የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ለተሰናባቿ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ዶክተር ኒኮሳዛና ዲላሚኒ ዙማ አሸኛኘት አደረጉላቸው።ትናንት በሂልተን ሆቴል በተደረገው የሽኝት ስነ ስርዓት ላይ አዲሱ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋቂ ማሃማት፣ ምክትላቸው እና ጥሪ የተደረገላቸው አምባሳደሮች ተገኝተዋል።
ዶክተር ወርቅነህ በዚህ ወቅት እንዳሉት፥ ዶክተር ኒኮሳዛና በህብረቱ ሊቀ መንበርነት ዘመናቸው ቁልፍ ተግባራትን አከናውነዋል።ተሰናባቿ ሊቀ መንበር በስልጣን ዘመናቸው ለአጀንዳ 2063 መሳካት ቁልፍ ሚና መጫወታቸውንም አንስተዋል።
በፈረንጆቹ 2020 ከግጭት የጸዳች አፍሪካን ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት እና የሴቶችን ተሳትፎ እና አቅም በማሳደግ በኩልም፥ ድላማኒ ዙማ በሊቀ መንበርነታቸው ጉልህ ድርሻ እንደነበራቸው ተናግረዋል።
ከዚህ ባለፈም የደቡብ አፍሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በነበሩበት ወቅት በኢትዮጵያና በሃገራቸው መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማሳደግ ለሰሩት ስራም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።ተሰናባቿ ሊቀ መንበር በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ በደማቅ አቀባበል ተቀብላ በደማቅ ሁኔታ ሽኝት እንዳደረገችላቸው ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ከህብረቱ ጋር ለነበረው ጠንካራ ትብብርም አመስግነዋል።ኢትዮጵያ በኢንዱስትሪ፣ በመሰረተ ልማት እና በሃይል እያሳየችው ያለው እድገት በመላው አፍሪካ ሊስፋፋ የሚገባው ምርጥ ተሞክሮ መሆኑንም ነው የገለጹት።መንግስት ባህላዊ ቅርሶችን በመንከባከብና በመጠበቅ ረገድ የሚያደርገውን እንቅስቃሴም ሌሎች የአፍሪካ ሃገራት ሊቀስሙት የሚገባ ነው ብለውታል።
ዲላሚኒ በንግግራቸው መላው አፍሪካውያን፥ ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ለአለም አቀፉ የጤና ድርጅት ዳይሬክተርነት በሚያደርጉት ፉክክር ድጋፍ እንዲያደርጉላቸውም ጥሪያቸውን አቅርበዋል።