Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የዕውነት ሚዛኑን ያዛባው፤ ባለሀብቱ ወይስ ሪፖርት አቅራቢው?

0 391

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

መንግሥት አገሪቱ ወደ ተሻለ ኢኮኖሚ ለመገንባት እየተገበራቸው ከሚገኙ ስልቶች አንዱ የተመቻቸ የኢንቨስትመንት ሁኔታዎችን መፍጠር ነው። እነዚህም ለልማት የሚሆን ቦታዎችን ማመቻቸት፤ መሰረተ ልማቶችን ማሟላትና ከቀረጥ ነፃ ማበረታቻ መስጠት የሚሉት ይጠቀሳሉ። የውጭና የአገር ውስጥ ባለሀብቶችም ይህን ምቹ ሁኔታ ተጠቅመው በመላ አገሪቱ በልማቱ እየተሳተፉ ይገኛሉ። ከእነዚህም ባለሀብቶች መካከል አቶ ፈረጃም ረዳ አንዱ ናቸው። እኝህ ባለሀብት፤ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከአሶሳ ከተማ 17 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ያምባሲዝም ቀበሌ የእርሻ ልማት እያኬዱ ይገኛሉ።

አራት ሚሊዮን 400 ሺ ካፒታል በማስመዝገብ፣ ሶስት ትራክተሮችን በመግዛት እንዲሁም በርካታ ሠራተኞችን በመቅጠር ነው ወደ እርሻ ኢንቨ ስትመንቱ የገቡት። ለእርሻ ልማቱ የተሰጣቸው 558 ሄክታር መሬት ሲሆን፤ የተለያዩ አዝዕርትና የቅባት እህሎች በማልማት አምስት ያህል ዓመታትን አስቆጥረዋል። እስካሁንም እንዲያለሙት ከተሰጣቸው መሬት 480 ያህሉን ሄክታር በማልማት ውጤታማ መሆን ችለዋል። በቆሎ፣ ማሽላ፣ አኩሪ አተር፣ ሰሊጥ፣ ሱፍ የመሳሰሉትን የአዝዕርት አይነቶችን ነው እያመረቱ ያሉት።

እንደ እርሳቸው ሁሉ አቶ ካህሳይ መብራቶም መንጌ ወረዳ ቱንዲፍቱ ቀበሌ ላይ በ2002 .ም ነው ለእርሻ ልማት በተሰጣቸው 60 ያህል ሄክታር መሬት ላይ ነበር ሥራቸውን የተለያዩ የቅባትና የምግብ እህሎችን እያመረቱ ናቸው። «በመሬታችን ላይ እንደ አኩሪ አተር፣ ሰሊጥ፣ ሩዝ የመሳሰሉትን አዝርዕቶች በማልማት ውጤታማ መሆን ችለናል» ነው ያሉት አቶ ካህሳይ።

የቢኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከ1986 .ም ጀምሮ ልክ እንደ አቶ ፈረጃና ካህሳይ ላሉ አንድ ሺ 544 ለሚሆኑ ባለሀብቶች ፍቃድ መሰጠቱን ከክልሉ የህዝብ ግንኙነት ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል። ከእነዚህ ውስጥም በርካቶቹ ወደሥራ ገብተው በማምረት ላይ ናቸው። በዝግጅት ላይ ያሉ ኢንቨስተሮች የዚሁ አካል ናቸው። ወደ ሥራ የገቡት ባለሀብቶች በአመዛኙ በግብርና ልማት ላይ ነው የተሰማሩት። ከሰሞኑ ደግሞ የክልሉ ኢንቨስትመንት ፅህፈት ቤት በክልሉ ወደሥራ ከገቡት ባለሀብቶች ውስጥ፤ የ27ቱን ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፍቃድ ሙሉ ለሙሉ እንደሰረዘ ነው ያስታወቀው።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግሥት የኢንቨስትመንት ፅህፈት ቤት ኃላፊ ተወካይ አቶ ጋሻው ሽሞ እንደገለፁት፤ በ2008 .ም ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በ225 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ላይ በተደረገ ክትትል መሰረት የባለሀብቶቹ የኢንቨስትመንት ፍቃድ ተሰርዟል። «27ቱ ባለሀብቶች በገቡት ውል መሰረት ባለማልማታቸውና ዝቅተኛ አፈፃፀም ያሳዩ በመሆናቸው ፍቃዳቸው ተሰርዟል» ሲሉ ነው ያስረዱት።

የኢንቨስትመንት ፍቃዳቸው ከተሰረዙት 27 ባለሀብቶች መካከልም አንዳንዶቹ፤ የፍቃድ ስረዛው በትክክለኛ መንገድ በተደረገ ጥናትና ግምገማ አይደለም በማለት ቅሬታቸውንና አስተያየታቸውን ለአዲስ ዘመን ሰጥተዋል። ቅሬታ ካቀረቡት ባለሀብቶች መካከል አንዱ በመግቢያችን ላይ የጠቀስናቸው አቶ ፈረጃ ረዳ ይገኙበታል።

አቶ ፈረጃ እንደሚናገሩት፤ ጥር 24 ቀን2009 .ም ከወረዳ የመጡ ሰዎች የሰጧቸው ደብዳቤ የኢንቨስትመንት ፍቃዳቸው ስለመሰረዙ ያብራራል። በምክንያትነት ከተጠቀሱት መካከልም ማልማት የሚገባችሁን ያህል ማልማት ባለመቻላችሁ፣ የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ አለማድረጋችሁ፣ የሠራተኞች ደህንነትና ጥበቃ አናሳ መሆኑ፣ በፕሮጀክቱ ሳቢያ ከመንግሥት የተገኘ ድጋፍን በአግባቡ ያለመጠቀም የሚሉት ይገኝበታል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አካባቢ ጉዳይና መሬት አስተዳደር ቢሮ የገጠር መሬት ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ታደለ ተረፈ፤ ባለፈው በጀት ዓመት በ225 የገጠር ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች እንቅስቃሴ ላይ ግምገማ ማድረጋቸውን ይናገራሉ። ይሄንንም መሰረት በማድረግ የተለያዩ ውሳኔዎችን አስተላልፈናል ነው የሚሉት። በዚሁ መሰረትም አፈፃፀማቸው ወጣ ገባ የሆኑ የ27 ባለሀብቶች ፍቃድ ሊሰረዝ መቻሉንም ነው የገለጹት።

በባለሀብቶቹ ላይ የተደረገው ግምገማም፤ የክልሉ አካባቢ ጥበቃና መሬት አስተዳደር፣ የኢንቨስትመንት ፅህፈት ቤት፣ የግብርና ቢሮ፣ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን፣ የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ፣ የዲያስፖራ ጉዳዮች ተወካዮች የተካተቱበት ቡድን ያካሄደው ጥናት ነው። የግምገማውም ይዘትም ከመንግሥት የተገኘ ማበረታቻ ለታለመለት ዓላማ ስለመዋሉ፣ ከቀረጥ ነፃ የገቡ የካፒታል እቃዎች ጥቅም ላይ የዋሉበት ደረጃ፣ ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ያለው ግንኙነትና የተፈጠረ ተጠቃሚነት፣ የሠራተኞች ደህንነትና ልማት ሥራዎች እንዲሁም ፕሮጀክቶች ከመንግሥት የተገኘ ድጋፍን በአግባቡ የመጠቀም ሁኔታ ላይ መሰረት አድርጓል። እነዚህ ነጥቦች ላይ በማተኮር የኢንቨስትመንት ቦታዎቹ ላይ በመሄድ ለሶስት ወራት የዘለቀ ጥናትና ግምገማ ከተደረገ በኋላ ነው እርምጃው ሊወሰድ የቻለው፤ እንደ አቶ ታደለ ማብራሪያ።

አቶ ፈረጃ ግን በዚህ አይስማሙም። በባለሙያዎቹ ተደረገ ስለተባለው ጥናትም ይሄን ብለዋል፤ « ይከታተለንና ይቆጣጠረን የነበረው የወረዳ ግብርና ቢሮ ነው። ባለሙያዎቹም ስንዘራ፣ ስናርም፣ ስናጭድ፣ ምርት ስናስገባ ይመጣሉ እንጂ ከዚህ የዘለለ ሚና አልነበራቸውም። የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ሰዎችም እየመጡ ይመለከቱናል። ከእነዚህ ውጪ የተመለከተን አካል የለም። እነሱ ያሏቸው ቡድኖች ወደ እኛ አልመጡም። እንግዲህ ሳይመለከቱና እኛ ሥራ ቦታ ሳይመጡ ነው መከታተያ ፎርም ሞልተው ሪፖርት ያቀረቡት» ሲሉ የተቋቋመው ቡድን ያደረገውን ጥናት እንደማይቀበሉት የተናገሩት።

አቶ ካህሳይም የኢንቨስትመንት ፍቃዳችሁ የተሰረዘው በአፈፃፀም ደካማነት፣ የተሰጣችሁን መሬት ለተገቢው አላማ አላዋላችሁም የሚልና መሰል ምክንያቶች ተጠቅሶ ደብዳቤው እንደ ደረሳቸው ተናግረዋል። በወረዳው የኢንቨስትመንት ቢሮ በኩል የደረሰንን የፈቃድ ስረዛ ደብዳቤ ተከትሎ ወደ ቢሮው በማቅናት ለምንድን ነው የሚሰረዘው? ቅድሚያ ለምን ማስጠንቀቂያ አልተሰጠንም? ስንል ጠይቀን ነበር። ይሁንና የተሰጠን ምላሽ ‘ፍቃዳችሁ ተሰርዟል፤ምንም አይነት ማስጠንቀቂያ አይሰጣች ሁም’ የሚል ምላሽ ነበር።

ውሳኔው ግራ እንደሆነባቸው የሚናገሩት አቶ ካህሳይ፤ ሆን ተብሎ ልማቱን እንዳናለማ በግለሰቦች የተውጠነጠነ ድርጊት ሲሉ ኮንነዋል። ይህን ለማለታቸው ምክንያት ያሉትን ነጥብ ወደ ኋላ መለስ ብለው ያስቃኛሉ። «እኛና የክልሉ የኢንቨስ ትመንት ቢሮ በ2000 .ም የኢንቨስት መንቱን ውል ስንዋዋል የተፈቀደልን መሬት 700 ሄክታር ነበር። እኛም ይሄንኑ መሰረት በማድረግ የልማቱን መሬት ጠየቅን። ከሁለት ዓመት ቆይታ በኋላም ያስረከቡን 60 ሄክታሩን መሬት ብቻ ነው። በውላችን የሰፈረው 700 ሄክታር ሆኖ እንዴት ይሄንን ብቻ ይሰጠናል ስንል ለወረዳው የገጠር መሬት አስተዳደር ቅሬታችንን አስገባን።

«በዚህ ሄክታር ላይ እንዴት ልናለማ ነው። ለማልማት ካቀድነው ጋር የሚመጣጠን አይደለም። ካልሆነ ተለዋጭ መሬት ስጡን በማለትም ጥያቄ አቀረብን። በወቅቱ ማንም ሊሰማን አልቻለም። ወደ ክልሉ ኢንቨስትመንት ዕህፈት ቤት ብናመራም የሚሰጠን ምላሽ ተስፋን የሚያኮላሽ እንጂ መፍትሄን የሚሰጥ አልነበረም። ስለዚህ ሁኔታው ከጅምሩ ጀምሮ እንቅፋቶች እንደነበሩና አሁን ደግሞ በሚገባው ደረጃ አላለማችሁም በሚል ፍቃድ መሰረዙ እንዳንሠራ ለማድረግ የተደረገ ደባ ነው» ብለዋል።

የወረዳው የገጠር መሬት አስተዳደርም ሆነ የክልሉ ኢንቨስትመንት ፅህፈት ቤት እርምጃውን ከመውሰዱ አስቀድሞ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷቸው እንደሆነ ለባለሀብቶቹ ጥያቄ አቅርበንላቸው ለማስጠንቀቂያም ሆነ ለግምገማ ብሎ ደጃችንን የረገጠ አካል የለም የሚል ምላሽ ነበር የሰጡት።

አቶ ፈረጃ በተመሳሳይ ክልሉ ግምገማ ማድረጉ ላይ ቅሬታም እንደሌላቸው ይገልፃሉ። ይሁንና ተደረገ የተባለው ጥናትም ሆነ ግምገማ በትክክለኛው መንገድ አለመሆኑ ላይ ነው ጥያቄያቸው። ምክንያቱም ቀደም ሲሉ ጥቅም ፈላጊ ባለሙያዎች ያቀረቡትን ጥያቄ አለመቀበላችን ሰለባ አድርጎናል የሚል እምነት አላቸው። አቶ ፈረጃ ሁኔታውን እንዲህ ያስቀም ጡታል፤ «የተጠየቅነው ነገር አለ። እኛ ደግሞ ለመስጠት ፍላጎት የለንምና እንሰጥም በማለታችን ነው ይሄ ሁሉ የደረሰብን። ጥቃት መሆኑም ሊታወቅ ይገባል» ሲሉ ነው ከእገዳው በስተጀርባ የኪራይ ሰብሳቢነት ጥያቄ ስለመኖሩ የተናገሩት።

የአምስት ዓመቱን የምርት እንቅስቃሴን ባስረጂነት አቅርበውም ፈቃዳቸው መሰረዙ በትክክለኛ ማስረጃ ላይ የተወሰደ አለመሆኑን ይከራከራሉ፤ «እንድናለማ ከተሰጠን 558 ሄክታር መሬት ውስጥ 480 ያህሉን አልምተናል። በዘንድሮ ዓመት ስድስት ሺ ሰባት መቶ ኩንታል አምርተናል። ባለፈው ዓመት ደግሞ ከሶስት ሺ ኩንታል በላይ ምርት አግኝተናል። በ2006 እና 2007 .ም ደግሞ ሁለት ሺ 200 መቶ ኩንታል አምርተናል። ለሠራተኛ ደመወዝ በአግባቡ ከፍለናል። የሚጠበቅብንንም ግብር በአግባቡ እፎይታ ሳንጠይቅ ከፍለናል። የሽያጭ ታክሱም በየዓመቱ ከ56 ሺ እስከ 120 ሺ ብር ነው የምንከፍለው። ለዚህም የከፈልንበት ደረሰኝ በእጃችን ይገኛል። ይህ በሆነበት ሁኔታ እኛን መሸለም ሲገባ እንዴት የኢንቨስትመንት ፍቃዳችሁ ታገደ እንባላለን» ሲሉ ይጠይቃሉ አቶ ፈረጃ።

የገጠር መሬት አስተዳደር ምክትል ቢሮ ኃላፊው አቶ ታደለ በቀረበው የባለሀብቶቹ ቅሬታ አይስማ ሙም፤ «ቅሬታዎቹ መሰረተ ቢስ ናቸው፤ በመረጃ የተጨበጡ አይደሉም። እኛ በዝርዝር ለማየት ሞክረናል። እነኚህ አካላት ለእኛም ሆነ ለመስተዳድርም ቅሬታ አቅርበዋል። ቅሬታቸውን በዝርዝር ስናይ ግን መሰረት የለውም። ይህንን አይነቱን ነገር የሚያራምዱ አካላት መሬቱን በማህበር ከወሰዱ በኋላ በመከፋፈል ለሌሎች አገልግሎቶች ያዋሉ ናቸው» በማለትም ነው የባለሀብቶቹን ወቀሳ ውድቅ ያደረጉት።

የክልሉ ኢንቨስትመንት ፅህፈት ቤት ኃላፊ ተወካይ አቶ ጋሻው፤ እርምጃው የተወሰደው አጥኝ ቡድኑ ባቀረበው ትክክለኛ ሪፖርት መሰረት ነው ይላሉ። ከዚያም በኋላ በቢሮ ደረጃ በአመራሩ ተገምግሞ፣ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ባሉበት ታይቶ ውጤቱ ለኢንቨስትመንት ቦርድ ቀርቦ ነው ውሳኔው የተሰጠው ሲሉም ነው የእርምጃውን ርቱዕነት የገለጹት።

 ዳንኤል ዘነበ

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy