Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለተጨማሪ አራት ወራት ተራዘመ

0 429

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለተጨማሪ አራት ወራት እንዲራዘም ወስኗል።

ከስድስት ወር በፊት በሀገሪቱ የተለያዩ አከባቢዎች ለተወሰኑ ጊዜያት በተፈጠረው ሁከትና ብጥብጥ በተለመደው የህግ ማስከበር ስርዓት መቀልበስ አልተቻለም ነበር።

ይህን ተከትሎ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሰላምና ጸጥታውን ለማስጠበቅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጆ ሲተገበር ቆይቷል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተቀመጠለት የስደስት ወራት ጊዜ ሊጠናቀቅ የአንድ ሳምንት ጊዜ መቅረቱን ተከትሎ ኮማንድ ፖስቱ የአዋጁን አፈጻጸምና ቀጣይነት በሚመለከት ዛሬ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሪፖርት አቅርቧል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ኮማንድ ፖስት ሴክሬታሪያትና የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ ለምክር ቤቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲራዘም ያስፈለገበትን ምክንያት አቅርበዋል።

አቶ ሲራጅ በሀገሪቱ ተጋርጦ የነበረውን የጸጥታ ችግር በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መቆጣጠር መቻሉን ነው የተናገሩት፡፡

ሆኖም ክልሎች በሚዋሰኑባቸው አካባቢዎች የሚነሱ ችግሮችን ለመጠቀም የሚፈልጉ ፀረ ሰላም ሀይሎች እየተንቀሳቀሱ መሆናቸው፣ በሁከት እና ብጥብጡ ቀንደኛ መሪዎች ከነበሩት ውስጥ አብዛኛዎቹ ቢያዙም ቀሪ በመኖራቸው እና በወረቀት ፅሁፎችን በመበተን አሁንም ሰላም እና መረጋጋትን ለማደፍረስ የሚጥሩ ወገኖች አልፎ አልፎ በመታየታቸው አዋጁን ማራዘም ማስፈለጉን ተናግረዋል።

በተጨማሪም በአንፃራዊነት ሰላም እና መረጋጋቱ የተሻለ ደረጃ ላይ ቢገኝም የማይቀለበስበት ደረጃ ላይ ለማድረስ ተጨማሪ ጊዜ ማስፈለጉን ለአዋጁ መራዘም በምክንያትነት አስቀምጠዋል።

በመላ ሀገሪቱ በተካሄደ የዳሰሳ ጥናት ህዝቡ የተሻለ ሰላም እንዲሰፍን አዋጁ ቢራዘም የሚል አስተያየት እንዳለው በመረጋገጡም ነው አዋጁ እንዲራዘም ያስፈለገው ብለዋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መርማሪ ቦርድም በመላ ሀገሪቱ ያደረገውን ቅኝት መሰረት አድርጎ አዋጁ ቢራዘም የሚል አስተያየት ለምክር ቤቱ አቅርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

ምክር ቤቱም በጉዳዩ ላይ ተወያይቶ አዋጁ ለተጨማሪ አራት ወራት እንዲራዘም በሙሉ ድምፅ ወስኗል።

ምክር ቤቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በተራዘመባቸው ወራቶች አፈፃፀሙ የዜጎችን ሰብአዊ መብት በጠበቀ መልኩ እንዲሆንም አሳስቧል።

በድንበር አካባቢዎች ኮማንድ ፖስቱ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ሰላም እና መረጋጋትን የበለጠ እንዲያሰፍንም ነው ምክር ቤቱ ያሳሰበው።

ምንም እንኩዋን አዋጁ ባስገኛቸው ጥቅሞች የተወሰኑ ማሻሻያዎች ተደርገው ያለ ፍርድ ቤት ትእዛዝ መያዝና ፍተሻ እንዲሁም በሚዲያ ላይ ተጥለው የነበሩ ክልከላዎች በከፊልና በሙሉ ቢነሱም አብዛኞቹ ክልከላዎች ግን አሁንም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ውስጥ እንደተካተቱ ነው።

በዚህም የአስቸኩዋይ ጊዜ አዋጁን ለማስፈጸም ወጥተው በስራ ላይ ያሉ ደንቦችና መመሪያዎች ተፈጻሚነታቸው የሚቀጥል ይሆናል።

በኮማንድ ፖስቱ የተወሰዱ እርምጃዎች፣ የተሰጡ ውሳኔዎች፣ በፍትህ አካላት የተወሰኑ ጉዳዮችና ሌሎች አግባብነት ያላቸው ውሳኔዎች በዚህ አዋጅ መሰረት ተፈጻሚነታቸው ይቀጥላል።

አባላቱ የአዋጁ አፈጻጸም በአንደኛው ዙር የመርማሪ ቦርድ ቅኝት የታዩ ችግሮች በሁለተኛው ዙር መሻሻላቸው መገለጹን በማንሳት አሁንም ከቀድሞ የተሻለ አፈጻጸም ሊኖር ይገባል ብለዋል። FBC

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy