም ቃጠሎ ነው፣ ሲበዛ ሞቃት ነው፡፡ በክረምት ብቻ ወደ አሌክሳንድርያ እንሄድ ነበር፡፡ አሁንም በጣም ሞቃት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎ የአሥራ ሦስት ወር ፀጋ ብለው ነበር ብዙ ፀጋ አለን ማለት ነው?

አቶ ሀብተሥላሴ፡- ደመወዝ የለውማ፡፡ የአሥራ ሦስት ወር ደመወዝ አይከፈልበትም፡፡

ሪፖርተር፡- እንደ ኬንያ ያሉት አገሮች ግን የዱር እንስሳት ሀብት ብቻ እያላቸው ነገር ግን ብዙ የተጠቀሙበት ሁኔታ አለ፤

አቶ ሀብተሥላሴ፡- እነሱ ስላሠሩ ነዋ፡፡ እኛ አንሠራም፡፡ አንዱ ሲሠራ አሥሩ ወደኋላ ይጐትታል፡፡ ምቀኝነት አለ፡፡ የሐበሻ ፀባይ አብሮ መሥራት ስለሌለው መድረስ ያለብን ቦታ አልደረስንም፡፡

ሪፖርተር፡- አየር በዕቃ ሞልተው ለመሸጥ የሞከሩበት ጊዜ እንደነበር ይነገራልና ስለእርሱ ቢነግሩን?

አቶ ሀብተሥላሴ፡- የኢትዮጵያ አየር የትም ዓለም ላይ አይገኝም፡፡ አንድ ጊዜ ንጉሡ ጋር ገባሁና አየር ይሸጣል አልኳቸው፡፡ ገንዘብ ሚኒስትሩ መጡና ምን ይለፈልፋል ብለው አጣጣሉኝ፡፡ አጋጣሚ ሆኖ እ.ኤ.አ. በ1970 በኦሳካ ኤግዚቢሽን ነበርና ወደ ቶኪዮ ዞር ዞር ብዬ ለማየት ሄድኩ፡፡ አንድ ቦታ ላይ የፊጂ ተራሮች የሚል ጽሑፍ ያለበት ቆርቆሮ አየሁ፡፡ ሳነሳው ባዶ ነው፡፡ ውስጡ ያለው የፊጂ አየር ብቻ ነው፡፡ ሰው ገዝቶ በአፍንጫው መማግ ብቻ ነው፡፡ ይህንን ገዛሁና ወደ ንጉሡ አመጣሁት፡፡ ስጦታ አምጥቼሎታለሁ አልኩና ሰጠኋቸው፡፡ አንስተው ሲያዩ ምንም የሌለው መስሏቸው ምን ትቀልዳለህ አሉኝ፡፡ አየር ይሸጣል ያልኩዎትኮ ይኼ ነው፤ ገዝቼ መጣሁ አልኳቸው፡፡ ገንዘብ ሚኒስትሩን ጠሩና ታስታውሳለህ ያልከውን ይኸውልህ አየር ይሸጣል አሏቸው፡፡ ይኼንን አሁንም ማድረግ ይቻላል፡፡ አየር በዕቃ ሞልቶ እንዲማግ ማድረግና መሸጥ ይቻላል፡፡ ውኃ በፕላስቲክ እየተሸጠ እኮ ነው፡፡ ሰው ግን አያምንም፣ አይቀበልም፡፡ አገሪቱን ያጠቃት በምቀኝነት፣ በዘር፣ በሃይማኖት መከፋፈላችን ነው፡፡ አንድ ሆነን ካልሠራን ከባድ ነው፡፡ አሁን ብዙ ለውጥ መጥቷል፡፡ ከሞት የተመለስኩ ያህል የሚሰማኝ ጊዜ አለ፡፡ ሴቱ ሁሉ እንደ ልቡ ነው፡፡ ወደ ዱባይ ወደ መሳሰሉት አገሮች ሲሄዱ፣ ሲሠሩ የሚታዩ ቆነጃጅቶች ብዙ አሉ፡፡ በእኛ ጊዜ እንዲህ አይታሰብም፡፡ ብዙ ለውጥ አለ፡፡ የሰው አስተሳሰብ ተቀይሯል፡፡

ሪፖርተር፡- አንድ ኒውዝላንዳዊ ሚሊየነር ኢትዮጵያን በሄሊኮፕተር ጐብኝቶ መደነቁን ሲናገሩ ነበርና ስለእርሱ ቢገልጹልን?

አቶ ሀብተሥላሴ፡- ፓይለቱ የሰውየው ልጅ ባል ነው፡፡ ሰውየው ደግሞ ባለሄሊኮፕተር ነው፡፡ የእርሱ አስጎብኚ ከእኔ ጋር የሚሠራ ነውና ተዟዙሮ አይቶ እኔን ማየት ፈለገና እራት ጋበዘኝ፡፡ ተኝታችኋል አለኝ፡፡ በሄሊኮፕተር እየተዘዋወርን ከ125 በላይ አገሮች አይተናል እንደ ኢትዮጵያ የሚሆን ግን አላየንም አለኝ፡፡ ሰውየው የምንም ፍላጎት የላቸውም፡፡ ለጥቅም ብለው ነው እንዳይባል አገራቸው ኤምባሲ እንኳ እዚህ የላትም፡፡ ሰውየው ደግሞ እጅግ ባለጠጋ ናቸው፡፡ ቢሊየነር በመሆናቸው ለጉብኝት ብቻ ነው የመጡት፡፡ ያዩትን አይተው ተኝታችኋል አሉኝ፡፡

ሪፖርተር፡- የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሽልማት ሲሰጥዎ፣ በሕይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሽልማት ተጠራሁ ብለዋል፡፡ ለምንድን ነው ከዚህ በፊት ይህን ሁሉ ሠርተው ያልተሸለሙት?

አቶ ሀብተሥላሴ፡- ምቀኞች ስለሆንን፡፡ ሁሌም ሲጠሩኝ ለአንድ ወቀሳ ነው፡፡ ቤተክህነት ተጠርቼ በቴሌቪዥን ለምን እንዲህ ተናገርህ እባላለሁ፣ የአገር ውስጥ ገቢ ይጠሩኝና እወቀሳለሁ፡፡ ያን ጊዜ ከቀረጥ ነፃ ሱቅ ከፍተን ነበር፡፡ የእኛ ቢሮ ከመንግሥት ቢሮዎች ሁሉ ሀብታም የሚባለው ነበር፡፡ ያን ጊዜ ቱሪዝም በጀት 220 ሺሕ ብር ስለነበር በዚህ በጀት እንዴት አገርን ማሳደግ ይቻላል እያልሁ ከጃንሆይ ጋር እጨቃጨቅ ነበር፡፡ አንድ ጊዜ ቁልፉን ይዤ ሄድኩና ጃንሆይ ይኼንን መሥሪያ ቤት ለሒሳብ ሹም ይስጡት ደመወዝ ከመክፈል ውጪ ሌላ ሥራ መሥራት አልቻልኩም አልኳቸው፡፡ የዲውቱ ፍሪ ፈቃድ ስጡኝ ብዬ ጃንሆይን ጠየቅሁ፡፡ ኋላ ላይ ገንዘብ ሚኒስትሩ መጡና እኛ ኮንትሮባንድ መቆጣጠር አቅቶናል፣ ሀብተሥላሴ ደግሞ አናታችን ላይ ኮንትሮባንድ ለመፍጠር ይፈልጋል አሉኝ፡፡ ንጉሡም ሥራህ መቆጣጠር ነው እንጂ ሥራ አይሥራ ነው የምትለው ወይስ መቆጣጠር አልችልም ነው? ብለው ጠየቋቸውና ተፈቀደልኝ፡፡

ሥራው ሊጀመር ሲል ደግሞ ገንዘብ ስለጠፋ የአባቴን ካርታ ወስጄ ለአንድ እብድ ሰጠሁና 5,000 ዶላር ተበደርኩ፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠር ብር ማግኘት ተቻለን፡፡ በአንድ ወቅት ከመላው ኢትዮጵያ የእኛ መሥሪያ ቤት ነበር ሀብታም የነበረው፡፡ አንድ ሚኒስትር ሲሾም በጊዜው እንዲነግድ አይፈቀድለትም ነበር፡፡ ለእኛ ተፈቅዶ ነበርና ብዙ ገንዘብ አስገብተናል፡፡ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ሕንፃ ተሠርቶ ሥራ ሲጀምር የእኛ መኪኖች ነበሩ የሚያገለግሉት፡፡ 46 ያህል ነበሩን፡፡ እኔ እንደ ሾፌር፣ እንደ አስጐብኚ፣ እንደ ፎቶግራፍ አንሺ እየሆንኩ ሠርቻለሁ፡፡ በኋላ ምቀኛ በዛና የዲውቲ ፍሪ ገንዘብ ወደ መንግሥት ይግባ አሉ፡፡ ያ አሠራር ዛሬ ቆይቶ ቢሆን ኖሮ አሥር ሚሊዮን ሰዎች በተሰማሩበት ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- በጊዜው ሴቶችን ፎቶግራፍ ያነሱ ነበርና ከንጉሡ ዘንድ የገጠመዎት ጉዳይ አለ ይባላል፤

አቶ ሀብተሥላሴ፡- አዎ፡፡ አንዲት የጋምቤላ ሴት ፎቶግራፍ አንስቼ ነበር፡፡ ሴትየዋ ጡቷ ቆንጆ ነበርና አንስቼ ፖስተሩ ከመታተሙ በፊት ናሙናውን ለንጉሡ አስገብቼ ጠረጴዛ ላይ እደረድር ነበር፡፡ ንጉሡ መጥተው ሲያዩ ይኼ ምንድን ነው አሉና ጠየቁኝ፣ አይ ቱሪስቶች እንዲህ ማየት ይወዳሉ ስላቸው፣ አንተም ትወዳለህ ይባላል አሉኝ፡፡ በኋላ ታትሞ ሲወጣ ሳንሱር ይደረግ ነበር ራቁት እያሳየ ነው ብለው ንጉሡ ጋር መልሰው ይዘው መጡ፡፡ ንጉሡም አይተናል አሉና መለሷቸው፡፡ ከዚያ በኋላ የቱንም ነገር ከመሥራቴ በፊት ቀድሜ ለንጉሡ ስለማሳይ አይተናል እያሉ ሚኒስትሮችን ይመልሷቸው ነበር፡፡ ብዙ መሥራት አንወድም፡፡ ስንሠራ ደግሞ ምቀኛው ወደኋላ የሚጐትት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎ ለባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር እሰጣለሁ ካሏቸው ፕሮጀክቶች አንዱ አንድ ብር ቢያንስ በአንድ ዶላር መመንዘር የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡ ይኼ አስማት አይደለም ሲሉም ሰምተናልና እንዴት ነው ይኼ የሚሆነው?

አቶ ሀብተሥላሴ፡- ይኼ አስማት አይደለም፡፡ እንዴት እንደሆን የምንነግረው ግን ለሚኒስትሩ ነው፡፡ እሳቸው ከተስማሙ በኋላ የእሳቸው ፕሮጀክት ይሁን፡፡ አሁን መናገሩ ጊዜው አይደለም፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy