Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ደሴ «የእግር ኳስ አብዮት» እያካሄደች ነው

0 2,196

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

አቶ ልኡልሰገድ አበራ ይባላሉ። አድሜያቸው በሰባዎቹ ውስጥ ይገኛል። በቀድሞው የወሎ ክፍለ አገር ነው የተወለዱት። እድገታቸውም ቢሆን በደሴ ከተማ ነው። እግር ኳስን ገና ከልጅነታቸው ነው መጫወት የጀመሩት። በወሎ በአገሪቷ እግር ኳስ ላይ ወርቃማ ታሪክ በነበራቸው ክለቦች ውስጥ በተጫዋችነት እና በአሰልጣኝነት ለ29 ዓመታት ቆይተዋል።

አቶ ሉኡልሰገድን ያገኘናቸው የዝግጅት ክፍላችን በደሴ ዙሪያ የእግር ኳስ መዳከም እና አሁን ላይ ማህበረሰቡ የቀድሞውን ድንቅ ታሪክ ለመመለስ በሚያደርገው ጥረት ላይ ሰፋ ያለ ዳሰሳ ለመስራት ጥረት በምናደርግበት ወቅት ነበር። በወጣትነት ዘመናቸው ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተመርጠው አገራቸውን ከወከሉ አንጋፋ ተጫዋቾች ጋር በጋራ በወሎ ክለቦች ውስጥ መሰለፍ ችለዋል። በአሰልጣኝነትም ቢሆን ጥሩ ደረጃ ላይ የደረሱ ልጆችን ማፍራት ችለዋል።

ሙሉጌታ ከበደን ፣ ብርሀኑ ተክለ ዮሀንስ፣ አዳሙ አለሙን ከመሳሰሉ አንጋፋ ተጫዋቾች ጋር አብረው የመሰለፍ እድል ያገኙት እኒህ ባለታሪክ ደሴ ውስጥ ስለነበረው የያኔው የእግር ኳስ መነቃቃት እና አሁን ስለተፈጠረው መቀዛቀዝ ይናገራሉ። መቀዛቀዙ የፈጠረው ቁጭት ደግሞ እግር ኳሱ በድጋሚ እንዲያንሰራራ ዕድል ይከፍታል ሲሉ የተፈጠረው ሁኔታ ለእግር ኳሱ ዳግም ትንሳኤ መሆኑን ያብራራሉ።

«ተወዳጁ የእግር ኳስ ስፖርት በአሁን ሰዓት ከፍተኛ የገቢ ምንጭ እና የኢኮኖሚ አቅም መፍጠሪያ በሆነበት ወቅት በአገሪቷ በተለይም በደሴ ከተማ ላይ ደካማ እንቅስቃሴ መኖሩ የሚያስቆጭ ነው» በማለት የሚናገሩት እኒህ አንጋፋ የእግር ኳስ ባለታሪክ ቀደም ባሉት ጊዜያት የነበረው ከፍተኛ የእግር ኳስ ፍቅር እና ዕድገት ቀጥሎ ቢሆን ኖሮ ስፖርቱ ሌሎች አገሮች የደረሱበት ደረጃ ላይ ማድረስ ይቻል እንደ ነበር ይገልፃሉ።

የደሴ ከተማ እግር ኳስ ስፖርት ካለፉት ሁለት እና ሶስት አስርት ዓመታት በፊት ከሌሎች የአገሪቷ አካባቢዎች በተለየ መልኩ ቀዳሚ ስፍራ የነበረው እና ስፖርቱም በማህበረሰቡ ዘንድ እጅግ ተወዳጅነት እና ተቀባይነት ያለው ነበር። ህብረተሰቡ አሁንም ድረስ ለእግር ኳስ ስፖርት ያለው ፍቅር ከፍተኛ ቢሆንም እድገቱ ግን ለበርካታ ጊዜያት አዝጋሚ ሆኖ ቆይቷል።

አቶ ቴዎድሮስ ታደሰ በደሴ ከተማ ነዋሪና የደሴ እግር ኳስ መዳከም እንደማንኛውም ዜጋ የሚቆጫቸው ናቸው። ሆኖም ግን በሁኔታው በመብሰልሰል ብቻ እጃቸውን አጣጥፈው አልተቀመጡም። በደሴ ከተማ ስፖርት ቦርድ ውስጥ በአመራርነት በመሳተፍ የተዳከመውን እግር ኳስ በድጋሚ ወደ ወርቃማ ዘመኑ ለመመለስ የድርሻቸውን እየተወጡ ይገኛሉ። አሁን በመላው የደሴ ነዋሪ የተፈጠረውን ቁጭትም በማስተባበር ከፍተኛ ሥራ እየሰሩ ናቸው። እኒህ እግር ኳስ ወዳድ ስለ ቀድሞው ታሪክ እና አሁን እየተደረገ ስላለው እንቅስቃሴ ይናገራሉ።

ደሴ በርካታ እግር ኳስ ተጫዋቾችን ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ማበርከት ችላለች። በከተማዋ ይገኝ የነበረው እና «የወሎ ምርጥ» በመባል የሚታወቀው የቡድን ስብስብ በእግር ኳስ ችሎታቸው ተደናቂ የሆኑ ተጫዋቾችን ማፍራት ችሎ ነበር። የወሎ ፔፕሲ ክለብም እንደዚሁ አስተዋፅኦው ከፍተኛ ነበር። በወሎ ክፍለ አገር የተወለደ እና ለኢትዮጵያ ወጣት ቡድን፣ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ፣ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አምበል ሆኖ የተጫወተ ድንቅ ተጫዋች ሙሉጌታ ከበደን ማንሳት ተገቢ ነው። ከዚህም ሌላ በቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ ጥሩ ትዝታ ያለው ብርሀኑ ፈየራን፣ በአጨዋወት ክህሎቱ የሚደነቀው ዮናታን በትረ፣ መሀመድ እንድሪስ በጊዜው እግር ኳስ ደሴ ላይ የደረሰበትን ደረጃ አመላካች ነበሩ። በአሰልጣኝም ቢሆን እንደነ ተስፋዬ ባልቻ ያሉ እግር ኳስን ጠንቅቀው የሚያውቁ ባለሙያዎችን አፍርታለች።

ከሶስተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ጀምሮ ደሴ እና አካባቢው በተለይ «የወሎ ምርጥ» በነበረበት ጊዜ ለእግር ኳሱ ዕድገት የራሳቸው ጉልህ ድርሻ የነበራቸው ተጫዋቾችን ማፍራት ተችሎ ነበር። የደሴ ነዋሪም ስፖርት ወዳድ በተለይም ለእግር ኳስ ልዩ ፍቅር ያለው ህብረተሰብ ነው። ህዝቡ ከስፖርት ወዳድነቱ ባሻገር በጥሩ ስነ ምግባር የሚታወቅ ደጋፊ ጭምር ነው። በጣም የሚያስደንቀው ደግሞ ደጋፊው በዚያን ጊዜ በርቀት የሚደረጉ ጨዋታዎችን የሚከታተለው በስልክ እና ከሰው በሚያገኘው መረጃ ነበር። ምክንያቱም ዘመናዊ የግንኙነት መሳሪያ የሆኑት ቴሌቪዥን እና ሬዲዮን በቀላሉ ለማግኘት ይቸገር ነበር። የከተማዋ ተጫዋቾች በድል ሲመለሱ ወጣቱ ከአካባቢው ሰላሳ እና አርባ ኪሎ ሜትሮችን በመሄድ አቀባበል ያደርግላቸው ነበር።

በደርግ ዘመነ መንግሥት በተለይ በ1970ዎቹ አካባቢ ዘመኑ የሚፈቅደውን ቴክኖሎጂ በመጠቀም በደሴ ከተማ የመጀመሪያው ስታዲዮም ተሰርቷል። ከዚያ በፊት በአዲስ አበባ፣ ድሬዳዋ እና በአስመራ ከተማ ነበር ስታዲዮም የነበረው። ከዚያ በመቀጠል ከሌሎቹ ክፍለ አገራት በተለየ መልኩ ለደሴ ትኩረት ተሰጥቶ የስታዲዮም ግንባታ ተካሂዷል። ይህ እንዲሆን የተፈለገበት ዋነኛ ምክንያት ደግሞ የደሴ ከተማ እግር ኳስ ስፖርት የሚወደድበት እና በርካታ እንቁ ተጫዋቾች ከከተማዋ የሚገኙበት በመሆኑ ነበር።

1976 .ም ኢትዮጵያ እና የቀድሞዋ ሶቪዬት ሶሻሊስት ሪፐብሊክ የእጅ ኳስ እና የመረብ ኳስ ጨዋታ በደሴ ከተማ አድርገዋል። ደሴ በዋናነት የተመረጠችበት ምክንያት ማህበረሰቡ ያለው የስፖርት ፍቅር እና የእግር ኳሱ በከተማዋ የነበረው ዕድገት ነበር።

በከተማዋ በርካታ የእግር ኳስ ከለቦች ነበሩ። ከፍተኛ አንድ፣ሁለት እንዲሁም ሶስት፣ ዋሊያ፣መብረቅ፣ወሎ ፔፕሲ፣ ከነማ፣ ኮምቦልቻ ጨርቃ ጨርቅ እንዲሁም ሌሎች ክለቦች ነበሩ። ከዚህም ሌላ በወቅቱ በየቀበሌ እና በወረዳው ውስጥ ቡድኖችን በመመስረት ውድድሮች ይደረጉ ነበር። ከቀድሞው የእግር ኳስ እንቅስቃሴ የተሻለ ባይሆንም አሁንም ድረስ እግር ኳስን በቡድን የሚጫወቱ እና በፕሮጀክት ታቅፈው የሚንቀሳቀሱ ክለቦች አሉ።

የእግር ኳስ መቀዛቀዝ

የደሴ ከተማ ስፖርት ቦርድ አመራር የሆኑት አቶ ቴዎድሮስ ከሶስት አስር ዓመታት በፊት የነበረው ወርቃማ የእግር ኳስ ታሪክ ለበርካታ ጊዜያት ተቀዛቅዞ መቆየቱንም ይናገራሉ። ከተማዋ እና አጠቃላይ የወሎ ክፍለ አገር በስፖርቱ የተነቃቃ ዘመን ያሳለፈ ቢሆንም አሁን ግን ያለበት ደረጃ የሚያኩራራ አይደለም። ሆኖም ስፖርቱ በከተማዋ ላይ የነበረውን ተቀባይነት እና ወርቃማ ዘመን በድጋሚ ለመመለስ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረገ ይገኛል። ለመሆኑ ለእግር ኳስ ስፖርት በተለየ መልኩ በከተማዋ የተዳከመበት ምክንያት ምን ይሆን?

እግር ኳስ በቀደሙት ዘመናት እድገቱ በጣም ከፍተኛ ነበር የሚል ድምዳሜ ላይ የሚያስደርስ ባይሆንም፤ አሁን ካለው በጣም በተሻለ መልኩ ጥሩ እንቅስቃሴ እንደነበረው መካድ አይቻልም የሚሉት አቶ ቴዎድሮስ ይህም ማለት በዋናነት እንደ ደሴ ከተማ ብቻ ሳይሆን አገሪቷ ላይ ስፖርቱ መፋዘዙን የሚያመላክቱ መነሻዎች መኖራቸውን ይናገራሉ።

ለስፖርቱ መዳከም በርካታ ምክንያቶችን የሚያነሱት አቶ ቴዎድሮስ የስርዓት ለውጥ ይዞት የመጣው አዲስ ሂደት ለስፖርቱ መዳከም የራሱን ድርሻ እንደሚወስድ፤ መንግሥት ከእግር ኳስ ውጪ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ የተለዩ ስራዎች ላይ ትኩረት በማድረግ ዘርፉን እረስቶት እንደነበር፤ ሌላኛው ምክንያት ደግሞ የህብረተሰቡ ግፊት ማነስ እንደሆነ ያብራራሉ።

በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ለስፖርቱ መዳከም ቀጥተኛ ተጠያቂ ቢኖርም ሁሉም ህብረተሰብ እግር ኳስ በተለይም በደሴ ከተማ ሲቀዛቀዝ አስቀድሞ ርብርብ ማድረግ ነበረበት። ተገቢውን ግፊት በቶሎ አለማድረጉ ስፖርቱ በድጋሚ ለማንሰራራት ጊዜ እንዲወስድ ዕድሉን ሊከፍት ችሏል። በዚህም በበርካታ የስፖርት ክለቦች ሲወከል እና ምርጥ ተጫዋቾችን ለብሄራዊ ቡድን ሲያስመርጥ የነበረው ከተማ መቀዛቀዝ ታይቶበታል።

የደቡብ ወሎ ዞንን የሚወክለው የደሴ ከነማ እግር ኳስ ክለብ በብሄራዊ ሊግ ውድድር ነው እየተሳተፈ የሚገኘው። ምንም እንኳን መዘግየት ቢታይበትም ይህን ክለብ በሱፐር ሊግ እና በዋናው ፕሪሚየር ሊግ በማሳተፍ እንዲሁም አጠቃላይ ስፖርቱን ወደ ነበረበት ገናና ታሪክ በድጋሚ ለመመለስ ስራዎች እየተሰሩ ናቸው። በቁጭት የሚሰሩ የስፖርቱ ቤተሰቦችም ተፈጥረዋል።

ደሴና የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ

እኒህ የስፖርት ቦርድ አመራር በማዘውተሪያ ስፍራ ላይ ያለውንም ቸግሮች በማንሳት ህብረተሰቡን በማስተባበርም በዚህ ዙሪያ መሰራት ያለባቸውን ስራዎች ለማከናወን ጅምር እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን ያስረዳሉ።

በቀደምት ጊዜያት በከተማዋ ካለው ሆጤ ስታዲዮም ውጪ ታዳጊዎች እና ወጣቶች እግር ኳስን በመጫወት ጊዜያቸውን የሚያሳልፉበት እንዲሁም ልምምድ የሚያደርጉበት ሜዳዎች ነበሩ። በየአካባቢው የመጫወቻ ሜዳዎች ላይ እግር ኳስን የሚጫወቱ ስፖርተኞች መመልከት ባለፉት ወርቃማ ዘመናት አዲስ አልነበረም።

ሆኖም ግን በተለያየ ጊዜ የከተማዋ የማስተር ፕላን ለውጥ ሲካሄድ እነዚህ የማዘውተሪያ ስፍራዎች ለሌላ አገልግሎት እንዲውሉ ተደርገዋል። በሜዳዎቹ የሚገነቡት ህንፃዎች እና የተለያዩ የኮንስትራክሽን ስራዎች ለልማት እንዲውሉ ታስበው የተሰሩ ቢሆንም፤ለወጣቱ እና ለስፖርት መለማመጃ ይውሉ የነበሩ ስፍራዎች ለሌላ አገልግሎት መዋላቸው ተገቢ እንዳልሆነ ይገልፃሉ።

ከልማት እኩል ለስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ትኩረት ሊሰጥ ይገባል። ከህክምና፣ የመኖሪያ ቤት፣ኢንዱስትሪ ስፍራዎች ባልተናነሰ የማዘውተሪያ ቦታ የመኖሩ አስፈላጊነት አጠያያቂ አይደለም። በተለይ በደሴ ከተማ ለማዘውተሪያ ስፍራ የተሰጠው ግምት እና በአስተዳደሩ በኩል ያለው አመለካከት አነስተኛ መሆኑን የሚገልፁት አቶ ቴዎድሮስ የስፖርት ስፍራዎችን መገንባቱ ቀርቶ የነበሩትንም የቀድሞ ማዘውተሪያዎችን ጠብቆ የማቆየት ችግር በስፋት ይስተዋላል፤ በዚህ የተነሳም መልካም ስም እና ወርቃማ ታሪክ የነበረው የደሴ እግር ኳስ ስፖርት አሁን በጣም ተቀዛቅዟል፤ ዘግይቶም ቢሆን ከፍተኛ ቁጭት ፈጥሯል እንጂ ጭርሱኑ ተዳፍኖ አልቀረም ይላሉ።

ቁጭት የፈጠረው መነቃቃት

አቶ ቴዎድሮስ ከተማዋ ስለ ነበራት የእግር ኳስ ታሪክ እየተረኩ ብቻ መኖር ተገቢ አለመሆኑን ፤ ይልቁንም ቀድሞ የነበረው ወርቃማ ትውልድ አሁን ላይ አለመኖሩ ቁጭትን እንጂ መዳከምን እንዳልፈጠረ ይገልፃሉ። በመላው ህብረተሰብ ርብርብ አሁን ያለውን የስፖርት ክለብ በመደገፍ ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎች ምን እንደሁኑም ሲገልፁ፡

እንደ ጅምር ከተማዋን የሚወክለው የደሴ ከነማ እግር ኳስ ክለብን ለማነቃቃቀት ብሎም በሚፈለገው ደረጃ ለማሳደግ ጥረቶች እየተደረጉ ነው። ክለቡ ካምፕ እንዲኖረው ተደርጓል። ከዚህም ባለፈ በተደራጀ ሁኔታ እንዲተዳደር ቡድኑ በቦርድ ነው የሚመራው። የከተማ አስተዳደሩም ለክለቡ ከፍተኛ ገንዘብ በማውጣት ዘመናዊ አውቶብስ አበርክቶለታል። አንጋፋ ተጫዋቾችም በየክፍለ ከተማው እንዲሁም በተለያየ አደረጃጀት ቡድኖችን እንዲይዙ እየተደረገ ነው። ይህ ደግሞ ተተኪ ተጫዋቾችን ለማፍራት ትልቅ እድል ይፈጥራል።

ከተማዋን በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሚወክል ክለብ እንዲኖራት ማህበረሰቡ እና የሚመለከተው ሁሉ በሙሉ አቅሙ እየሰራ ይገኛል። ከዚህም ሌላ ቡድኑን ሁሉም ህብረተሰብ እንዲደግፈው እና የአስተሳሰብ ለውጥ እንዲያመጣ የሚያስችል ስራም ጎን ለጎን እየተከናወነ ነው። ከዚህም ውስጥ የተለያዩ የውይይት መድረኮችን እና ዝግጅቶችን በማሰናዳት ህብረተሰቡ ማድረግ ያለበትን ሁሉ እንዲያደርግ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ። ከዚህም ሌላ የፊታችን ግንቦት 4 የሚጀመር አገር አቀፍ አውደ ርእይ እና ባዛር በደሴ ከተማ ይደረጋል። አውደ ርእዩ ሙሉ በሙሉ አላማው የደሴ ስፖርትን ለማነቃቃት ታስቦ የሚዘጋጅ ነው። ከዚህ በሚገኘው ገቢም ክለቡን በኢኮኖሚ ይደግፋል።

በአሁኑ ሰዓት በደሴ ከተማ የስፖርት አብዮት እየተካሄደ ነው ማለት ይቻላል። አሁን ያለውን ሁኔታ በየተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያዎች ብቻ መለወጥ አንደማይቻልም በመገንዘብ ህጋዊ ሰውነት ያለው የደሴ ከነማ እግር ኳስ ክለብ ደጋፊዎች ማህበር ተቋቁሟል።

ዘመናዊ ስታዲዮም ግንባታ

በደሴ ስፖርት እድገት ላይ ያገባናል ያሉ ሁሉ ችግሮቹን ለማስወገድ እና አዲስ ዘመን ለመፈንጠቅ የተነሱ ይመስላል። ስፖርቱ እንዳያድግ እንቅፋት ፈጥረው ነበር ካሏቸው ችግሮች መካከል የማዘውተሪያ ስፍራ አንዱ ነው። ትላልቅ አገር አቀፍ እና አለም አቀፍ ጨዋታዎች የሚያስተናግድ ስታዲዮምም ደሴ ትፈልጋለች። ለዚህ ደግሞ መፍትሄ አለን ሲሉ የንቅናቄው አስተባባሪዎቹ ይናገራሉ።

እግር ኳሱን ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት ላይ የስፖርት የመሰረተ ልማት ግንባታ እንቅስቃሴውንም አብሮ ለማስኬድ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው። አሁን ያለው መነቃቃት ከተማዋን የዘመናዊ ስታዲየም ባለቤት ለማድረግ ትልቅ ዕድል የከፈተ ነው። በተደረገው ውይይት ዘመናዊ ስታዲዮም ለመገንባት ሁሉም ህብረተሰብ ተሳታፊ ለመሆን ፍቃደኝነቱን አሳይቷል። የእግር ኳስ ቤተሰቡ የማንንም እጅ ሳይገባበት እኛው እራሳችን «ዘመናዊ ስታዲዮም እንገነባለን» ሲል አቋሙን ለዚሁ ሲባል በተሰናዱ ውይይቶች ላይ እየገለፀ ይገኛል።

በቅርቡ በሼክ ሙሀመድ ሁሴን አሊ አል – አሙዲ አማካኝነት ከተገነባው ዘመናዊና ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በተጨማሪ «ወሎ አለም አቀፍ ስታዲዮም» የሚል መጠሪያ የተሰጠው የእግር ኳስ ሜዳ ለመገንባት ጅምር እንቅስቃሴዎች አሉ። በዚህ ስታዲዮም ግንባታ ላይ በመላው ዓለም የሚገኙ የወሎ ተወላጆች ተሳታፊ እንዲሆኑ ዕድሎች ተመቻችቷል። ከዚህም ሌላ ያለፈው ወርቃማ ታሪክ የኛም ታሪክ ነው በማለት ቁጭት ያደረባቸው የኢትዮጵያ ልጆች ሁሉ ተሳታፊ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል። ግንባታው የሚደረግበት ቦታም ከወዲሁ መረጣ እየተካሄደ ነው። የተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ ስልቶች ተግባራዊ በማድረግ በህዝቡ አቅም ብቻ ዓላማውን ከግብ ለማድረስ ከፍተኛ ተነሳሽነት ተፈጥሯል።

የዝግጅት ክፍላችን በደሴ እግር ኳስ ታሪክ ላይ መሰረት አድርጎ አሁን ላይ ያለውን ሁኔታ ለመዳሰስ ጥረት አድርጓል። ከዚህ መረዳት የቻልነውም የአካባቢው ተወላጆች እንዲሁም በከተማዋ ያሉ ነዋሪዎች ስፖርቱን ለማሳደግ ተነሳሽነት ማሳየታቸውን ነው። እንደዚህ አይነት ርብርብ በእርግጥም ለውጥ የማምጣት አቅም እንዳለው እሙን ነው። ነገር ግን ይህ እንቅስቃሴ ግለቱን ጠብቆ መሄድ እና ተግባራዊ መደረግ ይኖርበታል፡፡

 ዳግም ከበደ

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy