ከ6 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ለ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታ የሚውል የኮንክሪት አርማታ ብረት ወጪ በማድረግ ለሌሎች ነጋዴዎች ያቀበለው ተከሳሽ በፅኑ እስራትና በገንዘብ ተቀጥቷል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር ቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራዝ የግብአት ክምችት እና ስርጭት ኦፊሰር የነበረው ተከሳሽ ተስፋለኝ በቀለ ቢረዳ ላይ ነው የቅጣት ውሳኔው የተላለፈበት።
ተከሳሹ ህዳር 10 ቀን 2009 ዓ.ም ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በወረዳ 06 ክልል በሚገኝ የኢንተርፕራዙ የ40/60 ቤቶች ፕሮጀክት ተከማችቶ የነበረውን ብረት ህገወጥ በመሆነ መልኩ ወጪ ማድረጉን የአቃቤ ህግ ክስ ያመለክታል።
ብረቱንም በ15 ሲኖትራክ ተሽከርካሪዎች በመጠቀም ከ4ኛ ተከሳሽ ጋር በመሆን ጀሞ ሳይት ፉሪ ተብሎ በሚጠራው በ2ኛ ተከሳሽ መጋዘን እንዲራገፍ ማድረጉ በክሱ ተጠቅሷል።
ሁለተኛ ተከሳሽም እስከ ሰባተኛ ተከሳሽ ላሉ ነጋዴዎች በማቀበል ወደ ተለያዩ አካባቢዎች ተሰራጭተው መሸጣቸው ነው በክሱ የተብራራው።ተከሳሾቹ ፍርድ ቤት ቀርበው ድርጊቱን ስለመፈፀም ለቀረበላቸው ጥያቄ 1ኛ ተከሳሽ ተስፋለኝ በቀለ ወንጀሉን መፈጸሙን ሙሉ በሙሉ አምኗል።ፍርድ ቤቱም ተከሳሽ ተስፋለኝ በቀለ ቢረዳን ጥፋተኛ በማለት በ11 ዓመት ፅኑ እስራትና በ7 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ወስኖበታል።የተቀሩት ተከሳሾች ድርጊቱን አልፈጸምንም ማለታቸውን ተከትሎ አቃቤ ህግ የሰነድና የሰው ምስክር እንዲያሳማ ታዟል። FBC