መልካም ነገር ሁሉ ለጽንፈኛው ዳያስፖራ
ራስ ምታት ነው
አባ መላኩ
ባለፉት 26 ዓመታት በተለይ ደግሞ ባለፉት 14 ዓመታት አገራችን በየዘርፉ በርካታ ስኬቶችን ማስመዝገብ ችላለች። በአገራችን እየተመዘገበ ካለው ዕድገት ሁሉም በየደረጃው ፍተሃዊ ተጠቃሚ እንዲሆን መንግስት የተቻለውን ሁሉ በማድረግ ላይ ነው። መንግስት በመላ አገሪቱ እየገነባቸው ካሉ በርካታ መሰረተ ልማቶችና እያስፋፋቸው ካሉ ማህበራዊ መገልገያዎች ህብረተሰቡ ተጠቃሚ ሆኗል።
በገጠር የአብዛኛው አርሶና አርብቶ አደር ህይወት ተለውጧል፤ በመለወጥ ላይም ይገኛል። በተመሳሳይ በከተማዎች አካባቢም የበረካታ ዜጎች የአኗኗር ዘይቤ በመለወጥ ላይ ነው። በርካቶች ቋሚ ቅርስ የሆነውን የመኖሪያ ቤት ባለቤት መሆን ችለዋል። ከአገራችን ዕድገት ዜጎች ብቻ ሳይሆኑ ጎረቤት አገሮችም ጭምር መጠቀም ጀምረዋል። ይህ የኢፌዴሪ መንግስት የአካባቢውን አገራት በኢኮኖሚያዊ ጥቅም በማስተሳሰር በቀጠናው ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የሚያደርገው ጥረት ለጽንፈኞቹ የዳያስፖራ ፖለቲከኞች ራስ ምታት ሆኗል። ምክንያቱም ለእነዚህ የጥፋት ሃይሎች ሰላም በሽታቸው ነው።
የአገራችን ኤኮኖሚ በፈጣን ሁኔታ ማደግ ሲጀምር ከጎረቤት አገራት ጋር በንግድ፣ በባህል፣ በሰላም ማስከበር፣ ወዘተ ትስስሩ እየጠነከረ መምጣት ጀምሯል። ኢትዮጵያ ካስመዘገበችው ፈጣንና ተከታታይነት ያለው የኢኮኖሚ እድገትም ሆነ በቀጠናው ማስፈን በቻለችው ሰላም ተጠቃሚ የሆኑት ህዝቦቿ ብቻ ሳይሆኑ የጎረቤት አገራት ህዝቦች ጭምር ናቸው። የኢትዮጵያ መንግስት ለአካባቢው ሰላም መስፈን ጠንክሮ የሚሰራው በአፍሪካ ቀንድ ወይም በቀጠናው የሚካሄዱ ማንኛቸውም ነገሮች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በኢትዮጵያ ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ስለሚረዳ ነው። ይህ በተግባርም ታይቷል።
ለአብነት ሶማሊያና ደቡብ ሱዳን ባለባቸው የውስጥ አለመረጋጋት እንዲሁም በኤርትራ ያለው አምባገነን መሪ ሳቢያ ኢትዮጵያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የእነዚህን አገሮች ስደተኞች ለማስተናገድ ተገዳለች። ይህ የኢትዮጵያ መንግስት መልካም ጥረት ለጽንፈኛው ዳያስፖራ የማይዋጥ ነገር ሆኖበታል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ያለው ፖለቲካዊውና ባህላዊው ግንኙነት በኢኮኖሚያዊ ትስስር እንዲጎለብት ለማድረግ የአካባቢውን አገሮች በኢኮኖሚ ጥቅም ሊያስተሳስሩ የሚችሉ በርካታ ፕሮጀክቶችን በመገንባት ላይ ትገኛለች። ለአብነት ዘመናዊ የመንገድ ግንባታ፣ የባቡር ሃዲድ ዝርጋታ፣ የአየር በረራ መስመሮች ማስፋፋት፣ የሃይል አቅርቦት ወዘተ በማካሄድ የአካባቢውን አገሮች ኢኮኖሚያዊ ትስስር በማካሄድ ላይ ነች። ይህን አገራችን እያከናወነች ያለችውን ተግባር ማንም የአካባቢው አገሮች እስካሁን አድርገውት አያውቁም።
ኢትዮጵያ የምትከተለው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ መሰረት የሚያደረገው የአገሪቱን ኤኮኖሚያዊ ጠቀሜታና አገራዊ ህልውናን በማረጋገጥ እንዲሁም በማንኛውም አገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ባለመግባትና ለአካባቢው ህዝቦች ጥቅም በጋራ በመስራት ላይ ነው። ኤኮኖሚክ ዲፕሎማሲን መሰረት ያደረገው የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት አገሪቱን ፈጣንና ቀጣይነት ያለው እድገት እንድታስመዘግብ ከማስቻሉም በላይ በአገር ውስጥና በአካባቢው አገራት ዘላቂ ሰላምን ማስፈን አስችሏታል። እነዚህ መልካም ስራዎች ሁሉ አገራችን የምትከተለው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ውጤት ነው። ውጤታማ የሆነው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲያችን የመነጨው ደግሞ ከህገመንግስታችን መሆኑን መዘንጋት የለበትም። እንግዲህ ይህን ህገመንግስት ነው የዳያስፖራ ፖለቲከኞች ለማጣጣል ጥረት ሲያደርጉ የነበረው።
ኢትዮጵያ የአካባቢውን አገሮች በኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማስተሳሰርና ዘላቂ ሰላም በቀንዱ አካባቢ ለማስፈን ጥረት ከምታደርግባቸው መስኮች አንዱ የኤሌክትሪክ ሃይል በማመንጨት በተመጣጣኝ ዋጋ ለአካባቢው አገሮች ማከፋፈል ነው። ኢትዮጵያ በርካታ የሃይል ማመንጫ ጣቢያዎችን በመገንባት ላይ ተገኛለች። ከእነዚህ የሃይል መመንጫ ፕሮጀክቶች መካከል የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ አንዱና ዋንኛው ነው። ይህ ፕሮጀክት በበርካታ ነገሮቹ የመንግስትንና የህዝብን ቀልብ ብቻ ሳይሆን የዓለም መንግስታትንና ድርጅቶችን ቀልብ መግዛት የቻለ ፕሮጀክት ነው።
የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ልዩ ከሚያደርጉት ነገሮች መካከል በቀዳሚነት የሚነሳው ይህ ብዙ ቢሊዮን ዶላር ወጪን የሚጠይቀው ፕሮጀክት በውስጥ አቅም መገንባቱ ነው። ከዚህም ባሻገር የፕሮጀክቱ ጠቀሜታ ከኢትዮጵያ ባለፈ በተፋሰሱ አገራት መካከል አዲስና ፍተሃዊ ግንኙነት እንዲፈጠር ማድረጉ ነው። እንዲሁም ሱዳንና ግብጽ ዓመቱን ሙሉ የተመጣጠነ የውሃ ፍሰት እንዲኖራቸው፣ ከጎርፍ ስጋት እንዲድኑ እንዲሁም ግድብቻቸውን ከደለል ይታደግላቸዋል። በመሆኑም የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ በተፋሰሱ አገራት መካከል መተማመን እንዲፈጠርም ምክንያት ሆኗል። አገራችን ከዚህ ግዙፍ ፕሮጀክቶች የሚመነጨውን ሃይል አቅርቦት ፍላጎቷን ካሟላች ብኋላ ለጎረቤት አገራት በተመጣጣኝ ዋጋ የሃይል ምንጭ በመሆን የውጭ ምንዛሬ ያስገኝላታል።
ከላይ ለማንሳት እንደሞከርኩት የኢፌዴሪ መንግስት ህዝባዊ መንግስት ነው። እኔ ብቻ ልጠቀም ሳይል ሁሉም የተፋሰሱ አገራት በየደረጃው የሚጠቀሙበትን ፕሮጀክት በመገንባት ላይ ይገኛል። የኢትዮጵያ መንግስት “ፍተሃዊ የውሃ ክፍፍል በተፋሰሱ አገራት መካከል” የሚለው መርህ አሁንም እየተከተለችው ያለው አቋም ነው። ይህ አቋም ትክክልኛና ወቅታዊ በመሆኑ በሁሉም የተፋሰሱ አገራት ዘንድ ተቀባይነት አለው በሚባል መልኩ ድጋፍ አገኝቷል። የኢትዮጵያ አቋም በተፋሰሱ በአገራት መካከል ፍተሃዊ የሃብት ክፍፍል እንዲኖር ያደረገ በመሆኑ አገራት የወንዙን ድህንነት መንከባከብ ጀምረዋል። በዚህ ረገድ አገራችን ሰፊ የተፋሰስ ልማት ስራዎችን ማከናወን በመጀመሯ የወንዙን ዘላቂ ህይወትም አስተማማኝ እንዲሆን አድርጎታል።
የኢፌዴሪ መንግስት የሚገነባቸው ፕሮጀክቶች ከአካባቢ ጋር ተስማሚ እንዲሁም በማንም ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደማያሳድሩ በተደጋገጋሚ ስገልጽ የቆየውን እውነታ በገለልተኛ አካል በተግባር እንዲረጋገጥም አድርጓል። የኢትዮጵያ መንግስት የሚገነባውን ፕሮጀክት በሌሎች ላይ ጉዳት እንደማያስከትል በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲገመገም የፈቀደ ብቸኛ መንግስት ይመስለኛል። እንዲህ ያለ ነገርን ማንም ሲያደርግ አላየንም፤ አልሰማንም። የትኛውም የተፋሰስ አገራት እስካሁን በወንዙ ላይ የገነቧቸውን ፕሮጀክቶች በገለልተኛ አካል ያስገመገመ የለም። ይህ አይነት የኢትዮጵያ መንግስት አቋም የመነጨው መንግስት ከሚከተለው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ነው። ይህ የሚያረጋግጠው የኢትዮጵያ መንግስት ህዝባዊነት በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ለአካባቢው አገሮች ህዝቦች ጭምር መሆኑን ነው።
ከላይ ለማንሳት እንደተሞከረው ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ በውስጥ አቅም የሚገነባ ፕሮጀክት ነው። እስካሁን ባለው ሁኔታ ለግድቡ ግንባታ ከዘጠኝ ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር በላይ ከህብረተሰቡ በስጦታና በቦንድ ሽያጭ ተሰብስቧል። ይህ የሚያሳየው የህዳሴው ግድብ የህዝብ ፕሮጀክት መሆኑን ነው። ይህ ግድብ ከሃይል ማመንጫነቱ ባሻገር በህዝቦች መካከል “የእንችላለን ስሜት” የፈጠረ፤ መተባበር ከቻልን በአጭር ጊዜ ከድህነት መውጣት የምንችልበትን መንገድ ያመላከተ ፕሮጀክት ነው። በተጨማሪም ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦችን አንድነት አጠናክሯል፤ ቁጠባ ባህላችንንም እንዲጎለብት አድርጓል፣ በተፋሰሱ አገራት መካከል መተማመን ፈጥሯል፣ የወንዙንም ዘላቂ ህይወት አረጋግጧል። እንግዲህ ይህን በርካታ ጠቀሜታ ያለውን ፕሮጀክት ከዳር ማድረስ የሁላችንም ሃላፊነት ሊሆን ይገባል።
!
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ መጀመሪያ ያመነጫል ከተባለው የ5250 ሜጋ ዋት አሁን ላይ በእኛው መሃንዲሶች 6450 ሜጋ ዋት ማመንጨት እንዲችል ተደርጓል። ይህ የሆነው በአገር ልጆች በሜቴክ ባለሙያዎች ነው። በታላቁ የህዳሴ ግድብ በተጨማሪ ያተገኘው 1200 ሜጋ ዋት ሃይል ቀድሞ የተገነቡትንና ዓለምን አስገርመው የነበሩትን ሶስቱ ትላልቹ የሃይል ፕሮጀክቶቻችን ማለትም ጊቤ ሁለት፣ ጣና በለስና ተከዜ የሚያመነጩትን የሚያክል ሃይል አስገኝቶልናል። ሜቴክ ችግር ወይም ድክመት የለበትም ማለት ግን አይደለም። አገራችን እንዲህ ላሉ ሜጋ ፕሮጀክቶች መገንባት ጀማሪ ሜቴክም ገና አዳጊ ተቋም ነው። ይሁንና ሜቴክ ከተቋቋመ አጭር ጊዜ ቢሆነውም በርካታ መልካም ነገሮችን ማሳካት የቻለ ተቋም ነው። በህዳሴው ግድብ ላይ የተገኘው ተጨማሪ 1200 ሜጋ ዋት በሜቴክ ጥረት መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ነው። አንዳንዶች በተለይ የዳያስፖራ ፖለቲከኞች ትናንሽ ነገሮችን በማጎን የተቋሙን ገጽታ ለማበላሸት የሚያደርጉት ጥረት አግባብነት የጎደለው አካሄድ ነው። በዕርግጥ ሁሉን ማንቋሸሽና ማጥላላት ከተጠናወተው ሃይል መልካም ነገር መጠበ ጅልነት ነው።