NEWS

ለሁሉም የፓርላማ አባላት ታብሌት ኮምፒዩተሮች ተገዙ

By Admin

March 31, 2017

የወረቀት ሰነዶች ሥርጭትና የኅትመት ወጪን በመቀነስ ዘመናዊ አሠራርን ተግባራዊ ለማድረግ ፕሮግራም የቀረፀው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት፣ ለምክር ቤቱ አባላት በሙሉ ታብሌት ኮምፒዩተሮችን ገዝቶ አከፋፈለ፡፡

ማክሰኞ መጋቢት 19 ቀን 2009 ዓ.ም. መደበኛ ስብሰባውን ባካሄደበት ወቅት የተገኙ የምክር ቤቱ አባላት አብዛኞቹ ታብሌት ኮምፒዩተራቸውን በመጠቀም፣ በዕለቱ የቀረበውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ ሪፖርት አዳምጠዋል፡፡

‹‹የምክር ቤቱን አሠራር ወደ ወረቀት አልባ እንቀይረው በማለት ነው የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ፕሮጀክት የቀረፅነው፤›› ሲሉ የምክር ቤቱ ጽሕፈት ቤት የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ከረዩ ባናታ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በምክር ቤቱ ሰፊ የሆነ የወረቀት ሥራ የሚከናወን መሆኑንና ትልቅ ማተሚያ ቤትም እንደሚገኝ የገለጹት አቶ ከረዩ፣ በተለይ ረቂቅ የበጀት ሰነድ በሚቀርበበት ወቅት ለአንድ የምክር ቤት ተመራጭ ሁለት እሽግ ወረቀት እንደማይበቃ ጠቁመዋል፡፡

ስለዚህ ምክር ቤቱ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሥርዓት በመዘርጋት አሠራሮቹን ወደ ዲጂታል እንዲቀይር አስፈላጊ እንዳደረገው ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በኋላ ለምክር ቤቱ አባላት የሚቀርቡ ሪፖርቶችና አዋጆች በሶፍት ኮፒ የሚሠራጩ መሆኑን፣ አባላቱም ለእያንዳንዳቸው የተገዛውን ታብሌት ኮምፒዩተር በመጠቀም መከታተል እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል፡፡

ከኮምፒዩተር ይልቅ ታብሌት ኮምፒዩተር ከስማርት ስልክ ጋር ተመሳሳይነት ያለውና ለመጠቀምም ሆነ ለእንቅስቃሴ ምቹ በመሆኑ፣ እንዲሁም ለንባብ ጋባዥ ስለሆነ ሊመረጥ መቻሉን አቶ ከረዩ አክለዋል፡፡

የተመረጠው ታብሌት ኮምፒዩተር ‹‹ሳምሰንግ ጋላክሲ ታብ S2›› የተባለው ሲሆን፣ ለምክር ቤቱ ያቀረበውም ኢትዮ ቴሌኮም እንደሆነ አቶ ከረዩ አስረድተዋል፡፡

ግዢው የተፈጸመው በምክር ቤቱ በጀት እንደሆነና ሰባት ሚሊዮን ብር ለታብሌት ኮምፒዩተሮች ግዢ መውጣቱን ጠቁመዋል፡፡

ከመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ምቹ የሆነ ‹‹አፕሊኬሽን›› በልፅጎ በታብሌት ኮምፒዩተሮቹ ላይ መጫኑንም ገልጸዋል፡፡ የምክር ቤቱ ጽሕፈት ቤት የመረጃ አስተዳደር ማዕከል ለምክር ቤቱ አባላት ሰነዶቹን በኢንተርኔት አማካይነት በአፕሊኬሽኑ ላይ እንደሚጭን አቶ ከረዩ አስረድተዋል፡፡ የምክር ቤቱ አካላት የመጠቀሚያ ስም (User Name) እና የይለፍ ቃል የተሰጣቸው በመሆኑ፣ ይህንን በመጠቀም የተላከላቸውን ሰነድ በማውረድ መጠቀም እንደሚችሉ አስረድተዋል፡፡

ወደፊት የፓርላማው አሠራር የድምፅ አሰጣጥን ጨምሮ ዲጂታል እንደሚሆን አቶ ከረዩ ተናግረዋል፡፡ eporter