Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የአዲስ አበባ መሪ ፕላን ለመኖሪያ ቤቶችና ለአረንጓዴ ቦታዎች ልዩ ትኩረት ሰጥቷል

0 534

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

አስረኛው የአዲስ አበባ ከተማ መሪ ፕላን ለመኖሪያ ቤቶችና ለአረንጓዴ ቦታዎች ልዩ ትኩረት የሰጠ መሆኑን የመሪ ፕላኑ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ገለጸ።

ጽህፈት ቤቱ በመሪ ፕላኑ ዙሪያ ከተማ አቀፍ የነዋሪዎች ማጠቃለያ መድረክ አካሂዷል።

10ኛው የ2017 እና የ2032 ዓ.ም መሪ ፕላን ይዘት ምን እንደሚመስልና ከቀደሙት መሪ ፕላኖች ጋር ያለው ልዩነት እንዲሁም ሊያመጣ በሚችለው ለውጥ ላይ እስካሁን ከ500 በላይ የህዝብ ውይይት መድረኮች መካሄዳቸው ተገልጿል።

የከተማ አስተዳደሩ ፕላን ኮሚሽነርና የጽህፈት ቤቱ ስራ አስኪያጅ አቶ ማቴዎስ አስፋው እንደተናገሩት፣ ከነዚህ ውይይት መድረኮች የተገኙ ግብዓቶች የተካተቱበት ይህ መሪ ፕላን በቅርቡ በከተማዋ ምክር ቤት ይጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል።

“መሪ ፕላኑ የአዲስ አበባ ከተማን እድገት በሚመጥን፣ የከተማዋን ዓለም ዓቀፋዊ ሚና የሚያሳድግና የዲፕሎማቲክ መዲናነቷን በማያሻማ መልኩ የሚያስቀጥል ነው” ብለዋል።

ከተማዋ የታዳሽ ኃይል ምንጭ እንድትሆን፣ የቱሪዝምና የኮንፍረንስ መዕከል እንዲሁም የአፍሪካ የባህል ማዕከልና ሙዚየም እንዲኖራት እድል ይፈጠራልም ነው ያሉት።

በአሁኑ ወቅት የአዲስ አበባ ነዋሪ 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን መሆኑን የጠቀሱት ስራ አስኪያጁ መሪ ፕላኑ በ2017 ከአምስት ሚሊየን በላይ የሚሆነውን ነዋሪ ማስተናገድ በሚችል መልኩ የተዘጋጀ መሆኑን አስታውቀዋል።

መሪ ፕላኑ መዲናዋ በደረጃቸው የተከፋፈሉ የንግድ፣ የአስተዳደር፣ የማህበራዊ አገልግሎት መስጫና የመዝናኛ አገልግሎት መስጫ ዋና ማዕከላት፣ የወረዳ ማዕከላትና የሰፈር ወይም የአጥቢያ ማዕከላት ያሉት ነው።

በመሆኑም መዲናዋ 30 በመቶ አረንጓዴ ቦታ፣ 30 በመቶ የመንገድ መሠረተ ልማትና 40 በመቶ ደግሞ የግንባታ ቦታዎች እንዲኖሯት ተደርጓል ብለዋል

ከዚህ በተጨማሪ ከተማዋ በአራት ዞኖች የተከፋፈለች ሲሆን ዞን አንድ የከተማ መዕከል፣ ዞን ሁለት ዋና ዋና ጎዳናዎች፣ ዞን ሶስት ከቀለበት መንገድ ርቀው ያሉ ቦታዎችና ዞን አራት ደግሞ አዲስ አበባ ዙሪያ ናቸው።

በዚሁ መሠረት ዞኖቹ 30 በመቶ፣ 40 በመቶ፣ 50 በመቶና 60 በመቶ እንደ ቅደም ተከተላቸው ለመኖሪያ ቤት ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ እንደሚደረግ ተገልጿል።

በመዲናዋ ቅይጥ መኖሪያ በሚባል ስልት ለንግድ ተብለው የሚገነቡ ሕንጻዎች ከአራተኛ ፎቅ በላይ ለመኖሪያ እንዲያገለግሉ የሚያስገድድ ደንብ ተዘጋጅቷል ብለዋል አቶ ማቴዎስ።

በአሁኑ ወቅት በመዲናዋ የሕዝቡን ኑሮ እያወኩ የሚገኙ የመንገድ ላይ የእንጨትና የብረት መስሪያ ቦታዎች፣ ጫት ቤቶች፣ መጠጥ ቤቶችና መሰል ቤቶች ወደ ዋና መንገድ ብቻ ተቃርበው ስራቸውን እንዲሰሩ ይደረጋል።

ፕላኑ የከፍለ ከተሞችን ቁጥር ወደ 13 የሚያሳድግ ሲሆን የወረዳዎች ቁጥርም ይጨምራል ተብሏል።

መሪ ፕላኑን ለማስተግበርም የመዲናዋ ፕላን ኮሚሽን የበላይነት በመያዝ የልማትና ግንባታ ባለስልጣንና የማዕከላትና ኮሪደሮች ልማት ኮርፖሬሽን የተባሉ ቢሮዎች ይፈጠራሉ ነው ያሉት።

በተጨማሪም የአረንጓዴ ቦታዎችን በአግባቡ ለማስተዳደር ይቻል ዘንድ የተፋሰስና የአረንጓዴ ልማት ኤጀንሲ ቢሮ ይቋቋማል ብለዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው መሪ ፕላኑ ሰፊና በቀላሉ ለመፈጸም የማይቻል በመሆኑ የማስፈጸም አቅም ታሳቢ ተደርጓል ወይ? የሚል ጥያቄ አንስተዋል።

ከዚህ ባለፈም እቅዱ ሲተገበር ነዋሪዎች እንዳይፈናቀሉ ለማድረግ፣ ከተፈናቀሉም ለችግር ሳይጋለጡ እዛው አካባቢ ሰርተው መኖር የሚችሉበት ሁኔታ መመቻቸቱን የተመለከተ ጥያቄ አንስተዋል።

በመሪ ፕላኑ መሠረት የሚሰሩት ሕንጻዎች ረጃጅም በመሆናቸው የተፈጥሮ አደጋን መቋቋም ስለመቻላቸውና ሌሎች ስጋት አዘል ጥያቄዎች ተሰንዝረዋል።

በጥቅሉ ነዋሪዎቹ የተዘጋጀው መሪ ፕላን ጥሩና ከተማዋን በተሻለ መልኩ ይለውጣል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።

የአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አቶ አባተ ስጦታው መሪ ፕላኑን ለማስፈጸም ከፍተኛ የአመራር ቁርጠኝነት መኖሩን ገልጸው ሕዝቡም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጠይቀዋል።

ፕላኑ ለከተማዋ ነዋሪዎች ተስፋ ሰጪ እንጂ የስጋት ምንጭ ባለመኆኑ ሕብረተሰቡ ጥርጣሬ ውስጥ መግባት የለበትም ብለዋል።

”የመዲናዋ ነዋሪዎች በባለቤት ስሜት ከመሪ ፕላኑ ውጪ የሚደረጉ ነገሮች ሲኖሩ የአስፈጻሚውን አካል በመከታተል የነቃ ተሳትፎ ማድረግ ይኖርባቸዋል” ብለዋል።

በረቂቅ ደረጃ ሳለ ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ ሲተገበር የቆየው መሪ ፕላን በቅርቡ በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ እንደሚገባ ተመልክቷል።

መሪ ፕላኑ የአዲስ አበባን የመጪዎቹን 10 እና 25 ዓመታት እጣ ፈንታ የሚወስን ነው ተብሏል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy