ዶ/ር ዓሊ ኢሳ አብዲ፣ የአፍሪካ ቀንድ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ፖሊሲ ኢንስቲትዩት ዳይሬክተርየአፍሪካ ቀንድ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ፖሊሲ ኢንስቲትዩት በቅርቡ በስደት ላይ ምርምር በማድረግ የውይይት መድረክ አዘጋጅቶ ነበር፡፡ አጥኚዎቹ በተለይ ‹‹ወደ አውሮፓ የማደረግ ስደት መነሻው ድህነት አይደለም›› በማለት ከዚህ በፊት ከተለመደው ወጣ ያለ መከራከሪያ አቅርበዋል፡፡ የአፍሪካ ቀንድ ከአቅሙ በላይ ስደተኞች ተሸክሞ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡ አንዳንድ የመፍትሔ ሐሳቦችንም አቅርበዋል፡፡ ዶ/ር ዓሊ ኢሳ አብዲ የተቋሙ ዳይሬክተር ሲሆኑ፣ የውይይት መድረኩንም በንግግር ከፍተዋል፡፡ በዚህና በተያያዥ ጉዳዮች ላይ የማነ ናግሽ ከዶ/ር ዓሊ ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል፡
ሪፖርተር፡– ስደትን በተመለከተ በተለይ በአፍሪካ ቀንድ ያለውን ሁኔታ ሊያብራሩልን ይችላሉ?ዶ/ር ዓሊ፡- ስደት ጠቅላል ተደርጎ ሲታይ ሁለት ገጽታ ነው ያለው፡፡ አንደኛው በአፍሪካ ቀንድ በጣም ብዙ ሰዎች መኖር ባለመቻላቸው የሚደረግ ስደት ነው፡፡ ይኼ በአብዛኛው በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ የሚከናወን ነው፡፡ እንዲሁም ደግሞ ከቀጣናው ወደ አውሮፓና መካከለኛ ምሥራቅ የሚደረግ ጉዞ ነው፡፡ ተቋማችን ጉዳዩን ከፖሊሲ ጋር አያይዞ ነው የሚመለከተው፡፡ አብዛኞቹ ተቋማት የስደተኞቹ ሕይወት የሚሻሻልበትን መንገድ ሲያፈላልጉ ይስተዋላል፡፡ በአሁኑ ወቅት በተለይ በአፍሪካ ቀንድ አገሮች (ኢትዮጵያ፣ ሱዳን፣ ሶማሊያ፣ ኡጋንዳ፣ ደቡብ ሱዳን) እንዲሁም ደግሞ አጠቃላይ በአፍሪካ አኅጉር ችግሩ በጣም ከባድ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ችግሩን ከሥሩ ለመፍታት መታገል አለባቸው ብዬ ነው የማምነው፡፡
ሪፖርተር፡– ተቋማችሁ ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ የቀረቡ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ በቀጣናው ከፍተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት የተመዘገበ ቢሆንም የስደት መጠኑ ግን አልቀነሰም፡፡ ይኼ እንዴት ሊሆን ቻለ?ዶ/ር ዓሊ፡- ትክክል ነው፡፡ በአፍሪካ ደረጃም ሆነ በአፍሪካ ቀንድ ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት ተከታታይ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት ተመዝግቧል፡፡ በተለይ ደግሞ በኢትዮጵያ ለአሥር ተከታታይ ዓመታት ባለ ሁለት አኃዝ ዕድገት ተመዝግቧል፡፡ የስደተኞች ቁጥር ግን ጨምሯል እንጂ አልቀነሰም፡፡ ይኼ እንዴት ሊሆን ቻለ? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡ በአንድ በኩል ዕድገቱ በተለይ ለወጣቱ የሥራ ዕድል የሚፈጥር አልሆነም፡፡ እንዲሁም ደግሞ ወጣቶቹ አስፈላጊውን ክህሎትና ሥልጠና እንዲያኙ አልተደረገም፡፡ ለምሳሌ በቂ የሰው ኃይል የሚፈልጉ ኢንዱስትሪዎችን ማስፋፋት አለመቻል አንዱ ተጠቃሽ ምክንያት ነው፡፡
ከተመራማሪዎቹ ግኝትና የጥናት ውጤት መገንዘብ እንደተቻለው ተደጋግሞ ሲባል እንደቆየው፣ ስደት የደቡብ [ሦስተኛ ዓለም] ብቻ ችግር አይደለም፡፡ እዚህ ላይ ብዙ ሰዎች ስደት ሲባል የሚያነሱት በተለይ ወደ አውሮፓ፣ ወደ መካከለኛው ምሥራቅና ወደ ደቡብ አፍሪካ የሚደረገውን ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ነው፡፡ ብዙ የተማሩ ወጣቶች ወደ እነዚህ የዓለም ክፍሎች በዚህ ሁኔታ ይሰደዳሉ፡፡ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ሰዎች የዕለት ገቢያቸው በጨመረ ቁጥር ወደ አውሮፓ የመሰደድ ፍላጎታቸው ጨምሯል፡፡ ወደዚህ አካባቢ የሚደረገው ጉዞ በድህነት ምክንያት ነው ለማለት አይቻልም፡፡ ዋናውና ትልቁን ድርሻ የሚይዘው ድህነት አይደለም፡፡ በአፍሪካ ቀንድ አገሮች መካከል ከአንዱ ጎረቤት ወደ ሌላው ጎረቤት የሚደረገው ስደት አለ፡፡ ለምሳሌ ኢትዮጵያን ውሰድ፡፡ ኢትዮጵያ ከደቡብ ሱዳን፣ ከሶማሊያ፣ እንዲሁም ከኤርትራ በብዙ መቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች አስጠልላለች፡፡ ምናልባት በአፍሪካ ብዙ ስደተኞች በማስጠለል ቁጥር አንድ ሳትሆን አትቀርም፡፡ ኬንያንም ብትወስድ የኢትዮጵያን ያህል ባይሆንም በጣም ብዙ ስደተኞች ተጠልለውባታል፡፡
ሪፖርተር፡- በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ በርካታ ስደተኞች አሉ፡፡ የስደተኞች መጠን አካባቢው ከሚሸከመው በላይ የሆነ ይመስላል፡፡ ምን ቢደረግ ነው ዘላቂ መፍትሔ የሚገኘው?ዶ/ር ዓሊ፡- ጥያቄው ይህንን የስደተኞች ችግር እንዴት እንፍታው የሚል ነው፡፡ በተለይ ደግሞ በግልጽና በሕግ ማዕቀፍ የተደገፈ መፍትሔ መጠቆም ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ አንድ መፍትሔ ሊሆን የሚችለው አፍሪካውያን ከአንድ አገር ወደ ሌላ አገር በነፃ እንዲዛወሩ የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ ማውጣት ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ወደፈለጉት አገር ድንበር ያለምንም እንቅፋትና መጉላላት ተንቀሳቅሰው መሥራት እንዲችሉ ማድረግ ይቻላል፡፡ ኢትዮጵያውያን ወደ ጎረቤት አገር ለመሄድ የግድ ቪዛ ለምን ያስፈልጋቸዋል? የሌሎች አገሮችም እንዲሁ ከአንድ የአፍሪካ አካባቢ ወደ ሌላ አካባቢ ሲንቀሳቀሱ ለምን ቪዛ ያስፈልጋል? ኬንያ ውስጥ የሚኖሩ አፍሪካውያን ወደ ሌላ አፍሪካ አገር ተንቀሳቅሰው ለመሥራት ለምን ቪዛ ያስፈልጋቸዋል? ይኼ መሠረታዊ ጉዳይ ነው፡፡
አሁን በኢትዮጵያ ያሉትም ሆነ በኬንያ የተጠለሉት ስደተኞች ይህንን መብት አግኝተው ቢሆን፣ ስደተኛ ሆነው በካምፕ ተቀምጠው የለጋሾች እጅ የሚጠብቁበት ሁኔታ አይኖርም ነበር፡፡ በነፃ ተዘዋውረው ሠርተው ይኖሩ ነበር፡፡ ይህ ቢደረግ ሁለት ነገሮችን መቀነስ ይቻል ነበር፡፡ አፍሪካውያን ወጣቶች ትኩስ ጉልበት ይዘው ወደ አውሮፓና ሌላ አኅጉር ሄደው ስደተኛ የሚሆኑበት ምክንያት አይኖርም ነበር፡፡ ለወጣቶች በቤታቸው የሥራ ዕድል ፈጠርንላቸው ማለት ነው፡፡ የአፍሪካውያን ስደት በአውሮፓ መነጋገሪያ ጉዳይ መሆኑ ይቀር ነበር፡፡ እንዲህ ቢሆን አፍሪካውያን በሜዲትራኒያን ባህር የዓሳ ዕራት ከመሆን ይድኑ ነበር፡፡ አውሮፓውያንም አንድ አፍሪካዊ ሠራተኛ የሚወስዱት ፈልገውና ከእነ ሙሉ ክብሩ ይሆን ነበር፡፡ የስደተኛና የሕገወጥ ዝውውር ሁኔታ ቀርቶ የአሠሪና ሠራተኛ ግንኙነት ይኖር ነበር፡፡ ይህ ደግሞ መረጋጋትን ይፈጥራል፡፡ ተቋማችንም ከሌሎች ተመሳሳይ ተቋማት ጋር በመሆን ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ አስፈላጊውን ጥናትና ምርምር እያካሄደ ነው፡፡
ሪፖርተር፡– አጥኚዎቹ እንደሚሉት እስከ ዛሬ በአውሮፓውያን ስለስደት የተነገረው ስህተት ነው፡፡ አሁንም በእነሱ እየወጡ ያሉት የመፍትሔ ሐሳቦች መፍትሔ እንደማይሆኑ ሞግተዋል፡፡ አውሮፓውያን በአብዛኛው ስደተኞችን ተቀባይ ሆነው ሳለ እነሱን ያገለለ የመፍትሔ ሐሳብ ችግሩን ሊያቀለው ይችላል ይላሉ? ዶ/ር ዓሊ፡- በእርግጥ ጉዳዩ በተለይ ከስደት ጋር በተያያዘ ነው፡፡ በጋራ መሥራት አይጠላም፡፡ አፍሪካ የተባለው አኅጉር ግን ሁሌም የመፍትሔ ሐሳብ ከውጭ ይመጣል ብሎ ተስፋ የሚያደርግ ነው፡፡ በተጨባጭ ግን የዚህን አኅጉርና ሕዝቦች ችግር የሚፈታ መፍትሔ መቼም ከውጭ መጥቶ አያውቅም፡፡ በተለይ የእኛ ተቋም አፍሪካውያን የራሳቸውን ችግር ራሳቸው መፍታት አለባቸው የሚል አቋም ነው የሚያራምደው፡፡ አንድ አገር የተሠራ ምርምር ሌሎች ቢጠቀሙበት የዕውቀት ልውውጥና የጋራ መቀራረብ ቢፈጠር፣ ስደትም በለው ሌላ ማኅበራዊ ችግር መፍትሔ ሩቅ ሳይኬድ እዚሁ ይገኛል የሚል አቋም ነው ያለን፡፡ ተመራማሪዎችም ለማለት የፈለጉት ይህንን ነው፡፡ አንድ ጎበዝ ሱዳናዊ ኦዲተር ካገኘሁ ለምን ወደ አሜሪካ አያለሁ? ኬንያውያን ኢትዮጵያ ውስጥ መሥራት ይችላሉ፡፡ በሌላ በኩል ጎበዝ ኢትዮጵያውያን ኬንያ ሄደው በሚፈልጉት መስክ መሥራት ይችላሉ፡፡ በመሀል የዕውቀት ሽግግርም ከአንድ አገር ወደ ሌላ አገር ይፈጠራል፡፡ እና ወደ ራሳችን ወደ ውስጥ ተመልክተን፣ ራሳችንን ፈትሸን፣ ተባብረን ካልሠራን መሪዎችም ይህንን ካልተገነዘቡ ችግሩ ይፈታል ተብሎ አይገመትም፡፡ ይህንን አድርገን የተሻለ መፍትሔ ማምጣት ካልቻልን ከአውሮፓውያንም ሆነ ከአሜሪካውያን መልካም ምላሽ ማግኘት አንችልም፡፡ ስለዚህም ነው ለስደት መፍትሔው በእጃችን ነው ያለው የምንለው፡፡
ይኼ ደግሞ በአንድ መንግሥት ወይም በተወሰኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጥረት የሚመጣ አይደለም፡፡ ጉዳዩን የጋራ አድርጎ በመቀበል በተባበረ ክንድ ነው መፍታት የሚቻለው፡፡ ለምሳሌ አንድ ኢትዮጵያዊ ኢንቨስተር በሱዳን ገንዘቡን አፍስሶ ቢሠራ የሚጠቀመው ሥራ ፈጣሪ ኢንቨስተሩ ብቻ አይደለም፡፡ የሱዳን ወጣቶች ናቸው ተቀጥረው የሚሠሩበት፡፡ ከአኅጉሩ ወደ ውጭ የሚወጣ ሀብታም አይኖርም ማለት ነው፡፡ ሌሎች የአፍሪካ ቀጣናዎች ለምሳሌ ኢኮዋስና ሳድክ እንዲሁም በምሥራቅ አፍሪካ ያሉት እነ ኬንያና ታንዛኒያ እንዲህ ዓይነት እንቅስቃሴ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ይኼ የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ግን ወደ ኋላ ተጎትቷል፡፡ ሌሎች ነፃ የጋራ ግብይትና ነፃ የሰው ኃይል ዝውውር ፈቅደዋል፡፡
ሪፖርተር፡– ስለዚህ ኢኮኖሚያዊ ውህደት መፍጠርን ለችግሩ እንደ መፍትሔ እየጠቆሙ ነው?ዶ/ር ዓሊ፡- በትክክል በአፍሪካ ላለፉት 30 ዓመታትና ከዚያ በላይ ስለውህደት ተወርቷል፡፡ በአፍሪካ ቀንድና በኢጋድ አካባቢ ግን ምንም የተሠራ ሥራ የለም፡፡ አውሮፓ ውስጥ ምን እየተፈጠረ እንደሆነ ተመልከት፡፡ አንድ ማንነት ለመፍጠር እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡ አፍሪካ ውስጥ በተለይ ደግሞ በዚህ የእኛ የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ግን ይህ አዝማሚያ አይታይም፡፡