Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የኦሮሚያ ክልል ድርቅ-ፈተናዎች፣ መልካም ተሞክሮዎች እና ጉራማይሌ ገፅታዎች

0 999

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ የጋዜጠኞች ቡድንን በመያዝ ከየካቲት 21ቀን 2009 .ም ጀምሮ ለ10 ቀናት በክልሉ ድርቅ በተከሰተባቸው ቦረና እና ጉጂ ዞኖች ጉብኝት አድርጎ ነበር፡፡ ለመሆኑ እነዚህ ድርቅ የፀናባቸው አካባቢዎች ገፅታ ምን ይመስላል? ድርቁን ለመመከት የህዝቡ፣ የመንግሥት እና አርብቶ አደሩ የጋራ ጥረት ምን ገፅታ አለው? ድርቁ ያስከተለው ተፅዕኖስ ምን ያህል ነው? በቀጣይ ምን መሠራት አለበት? በሚለው ላይ አርብቶ አደሩ፣ ባለሙያዎችና የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የሰጡትን አስተያየት እንደሚከተለው አጠናቅረናል፡፡

በጉጂ ዞን ጉሚእርዳሎ፣ ሊበን፣ ሳባቦሩ እና አጋዋዩ ወረዳዎች በከፍተኛ ደረጃ ለድርቅ ተጋልጠዋል፡፡ በዞኑ 2ነጥብ3 ሚሊዮን እንስሳት ይገኛሉ።ከዚህም ውስጥ አብዛኞቹ ውሃና መኖ ይፈልጋሉ፡፡ 171ሺህ ሰዎችም አስቸኳይ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ይሁንና ተከታታይ እገዛ እየተደረ ገላቸው ያለው 106ሺህ ሰዎች ናቸው። ቀሪዎቹ ደግሞ በአስቸኳይ ጊዜ እየተረዱ ነው፡፡ በቦረና ዞንም አራት ሚሊዮን እንስሳት ያሉ ሲሆን፤ በድርቅ ሳቢያ በርካታ እንስሳት መሞታቸውን የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሊበን አሬሮ ገልጸዋል፡፡ በቦረና ዞን ያለው የዘንድሮ ድርቅም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻፀር የተረጂዎች ቁጥር በ25ሺ ከፍ ብሏል፡፡

ጉጂ ዞን

ወይዘሮ ፌቲሳ ጉሚኢ በጉጂ ዞን የጎሮዶላ ወረዳ ነዋሪ ናቸው። በድርቁ ሳቢያ የቤት እንስሶቻቸው ሰውነታቸው እያበጠ ሲሞቱ እየተመለከቱ ነው፡፡ የእርሳቸው ኑሮ ሙሉ ለሙሉ የተመሰረተው ደግሞ በእንስሳት እርባታ ላይ ነው፡፡ ቀድሞ ከብቶች ዋጋቸው ጥሩ በሆነ ሰዓት እህል አማርጠው ይገዛሉ፡፡ አሁን ግን እህል እንደ ልብ ማግኘት አልቻሉም፡፡ አንድ ጣሳ እህልም በ14 ብር ነው የሚገዙት፡፡ እናም ድርቁ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ክንዱን እያበረታባቸው ነው፡፡ ይሁንና መንግሥት የሚያደርገው ድጋፍ ደግሞ ለጊዜውም ቢሆን ተስፋ ሰጥቷቸዋል፡፡

ተማሪ ለታ ሁዴሳ በጉጂ ዞን ጎሮዶላ ወረዳ ነዋሪ ሲሆን በድርቁ ምክንያት ከአራተኛ ክፍል ትምህርቱን አቋርጧል፡፡ በአካባቢያቸው ቀድሞ ይዘሩ የነበረው በቆሎ እና ቦለቄ በዚህ የምርት ዘመን ጠፍቷል፡፡ እናም ከሚወደው ትምህርቱ ለመለያየት ተገዷል፡፡ እስካሁን ከግመሎቹ በቀር ሌሎች እንስሳት እየሞቱ መሆኑ ጭንቀቱ አይሎበታል፡፡ ምናልባት ለሚቀጥለው ዓመት ድርቁ የሚጠፋ ከሆነ ትምህርቱን ለመቀጠል ተስፋ ማድረጉን ይናገራል፡፡

አቶ ይልማ መንገሻ ጎሮዶላ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና አርብቶ አደር ፅህፈት ቤት ኃላፊ ናቸው። በወረዳው 112ሺ ነዋሪዎች ሲገኙ ከእነዚህ ውስጥ 90ሺ የሚሆኑት ለእርዳታ መጋለጣቸውን ይናገራሉ። በወረዳው 280ሺ እንስሳት ሲገኙ፤ ከእነዚህ ውስጥ እስካሁን 7200 እንስሳት መሞታቸውን አረጋግጠዋል፡፡ እስካሁን የአንድም ሰው ሕይወት አለማለፉ አፅናንቷቸዋል፡፡ ቀደም ብሎ በየቦታው 60 ኩሬዎች ቢቆፈሩም አብዛኞቹ ደርቀዋል፡፡ ለክፉ ቀን ተብለው የተቆፈሩት ጉድጓዶች ናቸው እስካሁን ድረስ ለማህበረሰቡ ተስፋ የሆኑት፡፡ ግን ቀድሞ ዓመቱን ሙሉ ይቆይ የነበረው የውሃ መጠን አሁን የለም፡፡ በቀጣይ ችግሩን የሚያቃልሉ ሥራዎች ይኖራሉ ብለው ተስፋ አድርገዋል፡፡ በወረዳው አምስት ሰፋፊ ጉድጓዶች በመንግሥት ተቆፍረዋል፡፡ እስከ 21ሺህ ሜትር ኩብ ውሃ የሚይዙ ናቸው፡፡ የምስራቅ አፍሪካ በየነ መንግሥታት (ኢጋድ) በወረዳው አንድ ኩሬ ለመስራት እና አንድ ኩሬ ለመጠገን በእንቅስቀሴ ላይ ነው፡፡ ይህም ድርቁን ለመመከት የራሱ ድርሻ እንደሚኖረው ታምኗል፡፡

አቶ ሰይዶ ጎዳና በጉጂ ዞን ጉሚኤርዳሎ ወረዳ የአደጋ ስጋት አመራር ሲሆኑ፤ አካባቢውን በተደጋጋሚ ድርቅ እንደሚጎበኘው ይናገራሉ፡፡ በወረዳው 255ሺህ የቀንድ ከብቶች፣ በርካታ ፍየሎች፣ ግመሎችና በጎች ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል በድርቁ 24ሺህ እንስሳት መሞታቸውን አረጋግ ጠዋል፡፡በድርቅ የተጎዳው ህዝብ ደግሞ 48ሺህ ደርሷል፡፡ መንግሥት አስቸኳይ እገዛ እያደረገ በመሆኑ 4ሺህ 600 ኩንታል እህል እና የእንስሳት መኖ እየተከፋፈለ ነው፡፡ «አሁን ያለንበት ድርቅ አስቸጋሪ እና አሳሳቢ ነው፡፡ በድርቅ ሳቢያ አሎዮ፣ ሶሎቅ፣ ዱሬሳ የሚባሉ ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል፡፡ ከ400 በላይ ተማሪዎች ትምህርታቸውን አቋርጠዋል፡፡ በዘላቂነት የድርቅ መንስኤዎች ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት ይገባል። ድርቅ የሚቋቋሙ እፅዋት መትከል ዋነኛ አጀንዳ ተደርጎ በመወሰዱ እስካሁን 22 ሄክታር ላይ ተተክሏል፡፡ ይህን ልምድ ማስፋፋቱ ግድ ይላል» ይላሉ፡፡

የጉጂ ዞን የአደጋ ስጋት አመራር ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አበበ አባቡልጉ እንደሚሉት፤ ለድርቁ ዋነኛ ምክንያት አርብቶ አደሩ ዝናብ ሲጥል ሳር ማብቀል፣ ተፋሰስ ልማት እና ሌሎች ሥራዎች ማከናወን አለመቻሉ ለችግሩ መባባስ ዋነኛ ምክንያት ነው ይላሉ፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ መንግሥት በአካባቢው ያለው የእንስሳት ሃብት በገበያ ሰንሰለት ትክክለኛ ተጠቃሚ አለመሆናቸው ለችግር ጊዜ የሚያስቀምጡት ገንዘብ የላቸውም፡፡በአካባቢው የቁጠባ ባህል ቢኖር ድርቅን ለመቋቋም በሚደረገው ጥረት አዎንታዊ ሚና ሊኖረው ይችል እንደነበር ይገልጻሉ፡፡ ስለሆነም የማህረሰቡ የአኗኗር ዘይቤ ድርቅን ለመከላከል አመቺ በሆነ መልኩ መቃኘት አለበት ይላሉ፡፡ ዝናቡ ካልጣለ ችግሩ ሊቀጥል ይችላል የሚል ስጋት አድሮባቸዋል፡፡ እየተሰጠ ያለው እርዳታም ቢሆን ሙሉ ለሙሉ እርዳታ ፈላጊውን እያዳረሰ ባለመሆኑ የክልሉም ሆነ የፌዴራል መንግሥት እገዛ እና ክትትል ማጠናከር እንደሚገባ ይጠቁማሉ።

ቦረና ዞን

በቦረና ዞን፤ የውሃ ሽፋን 47 በመቶ ነው፡፡ በርካታ ኩሬዎች ቢኖሩም አሁን ላይ ደርቀዋል፡፡ በመብራት ተደጋግሞ መጥፋት ሳቢያ በከተሞች አካባቢ የውሃ እጥረት እየተከሰተ ነው፡፡ ይህን ችግር ለማቃለል ድርቁ በተከሰተባቸው አካባቢዎች 27 ተሽከርካሪዎች ተመድበው ውሃ በማዳረስ ላይ ናቸው፡፡

አርብቶ አደር ቁሩ ጡኑሴ ቦረና ዞን ሚኦ ወረዳ ነዋሪ ናቸው፡፡ ድርቁን ለመቋቋም የማይፈነቅሉት ድንጋይ አልነበረም፡፡ አሁን ግን የተሸነፉ ይመስላሉ የእራሳቸውንና የቤተሰባቸውን ሕይወት ለማቆየት ያላቸውን ከብቶች ለመሸጥ ተገደዋል፡፡ችግር የሆነባቸው በቅርብ ገበያ አግኝተው በጥሩ ዋጋ መሸጥ አለመቻላቸው ነው፡፡ ከድርቁ ባሻገር ነጋዴዎች የእንስሳት ዋጋ እንዲወርድ ከፍተኛ ተፅዕኖ ፈጥረዋል፡፡ ቀድሞ 11ሺህ ብር ያወጡ የነበሩት ከብቶች በአሁኑ ወቅት በ5ሺህ እንኳ የሚገዛቸው ጠፍቷል፡፡ የሆነው ሆኖ ከድርቁ ጋር ግብግብ ገጥመዋል፡፡ ከመንግሥት እየጠየቁ ያለው መኖ እና የምግብ እርዳታ ብቻ ሳይሆን «ለሃብታችን በቂ ገንዘብ የምናገኝበት ጥሩ ገበያ ይፈጠርልን» የሚል ነው፡፡

በሰዎች ቀለብ በኩል ግን በቂ እርዳታ እየተደረገ በመሆኑ ለመንግሥት ምስጋና ይግባው ይላሉ፡፡ ግን ደግሞ ከዛሬ ነገ ድርቁ ይወገዳል፤ ዝናብ ይመጣል ብለው ያስባሉ፡፡ አማካይ የገበያ ቦታ እና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ግን የማያባራ የአካባቢው ጥያቄ መሆኑን አፅንኦት ሰጥተውበታል፡፡

ጎዳና ዱዋ የቦረና ዞን የአደጋ ስጋት አመራር ፅህፈት ቤት ኃላፊ እንደሚሉት፤ እርዳታ እየተደረገ ቢሆንም በቂ አይደለም፡፡103ሺ ሰዎች እርዳታ ያስፈልጋቸዋል፡፡ አራት ሚሊዮን እንስሳት በዞኑ ስለሚገኙ እያንዳንዱን ማድረስ አልተቻለም፡፡ በዞኑ ያሉት 13 ወረዳዎች ሁሉም የውሃ ችግር አለባቸው፡፡ ለዚህም ውሃ ለማደል 39 ተሽከርካሪዎች ያስፈልጋሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት የተገኙት 27 ብቻ ቢሆኑም ቀሪዎቹ ደግሞ በቅርቡ እንደሚመጡ ተስፋ አድርገዋል፡፡ ውሃ ለማከም የሚውሉ መድሃኒቶችም እጥረት እንዳለ እና ለዚህም ተገቢው ርብርብ እየተደረገ ነው፡፡ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው የማቋረጥ ሁኔታ ተከስቷል፡፡ በዞኑ ካሉ 339 ትምህርት ቤቶችም 326 የምገባ መርሐ ግብር ማስጀመር አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ 25 ሚሊዮን ብር ተመድቦላቸዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በርካታ እንስሳት በመሞት ላይ በመሆናቸው መኖ የማቅረቡ ጉዳይ ግን ገና ብዙ እንደሚቀረው ይናገራሉ፡፡

የቦረና ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሊበን አሬሮ ድርቁ ከፍኛ ጉዳት እያደረሰ ነው ይላሉ፡፡ የህዝቡም ሆነ የእንስሳት ቁጥር እየጨመረ በመሆኑ ችግሩን አባብሶታል፡፡ የተረጂዎች ቁጥር ከ90ሺ ወደ 147 ሺ ከፍ ብሏል፡፡ በዛው ልክ የፌዴራልም ሆነ የክልሉ መንግሥት ጥረትና እገዛ ጨምሯል፡፡ በእንስሳት መኖ፣ በአልሚ ምግቦች፣ ለአዋቂዎች ምግብ እየተሰጠ ነው፡፡ ከዚህ በዘለለ ግን የከርሰ ምድር ውሃ አጠቃቀም ባህል በጣም ደካማ ነው፡፡ ስለዚህ ይህን ማስተካከል ተገቢ መሆኑን ያምናሉ፡፡ በዞኑ በርካታ መንደሮች የከርሰ ምድር ውሃ ቢኖራቸውም ለመጠቀም የተደረገው ሙከራ በጣም ደካማ መሆኑን ነው የታዘቡት፡፡ ከዚህ በዘለለ ግን በድርቅ ምክንያት ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ስለመቅረታቸው መረጃ የለኝም ብለዋል፡፡

ጉራማይሌ ገጽታ

ወይዘሮ አሚኖ አሊ የጎሮዶላ ወረዳ ቢታታ ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ፤ በድርቅ በርካቶች በተጎዱበት ጉጂ ዞን ነዋሪ ናቸው፡፡ ጥልቅ ጉድጓድ ቆፍረው በመስኖ ያለማሉ፡፡ በዓመት እስከ ሶስት ጊዜ ያመርታሉ፡፡ ከቤተሰቦቻቸው ጋር አንድ ለአምስት ተደራጅተው መስራታቸው ውጤታማ አንዳደረጋቸው ይናገራሉ፡፡ «ገናሌ ወንዝ ቅርባችን ሆኖ ሳለ መንግሥት ቢጠልፍልን እኛ ለማልማቱ አንሰንፍም ነበር። ያ! ግን አልሆነም»ይላሉ። እርሳቸው በእጃቸው በቆፈሩት ጉድጓድ መስኖ አልምተው 50ሺህ ብር ባንክ መቆጠብ ጀምረዋል፡፡ ነገ ከዚህ በበለጠ ለመስራት እና እራሳቸው ብቻ ሳይሆን ከአገሬው ሰው ጋር ማደግን ይመኛሉ፡፡ ይሁንና የመንግሥት እገዛ መጠናከር እንደሚገባው ነው የሚናገሩት፡፡

አቶ ዱብ ኮንሶሌ በቦረና ዞን ሚኦ ወረዳ ነዋሪ ናቸው፡፡ ትምህርታቸውን ምስራቅ አውሮፓ ቡልጋሪያ በሲቪል ኢንጅነሪንግ አጠናቀው ነበር የመጡት፡፡ በተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ሰርተዋል፡፡ አሁን ደግሞ አርብቶ አደር መንደር ዘልቀው በመስኖ እያለሙ ነው፡፡ የባለሙያዎች ምክር ውስንነት እራሳቸውን ወደ መንደሩ እንዲዘልቁ እንዳስገደዳቸው ይናገራሉ። እየመጡም ይከታተላሉ፡፡ ይሁንና የአገሬው ሰው የከርሰ ምድር ውሃ መጠቀም ባህሉ እጅግ ደካማ መሆኑን ታዝበዋል፡፡ በመሆኑም አካባቢው ትንሽ ድርቅ በተከሰተ ቁጥር እርዳታ መጠየቅ ለእርሳቸው አይዋጥላቸውም፡፡ ይህ ደግሞ እርዳታ የአርብቶ አደሩን ሥነ ልቦና ለበለጠ ሥራ እንዳያነሳሳ እያደረገ መሆኑን ተረድተዋል፡፡ «ሌላ አማራጭ እንዲመለ ከትም አላደረገውም፡፡ ይልቁንም አማራጭ ሥራዎች ላይ እንዲሰማሩ መንግሥት ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅበታል» የሚል እምነት አላቸው፡፡

ፈተናዎች

በርካቶች እንደሚስማሙት፤ በክልሉ የተከሰተው ድርቅ ከአምናው አኳያ ሲታይ በአንዳንድ አካባቢዎች የጨመረ ቢመስልም በአጠቃላይ ሲታይ በተወሰነ መልኩ ቀንሷል፡፡ ቢሆንም በቀጣይ ሊጨምር ይችላል የሚል ስጋት አለ፡፡ ይህም የመንግሥትን ካዝና መፈተሹ አይቀሬ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የቁም እንስሳት ቀድሞ ከሚሸጡበት ዋጋ እጅግ ባነሰ ዋጋ በመሸጥ ላይ ናቸው፡፡ ይህም አርብቶ አደሩ ጥሪቱን ለሟሟጠጥ እየተገደደ ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር እንስሳትን ፍትሃዊ በሆነ ዋጋ ለመሸጥ አማራጮች የሉትም፡፡ ይህም አርብቶ አደሩ በቀጣይ ከድርቁ አገግሞ ወደቀደመ ህይወቱ ለመመለስ አስቸጋሪ ሊሆንበት እንደሚችል አያጠራጥርም፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ የቅንጅታዊ አሰራር መጓደል ይስተዋላል፡፡ የእንስሳት መኖ በሚፈለግበት አካባቢ ውሃ ቀድሞ የሚደርስበት አጋጣሚ እንዳለ ነዋሪዎች ይናራሉ፡፡ እንደ ነዋሪዎቹ ፍላጎት ሁሉም በተቀናጀ መልኩ ውሃ፣ የእንስሳት መኖ እና ለሰውም ቀለብ እንዲደርስ ይጠበቃል፡፡ ከሁሉም በተለይ ግን የመረጃ መጣረስም በመስተዋሉ መንግሥት ለሚያደርገው የእርዳታ አቅርቦት አስቸጋሪ ሁኔታ መፍጠሩ አይቀርም፡፡

«ተማሪዎች ከትምህርት ቤት ቀርተዋል» ብለው የወረዳ ኃላፊዎች ሲናገሩ ዞኖች «ወይ ፍንክች ነጭ ውሸት ነው» ይላሉ፡፡ በድርቅ ምክንያት አንድም ተማሪ ትምህርት እንዳላቋረጠም ይናራሉ፡፡ በአጭሩ የሞቱት እንስሳትም ቁጥርም ሆነ ከትምህርት ያቋረጡ ተማሪዎች ቁጥር ላይ ወጥነት የጎደለው እና የሚጣረስ መረጃ እየቀረበ በመሆኑ መንግሥት ለሚያደርገው እርዳታ አስቸጋሪ ስለሚሆን ሊታሰብበት ይገባል፡፡ ማህበረሰቡ ሌላ የሥራ አማራጭ ያለመልመድና በእንስሳት ማርባት ላይ ብቻ የተመሰረተ መሆኑም በቀጣይም ፈተና ሆኖ የሚቀጥል ነው፡፡የተፋሰስ ልማት ሥራም ደካማ ነው፡፡ መሰረተ ልማት ማሟላት ሌላው ፈተና ነው፡፡ ቀበሌን ከቀበሌ ለማገናኘትም የሚያስችሉ አዳዲስ መሰራት ያለባቸው ድልድዮች አሉ፡፡

አርብቶ አደሮቹ እንደሚሉት፤ ትልቁ ችግር ገበያ ነው፡፡ ስጋ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ በአካባቢው አለመኖሩም አርብቶ አደሩ ተገቢውን ጥቅም እንዳያገኝ አድርገውታል፡፡ በዚህ ላይ መንግሥት ቢያስብበት እና አማራጮችን ቢዘረጋ አርብቶ አደሩ ፍትሃዊ ገበያ ተጠቃሚ ከመሆንም በተጨማሪ ችግሮችን ለመቋቋም የሚያስችለው ገንዘብ ለመቋጠር ይችላል፡፡ በዚህ ረገድ በአጽንኦት ሊሰራ እንደሚገባ ነው የሚናገሩት፡፡ ወደ መስኖ እየገቡ ያሉ አርብቶ አደሮች አሉ፡፡ በአንድ ዙር ብቻ እስከ 300ሺህ የሚጠጋ ብር ያገኙ አሉ፡፡ ይሁንና በርካቶችን በዚህ ረገድ ማሳተፍ አልተቻለም፡፡ ገናሌ ወንዝ፤ ጉጂ ዞን እና ባሌን አቋርጦ ያልፋል፡፡ ጉጂ እና ቦረናን ደግሞ የዳዋ ወንዝ አቋርጦ ይፈሳል፡፡ ግን እነዚህን የውሃ ሀብቶችን ጠልፎ ሥራ ላይ ለማዋል በዞኑ አቅም የሚደፈር አይደለም፡፡ ስለዚህ ይህ የክልሉና እና የፌዴራል መንግሥት ጣልቃ ካልገቡ ፈተናው የሚቀጥል ይሆናል። እንደ ዞን የሥራ ኃላፊዎች አስተያየት፡፡

መልካም ተሞክሮዎች

በጉጂ ዞን ሁለት ሚሊዮን እንስሳት ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 800ሺ እንስሳት በቂ መኖ እና ውሃ የሚያስፈልጋቸው ናቸው፡፡ በድርቁ ያልተጠቁት ወረዳዎች የተጠቁትን እያገዙ ነው፡፡ መንግሥትም በሰባት ወረዳዎች ውሃ እያቀረበ ነው፡፡ አልፎ አልፎ የውሃ ማጠራቀሚያ «ሮቶ» የሌለበት ቦታ አለ፡፡ በአሁኑ ወቅት 17 ኤፍ ኤስ አር መኪናዎች ተመድበው ውሃ እና መኖ እያደረሱ ነው፡፡ በደጋማ አካባቢዎች ያሉ ሰዎችም በቆላማ ያሉትን እያገዙ ነው፡፡ ከሦስት ሚሊዮን ብር በላይ «ህዝብ ለህዝብ» በሚል የተሰበሰበ ብር አለ፡፡ ከዚህም እህል ተገዝቶ በአምስት ወረዳዎች እየተከፋፈለ ነው፡፡ የመንግሥት ሰራተኞችም የአንድ ወር ደመወዛቸውን በመስጠት ለማገዝ ጥረት እያደረጉ ነው፡፡

የገናሌ እና ዳዋ ወንዞች አካባቢውን ለሁለት ከፍለው ቢሄዱም አርብቶ አደሩ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ይህን ውሃ ቢጠቀም ችግርን በዘላቂነት መቋቋ ይችላል፡፡ እርጥበት ባለበት አካባቢ ደግሞ የተለያዩ የጓሮ አትክልት እየለማ ችግሩን ለመመከት ጥረት ተጀምሯል፡፡ እነዚህ ችግሮች በቀጣይነት ለማቃለል እንስሳትን ማርባት ብቻ ሳይሆን በሌላ የሥራ መስክ ላይ ለመሰማራት አማራጮች እንዳሉ ማሳያ ነው፡፡

የክልሉ ምላሽ

አቶ ናስር ሁሴን በኦሮሚያ አርብቶ አደር ኮሚሽን የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች የሥራ ሂደት መሪ ናቸው። ድርቁ የተከሰተባቸውን አካባቢዎች የተለያዩ ድጋፎቸን ከማድረግ በዘለለ የእንስሳትን ዝርያ ለማቆየትም ሌላ ዘዴ መኖሩን ይናገራሉ፡፡የተደራጁ እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ጉዳዩ ላይ እየሰሩ ነው፡፡ እንስሳት ጥሩ ገበያ እንዲያገኙ እየተደረገ ነው፡፡ ዝርያዎችን ለመታደግም ድርቅ ከተከሰተባቸው አካባቢዎች በክልሉ መንግሥት 15 ሚሊዮን ብር ተመድቦ እንስሳት ተገዝተዋል፡፡ እነዚህም ድርቅ ባልተከሰተባቸው አካባቢዎች እንዲቆዩ ይደረጋል፡፡ በአጠቃላይ ግን ድርቁን በዘላቂነት ለመቋቋም የአርብቶ አደሩን ሕይወት በመሰረታዊነት የሚቀይር አሰራር ለመተግበር መንግሥት ትልቅ ትኩረት እንደሰጠ ይናገራሉ፡፡

የኦሮሚያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ግርማ ወተሬ በበኩላቸው፤ የተረጂዎች ቁጥር ባለፈው ዓመት 3ነጥብ7 ነበር፡፡ በዚህ ዓመት ደግሞ 2 ነጥብ4 ነው፡፡ ቦረና፣ ጉጂ፣ ሀረርጌና ባሌ አካባቢዎች ጉዳት የደረሰባቸው ናቸው፡፡ የተረጂዎች ቁጥር አሁን ካለበት ይጨምራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ለዚህም ዝግጅት ተደርጓል፡፡ እስካሁን 3ነጥብ8 ሚሊዮን ብር የሚገመት ዕርዳታም ተሰራጭቷል፡፡ በህዝብ ለህዝብ ድጋፍ 12 ሺ ኩንታል እርዳታ ተገኝቷል፡፡ የመንግሥት ሰራተኞች አለኝታነትም እየተጠናከረ ነው።

በተለያዩ ምክንያቶችም ለተፈናቀሉ 35ሺ ሰዎችም እርዳታ እየተደረገላቸው ነው፡፡ የክልሉ መንግሥትም 186 ሚሊዮን ብር መድቧል፡፡ ከዚህም ውስጥ 65 ሚሊዮኑ ለእህል ግዥ ውሏል፡፡ በአጠቃላይ በፌዴራል፣ በክልል እና በተለያዩ ፈንዶች 568 ሚሊዮን ብር ለዚህ ዓላማ ተመድቧል፡፡ የተረጂዎች ቁጥር እንደሚጭርም ታሳቢ በመደረጉ እገዛው ይጠናከራል፡፡ «በምግበ እጦት የአንድም ሰው ሕይወት አይጠፋም» የሚለው የመንግሥት አቋም ነው፡፡ የተማሪዎች ማቋረጥ እንዳይኖርም የምግባ መርሃ ግብሮችን ለማጠናከር እየተሰራ ነው፡፡ 57 ሚሊዮን ብር ከክልል መንግሥት፤ ከፌዴራል ደግሞ 27 ሚሊዮን ብር ለእንስሳት መኖ መግዣ መመደቡ ችግሩን ለመቋቋም እንደሚያስችል ተስፋ አድርገዋል፡፡

 ክፍለዮሐንስ አንበርብር

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy