Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ

0 24,463

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ በሰሜን ሸዋ በምትገኘው አንኮበር ላይ ጥቅምት 13 ቀን 1925 ዓ/ም ከአባታቸው አቶ ተክሌ ማሞ እና ከእናታቸው ከወይዘሮ ፈለቀች የማታወርቅ ተወለዱ።

የጠላት የግፍ ወረራ እና እልቂት ያስከተለውን የሰው፣ የንብረት እና የባህል ጥፋት ገና በህጻንነት ዕድሜያቸው የተመለከቱት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ከነጻነት በኋላ ሃገራቸውን እንደገና እንዴት መገንባት እንደሚቻል ሲያወጡ እና ሲያወርዱ ከቆዩ በኋላ ዋናው እና ቀዳሚው ጉዳይ እውቀት መሸመት መሆኑን የተረዱት ገና በልጅነት እድሜያቸው ነበር ፡፡

ግንዛቤያቸውን በማሳደግም በማዕድን ምሕንድስና ዘርፍ ላይ እውቀት በመጨበጥ ሃገራቸውን መጥቀም እንዳለባቸው ቢወስኑም ወላጆቻቸውና ዘመድ አዝማዶቻቸው ግን የኪነ ጥበብ ስጦታቸውን በቤታቸውና በከተማው ዙሪያ በሚስሏቸው ስዕሎች በመመልከታቸው በዚሁ ሙያ እንዲሰማሩ ይጎተጉቷቸው ነበር።

የመጀመሪያና መካከለኛ ትምህርታቸውን የት እና መቼ እንዳጠናቀቁ የተጻፈ መረጃ ባናገኝም፤ ገና በአሥራ አምስት ዓመታቸው በ1940 ዓ/ም ለከፍተኛ ትምህርት ተመርጠው የምሕንድስና ትምህርት ለመከታተል ወደ እንግሊዝ አገር መላካቸው ተዘግቧል ፡፡

ለትምህርት የተመረጡት ተማሪዎች ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ሲሰናበቱ የተሰጣቸውን ምክር ሁሌም እንደሚያስታውሱት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ሲናገሩ ‹‹ንጉሠ ነገሥቱ ተግታችሁ አጥኑና ተማሩ ፣ ጠንክራችሁ ለመስራትና ሀገራችሁ ኢትዮጵያን የምትገነቡበትን ዕውቀት ይዛችሁ ተመለሱ።

‹‹ ከናንተ የሚፈለገው አዕምሯችሁን ዝግጁ አድርጋችሁ ኢትዮጵያን ለመገንባት የሚያስችል እውቀትንና ጥበብን ሸምታችሁ እንድትመለሱ ነው እንጂ አውሮፓ ውስጥ ስላሉት ረዣዥም ፎቅ ቤቶች ወይም ስለመንገዶቻቸው ስፋት በአድናቆት እንድትነግሩን አይደለም ›› ብለዋቸው እንደነበር ሁሌም ያስታውሱ ነበር፡፡

እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ በእንግሊዝ አገር በትምህርት ላይ ሳሉ የአዳሪ ትምህርት ቤትን ኑሮ በማስታወስ የባእድ ሃገር እንግዳ በዓላት እና የአየር ሁኔታው መለዋወጥ እንዳስቸገራቸው ያወሳሉ።

በትምህርት አቀባበላቸውም በሒሣብ፣በኬሚስትሪ እና በታሪክ ትምህርቶች ጥሩ ውጤት በማምጣት ከመምህሮቻቸው ተደጋጋሚ አድናቆት ቢያገኙም የተፈጥሮ ስጦታቸው ኪነ ጥበብ እንደሆነ መምህሮቻቸው ለመገንዘብ ግን ብዙ ጊዜም አልወሰደባቸውም።

በመምህራቸው አበረታችነት በዚህ ስጦታቸው ላይ የበለጠ ለማተኮር ወስነው በለንደን ማእከላዊ የኪነ ጥበብ ትምሕርት ቤት የገቡት አፈወርቅ ከዚህ ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን በጥሩ ውጤት በማጠናቀቅ ለከፍተኛ ጥናት በስመ ጥሩው የለንደን ዩኒቨርሲቲ የስሌድ ኪነ ጥበብ ማዕከል የመጀመሪያው አፍሪካዊ ተማሪ ሆነዋል ፡፡
በዚህ ትምህርት ቤት ቆይታቸውም በቀለም ቅብ፣ በቅርጻ ቅርጽ እና በኪነ ህንጻ ጥናቶች ላይ በመስራት ተመርቀዋል።

እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ትምህርታቸውን አጠናቀው ወደ ኢትዮጵያ እንደተመለሱ በተለያዩ ግዛቶች በመዘዋወር በአንዳንድ ቦታም እስከ ሦስት ወራት በመቀመጥ የኢትዮጵያን ታሪክ እና የብሔረሰቦቿን ባህልና ወግ ሲያጠኑ ቆይተዋል።
በ1946 ዓ/ም በሀያ ሁለት ዓመታቸው የተለያዩ የስነ ጥበብ ሥራቸውን የሚያሳይ የመጀመሪያውን ኤግዚቢሽን በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት አቅርበዋል።

ከትርዒቱ ባገኙት ገቢ በድጋሚ ወደ አውሮፓ በመሄድ ለሁለት ዓመት በጣሊያን፣ በፈረንሳይ፣ በስፔን፣ በፖርቱጋል፣ በእንግሊዝና ግሪክ ጥልቅ የኪነ ጥበብ ጥናት አከናውነዋል።
በጦርነትና በሌሎች ምክኒያቶች ተዘርፈው በነዚህ ሃገራት የሚገኙትን የኢትዮጵያ ጥንታዊ የሃይማኖትና የታሪክ የብራና መጻሕፍትን በጥልቅ አጥንተውና የመስታወት ላይ ስዕል ( የሞዛይክ አሠራር ጥበብን ) ቀስመው ወደ አገራቸው ተመልሰዋል።

እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ወደ ሃገራቸው እንደተመለሱ ንጉሠ ነገሥቱ አዲስ አበባ በሚገኘው የመናገሻ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ግድግዳ፣ ጣሪያና መስኮቶችን በሃይማኖታዊ ምስሎች በቀለምና በመስታወት ስዕሎች እንዲያስውቡት ባዘዟቸው መሰረት አሁን የሚታዩት ፡-የዳግም ምጽአት ፍርድ፣ የድንግል ማሪያም ንግስና ፣ ኪዳነ ምሕረት፣ እና የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን የዘውድ ስርዓት የሚያሳዩ ሥራዎችን ሰርተዋል ፡፡

ከዚህም ሌላ አሁን በሐረር ከተማ ቆሞ የሚታየውን የልዑል ራስ መኮንን ሀውልት የቀረጹት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ናቸው ፡፡
ከታዋቂ ሥራዎቻቸው በከፊል
• በአዲስ አበባ በቀድሞው የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት አዳራሽ መግቢያ የሚታየው በመቶ ሃምሳ ካሬ ሜትር ላይ የተሳለው ትልቅ የመስታወት ስዕል
• አዲስ አበባ በመናገሻ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን የውስጥ ስዕሎች፣ ሞዛይኮች
• አዲስ አበባ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የሚገኘውን የመጀመሪያውን የ’ዳግም ምጽዓት ፍርድ ስዕል
• በሐረር የልዑል ራስ መኮንን ሐውልት
• በአዲግራት የ’ዳግም ምጽዓት ፍርድ ስዕል
• በለንደን ‘ታወር ኦፍ ለንደን’ የቅዱስ ጊዮርጊስ ጸሎት ቤት ከብር እና ከእንጨት የተሠራ የመንበር መስቀል
• በሩሲያ፣ አሜሪካ እና በሴኔጋል ኤግዚቢሽን ላይ የቀረበው ‘የመስቀል አበባ’ ስዕል
• “እናት ኢትዮጵያ’
• የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ምስል እና
• ‘ደመራ’ ተጠቃሾች ናቸው ፡፡
እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ማክሰኞ ሚያዝያ 2 ቀን 2004 ዓ/ም በተወለዱ በ79 ዓመታቸው ከዚህ አለም በሞት ተለይተው ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ፣ወዳጅ ዘመዶቻቸውና አድናቂዎቻቸው በተገኙበት አዲስ አበባ በሚገኘው መንበረ ጸባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ቀብራቸው ተፈጽሟል ፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy