Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ጥልቅ ተሃድሶውን በማጠናከር ጉዞው ይቀጥላል

0 328

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች በጀመሩት አዲስ የህዳሴ ጉዞ ውስጥ ገዥው ፓርቲ የመሪነት ሚና ተጫውቷል። የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) የመሠረቱት ደግሞ የየራሳቸው ታሪክ ያላቸው ብሔራዊ ድርጅቶች ናቸው።

ከእነዚህ ድርጅቶች መካከል ደግሞ የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) አንዱ ነው። ድርጅቱ ከተመሠረተ እነሆ 27 ዓመታትን በትግልና በድል እየተጓዘ እዚህ ደርሷል።

የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽሕፈት ቤት ኃላፊና የግንባሩ ሥራ አስፈፃሚ አባል አቶ በከር ሻሌ የድርጅቱን የምስረታ በዓል አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል። «የድርጅቱ በዓል ሲከበር መላው የኦሮሞ ህዝብና መሪ ድርጅቱ ብሎም እንደሀገር የተጀመረውን ጥልቅ ተሃድሶ ይበልጥ በማጠናከርና ለህዝቡም ተጨባጭ ውጤቶችን በማሳየት ላይ በመመስረት ነው» ሲሉ በአፅንኦት ገልጸዋል።

ኦህዴድ ከተለያዩ የፖለቲካ ትግሎች በኋላ በይፋ የተመሠረተው በሰሜን ሸዋ ደራ አካባቢ በ1982 ዓ.ም ነው። እንደ ሌሎቹ እህት ድርጅቶቹ (ህወሓትና ብአዴን) ሁሉ ጥቂት ቆራጥ ታጋዮችን አቅፎ ወደትግል የገባው ኃይል ከሌሎች ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ጋር ተቀናጅቶ ለድል በቅቷል። ሀገሪቱን በጭቆና እየገዛ ወደብትና ሲወስዳት የነበረው የደርግ ስርዓትንም ለመገርሰስ በቅቷል።

ኦህዴድ ከደርግ ውድቀት በኋላም በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ግንባታ ላይ ግንባር ቀደም ሚናውን እየተጫወተ ነው። በአንድ በኩል መላው የኦሮሞ ህዝብም ሆነ የኢትዮጵያ ህዝቦች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብታቸው፤ የእኩል ተጠቃሚና ተሳታፊነት ዕደላቸው እንዲረጋገጥ ማድረግ ችሏል።ህገ መንግሥታዊ ዋስትና እንዲኖረውም ታግሏል።

በሌላ በኩል የሚመራው ክልል በሰላም፣በልማትና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እንዲጠቀም በብርቱ ታግሏል። በተለይ አንዳንድ ፀረ ሠላም ኃይሎች የክልሉን ህዝብ መጠቀሚያ በማድረግ የጠባብነት አስተሳሰብን ሲያቀነቅኑ ምልዐተ ህዝቡን ባሳተፈ መንገድ ተፋልሟቸዋል። የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነትና ህብረብሔራዊ አንድነት የመገንባት ፍላጎቱ እንዲጎመራም ሠርቷል።

ክልሉም ሆነ ሀገራችን ለተያያዙት የፈጣን ዕድገትና የብልጽግና ጉዞ የመሪ ድርጅቱ ሚናም የጎላ ነበር። በተለይ በአመራሩ፣ አባሉና ምልዓተ ህዝቡ ተሳትፎ ድልን ከመጎናፀፍ ባለፈ ለመጭው ጊዜ መደላድልም መፈጠር ችሏል።

ኦህዴድና የኦሮሞ ህዝብ በድል እየተጓዙም ቢሆን ፈተና ማጋጠሙ ግን አልቀረም። አንደኛው አሁንም ጠባብና ፀረ ሠላም ኃይሎች በህጋዊው የህዝብ ጥያቄ ውስጥ ሰርገው እየገቡ ለማተራመስ የሚያደርጉት ጥረት አለመክሰሙ ነው።

ይህ አስተሳሰብ ምቹ ሁኔታ የሚያገኘው ደግሞ በድርጅቱ ውስጥ የውስጠ ዴሞክራሲ ትግል ሲዳከም ነው። ሥልጣንን አለአግባብ መጠቀም፣ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር ማቆጥቆጥም የተዛባው አስተሳሰብ ቦታ እንዲያገኝ ያደርጉታል።

በዓሉ የሚከበረው «በጥልቅ ተሃድሶው ሂደቱ የተገባ ቃል እንፈፅማለን» በሚል ነው። ለዚህም ነው ኦህዴድና መላው የእህት ድርጅቶች ጥልቅ ተሃድሶ በማድረግ ስር ነቀል ለውጥ ለማምጣት እየተረባረቡ የሚገኙት።

ከዚህ አንፃር የኦህዴድ የምስረታ በዓል ከፌስቲቫልና ልዩ ልዩ ሥነስርዓቶችም ባለፈ በየደረጃው የተጀመረውን ተሃድሶ ግቦች ለማሳካት በመነሳሳት መከበር አለበት። መሪ ድርጅቱና የክልሉ መንግሥት ልማት፣ መልካም አስተዳደርና ዴሞክራሲን ለማስፈን፣ ለወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር፣ ልዩ ልዩ ህዝባዊ ልማቶችን በማከናወን የነዋሪውን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የጀመሩት ርብርብ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት።

ሥልጣንን አለአግባብ በመጠቀም በተለይ የኪራይ ሰብሳቢነትና የሙስና ተግባርን በመታገል ረገድ የጀመረ ብርቱ ሥራም ከዳር ሊደርስ ይገባዋል። ይህ ሲሆን ነው ኦህዴድ ከክልሉም አልፎ በሀገር ግንባታው ረገድም እያደረገ ያለውን ብርቱ ተጋድሎ አጠናክሮ መቀጠል የሚችለው። ለኦሮሞ ህዝብ የገባውንም ቃል በፅናት እየተገበረ የሚቀጥለው። ethpress

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy