Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የወጪ ንግዱ ያሳየው ማሽቆልቆል ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትን በስብሰባ ወጥሯል

1 475

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

  • ላኪዎች ነገ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ለስብሰባ ተጠርተዋል    
  • የንግዱ ማኅበረሰብ በጥናት ላይ የተመረኮዘ መትፍሔ እንዳቀርብ ዕድሉን አላገኘሁም ይላል

የአገሪቱ የወጪ ንግድ እያሳየ ያለው ማሽቆልቆል እየተባባሰ በመምጣቱ፣ መንግሥት አስቸኳይ መፍትሔ ለመስጠት የሚያስችሉ የአጭር ጊዜ ዕርጃዎችን መውሰድ እንደሚጀምር በመግለጽ ላይ ይገኛል፡፡ ይህንኑ ለማድረግም የተለያዩ ስብሰባዎችን በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡

ከጥቂት ቀናት በፊት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍተኛ አማካሪ አቶ አርከበ ዕቁባይ (ዶ/ር) የተመራ ስብሰባ ተጠርቶ እንደነበር ይታወሳል፡፡ መንግሥት በተለይ ላኪዎችን ባነጋገረበት ወቅት በአገሪቱ ለሚታየው አሳሳቢ የወጪ ንግድ ማሽቆልቆል መንስዔው ምን እንደሆነና መትፍሔውንም ያመላከተ ውይይት ማድረጉም ታውቋል፡፡

በስብሰባው ወቅት እንደተነሱ ከተገለጹ ነጥቦች መካከል የመንግሥት ቢሮክራሲያዊ አሠራር የፈጠራቸው ችግሮች ትልቁን ድርሻ ይዘዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር በተለይ ቡና ላኪዎች በአሻጥር የፈጸሙት ተግባር ተብሎ የቀረበውና በአገር ውስጥና በዓለም ገበያ መካከል ያለውን የዋጋ ክፈተት መንስዔ በማድረግ ወደ ውጭ ከመላክ የተቆጠቡ ነጋዴዎች መታየቸው በመንግሥት ሲገለጽ ተደምጧል፡፡ በዘንድሮው ስድስት ወራት ውስጥ ከወጪ ንግዱ ዘርፍ ይጠበቅ የነበረው የውጭ ምንዛሪ ገቢ 2.5 ቢሊዮን  ዶላር ገደማ ነበር፡፡ ይሁንና የተገኘው ግን 1.4 ቢሊዮን ዶላር እንደሆነ መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ይህ አፈጻጸም በዕቅድም ከዚህ ቀደም ሲገኝ ከነበረውም ያነሰ ሆኗል፡፡

ምንም እንኳ ላኪዎችና ገዥዎች በዋጋና በዓለም አቀፍ ገበያ መቀዛቀዝ ምክንያት የተፈጠረ እንደሆነ ቢገልጹም፣ በአገሪቱ የተከሰተው የፀጥታ ችግር፣ በፀጥታው መናጋት ምክንያት የተፈጠረው ሥጋትም ለወጪ ንግዱ መቀዛቀዝ ዋቢ ተደርጓል፡፡ ነገሮች በዚህ አኳኋን ከቀጠሉ አገሪቱ የወጪ ንግድ ክፉኛ አደጋ እንደተጋረጠበት የተረዳው መንግሥት፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ የዘርፉን ችግሮች ይቀርፉልኛል ያላቸውን ያልተጠበቁ የመፍትሔ ሐሳቦችን እያቀረበ ይገኛል፡፡

በመንግሥት ከቀረቡት ሐሳቦች መካከል የኢትዮጵያ ምርት ገበያን እንዲሁም የኢትዮጵያ የግብርና ምርቶች አገልግሎትን የሚመለከቱ ለውጦች ይገኙበታል፡፡ ላኪዎች ከሁለቱ ተቋማት ጋር ያላቸውን ግንኙነት ሊለውጥ የሚችል አሠራር እንደሚተገበር ከሚጠቅሰው የመንግሥት ምልከታ አንዱ እንደሆነ የሚጠቀሰው፣ ላኪዎች በመኪና የጫኑት ጭነት በቀጥታ ኤክስፖርት መደረግ የሚችልበትን አሠራር ለማምጣት የሚያስችል አማራጭ ማቅረቡ ተነግሯል፡፡ ይህ አሠራር የወጪ ንግዱን የተቀላጠፈ ለማድረግ ያሰበ ሲሆን፣ ሌሎችም በርካታ ለውጦች እንደሚደረጉ የቡናና ሻይ ልማትና ግብይት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳኒ ረዲ መናገራቸው ይታወሳል፡፡

እነዚህን ለውጦችና ሌሎችም የአሠራር ማሻሻዎች በአጭርና በረጅም ጊዜ ውስጥ ለመተግበር የተነሳው መንግሥት፣ ከሁለት ሳምንት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ላኪዎችና ሌሎች የሚመለከታቸውን ተዋንያን ለማነጋገር ነገ ስብሰባ ጠርቷል፡፡ የስብሰባው ዓብይ አጀንዳ ምን እንደሆነ ለማወቅ ሪፖርተር ሞክሮ በአብዛኛው ከወጪ ንግዱ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ እንደሚሆን ተረድቷል፡፡

ስለዚሁ ጉዳይ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ሰሎሞን አፈርቅንም ለማነጋገር ተሞክሯል፡፡ አቶ ሰሎሞን እንደገለጹት የንግዱ ማኅበረሰብ በተለይም ላኪዎች በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ለስብሰባ ተጠርተዋል፡፡ ንግድ ምክር ቤቱም ለተሳተፎ መጋበዙን ገልጸዋል፡፡

ይሁንና መንግሥት በጊዜያዊ ጉዳዮች ላይ የሚያደርገውን ርብርብ በዘላቂ መፍትሔዎች ላይ በማድረግ ለውጥ እንዲኖር መሥራት እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል፡፡ የአገሪቱ የወጪ ንግድ ለውጥ እንዲያሳይ ከግብርና ሸቀጦች ላኪነት ወደ ፋብሪካ ውጤቶች ላኪነት መለወጥ እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡ መንግሥት በአገር ውስጥ እየታየ ያለውን ከፍተኛ የፍላጎት ዕድገት ከማሟላት ባሻገር ትርፍ ምርት በማምረት ለውጭ ገበያ ማቅረብ የሚችልበትን የተሟላ መሠረተ ልማት መዘርጋት እንደሚጠበቅበትም ጠቅሰዋል፡፡

አገሪቱ ዘንድሮ የሚጠበቀውን የወጪ ንግድ አፈጻጸምና የውጭ ምንዛሪ ገቢ ማግኘት ካልተቻለባቸው አንኳር ጉዳዮች መካከል የአገሪቱ የፀጥታ ችግር እንዲሁም ከቦታ ቦታ ምርት ለማዘዋወር ያለው ሥጋት ተጠቃሽ እንደሆነ አቶ ሰለሞን ጠቅሰዋል፡፡ የዓለም ኢኮኖሚ ያሳየው መዳከምና ለሸቀጥ ዕቃዎች የታየው የገበያ መቀዛቀዝም ምክንያት እንደሆኑ አስታውቀው፣ መንግሥት ከቢሮክራሲው ባሻገር በአገር ውስጥ ለሚመረቱ የፋብሪካ ውጤቶች ትኩረት መስጠት እንደሚጠበቅበት፣ የሜካናይዝድ እርሻን በማስፋፋት ልማዳዊውን የግብርና ስልት መቀየርም የመንግሥት የቤት ሥራዎች እንደሆኑ አብራርተዋል፡፡

‹‹ዋናው መሠረታዊ ለውጥ ትርፍ ምርት እንዲመጣ ማድረግ፣ አዲስ ምርት ወደ ኢኮኖሚው ማምጣት መቻል እንዲሁም ከውጭ የሚገቡ ምርቶች የሚተኩ ምርቶችን በአገር ውስጥ ማምረት መቻል ነው፤›› ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ ስንዴ ከውጭ እያስመጡ ያንን ለየዱቄት ፋብሪካዎች ሰፍሮ በመስጠት ለውጥ አይመጣም ብለዋል፡፡ ይልቁንም መንግሥት ከገበሬው የሚተርፈውን አነስተኛ ምርት ከመጠበቅ ይልቅ ትርፍ ማምረት የሚያችሉ አሠራሮችን በመዘርጋት ለፋብሪካዎች እንደልብ ማቅረብ የሚቻልባቸውን ለውጦች ማምጣት መቻል እንዳለበትም መክረዋል፡፡

ይሁንና በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ነገ እንደሚደረግ ለተጠራው ስብሰባ የንግድ ምክር ቤቱ የተጠራው እንዲሁ ለተሳትፎ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ሰለሞን፣ ከዚህ ይልቅ ግን የጉዳዩ ባለቤት የንግድ ማኅበረሰቡ እንደመሆኑ መጠን ውክልናው ያለው ተቋም በጥናት ላይ የተመሠረተ የመፍትሔ ሐሳብ ይዞ መቅረብ የሚችልበት ዕድል ሊሰጠው ይገባል ብለዋል፡፡ መንግሥትም ‹‹ነገሩን ለባለቤቱ›› በመተው የችግሩን ምንጭ ከነመፍቻው አጣቅሰው እንዲቀርቡ ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

 

  1. Mulugeta Andargie says

    Dears!!!! It is important to expect foreign exchange from Asians not from the developed nations. The expected finance will be poured slowly but make strength the market exchange and close relations in so many ways. As I have seen you, you are doing the best you can. Economical development couldnt be seen randumly. It goes slowly!!

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy