Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ፓርቲዎች በቀጣይ የክርክርና የድርድር መድረክ የአደራዳሪ ጉዳይ ላይ ሳይስማሙ በቀጠሮ ተለያይተዋል

0 301

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

22ቱ ሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች በቀጣይ የክርክር እና የድርድር መድረክ የአደራዳሪ ጉዳይ ላይ ሳይስማሙ በቀጠሮ ተለያይተዋል።

ፓርቲዎቹ ዛሬ ባካሄዱት ውይይት ከዚህ በኋላ በሚካሄዱ ድርድሮች ላይ ሶስተኛ ወገን አደራዳሪ ይኑር አይኑር በሚለው ጉዳይ ላይ ለመወሰን ነበር የተገናኙት።

በውይይቱ ሁሉም ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ድርድሩ በገለልተኛ እና ነጻ አደራዳሪዎች ይመራ የሚል ሀሳብ እቅርበዋል።

ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ድርድሩ በፖለቲካ ፓርቲዎች በዙር ይመራ የሚል ሀሳብ በማቅረብ፤ ከሶስተኛ ወገን የሚመጣ አደራዳሪ አያስፈልግም የሚል አቋሙን አንጸባርቋል።

ፓርቲዎቹ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ስድስት ሰዓታትን የፈጀ የሃሳብ ልውውጥ ያካሄዱ ሲሆን፥ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ወገን ድርድር ያለ አደራዳሪ ሊካሄድ አይችልም የሚል ሀሳብ ቀርቧል።

ኢህአዴግ ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች ራሳቸው በዙር ድርድሩን መምራት ይችላሉ፤ አደራዳሪው ለተናጋሪዎች እድል ከመስጠት ያለፈ ሚና ስለማይኖረው አስፈላጊነቱ አይታይም የሚል መከራከሪያ ሀሳብ ሰንዝሯል።

ፓርቲዎቹ በአደራዳሪዎች ሚና ላይ ለመደራደር የቀረበውን ሀሳብም የአደራዳሪ መኖር አለመኖር ሳይወሰን አይገባም በማለታቸው ይህ ነጥብም በይደር እንዲቆይ ተወስኗል።

በመጨረሻም ሁሉም ፓርቲዎች በሶስተኛ ወገን አደራዳሪ መኖር አለመኖር ዙሪያ ውሳኔ ለማሳለፍ መጋቢት 20 2009 ዓ.ም ለመገናኘት ቀጠሮ ይዘው ተለያይተዋል።

በውይይቱ ላይ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ ብቻዬን ከኢህአዴግ ጋር መደራደር ወይም በዋና ተደራዳሪነት መቅረብ እፈልጋለው የሚል ሀሳብ አቅርቦ ከሌሎች ፓርቲዎች ተቃውሞ ገጥሞታል።

የመድረክ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ፥ የፓርቲውን አቋም ብቻዬን መቀየር አልችልም በማለታቸው ፓርቲው በዚህ ጉዳይ ላይ እንዲያስብበት ከሌሎች ፓርቲዎች የቀረበውን ሀሳብ ተቀብለዋል።

ፓርቲዎቹ በቀጣይ የክርክር እና የድርድር አካሄድ ስነ ስርዓት ረቂቅ ደንብን እንደሚያፀድቁም ይጠበቃል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy