Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ጉዞ ወደ አባገዳ ምድር

0 1,049

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የገዳ ስርዓት ምንጭ ብቻ አይደሉም፤ ይልቁንም ዛሬም ድረስ የኦሮሞን ባህል  ጠብቀው ማቆየት መቻላቸው መላያቸው ነው፤ ቦረናዎች። ዘንድሮ ግን ፈታኝ ጉዳይ ገጠማቸው፤ ቦረና እና ጉጂ በድርቅ ተጎብኝተዋል። ሊሸጡአቸው የሚሳሱላቸው፣ ከልጆቻቸው ለይተው የማያዩአቸው ከብቶቻቸው ዓይናቸው እያየ ሲሞቱም ተመልክተዋል። በዚህም ክፉኛ አዝነዋል። መንግስት እያደረገላቸው ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ይጠይቃሉ፣ ቦረናና የቦረና ምድር።

በቦረናና አከባቢው የተከሰተው ድርቅ ምን ጉዳት እንዳስከተለ፣ እንዴትስ ችግሩን ለማቃለል ድጋፍ እየተደረገ እንደሆነ ለማወቅ የጋዜጠኞች ቡድን የካቲት 21 ቀን 2009 ማልዶ ተነሳ። ቡድኑን ወደ ስፍራው እንዲያመራና በመንግስትና ረድኤት ድርጅቶች በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች እየተደረገ ያለው ድጋፍ ምን ገፅታ እንዳለው እንዲዘግብ የጋበዘው የኦሮሚያ ክልል ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ነው።

ቡድኑ የቪዲዮ  ካሜራና መቅረጸ ድምፁን  ታጥቆ በዕለቱ ከጠዋቱ አንድ ሰዓት  አዲስ አበባን በመልቀቅ በፈጣኑ የአዳማ መንገድ ይምዘገዘግ ጀመረ። ፀሃይ ሳትበረታ ፈጣን መንገዱን በፍጥነት ለማለፍ የሚከንፈው ሾፌራችን የተሽከርካሪውን ፊት ወደ ደቡብ አቅጣጫ አዙሮ መሃል ለመሃል ተሰባብሮ እየተጠገነ ያለውን የሞጆ – ሀዋሳ መንገድ ተያያዘው፤ መዳረሻችን ሀዋሳ እስኪሆን ድረስ ፍጥነቱ እንደቀጠለ ነበር።

‘’ከባድ መንገድ ይጠብቀናል፤ ቶሎ ምግብ  በልተን እንውጣ’’ ተባብለን ከደቡቧ ምድር ሀዋሳ ለምሳ ቆይታ አደረግን። ከጥቂት ቆይታ በኋላ  ሀዋሳን ለቀን እንደወጣን፣ የመጣንበትን የፍጥነት መንገድ እያሰብን የሚያንገራግጨውን  የጠጠር መንገድ ጀመርን፤ መንገራገጩ አቦስቶ የሚባለው ትልቅ የፍተሻ ኬላ እስክንደርስ ድረስ ቀጥሏል።

ወደ አካባቢው ስሄድ የመጀመሪያዬ ነበርና ”እንዴ ይሄ መንገድ እኮ ለም፣ ብዙ ሃብት ያለበት፣ ትልቅ ኢኮኖሚ የሚያንቀሳቅሱ አከባቢዎችን የሚያስተሳስር፣ ከዚያም አልፎ ወደ ጎረቤታችን ኬኒያ ጭምር የሚዘልቅ  ነው። እንዴት ፒስታ ሊሆን ቻለ?” ስል ጠየቅኩኝ።

”አይ ፒስታ” ”ገና መች አየህ” አሉኝ፣ አብረውኝ እየተጓዙ ያሉ ጋዜጠኞች።  የመጀመሪያው የስራ ጉዞአችን ጉጂ በመሆኑ ወደ ቦረና ከሚወስደው  የተበላሸ መንገድ ለአፍታ ተለያየን። ለካ ወደ ነጌሌ  የሚዘልቀው መንገድ አስፋልት  ነበር።

ሆኖም ጉዞው ሲጨምር መንገዱም መለዋወጡን ቀጠለ።  የስራ ጓደኞቼ መንገዱ አርጅቶ በመቆፋፈሩ፣ በጣምም አስቸጋሪ መንገድ እንደሆነ ነገሩኝ። የሚያሳዝነው ግን መንገዱን የማደስ ስራ ከተጀመረ  ዓመታት ማለፋቸው ነው።  የምንጓዝበት ተሽከርካሪ እየከነፈ፣  እኛም የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮችን እያነሳን፣ በጉዟችን  ላይ የምናየውንም በካሜራችን እየወሰድን ፣ አለታ ወንዶ፣ አገረ ሰላምና ሌሎች የደቡብ ክልል ከተሞችን አቋርጠን መዳረሻችን ወደ ሆነችው ኦሮሚያ ክልል የጉጂ ዞን አዋሳኝ   ገባን።

ጉጂ ዞን ከገባን  በኋላም ቢሆን  ስንደመምበት በነበረው አረንጓዴ ውበት ግራና ቀኝ ታጅበን ነበር። ጭራሽ ሌሎች አካባቢዎች ያላየናቸው ለየት ያሉ ዛፎችንም ማየት ጀመርን። ይህን ጊዜ ግራ ተጋባሁ። ድርቅ አለ የተባልነው ጉጂ ሆኖ እንዴት አረንጓዴ ውበት? ስል ራሴን ጠየቅኩ። ”ነው ወይስ ጉጂ አልደረስንም?” አልኩ።

ጉዟችን ቀጥሎ ቦሬ ከተማ የሚል ታፔላ ተመለከትኩ።  እውነት ነው  ጉጂ ደርሰናል አልኩኝ – ለራሴ። ምክንያቱም ቦሬን በስሟ አውቃታለሁ። ለዘገባ እየሄድኩ ያለሁት ይህቺ ከተማ ወዳለችበት  ጉጂ ነው።

ጉጂ የገዳ ስርዓት የሚካሄድባት፣ አባ ገዳዎች በየስምንት ዓመቱ ስልጣን የሚረካከቡበት፣ የተከበረው ”የሚዔ ቦኮ አረንጓዴ ሜዳ”፣ ከዚያም አልፎ ጥቅጥቅ ያለው የአንፈራ ጫካ ያለባት ናት፤ እና በጉጂ ታሪካዊነት ተመስጬ  ፎቶ በማንሳትና ቪድዮ በመቅረጽ ተጠመድኩ።…

መንገዳችን ቀጥሏል፤ አዶላ ከተማን አለፍን፡፡ ወደ ነጌሌ የሚወስደውን መንገድ ተያይዘነዋል። እኔም ፎቶ ማንሳትና ቪዲዮ መቅረጼን ተያይዥዋለሁ። በካሜራዬ ወስጥ እያየው ለውጥ አስተዋልኩኝ፣ አረንጓዴው መሬት እየጠፋ፣ ቅጠላቸው የረገፈ ዛፎች፣ የተሰነጣጠቀና ውሃ የተጠማ መሬት ይታየኝ፣ ይከታተለኝም ጀመር። ይህን ጊዜ ውስጤ የተፈጠረው አረንጓዴ ቀለም እየጠፋብኝ መጣ።

የተጎሳቆሉ ግመሎች፣ አካላቸው የተጎዳ ፍየሎች፣ በተለይ ደግሞ እግራቸውን አንስተው  መራመድ የተሳናቸው የቦረና ከብቶችን የመንገዱ ግራና ቀኝ ያሳየን ጀመር። ድርቅ በከብቶቹ በርትቷል። ሃራ ቀሎና ወዳራ የሚባሉትን ከተሞች እያለፍን ወደ ነጌሌ እየተጠጋን ስንሄድ ጭራሽ መንገድ ዳር የሞቱ ከብቶች ይታዩን ጀመር። ሀዘኔ በረታ። ምስል መያዛችንን አላቆምንም። አሁን ችግሩ ምን ያህል የበረታ እንደሆነ ማሳየት ግድ አለን። ተሽከርካሪያችንን አቁመን ሁኔታውን ይበልጥ እንታዘብ ጀመር።

ለአባ ገዳዎቹ ቦረና እና ጉጂ ምድር ኩራትና ክብራቸው የሆኑ፣ ገበያ እንኳን አውጥቶ በገንዘብ ለመለወጥ የሚሳሱላቸው፣ ስንት ዘመን ”ዳሌ ሎን ቦረና” /የቦረና ዳለቻ ከብት/ እየተባለ የተዘፈነላቸው፣  የከብቶቹ ሥጋ አዲስ አበባን ያስደመሙ፣  ኢትዮጵያንም በቀንድ ከብት ከአፍሪካ አንደኛ ያስባሉ የቦረና ሰንጋና ከብቶች እንደ ቀልድ መንገድ ዳር ወድቀው ተመለከትኩ።

እዚያው ሳለን  እድሜው  15 ዓመት የሚሆን ታዳጊ  አጥንታቸው ወጣ ወጣ ያሉ ጎስቋላ ከብቶች እየነዳ መጣ። ተጠግቼው ስለሞቱት ከብቶች እንዲነግረኝ ጠየቅኩት፣ ”የነ ጣርሮ ናቸው” አለኝ የእነ ጣርሮን ሰፈር  በእጁ ጣቶች እየጠቆመኝ። ”የኛም አንድ ሁለት ሞቶብናል ግን የነሱ ብዙ ከበቶች ናቸው ያለቁት” አለኝ። ቀጠል አድርጎም ”ከብቶቹ አሁን ምንም የሚበሉት ነገር የላቸውም፣ ውሃም በጣም ረዥም መንገድ ተጉዘን ፈልገን ነው የምናጠጣቸው፣ ከባድ ነው” አለኝ። በልጁ ገለፃ እያዘንን ጉዟችንን ቀጠልን።…ነገሌም ገባን። ለሁለት ቀናት እዚያው ከትመን የተለያዩ ወረዳዎች ላይ እየተንቀሳቀስን ቅኝት ስናደረግ ቆየን። በቆይታችን የተረዳነው አንዱ ነገር ድርቁ እንስሳትን በተለይ ደግሞ ከብቶችን በጣም የጎዳ መሆኑን ነው።

በመንግስት በኩል ለመኖ የሚሆን ሳር እየቀረበ ነው ቢባልም እኔ በቆየሁበት የአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ አንድም ቦታ የተከመረ ወይም እየተከፋፈለ ያለ ሳር አላየሁም። የጠየቅኳቸው አርብቶ አደሮችም  በወር አንድ እስር ሳር ለአንድ ቤተሰብ እንደሚሰጥ፣ ነገር ግን ሳሩ ካላቸው የከብት ብዛት አኳያ እንኳን ለወር ለሳምንትም ስለማይበቃ ከብቶቻቸው እየሞቱባቸው መሆኑን ነው ያወጉኝ። የቀሩትንም ለማዳን ተስፋቸው እየተሟጠጠ መሆኑን ነው የገለጹልኝ።

መንግስት ለዚያ ሁሉ ከብት የሚበቃ ሳር ማቅረብ ስለማይችል አርብቶ አደሩ የሚከፋፈለውን  መኖ ለጥቂት ከብቶቹ ብቻ እየሰጠ ዘራቸው እንዳይጠፋ ቢያደርግ ጥሩ ነው የሚል ነገርም ከዞኑ የስራ ሃላፊዎች ሰምቻለው። እኔ ግን ለከብቶቻቸው ያላቸውን ልዩ ፍቅር እያሰብኩ ”እንዴት ነው አንዱ ከብት እንዲሞት ተፈርዶበት ሌላውን እያበላህ አቆይ  የሚባላው፣ ሌላ መፍትሄ ጠፍቶ ነው ወይ” ብዬ እራሴን ጠየቅኩ። መፍትሄ ከጠፋ የቦረና ከብት ዘር እንዲቀጥል ያንን ማድረግ ግድ ይላቸው ይሆናል ብዬም አሰብኩ።

በዞኑ  በነበረኝ ቆይታ፣ ለድርቅ ተጎጂዎች መንግስት የሚያደርገውን የምግብና የመጠጥ ውሃ ድጋፍ ተመልክቻለሁ። ተረጂዎችም “ስለሚደርግላቸው ድጋፍ ትልቅ ምስጋና አለን” ይላሉ። ይህም ሆኖ “እጥረት መኖሩን መንግስት ይወቅልን” ሲሉ መልዕክታቸውን አክለው ነበር።

በቆይታዬ  ቀልቤን የሳቡና ”ለካ እንደዚህም ማድረግ ብዙ ችግር ያቃልላል” ካሰኙኝ ነገሮች ህዝብ ለህዝብ የሚያደርገው የምግብና የከብት መኖ ድጋፍ ነው። የነጌሌ ነዋሪዎች በርካታ ተሽከርካሪዎችን አከታትለው የሰው ምግብና የከብት መኖ ጭነው የጉሚ ኤልደሎ ወረዳ ነዋሪዎችን በተወካዮቻቸው በኩል ”ችግራችሁ ችግራችን ነውና አይዞአችሁ፣ ከጎናችሁ ነን” ሲሉ በስፍራው ተግኝቼ ስሰማ ደስ አለኝ። ወገን ለወገን ደራሽ ነው ማለትም ይሄ ነው።

“እንዴት ናት? ይች ነገር” ብዬ በመጠጋት እንዱን የወረዳ የስራ ሃላፊ ሳነጋግር ”ይሄ ብቻ አይደለም” አለኝ፣ “ተመሳሳይ ድጋፍ ድርቅ ካልነካቸው አከባቢዎች ለሌሎች አምስት ወረዳዎች ሲደረግ ነበር” ብለውኛል። የመንግስት ሰራተኞችም የቻሉ ሙሉ የወር ደመወዛቸውን ያልቻሉ ደግሞ በመቶኛ እያሰሉ ነው አሉኝ። ይህን በጎ ተግባር  በሁለቱም ዞን  ተመልክቻለሁ። ታዲያ ይሄ ሁሉም አካባቢ ቢለመድ፣ በራስ አቅም ማለት ይሄ አይደለምን?

ሌላው ቀልቤን የሳበው ነገርና በሁለቱም ዞን ላይ የተመለከትኩት ሰናይ ነገር፣ በዚያ የበረሃ መሬት ፣ በክረምቱ ወቅት የታቆረውን ውሃ እና የከርሰ ምድር ውሃን በመጠቀም የተለያዩ አትክልትና ፍራፍሬ ያመረቱ ነበሩ። እነዚህ በዚህ ክፉ ጊዜ የቤተሰባቸውን ህይወት መደጎም እንደሌሎቹ አልከበዳቸውም። በእርግጥ ቁጥራቸው ትንሽ ነው። ቢሆንም ይቻላል ብሎ ለማውራትና ለማሰብ ምሳሌዎች ናቸው ነው የምለው።

በዞኖቹ ገናሌና ደዋ የመሳሰሉ ትላልቅ ወንዞችን ጨምሮ ሁለት፣ ሶስት ሜትር ቢቆፈር የሚወጣ የከርሰ ምድር ውሃ አለ፣ ክረምት ሲፈስ የሚቆየውን የዝናብ ውሃም አቁሮ ማቆየት እኮ በአገሪቷ እየተለመደ መጥቷል። ስለዚህ የሰውም፣ የከብትም ምግብ ማምረት ይቻላል ማለት ነው። ”ከተሰራበት” ።…

የሁለት ቀን ቆይታችንን ጨርሰን ወደ ቦረና ዞን ያቀናነው ከቀትር በኋላ ነበር። ወደ አዶላ ተመልሰን ነው በሻኪሶ አድርገን ወደ ቡሌሆራ፣ ከዚያም ያቤሎ ቀጥለን ደግሞ ሞያሌ ለመድረስ ያሰብነው። ከአዶላ እንደወጣን በጣም ከባድ ኮሮኮንች ወይም በተለምዶ ፒስታ መንገድ አጋጠመን። የሚገርማችሁ  አፈር ምድሩ ወርቅ የሆነበት፣ ሚድሮክን የሚያክል ግዙፍ ኩባንያ ወርቅ የሚዝቅበት፣ ሻኪሶን ከአዶላና ቡሌሆራ ጋር የሚያገናኘው ይህ መንገድ እንዲህ አይነት ደረጃ ያለው መሆኑ ነው። ለዚች መንገድ አሁን ሚድሮክ እራሱ አይበቃም?

የሆነው ሆነና ከአንድ ቀን ተኩል ጉዞ በኋላ ቀጣይ መዳረሻችን ወደ ሆነው ቦረና ዞን አቀናን። ለጉብኝት በተመረጡልን ወረዳዎችም ደርሰን ተዘዋውረን ተመለከትን። እዚያም ድርቁ ትንሽ ከፋ ይላል። ሁሉንም ወረዳዎች ነው ያዳረሰው፣ የከብቶች ሞትም ከጉጂው የከፋ ይመስላል። የዞኑ ሃላፊ ሲናገሩ እንደሰማሁት ብዙ ከብቶች ሞተው፣ የቀሩት ደግሞ ወደ ሌላ አካባቢ ተሰደው አንድም ከብት የሌለበት ወረዳ ጭምር አለ።…

ሚዮ የሚባል ወረዳ ላይ የገብያ ቀን ስለደረስን የከብቶች ገበያ የመጎብኘት እድሉ ነበረኝ። አርብቶ አደሩ ድርቁ የተጫጫናቸውን፣ አንገታቸውን እንኳን ቀና አድርገው መቆም ያቃታቸው፣ ካላቸው ከብቶች ግን የተሻሉ የሚላቸውን ገበያ አምጥቶ ነበር።

ቃለመጠየቅ ያደረግኩላቸው አርብቶ አደሮች፣ ”ገበያ የለም”  ”ገዥ ነጋዴ የለም” ”ይዘን ወደ ቤታችን እንዳንመለስ ይሞቱብናል፣ የሚገዛን ደግሞ የለም” “መንግስት አንድ ሊለን ይገባል” የሚል የእሮሮ ድምጽ ያሰማሉ።

መንግስት ለሰዎች እያደረገ ያለውን የምግብ፣ የመጠጥ ውሃና የተጨማሪ ምግብ እርዳታም ተመልክቻለሁ። እዚህ ግን ለከብቶች የሚቀርበው መኖ ይቀርባል ሲባል ሰማው እንጂ አላየሁም።

በዞኑ ተማሪዎች በድርቁ ምክንያት ትምህርታቸውን እያቋረጡ ነው ሲባልም ሰምቼ ስለነበረ፣ በሞያሌ ወረዳ  ከነዋሪዎቹ አንዳንዶቹን  ጠጋ ብዬ ለማነጋገር ሞክሬ ነበር። “አዎ እኔ ራሴ አቋርጬ ለዕለት ጉርስ የቀን ስራ እየሰራሁ ነው። አብረን ስንማር ከነበሩ ተማሪዎች ከግማሽ በላይ የሚሆኑት አሁን አይማሩም” የሚል አጋጥሞኛል። እንዲሁም “ሶስት ልጆቼ ትምህርት አቋርጠው ቤት ቁጭ ብለዋል” የሚሉ እናትም አጋጥመውኝ ነበር። አስደንጋጭ ነው።

ይህን ከሰማሁ በኋላ ትምህርት ሚኒስቴር “ተማሪዎች በድርቁ ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው እንዳይቀሩ ለዞኑ ብቻ 25 ሚሊዮን ብር መድቦ የምገባ ፕሮግራም አስጀምሯል” የሚል  መልካም ዜና ሰማሁ። ችግሩም ይፈታል፣ ከትምህርት የቀሩትም ወደ “ትምህርት ቤት ይመጣሉ” ብዬ አስባለሁ።

የተያዘልን ጊዜ እያለቀ ስለሆነ ፊታችንን ወደ አዲስ አበባ አዙረን መንገድ ላይ ያሉትን አንዳንድ ወረዳዎች እየጎበኝን ለመመለስ በማለዳ ከሞያሌ ስንወጣ ያየሁት የተሽከርካሪ አደጋ ግን በጣም አስደንጋጭ ነበር። ይህ ገጠመኝ ስራችንን ከጋዜጠኝነት ወደ ነብስ አድን የህክምና ባለሙያነት የቀየረው ነበር። ከፊታችን ከተፈቀደለት ፍጥነት በላይ  ሲከንፍ የነበረ የህዝብ ማመላለሻ ቅጥቅጥ ተሽከርካሪ አንድ ሞተረኛ አድናለሁ ብሎ ያሳፈረውን  ህዝብ እንደያዘ ተገለበጠ።

በቅርብ የነበርነው እኛ ስለሆንን ደርሰን ሰዎችን ለማትረፍ እያወጣን፣ በያዝነው ተሽከርካሪ ወደ ሞያሌ ሆስፒታል ስናመላልስ ቆየን። በርካታ ሰዎች ክፉኛ ቆስለዋል፤ ደግነቱ በቦታው የሞተ ሰው አልነበረም።

የተሽከረካሪው ፍጥነት ጉዳይ እንደተጠበቀ ሆኖ “በርካታ እቃ አናቱ ላይ የጫነ መሆኑ መሰለኝ በቀላሉ እንዲወድቅ ያደረገው” ልል አሰብኩና የትራፊክ ባለሙያ ስላልሆንኩ ግምቴን ተውኩት። አንድ ነገር ግን በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። ድርቅን ለመቋቋም የሚያስችል አቅም ፈጥረን ተፈጥሮን እየታገልነው ነው። ታዲያ ልንቆጣጠረው በምንችለው  በሰው ሰራሹ ተሽከርካሪ አደጋ ለምን እንሙት? አብዱራዛቅ ጂማ (ኢዜአ)

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy