Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ያለ ሰላም ኢንቨስትመንትን የለም

0 360

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ያለ ሰላም ኢንቨስትመንትን የለም  (ዳዊት ምትኩ)

በህገ መንግስቱ በተደነገገው የገበያ መር ኢኮኖሚ ሥርዓትን ተከትሎ የኢንቨስትመንት ፖሊሲ ተነድፎ በሥራ ላይ ውሏል፡፡ በዚህም በኢኮኖሚው ውስጥ የመንግሥት ሚና የተለያዩ የልማት ኃይሎችን በማቀናጀት የመምራት፣ መሠረተ ልማት የማቅረብና የሰው ሃብት ልማትን የማካሄድ እንዲሁም ፈጣንና ውጤታማ የመንግሥት አገልግሎት የመስጠትና የመደገፍ ተግባራት በመከናወን ላይ ይገኛሉ።  ከዚህ በተጨማሪም የኪራይ ሰብሳቢነት ምንጮችን መዝጋት እና በግሉ ሴክተር የማይሰሩ የልማት ሥራዎችን መንግስት ገቢራዊ እንዲያደርጋቸው የሚያስችሉ ሁኔታዎች ተመቻችተዋል፡፡

ባለፉት ሥርዓቶች የወጡና የግሉን ዘርፍ ቀጥተኛ ተሳትፎ የሚገቱ ህጎችና ደንቦች ተወግደው በልማታዊ መስመር ራዕይዎች ተተክተዋል። በዚህም ለውስጥም ሆነ ለውጭ ባለሃብቶች ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል። በዚህም መሰረት በአሁኑ ወቅት ሀገራችን ለኢቨስትመንት የምትመች ሀገር ሆናለች። እርግጥ ለዚህ አባባሌ ከሰሞኑ ስለ ኢትዮጵያ ምቹ የኢንቨስትመንት ሀገርነት መጥቀሱ ተገቢ ይመስለኛል።

ስታንደርድ ሚዲያ የተሰኘው ድረ-ገፅ እስካዛሬ ድረስ ጎረቤት ኬንያ በአበባ ምርት ቀዳሚ እንደነበረች አትቶ፣ በአሁኑ ወቅት ግን ሀገራችን ዋነኛ ተፎካካሪ ሀገር እንደሆነችባቸው የሀገሪቱ የአበባ አምራቾች ምክር ቤት ኃላፊ ዣኔ ኚንጊ ገልፀዋል። ሌላም ላክል።… ኢትዮጵያ የመጓጓዣና ኃይል ማመንጫ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን በማስፋፋቷ ወደ አፍሪካ ለመምጣት የሚሹ የማኑፋክቸሪንግ ኩባንያዎችን መሳብ መቻሏን “ኮንትሮል ሪስክስ” የተሰኘ ዓለም አቀፍ ተቋም ይፋ “ዘ ስታር” የሚባል የኬንያ ጋዜጣ ከመሰንበቻው ይፋ አድርጓል። ሀገራችን በተለይም የቻይናን ኩባንያዎች በመሳብ የሚያበረታታ ተግባር በማከናወን ላይ መሆኗንም ጋዜጣው አትቷል።

ምን ይህ ብቻ! ። “ኢኒሼቲቭ ፎር ግሎባል ዲቭሎፕመንት” የተባለ የቋምም የሀገራችን የቆዳ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ጥራት ያለው የቆዳ ጫማዎች እና ምርቶች በማቅረብ በዓለም ገበያ እየታወቀ መምጣቱን አስታውቋል። በተለይም ሀገራችን ባላት አስተማማኝ የኃይል ምንጭ፣ ተመጣጣኝ የጉልበት ዋጋ እና እያስመዘገበችው ያለው ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ዓለም አቀፍ ኩባንያዎችን እየሳበች መሆኑ ተጠቅሷል።

በተለይም ሀገራችን አስፈላጊውን መሠረተ ልማት በማሟላት እና አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት በማዘጋጀት የተለያዩ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ዝቅተኛ የማምረቻ ወጪ ወደሚጠይቃቸውና ምቹ የኢንቨስትመንት ፖሊሲ ወዳላት ኢትዮጵያ ነቅለው እንዲመጡ እያደረገች ነው። ሌላም…ሌላም መጥቀስ ይቻላል።…ይሁንና ሀገራችን ለምን ለኢንቨስተመንት ተመራጭ እንደሆነች ማውሳቱ ፋይዳው የላቀ በመሆኑ ወደዚያው ማምራት የሚገባ ይመስለኛል።

እንደ እውነቱ ከሆነ ቀደም ሲል የጠቀስኳቸው የሀገራችን ኢንቨስትመንትን የመሳብ ብቃት የመነጨው ከምንም ተነስቶ አይደለም—ካለን የኢንቨስትመንት አረራር ተመራጭነት  የመነጨ እንጂ። እንደሚታወቀው የኢፌዴሪ መንግስት በሀገሪቱ መዋዕለ ንዋያቸውን በማፍሰስ፣ በኢንቨስትመንት ለመሰማራት ፍላጎት ያላቸው የውጭ ባለሃብቶችን ለመሳብ የተለያዩ ማበረታቻዎችን በማመቻቸት በሩን ከፍት በማድረግና በተለያዩ አለም አቀፋዊ መድረኮች ተጨባጭ ሁኔታውን በማስረዳት በርካታ ባለሃብቶችን በመሳብ ላይ ነው፡፡

በዚህም በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች በተለይም በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግና ኢንዱስትሪ ዘርፎች የተሰማሩ የውጭ ባለሀብቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ መምጣት ችሏል፡፡ በዚህም ሳቢያ ቀደም ሲል በምሳሌነት ያነሳኋቸውና ሀገሪቱ ለኢንቨስትመንት ምቹ መሆኗን የተገነዘቡ በርካታ የውጭ ኩባንያዎችና ባለሃብቶች መዋዕለ ንዋያቸውን እያፈሰሱ ነው— በርካታ ዜጎችንም የስራ ባለቤት በማድረግ።

እርግጥ ሀገራችን እየተከተለችው ባለው ምቹ የኢንቨስትመንት ምህዳር ነፃ የመሬት አቅርቦት መዘጋጀቱ፣ የአበባ ማምረቻ ስፍራዎች በመንገድ እና በኤሌክትሪክ እንዲተሳሰሩ መደረጋቸው፣ የታክስ እፎይታ ጊዜ መኖሩ በርካታ የውጭ ባለሃብቶች ወደ ሀገራችን እንዲሳቡ ዋነኛው ምክንያት ሆኗል ማለት ይቻላል። ሀገራችን የምትከተለው የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመር አሁን ለተገኘው የኢንቨስትመንት አመቺነት ምህዳር ወሳኙን ሚና መጫወቱም እንዲሁ።

የኢፌዴሪ መንግስት ሀገሪቱንና ህዝቦቿን ከድህነት ከኋላቀርነት ለማላቀቅ የነደፈው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መስመር ተግባራዊ በማድረግ ተስፋ ሰጪ ዕድገት በማስመዝገብ ላይ እንደሚገኝ የውጪው ዓለምና ባለሃብቶቻቸው ሳይቀሩ እየመሰከሩለት ይገኛሉ። ከመመስከር ባለፈም፤ የሀገራችንን መፃዒ ዕድል ከወዲሁ በአንክሮ አጢነው በኢንቨስትመንት ዘርፍ ለመሳተፍ በልማት እግሮቻቸው ወደ ሀገራቸን እየተመሙ ነው። አዎ! ዛሬ የኢንቨስትመንት መንገዶች ወደ ኢትዮጵያ በማምራት ላይ ይገኛሉ።

እንደ እኔ እምነት በሀገራችን ውስጥ እየደገ የመጣ፣ ተጠቃሚ እንዲሁም መካከለኛ ገቢ ያለው የህዝብ ቁጥር መጨመሩ፣ ፈጣን የከተሞች ዕድገት መታየቱና ሳቢ የኢንቨስትመንት አሰራር መኖሩ ባለሃብቶችን እየሳበ ነው። ከዚህ በተጨማሪም ሀገራችን በምስራቅ አፍሪካ ፈጣን ዕድገት እያስመዘገቡ ካሉ ሀገራት ውስጥ አንዷ ስለሆነችና እያደገ የመጣውን ፍላጎት ለማሟላት አቅም ያላት መሆኗ ባለሃብቶቹ ለሚሳተፉበት የኢንቨስትመንት ዘርፍ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል።

እርግጥ በኢትዮጵያ ፈጣን ኢኮኖሚ ውስጥ የፋይናንስ፣ የቴሌኮም እና የጅምላ ንግድን ጨምሮ ሌሎች ዋና ዋና የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለውጭ ባለሃብቶች የተከለከለ ነው። ይህም የሀገራችን የፋይናንስና ለሌሎች ተቋማት ራሳቸውን እስኪያጎለብቱና በአስተማማኝ ሁኔታ ተወዳዳሪ እስኪሆኑ ድረስ እንዲሁም መንግስት በተመረጠ አኳኋን በልማት ስራው ላይ ስለሚሳተፍ ነው። ይሁንና የውጭ ባለሃብቶች በሲሚንቶ፣ በቡና፣ በወይን እና በብስኩት ማምረት ዘርፎች ውስጥ በመሳተፍ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ መገኘታቸው ሀገራችን የውጭ ባለሃብቶችን የሚያበረታታ አካሄድ እየተከተለች መሆኑን መገንዘብ የሚገባ ይመስለኛል።

የውጭ ባለሃብቶች ሀገራችን ከምትከተለው ፖለቲካል-ኢኮኖሚ ስርዓት አኳያ በመንግስት የተያዙ የምጣኔ ሃብት ዘርፎች ውጪ እንዲሁም በህግ ተደነገጉ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች በስተቀር ኢንቬስተሮቹ ወደ ሀገራችን ገብተው በኢንቨስትመንት ዘርፍ እንዲሳተፉ የተመቻቸ ሁኔታ ተፈጥሯል።

እንደ እውነቱ ከሆነ ሀገራችን ያላት የተረጋጋ ሥርዓት እና ርካሽ የጉልበት ክፍያ እንዲሁም ለባለ ሃብቶች የተዘጋጀው የተሻለ የታክስ ድጎማና የእፎይታ ጊዜ ብሎም በታዋቂው አየር መንገዷ የዓለም ገበያን በቀላሉ ለመድረስ መቻሏ ለኢንቨስትመንት ምቹ እንድትሆን አድርጓታል።

ታዲያ  ይህን ኢንቨስትመንት ምቹ የሆነ የሀገራችንን አካሄድ በአግባቡ መጠቀም ይገባል። ለዚህ ደግሞ አስተማማኝ ሰላም ወሳኝ ነው። ሰላም ከሌለ ስለ ልማት ማሰብ አይቻልም። ስለ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መጎልበትም እንዲሁ። ያለ ሰላም እንኳንስ የውጭ ኢንቬስተሮችን መሳብ ቀርቶ፣ እንደልብ ወጥቶ መግባትም አይቻልም። እናም የሀገራችንን ሰላም አስተማማኝ ማድረግ ከሁሉም ዜጋ የሚጠበቅ ወቅታዊ ተግባር መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy