Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ድርቅ የፈተነው ‹‹ለጋ ፖለቲካ››

0 693

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ከዓመታት በኋላ በሶማሊያ ሰማይ ላይ የደመቀችው የመረጋጋት ፀሐይ ዳግም ማዘቅዘቅ እንዳትጀምር የሚሉ ስጋቶች እየተንጸባረቁ ነው፡፡ ከሦስት ወር በፊት ዘጠነኛው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት በመሆን የተመረጡት ሞሐመድ አብዱላሂ (ፋርማጆ)፤ ለዓመታት በቀውስ ውስጥ የቆየች አገራቸውን ለማስተዳደር ዕድል ሲያገኙ ለሶማሊያውያን አዲስ ተስፋ ሆነው ነበር፡፡ ለዓመታት የአገሪቱን አለመረጋጋት ተከትሎ ‹‹አገሬ በቃሽኝ!›› ብለው በምሬት የተሰደዱ ዜጎች ሳይቀሩ በአዲሱ የፖለቲካ ለውጥ በወጡበት ድንበር መመለስም ጀምረው ነበር፡፡

አልጀዚራ በቅርቡ እንደዘገበው በፕሬዚዳንት ሞሐመድ መንግስት ምስረታ ማግስት ከአምሳ ሺ የማያንሱ ሶማሊያውያን ወደ አገራቸው ተመልሰዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱም በዓለም ዙሪያ ስደት መገለጫው የሆነውን የሶማሊያ ሕዝብ ወደ ሰላም ጎዳና ለመምራት ብዙ ተስፋ ሰንቀዋል፡፡ በእርግጥ በስልጣን ዘመናቸው ጅማሬ ፈተና ይሆናል ተብሎ የተጠበቀው አካባቢውን መሸሸጊያ ያደረገውን የሽብር ቡድን የአልሸባብን መረብ መበጣጠስ ነበር፡፡

ይሁንና ‹‹የጠበቅነው ሌላ፤ የሆነው ሌላ›› እንዲሉ፤ የአልሸባብ ሽብር ቡድን ስጋትነቱ እየቀነሰ ቢመጣም የተፈጥሮ መዛባት ከሰላም ማጣት ጋር ተዳምሮ በአገሪቱ የተከሰተው አስከፊ ረሃብ በአካባቢው ታላቅ ቀውስ አስከትሏል፡፡ በዚህም ምክንያት የአዲሱ ፕሬዚዳንት በዓለ ሲመት በድጋፍ ጥያቄ የተሞላ እንዲሆን አድርጓል፡፡ ፕሬዚዳንቱ በተመረጡ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ‹‹የሶማሊያን ሕዝብ እርዱ›› በማለት ለአለም አቀፉ ማሕበረሰብ የድጋፍ ጥሪ አድርገዋል፡፡

በቅርቡም የብሪታኒያው ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን በአገሪቱ እንዲሁም በቀጣናው በነበራቸው ቆይታ የሶማሊያ ረሃብ አለም አቀፍ ትኩረት እንደሚያስፈልገው አሳስበው ነበር፡፡ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩን ጉብኝት ተከትሎም እንግሊዝ 110 ሚሊዮን ፓውንድ ለሶማሊያ ድጋፍ አድርጋለች፡፡ አለም አቀፍ የረድኤት ድርጅቶች ባለስልጣናትም በአገሪቱ በመገኘት ችግሩ ይበልጥ ትኩረት እንዲያገኝ አሳስበዋል፡፡ ጥሪውን ተከትሎም የተለያዩ ወገኖች ለሶማሊያ ድጋፋቸውን ማድረግ ጀምረዋል፡፡

ወትሮም ቢሆን በአካባቢው የሰላም አየር እንዲነፍስ የማይሻው አልሸባብ በተደቀነው ችግር ተከልሎ አጋጣሚውን የመጠቀም ፍላጎት እንደሚኖረው ይገመታል፡፡ ምክንያቱም የሽብር ቡድኑ በአፍሪካ ሕብረት የሶማሊያ ልዑክ (አሚሶም) ጦር በተሰነዘረበት ተደጋጋሚ ጥቃት በመዳከሙ ዳግም ለማንሰራራት እንዲህ ያለውን ክፉ አጋጣሚ መጠቀሚያ ሊያደርገው ይችላል፡፡ ከሳምንት በፊት በዋና ከተማዋ ሞቃዲሾ ያደረሰው ጥቃትም የዚህ ፍላጎቱ ማሳያ ከመሆኑ ባሻገር ጥቃቱ የአልሸባብን አስከፊነትና ፀረሰብዓዊነት ድርጊት የሚያሳይ ሴራ ነው፡፡

በተሸከርካሪ ላይ የተጠመደው ቦምብ ከፕሬዚዳንቱ ቤተ መንግስት አጠገብ ፈንድቶ ለአምስት ሰዎች መሞት ምክንያት ሆኗል፡፡ የሽብር ቡድኑም ከጥቃቱ በኋላ በድረ ገጹ ኃላፊነቱን እንደሚወስድ አስታውቋል፡፡ የመንግስትን የደህንነት ኃይሎች ላይ ያነጣጠረው ጥቃት የሽብር ቡድኑ አሁንም የአልሞት ባይ ተጋዳይነት መፍጨርጨሩን ያሳያል፡፡ ነገር ግን አከርካሪው የተሰበረው የሽብር ቡድን ዳግም ለማንሰራራት እንዳይችል የሚያደርጉትን ተጨማሪ እርምጃዎች መውሰድ ተገቢ መሆኑን ብዙዎች ይስማማሉ። በቅርቡ ወደ ስፍራው ያቀናው የአፍሪካ ሕብረት አንድ ቡድንም የሶማሊያን አዲስ መንግስት እየተፈታተኑ የሚገኙ ሁለት ጉዳዮች በማስመልከት ከአገሪቱ መንግስት ጋር ውይይት አድርጓል፡፡ 24 አባላትን ያካተተው የሕብረቱ የሰላምና ደህንነት ምክር ቤት በአገሪቱ እየታዩ የመጡትን ለውጦች ጎብኝቷል፡፡ አሚሶም በድረ ገፁ እንዳስነበበው ልዑኩ በአንድ በኩል የአገሪቱን ዘላቂ ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ የሚገነባውን ብሔራዊ ጦር በተመለከተ መክሯል፡፡

የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀሰን አሊ ኬይሬ የአሚሶምን የእስከዛሬ አስተዋፅኦ በማድነቅ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ አዲሱ መንግስትም ዘላቂ ሰላም ከማረጋገጥ አንፃር የሚፈለገውን ግብ ለመምታት የሁለት ዓመት የጊዜ ቀጠሮ ማስቀመጡን አስታውሰዋል፡፡ ሕብረቱም በአሚሶም በኩል የሰላም ማስፈን ስራውን እንደተወጣው ሁሉ አሁን ያጋጠመውን ድርቅም በጋራ የመከላከል ስራ እንደሚወጣው እምነታቸው ሆኗል፡፡

የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚገልጹት የሕብረቱ ተግባር ከአሚሶም የእስካሁን ተልዕኮ ባሻገር በዘላቂነት አገሪቱ በአዲሱ አስተዳደሯ ራሷን የምትከላከልበትን አቅጣጫ የሚያመላክት ይሆናል፡፡ ምክንያቱም በአገሪቱ የአልሸባብ ተፅዕኖ በግልፅ እየተዳከመ መጥቷል፡፡ የአፍሪካ ሂውማኒተሪያን አክሽን ምክትል ፕሬዚዳንት የሆኑትና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሚያስተምሩት የፖለቲካ ምሁር ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርኸተስፋ፤ አልሸባብ በተወሰዱበት ተደጋጋሚ እርምጃዎች በመዳከሙ በአሁኑ ወቅት ከግዛት ማስተዳደር ወደ ፅንፈኝነት የማጥቃት ሂደት መሸጋገሩን ይገልጻሉ፡፡

በመሆኑም ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት መንግስት አልባ የነበረችውን ሶማሊያ የማረጋጋት ሂደቱ አገሪቱ የራሷን መንግስት እስከመመስረት አድርሷታል፡፡ በአገሪቱ ጠንካራ ብሔራዊ ጦር የመገንባት ጉዞ የሚጀምረውም ጠንካራ የፖለቲካ መዋቅርን ከመዘርጋት መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ የአዲሱ መንግስት ቀዳሚ ስራ አሁን የተደቀነውን የረሃብ አደጋ ከመከላከል ጎን ለጎን የአገሪቱን ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ ህግ አውጪውና አስፈፃሚውን በሚገባ ማጠናከር ይጠይቃል፡፡

ለአገሪቱ ዘላቂ ሰላም የሕብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ ነው፡፡ ይሄን በተመለከተ ‹‹አገር ሁልጊዜ በፖሊስና በወታደር እየተጠበቀ አይኖርም›› የሚሉት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፤ በየአካባቢው የሚፈጠሩ ግጭቶችን ለማጥፋት በየአካባቢው የሚገኙ መሪዎችን ሚና ማሳደግ ያስፈልጋል፡፡ ሰላም ያለሕዝቡ ንቁ ተሳትፎ ይረጋገጣል ማለት የዋህነት ነው፡፡

የተጠቀሱት የመንግስት ፖለቲካ መዋቅሮች በአገሪቱ ባለመጠናከራቸው አሁንም ፕሬዚዳንቶች የሚመረጡት በጎሳ መሪዎች መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ በእርግጥም አሁን ካለው ሁኔታ በመነሳት ምርጫውን ለማካሄድ ያለው አማራጭ ይሄ ብቻ ቢሆንም በቀጣይ ግን ከመንግስት መዋቅር ማጠናከር ባሻገር የአገሪቱን ገዢ ሕግ (ሕገ መንግስት) ጨምሮ የተለያዩ ደንቦችን ማዘጋጀት ወሳኝ ነው፡፡ በመሆኑም ይላሉ፤ ለሶማሊያ የሚያስፈልገው ድጋፍ በአፍሪካ ሕብረት ብቻ የሚመለስ አይደለም፡፡ ይልቁኑም የአገሪቱ ሕዝብ ‹‹ሰላምን እንፈልጋለን›› በሚል አልሸባብን ሙሉ በሙሉ የመደምሰሱን ስራ የተሳካ ማድረግ ይገባቸዋል፡፡

እንዲህ አይነቱ የሰላም ፍላጎት ከሕዝቡ ሲመጣ በአግባቡ መመለስ የሚቻለው የሚመረጡት የአገሪቱ ባለስልጣናት ስልጣናቸውን በአግባቡ ለሕዝብ ጥቅም ማዋል ሲችሉ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም የነበሩት የአገሪቱ መሪዎች ላይ የሚስተዋለው ችግር ሙስና እንደነበር የሚገልጹት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፤ ለአገሪቱ የፀጥታ ችግር መባባስ ምክንያት የሆኑትም እነዚሁ የቀድሞ አመራሮች መሆናቸውን ይጠቅሳሉ፡፡

በመሆኑም አዲሱ አስተዳደር በሚያደራጀው መንግስት ላይ ለሌላ ችግር የሚያጋልጡ ሙሰኛ አመራሮችን ቀድሞ መለየት ይጠበቅበታል፡፡ በአገሪቱ ለፅንፈኛ ሴራው የሕዝቡን ልብ ለመግዛት የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርግ የቆየው አልሸባብን በአቅም ከማዳከም ጎን ለጎን በወጣቱ ላይ የአስተሳሰብ ለውጥ መፍጠርም የአዲሱ መንግስት የቤት ስራ ሆኗል፡፡ ሶማሊያም ሆነች የቀጣናው አገሮች የሽብር ቡድኑን ተፅዕኖ እያዳከሙ ቢመጡም የሶማሊያ ወቅታዊ ችግር ረሃብ ሆኗል፡፡

የአፍሪካ ሕብረት ድርቁን መመልከት ያለበት በከፍተኛ ሁኔታ ነው፡፡ ምክንያቱም እንደዚህ አይነት የተፈጥሮ አደጋዎች ከሕዝቦች አልፎ የመንግስት ስርዓትን እስከማፈናቀል እንደሚደርስ ምሑሩ ይናገራሉ፡፡ በመሆኑም ሕብረቱ በተለይ በአህጉሩ ከፍተኛ ኢኮኖሚ የሚያንቀሳቅሱ አገሮችን ተጠቅሞ የፋይናንስ አቅሙን በማጠናከር እንዲህ ያሉትን የተፈጥሮ አደጋዎች መመከት መቻል አለበት፡፡ ከዚህ ባሻገር የአካባቢው አገሮችም ይሄን ድርቅ ተቋቁሞ የማለፍ ጥረትን መደገፍ እንደሚኖርባቸው ይገልጻሉ፡፡ ምክንያቱም በቀጣናው የትኛውም ስኬት የጋራ፤ ማንኛውም ስጋትም የሁሉም መሆኑ በግልፅ የሚታይ ነውና፡፡

በቀጣናው ከሶማሊያ የቅርብ ጎረቤቶች ኢትዮጵያ ቀዳሚዋ ነች፡፡ በመሆኑም ድርቁን መከላከል የጋራ የቤት ስራ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ኢትዮጵያ ከምትከተለው የውጪ ፖሊሲ ባሻገር በቀጣናው ባላት ሚና ምክንያት ማናቸውንም ጉዳዮች በትኩረት ነቅታ የምትከታተለው ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በአካባቢው ያጋጠመው የረሃብ አደጋም ለመከላከልም የጋራ ጥረት ይፈልጋል፡፡ ይሄን በአግባቡ የምትረዳው ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት አልሻባብን ከሶማሊያ የመጠራረግ ተልዕኮ ላይ የተወጣችውን ሚና ድርቅን በመከላከሉም ድርሻዋ የጎላ ነው፡፡

የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አቶ ተወልደ ሙሉጌታ ይሄን ያረጋግጣሉ፡፡ በተጎራባች ክልሎች የተፈጠረውን ተመሳሳይ የድርቅ አደጋ በመከላከል በኩል ኢትዮጵያ የተለያዩ እርምጃዎችን ወስዳለች፤ እየወሰደችም ትገኛለች ይላሉ፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት አልሸባብን በማዳከም በኩል በተለይ በአሚሶም ላይ ያላት አተዋጽኦ አዲስ ከተመረጠው የሶማሊያ መንግስት ጋር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ይገልጻሉ፡፡ አልሸባብን ማጥፋት በቅድሚያ ለሶማሊያ ሕዝብ ወሳኝ ቢሆንም ለቀጠናውም ከፍተኛ ትርጉም ይኖረዋል፡፡ ከፀጥታው ባሻገር አሁን በቀጣናው ያጋጠመውን ድርቅ ለመከላከልም በጋራ መስራቱ ይቀጥላል፡፡ አዲሱን የሶማሊያ መንግስት በማጠናከር በኩል በተለይ በፀጥታው ረገድ የአገራት ድጋፍ ወሳኝ ነው፡፡

ከመንግስት ምስረታው በተጨማሪ ተቋማትን የማጠናከሩ ስራ ወሳኝ ነው በሚለው የምሁራን ምክረ ሃሳብ የሚስማሙት አቶ ተወልደ፤ በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ የፀጥታውን ኃይል በስልጠናና በተለያዩ ድጋፎች አብራ ከመስራት ባሻገር ተቋማቱን በማጠናከር በኩል የበኩሏን ስልጠናና የልምድ ልውውጥ ታደርጋለች፡፡ በቅድሚያ ግን ለቀጣናው አዲስ ስጋት ለሶማሊያም ተጨማሪ ፈተና የሆነውን ድርቅ መከላከል ቀዳሚ አጀንዳ ሆኗል

ብሩክ በርሄ

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy