Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ መደበኛ ስብሰባውን አጠናቀቀ

0 335

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ መደበኛ ስብሰባውን አጠናቀቀ።

የግንባሩ ፅህፈት ቤት ለጣቢያችን በላከው መግለጫ፥ የጥልቅ ተሃድሶ ንቅናቄው የደረሰበትንና በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽ ዘመን የሁለተኛው ዓመት አጋማሽ አፈፃፀም ሪፖርት ላይ ለሁለት ቀናት የገመገመው ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ መደበኛ ስብሰባውን አጠናቋል።

በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄ መድረኮች በተቀመጠላቸው አቅጣጫ መሰረት የተፈፀሙ መሆናቸውን የገመገመው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው፥ የተሃድሶ ንቅናቄው በየደረጃው ባለ አመራር፣ አባላት፣ በሲቪል ሰርቫንቱ እና በህዝቡ ደረጃ ሰፊ ውይይት መደረጉንና በተሃድሶ አጀንዳዎቹ ላይም በተሻለ ሁኔታ የጋራ መግባባት ላይ መደረሱን ተመልክቷል፡፡

ሀገሪቱን በመስቀለኛ መንገድ ላይ እንድትቆም ያስገደዳትን አስከፊ ሁኔታ በመቀልበስ የተጀመረው ሀገራዊ የህዳሴ ጉዞ ለማሳካት የሚያስችል መግባባት እንደተፈጠረ አንስቶ፥ ባለፉት 15 የተሃድሶ ዓመታት በልማት፣ በሰላም እና በዴሞክራሲ መስኮች የተመዘገቡ ስኬቶች ላይ ህዝቡ ከፍተኛ ድርሻ እንደነበረውም የጋራ መግባባት መፈጠሩን ጠቅሷል።

የትምክህትና ጠባብነት አመለካከቶችና ተግባራት የዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ አደጋ መሆናቸውን በመግባባት፥ በቀጣይ የህዳሴ ጉዞውን ማደናቀፍ ከማይችሉበት ደረጃ ላይ በማድረስ ሀገራዊ ህዳሴውን እውን ለማድረግ ህዝቡ መነሳሳቱንም ኮሚቴው ተመልክቷል፡፡

በአስፈፃሚ አካላት ምደባ ላይም ህዝቡ ቀጥተኛ፣ ነፃና ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎን ባረጋገጠ አኳኋን ባለቤትነቱን ያረጋገጠበት መሆኑን ያነሳው ኮሚቴው፥ አሰራሩ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አቅጣጫ መቀመጡንም ገልጿል።

ከወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ ጋር በተያያዘም ነባሩ የወጣቶች የዕድገትና የለውጥ ፓኬጅ የነበሩበትን ክፍተቶች በማረም ከሀገራዊ ዕድገቱ ጋር በማጣጣም የወጣቶች የተሳትፎና ተጠቃሚነትን መመለስ በሚያስችል ሁኔታ በአዲስ መልክ መዘጋጀቱን ኮሚቴው አረጋግጧል፡፡

የተሃድሶ ንቅናቄው እና የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች ሳይነጣጠሉ ለማስኬድ እየታደስን እንሰራን፤ እየሰራን እንታደሰሳለን በሚል አቅጣጫ እየተፈፀመ እንደሆነ የገመገመው ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው፥ በቀጣይም የተሃድሶ ንቅናቄው በተመሳሳይ አኳኋን እንዲፈፀም አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡

የተጀመረው ፈጣን እና ተከታታይነት ያለው ኢኮኖሚያዊ ዕድገት መቀጠሉን ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ማረጋገጡን በመግለጫው ጠቅሷል።፡

በያዝነው ዓመት በመስኖ እና በበልግ ስራዎች ላይ የተሻለ ከተሰራ፥ በመኸር ግብርና በአማካይ ይመዘገባል የተባለውን የ12 በመቶ ትንበያ ከተጠቀሰው በላይ ማሳደግ እንደሚቻልም ኮሚቴው ተመልክቷል፡፡

ከዝናብ ስርጭቱ ጋር ተያይዞ በሃገሪቱ አንዳንድ አካበቢዎች ድርቅ መከሰቱን የገመገመው ኮሚቴው፥ መንግስት ለጉዳዩ ቅድሚያ ሰጥቶ አደጋውን ለመቀነስ ርብርብ እያደረገ መሆኑንን በመገምገም ስራው ተጠናክሮ እንዲቀጥል አቅጣጫ ማስቀመጡም ነው የተጠቀሰው።

ከኢንዱስትሪው ጋር በተያያዘ በተጠናቀቀው በጀት አመት በዘርፉ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች ወደ ስራ በመግባታቸው የማምረቻ ኢንዱስትሪው በ18 ነጥብ 4 በመቶ እድገት ማስመዝገቡንም በመግለጫው ጠቅሷል።

የማምረቻውን ኢንዱስትሪ ልማት በማፋጠን የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ለማምጣት እየተሰራ መሆኑን የጠቀሰው መግለጫው፥ 13 የሚሆኑ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ስራ በተሻለ አፈፃፀም እየተከናወነ ነው ብሏል።

በአንዳንድ የኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚገኙ የፋብሪካ ሼዶች ወደ ምርት በመግባት የውጭ ምንዛሬ ማስገኘት መጀመራቸውንም የጽህፈት ቤቱ መግለጫ ያመለክታል።

ከወጪ ንግድ ጋር በተያያዘም በተለይም በግብርና ምርቶች፣ በቁም እንስሳትና በወርቅ የሚስተዋለው ህገ ወጥ ንግድ፥ የወጪ ንግድ ግኝቱን እየጎዳው በመሆኑ ባለ ድርሻ አካላት ችግሩን መፍታት ይገባቸዋልም ነው ያለው።

ከመሰረታዊ ሸቀጦች ጋር በተያያዘ የሚስተዋለው የስርጭት ችግርም ቀጣይ ትኩረት እንደሚያሻው ገልጿል።

የዋጋ ንረቱን በነጠላ አሃዝ ገድቦ ለመያዝ የተደረገው ጥረት ውጤታማ መሆኑን የጠቀሰው መግለጫው፥ ይህም የማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገቱን ቀጣይነት ለማረጋገጥ በተከናወኑ ስራዎች መገኘቱን አንስቷል።

በእቅድ ዘመኑ በርካታ ሜጋ ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ መሆኑን ያነሳው መግለጫው፥ በተለይም በኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት 2 ሺህ 100 ሜጋ ዋት የሚያመነጨው የኮይሻ ፕሮጀክት እና 120 ሜጋ ዋት የሚያመነጨው የአይሻ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የግንባታ ስራቸው እንደተጀመረም ገምግሟል፡፡

የትምህርት ተደራሽነትና ጥራት ለማረጋገጥ የተከናወኑ ስራዎች ውጤታማ እንደነበሩ የገመገመው ኮሚቴው፥ በቀጣይም በትምህርት ስርዓቱ ላይ ሰፋ ያለ ጉድለት የሚታይባቸውን የመዋዕለ ህፃናትና የከፍተኛ ትምህርት ተሳትፎ ለማሳደግ ትኩረት እንደሚሻም አጽንኦት ሰጥቷል።

በቀጣይም በአንደኛ ደረጃ ትምህርት የሚስተዋለውን መጠነ ማቋረጥ ማስቀረትና የጎልማሶች ትምህርትን በመመዘን ውጤታማ ስራ ለማከናወን መረባረብ እንደሚገባም አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡

በጤናው መስክ በተለይ የእናቶችና የህፃናት ሞት በመቀነስ ስኬታማ ስራዎች ቢከናወኑም፥ የጤና ኤክስቴንሽን ስርዓቱና ሙያተኞች የሚያጋጥሟቸውን ማነቆዎች በጥናት ላይ የተመሰረተ ምላሽ ለመስጠት መዘጋጀት ይገባልም ነው ያለው።

በዘርፉ የሚስተዋለውን የጥራት መጓደል ችግር ለመፍታት ቀጣይ ትኩረት እንደሚሻ በመጥቀስ።

በመጨረሻም ህዝቡ የተጀመረውን የጥልቅ ተሃድሶ ንቅናቄ ይበልጥ በማስፋትና በማጎልበት እንዲሁም ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽ ዕቅድ በላቀ ደረጃ ለመፈፀም እንዲረባረብ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy