Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ሕዝቡ የጥልቅ ተሃድሶ ንቅናቄውን ይበልጥ እንዲያሰፋውና እንዲያጎለብተው ጥሪ ቀረበ

0 310

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ሕዝቡ የተጀመረውን የጥልቅ ተሃድሶ ንቅናቄ ይበልጥ እንዲያሰፋውና እንዲያጎለብተው የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ጥሪ አቀረበ።

የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ መደበኛ ስብሰባውን ማጠናቀቁን አስመልክቶ የግንባሩ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ማምሻውን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት መግለጫ ልኳል።

ሕዝቡ የጥልቅ ተሃድሶ ንቅናቄውን ይበልጥ በማስፋትና በማጎልበት ሁለተኛውን የእድገትና ትራስፎርሜሽን እቅድ በላቀ ደረጃ ለመፈጸም እንዲረባረብ ጥሪ ማቅረቡ በመግለጫው ተመልክቷል።

የተሃድሶ ንቅናቄው እና የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን ሳይነጣጠሉ ለማስኬድ “እየታደስን እንሰራለን፤ እየሰራን እንታደሳለን” በሚል አቅጣጫ እየተፈፀመ መሆኑን የገመገመው ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ፤ በቀጣይም የተሃድሶ ንቅናቄው በተመሳሳይ አኳኋን እንዲፈፀም አቅጣጫ አስቀምጧል።

የተሃድሶው ንቅናቄውና የሁለተኛው ዓመት አጋማሽ የእድገትና ትራስፎርሜሽን እቅድ አፈጻጸም አበረታች ውጤቶች የተገኙበት መሆኑን አመልክቶ፤ ትምክህትና ጠባብነት ቀጣይ ትግል ሊደረግባቸው እንደሚገባም አጽንኦት መስጠቱን መግለጫው አትቷል።

በእቅዱ ሁለተኛ ዓመት አጋማሽ በገጠር የግብርና ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚገባ ያመለከተው ኮሚቴው፤ በከተማ የኢንዱስትሪ እድገትን የማስቀጠል አስፈላጊነትን አጽንኦት ሰጥቶታል።

በአገሪቷ የተከሰተው ድርቅ በሰው ሕይወት ላይ የከፋ ጉዳት ሳያስከትል ለመቋቋም ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚያስፈልግም ገልጿል።

የወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ እና የህዝቡን ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ የመስጠት ጉዳይ በልዩ ትኩረት መከናወን እንዳለበት አቅጣጫ ማስቀመጡም በመግለጫው ተመልክቷል።

የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል።

የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ መደበኛ ስበሰባውን አጠናቀቀ

የጥልቅ ተሃድሶ ንቅናቄው የደረሰበትንና በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን የሁለተኛው ዓመት አጋማሽ አፈፃፀም ሪፖርት ላይ ለሁለት ቀናት የገመገመው የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ መደበኛ ስብሰባ መጠናቀቁን የግንባሩ ምክር ቤት ፅሕፈት ቤት በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡

ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ከየካቲት 27-28/2009 ዓ.ም ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ እንደገና በጥልቀት የመታደስ የንቅናቄ መድረኮች በተቀመጠላቸው አቅጣጫ መሰረት የተፈፀሙ መሆናቸውን ገምግሟል፡፡ የተሃድሶ ንቅናቄው በየደረጃው ባለ አመራር፣ አባላት፣ በሲቪል ሰርቫንቱ እና በህዝቡ ደረጃ ሰፊ ውይይት መደረጉንና በተሃድሶ አጀንዳዎቹ ላይም በተሻለ ሁኔታ የጋራ መግባባት መደረሱንም ተመልክቷል፡፡  መድረኩ በአመራርና በአባላት ለመተጋገል ምቹ ሁኔታ የፈጠረ ከመሆኑም በላይ በሲቪል ሰርቫንቱና በህዝቡ ዘንድም የተነሱ ችግሮች ይፈታሉ የሚል ተስፋ ማሳደሩን አይቷል፡፡ በተሃድሶው ሀገራችን በመስቀለኛ መንገድ ላይ እንድትቆም ያስገደዳትን አስከፊ ሁኔታ በመቀልበስ የተጀመረውን ሀገራዊ የህዳሴ ጉዞ ለማሳካት የሚያስችል መግባባት እንደተፈጠረም ኮሚቴው ገምግሟል፡፡

በአጠቃላይ የጥልቅ ተሃድሶ ንቅናቄው ባለፉት 15 የተሃድሶ ዓመታት በልማት፣ በሰላም እና በዴሞክራሲ መስኮች የተመዘገቡ ወርቃማ ስኬቶች ላይ ህዝቡ ከፍተኛ ድርሻ እንደነበረውም የጋራ መግባባት ተፈጥሮበታል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ የኪራይ ሰብሳቢነት ወኪል የሆኑት የትምክህትና ጠባብነት አመለካከቶችና ተግባራት የፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ አደጋ መሆናቸውን በመግባባት በቀጣይ ትግል የህዳሴ ጉዞውን ማደናቀፍ ከማይችሉበት ደረጃ ላይ በማድረስ ሀገራዊ ህዳሴውን እውን ለማድረግ ህዝቡ መነሳሳቱንም ኮሚቴው ተመልክቷል፡፡

የመልሶ ማደራጀት ስራውን በተመለከተም በተለይ ከክልል ቀጥሎ ባሉ የአስፈፃሚ አካላት ምደባ በብዙ አካባቢዎች በአባላትና በህዝቡ ቀጥተኛ፣ ነፃና ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ ባረጋገጠ አኳኋን በአመራሮቹ ምደባ ላይ ባለቤትነቱን በማረጋገጥ ያገለግሉኛል ያላቸውን እውቅና የሰጠበት በተቃራኒው አያገለግሉኝም ያላቸውን ደግሞ በትግል በአመራርነት እንዳይቀጥሉ ማድረጉን ኮሚቴው የገመገመ ሲሆን አሰራሩ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡

 

የወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራ በተመለከተም ነባሩን የወጣቶች የዕድገትና የለውጥ ፓኬጅ የነበሩበትን ክፍተቶች በማረም ከሀገራዊ ዕድገቱ በማጣጣም የወጣቶች የተሳትፎና የተጠቃሚነት በመሰረታዊነቱ መመለስ በሚያስችል ሁኔታ በአዲስ መልክ መዘጋጀቱን አረጋግጧል፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ  ስራ ፈላጊ ወጣቶችን በህዝብ ተሳትፎ የመለየትና የማደራጀት ስራው እየተሰራ ሲሆን በቀሪው ጊዜ ወጣቱንና ስራን በተጨባጭ ለማገናኘት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ መከናወን እንዳለበት አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡

በአጠቃላይ የተሃድሶ ንቅናቄው እና የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች ሳይነጣጠሉ ለማስኬድ እየታደስን እንስራን፤ እየሰራን እንታደሳለን በሚል አቅጣጫ እየተፈፀመ እንደሆነ የገመገመው ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በቀጣይም የተሃድሶ ንቅናቄው በተመሳሳይ አኳኋን እንዲፈፀም አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡

የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን የሁለተኛው ዓመት አጋማሽ አፈፃፀም ሪፖርት በተመለከተም የማክሮ ኢኮኖሚ ጉዳዮች፣ የኢኮኖሚና ማሕበራዊ ዘርፎች፣ የልማታዊ መልካም አስተዳደርና የዴሞክራሲ ግንባታ  እንዲሁም የሴቶችና ወጣቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት አፈፃፀሞችን በዝርዝር የገመገመው  የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የተጀመረው ፈጣን እና ተከታታይነት ያለው ኢኮኖሚያዊ ዕድገት መቀጠሉንም አረጋግጧል፡፡

በያዝነው ዓመት የመኸር ግብርና እድገት በአማካይ 12 በመቶ እንዲሚያድግ ትንበያዎች እንደሚያመላክቱ የገመገመው ኮሚቴው በመስኖ  እና በበልግ ስራዎች ላይ የተሻለ ርብርብ ከተደረገ ከዚህም በላይ ማሳደግ እንደሚቻል ተመልክቷል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ህዝቡ በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃና በተፋሰስ ልማት በስፋት በማሳተፍ የተከናወኑ ስራዎችም ውጤታማ እንደነበሩ ገምግሟል፡፡

በሀገራችን ደቡብና ደቡብ ምስራቅ አካባቢዎች በተፈጠረው የዝናብ አገባብ፣ መጠንና ስርጭት መዛባት ምክንያት በኢትዮጵያ ሶማሌ፣ በተወሰኑ የኦሮሚያ እና ደቡብ አካባቢዎች ድርቅ መከሰቱ ተመልክቷል፡፡ መንግስት ለጉዳዩ ቅድሚያ ሰጥቶ የድርቁን አደጋ ለመቀነስ ከፍተኛ ርብርብ እያደረገ መሆኑን ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በዝርዝር ከመገምገሙም በላይ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡

የኢንዱስትሪ ዕድገትን በተመለከተም በ2008 በጀት ዓመት አዳዲስ የኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንቶች ወደ ስራ በመግባታቸው ምክንያት  የማምረቻ ኢንዱስትሪው በ18.4 በመቶ እድገት ማስመዝገቡን የገለፀው ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በዘርፉ ለተመዘገበው ፈጣን ዕድገትም ከፍተኛ አስተዋፅኦ ነበረው ብሏል፡፡ የማምረቻ ኢንዱስትሪ ልማትን በማፋጠን የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ለማምጣት ትኩረት ተሰጥቶት እየተከናወነ መሆኑን የተመለከተው ኮሚቴው 13 የሚሆኑ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ስራ በተሻለ አፈፃፀም እየተከናወነ መሆኑን አይቷል፡፡ ከእነዚህ የኢንዱስትሪ ፓርኮች መካከል የቦሌ ለሚ ምዕራፍ አንድ 20  እንዲሁም በሐዋሳ 11 የሚሆኑ የፋብሪካ ሼዶች ወደ ምርት በመግባት የውጭ ምንዛሬ ማስገኘት ጀምረዋል ያለው ኮሚቴው የሌሎች ኢንዳስትሪያል ፓርኮች ግንባታ በተመለከተም በተለያየ ደረጃ እንደሚገኙ ተመልክቷል፡፡ እነዚህ የኢንዱስትሪ ፓርኮች የሀገራችን የኢኮኖሚ አወቃቀር ወደ ማምረቻ ኢንዱስትሪው እንዲያዘነብል ከማስቻላቸውም በላይ ሰፊ የስራ ዕድል ለመፍጠር፣ የኤክስፖርት ዓቅምን ለማሳደግና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማፋጠን በሚያግዝ መልኩ እየተከናወኑ መሆኑ ተገምገሟል፡፡

በውጭ ንግድ ረገድ በተለይ ደግሞ የግብርና ምርቶች፣ የቁም እንስሳትና የወርቅ ሕገ-ወጥ ንግድ ኤክስፖርት ግኝቱን እየጎዳ መሆኑን የገለፀው ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በየደረጃው ያለ አመራር እና የዘርፉ ተዋናዮች ተቀናጅተው በመስራት ችግሩን መፍታት እንዳለባቸውም አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡

የመሰረታዊ ሸቀጣሸቀጦች አቅርቦት በተመለከተም በመንግስት የዋጋ ተመን ወጥቶላቸውና የአሰራር ስርዓት ተዘርግቶላቸው በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ ቢሆንም አሁንም በስርጭት ላይ  ችግር በመኖሩ ቀጣይ ትኩረት እንደሚሻ ኮሚቴው አፅንኦት ሰጥቶበታል፡፡ በተያዘው በጀት ዓመት የዋጋ ንረቱን በነጠላ አሃዝ ገድቦ ለመያዝ የተደረገው ጥረት ውጤታማ መሆኑንም የተመለከተው ኮሚቴው ይህም የብርን የመግዛት ዓቅም ጠብቆ ለማቆየት፣ ቁጠባንና ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት፣ የገቢ ክፍፍልንና የሃብት ድልድልን ሚዛናዊ ለማድረግና የማሕበራዊና ኢከኖሚያዊ እድገት ቀጣይነት ለማረጋገጥ በተከናወኑ ስራዎች አማካይነት የተገኘ እንደሆነ አስምሮበታል፡፡

የመሰረተ-ልማት አቅርቦት ማሻሻል የሚያስችሉ በርካታ ሜጋ ፕሮጄክቶች በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ለማጠናቀቅ  ትኩረት ተሰጥቶት ርብርብ እየተደረገ መሆኑንም ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው አረጋግጧል፡፡ በተለይ በኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ከተያዙ ፕሮጄክቶች መካከል 2100 ሜጋ ዋት የሚያመነጨው የኮይሻ ፕሮጄክት እና 120 ሜጋ ዋት የሚየመነጨው የአይሻ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጄክት የግንባታ ስራቸው እንደተጀመረ ገምግሟል፡፡

በማሕበራዊ ልማት ዘርፍ የትምህርት ተደራሽነትና ጥራት ለማረጋገጥ የተከናወኑ ስራዎች ውጤታማ እንደነበሩ የገመገመው ኮሚቴው በቀጣይም በትምህርት ስርዓቱ ላይ ሰፋ ያለ ጉድለት የሚታይባቸውን የመዋዕለ ህፃናትና የከፍተኛ ትምህርት ተሳትፎ ለማሳደግ ትኩረት ይሻል፡፡ የአንደኛ ደረጃ መጠነ ማቋረጥ ለማስቀረት መረባረብ ይገባል ያለው ኮሚቴው የጎልማሶች ትምህርትም ለህዳሴ ጉዞው ከሚኖረው ፋይዳ አንፃር በመመዘን በቀሪ ጊዜ ውጤታማ ስራ ለማከናወን መረባረብ እንደሚገባ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡ በጤና መስክም በተለይ የእናቶችና የህፃናት ሞት በመቀነስ ስኬታማ ስራዎች እንደተከናወነ ገልጿል፡፡ ይሁንና የጤና ኤክስቴንሽን ስርዓቱና የኤክስቴንሽን ሙያተኞች የሚያጋጥሟቸውን የማሕበራዊና የሙያ ማነቆዎች በጥናት ላይ የተመሰረተ ምላሽ ለመስጠት መዘጋጀት እንደሚገባ በመጠቆም በዘርፉ የሚስተዋለውን የጥራት መጓደል ችግር ለመፍታትም ቀጣይ ትኩረት እንደሚሹ አስምሮበታል፡፡

በአጠቃላይ የተሃድሶው ንቅናቄና የሁለተኛ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ሁለተኛው ዓመት አጋማሽ አፈፃፀም አበረታች ውጤቶች የተገኙበት መሆኑን አስምሮ በቀጣይ ከተሃድሶ አኳያ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር ወኪል የሆኑትን ትምክህትና ጠባብነት ቀጣይ ትግል ሊደረግባቸው እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥቶበታል፡፡ የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ሁለተኛው ዓመት አጋማሽ በገጠር የግብርና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በከተማ ደግሞ የኢንዱስትሪውን ዘርፍ ሚና በማጎልበት በአንድ በኩል የተጀመረውን ፈጣንና ተከታታይ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ማስቀጠል በሌላ በኩል የጋጠመንን ድርቅ በሰው ህይወት ላይ የከፋ ጉዳት ሳያስከትል ለመቋቋም ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይገባል ብሏል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ የወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራ እና የህዝቡን ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ የመስጠት ጉዳይ በልዩ ትኩረት መከናወን እንዳበት አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡

በመጨረሻም ህዝቡ የተጀመረውን የጥልቅ ተሃድሶ ንቅናቄ ይበልጥ በማስፋትና በማጎልበት እንዲሁም ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽ ዕቅድ በላቀ ደረጃ ለመፈፀም እንዲረባረብ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy