በአዲስ አበባ ሜክሲኮ አረቄ ፋብሪካ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከእኔ ጋር ያለሽን የፍቅር ግንኙነት አቋርጠሽ ከሌላ ጋር ግንኙነት ጀምረሻል በሚል የአንዲት ወጣትን ሀይወት በማጥፋት የተጠረጠረው ግለሰብ ክስ ተመሰረተበት።
የአቃቤ ህግ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው ተጠርጣሪው፥ የግል ተበዳይና ሟች ኑሀሚ ጥላሁንን ከእኔ ጋር ያለሽን የፍቅር ግንኙነት አቋርጠሽ ከሌላ ጋር ጀምረሻል በማለት የካቲት 21 ቀን 2009 ዓ ም ከቀኑ በ10 ሰዓት ህይወቷን የሚያሳጣ የወንጀል ድርጊት ፈጽሞባታል ነው ያለው።
ተጠርጣሪው ከሟች ኑሀሚን ጋር ካሳንችስ ታክሲ ተራ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ የጥርስ መፋቂያ ይሸጥ ከነበረ ግለሰብ ስለት በመግዛትና በመደበቅ በአዲስ አበባ ሜክሲኮ አረቄ ፋብሪካ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ሲደርሱ “እኔን ትተሽ ከሌላ ሰው ጋር የፍቅር ግንኙነት ጀምረሻል” በማለት በያዘው ስለት አንገቷና ጀርባዋ ላይ በመውጋት ህይወቷ እንዲያልፍ አድርጓል ይላል አቃቤ ህግ በክሱ።
ተጠርጣሪው የአንደኛ ዓመት የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሲሆን፥ በግል ተበዳይዋ ኑሀሚን ጥላሁን ላይ ጥቃቱን ከሰነዘረ በኋላም ለማምለጥ ሲሞክር በስፍራው ታክሲ በመጠበቅ ላይ በነበሩ ሰዎች እርዳታ በቁጥጥር ስር መዋሉንም ጠቅሷል።
ጥቃቱ የደረሰባት ወጣት ለህክምና እርዳታ ወደ ሆስፒታል ብትወሰድም በፈሰሳት ከፍተኛ ደም የተነሳ ህይወቷ ሊያልፍ ችሏል።
አቃቤ ህግም በተጠርጣሪው ላይ ወንጀሉ ሲፈጸም በስፍራው የነበሩ የአይን እማኞችን እንዲሁም የሰነድ ማስረጃዎችን በማጠናቀር ግለሰቡ ላይ ከባድ የሰው መግደል ወንጀል ክስ መስርቶበታል።
ተከሳሹም በህግ ቁጥጥር ስር ውሎ ዛሬ ረፋዱን ፍርድ ቤት ቀርቧል።
የፌደራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የወንጀል ችሎት አቃቤ ህግ በተጠርጣሪው ላይ የመሰረተበትን ክስ በንባብ እንዲረዳው አድርጓል።
ተጠርጣሪው ግለሰብም ጠበቃ የማቆም አቅም የሌለኝ በመሆኑ መንግስት ጠበቃ ያቁምልኝ በማለት ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።
ፍርድ ቤቱም የተጠርጣሪውን ቃል በመሀላ በማረጋገጥ ጠበቃ እንዲቆምለት ትእዛዝ ሰጥቷል።
የፌደራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የወንጀል ችሎት የግለሰቡን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረግም የክስ መቃወሚያ ለመስማት ለመጋቢት 26 ቀን 2009 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል። FBC