ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከትናንት በስቲያ ቅዳሜ ምሽት ቆሼ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በተከተሰው የቆሻሻ መደርመስ አደጋ በደረሰው ጉዳት ጥልቅ ሀዘን እንደተሰማቸው ገልፀዋል።
በአደጋው ህይወታቸውን ላጡ ሰዎች ወዳጅ ዘመዶችም መፅናናትን መመኘታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤትም በዚህ አደጋ ህይወታቸውን ላጡ ዜጎችን የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን ገልጾ ለቤተሰቦቻቸው መጽናናትን ተመኝቷል።
በተያያዘ በቆሻሻ መደርመስ አደጋው ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር 50 መድረሱ ተገልጿል።
የእነዚህ ዜጎች የቀብር ስነ ስርአትም ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት እና ወዳጅ ዘመዶቻቸው በተገኙበት ዛሬ ከስአት በኋላ ይፈፀማል።
በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸው 37 ሰዎች በአለርት ሆስፒታል የህክምና እርዳታ ተደርጎላቸው መሸኘታቸው ተጠቁሟል።
የአደጋው ሰለባዎችን የማፈላለጉ ስራ አሁንም ተጠናክሮ ቀጥሏል።
የአዲስ አበባ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሀላፊ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ፥ በአደጋው ተጎጂ ለሆኑ ሰዎች እንደ ምግብ እና መጠለያ ያሉ መሰረታዊ ፍላጎቶችን የሚያቀርብ ራሱን የቻለ አደረጃጀት ተቋቁሞ እየሰራ መሆኑን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል።
በቀጣይ ለተመሳሳይ አደጋ ተጋላጭ ይሆናሉ የተባሉ 300 ዜጎችም በጊዜያዊ መጠለያ እንዲያርፉ ተደርጓል ነው ያሉት።
በአደጋው ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች መንግስት እያደረገ ካለው ድጋፍ ባሻገር የአካባቢው ነዋሪዎች ያሳዩት አጋርነትም የሚደነቅ ነው ብለዋል።