Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

መልካም አስተዳደርን ለማስፈንና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን ለማጎልበት በሚደረገው ጥረት የአስፈጻሚ አካላት ጣልቃ ገብነት ዋነኛ ማነቆ መሆኑን

0 398

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

መልካም አስተዳደርን ለማስፈንና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን ለማጎልበት በሚደረገው ጥረት የአስፈጻሚ አካላት ጣልቃ ገብነት ዋነኛ ማነቆ መሆኑን አንድ ጥናት አመለከተ።መገናኛ ብዙኀን ኃላፊነታቸውን እንዳይወጡና የሕዝብ ምክር ቤቶችና ማኅበራትም ተጽዕኖ ፈጣሪ እንዳይሆኑ የአስፈጻሚ አካላት ጫና ዋነኛ ማነቆ መሆኑ በጥናቱ ተገልጿል።

ጥናቱን ያካሄደው የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል ሲሆን “መልካም አስተዳደርን ከማስፈን አንጻር የሕዝብ ተሳትፎ ማነቆዎች፣ መንስኤዎችና የመፍትሔ ሀሳቦች” በሚል በተደረገው ጥናት ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት ተደርጓል።

ጥናቱን ያቀረቡት በማዕከሉ የአቅም ግንባታና የመልካም አስተዳደር ዘርፍ ከፍተኛ ተመራማሪ ወይዘሮ ውብአምላክ እሸቱ እንደገለጹት በመልካም አስተዳደርና በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ላይ አመራሩ ጋር የሚታይ ክፍተት አለ።

ይህ ደግሞ ሕብረተሰቡን የሚያሳትፉ ምክር ቤቶች፣ መገናኛ ብዙኃን እንዲሁም ሕዝባዊ ማኅበራት እንዳይጠናከሩ አድርጓል ብለዋል።

በሚኒስትር ማዕረግ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አቶ አባይ ፀሐዬ እንደገለጹት መንግሥት ከዚህ ቀደም በልማት፣ በመልካም አስተዳደር ሥራዎች፣ በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሕዝቡን በስፋት ሲያሳትፍ ቆይቷል።ይሁን እንጂ የሕዝቡ ተሳትፎ ጫና ፈጣሪ ባለመሆኑ ማነቆዎችን ለመለየት፣ መንስኤና የመፍትሔ አቅጣጫዎችንም ለማስቀመጥ ታልሞ ጥናቱ መካሄዱን ገልጸዋል።

የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት በሕዝባዊ ማኅበራት፣ በመገናኛ ብዙኀንና በሕዝብ ምክር ቤቶች ላይ በሚያሳድሩት አሉታዊ ጫና የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና የዴሞክራሲ ጥያቄ አጥጋቢ ምላሽ እንደማያገኝ በጥናቱ መረጋገጡን ተናግረዋል።

ምክር ቤቶች፣ መገናኛ ብዙኀንና የሕዝብ ማኅበራት መብቶቻቸውን በተቀመጡ ህጎችና በህገ-መንግሥቱ አግባብ የመጠየቅና ፊትለፊት መጋፈጥ ላይ ክፍተቶች መኖራቸውን አቶ አባይ ገልጸዋል።

ጥናቱ ምክር ቤቱ፣ ማኅበራትና መገናኛ ብዙኀን ከመከሩበት በኋላ ከተሳታፊዎች በተነሱት ሀሳቦች ዳብሮ የጋራ ሀሳብ ሆኖ ለአመራር አካላት ይቀርብና መፍትሔ እንዲያመጣ ሥራ ላይ እንደሚውል አቶ አባይ ገልጸዋል።

ከተሳታፊዎች የተለያዩ ሀሳቦች የቀረቡ ሲሆን በተለይ በሁሉም ዘርፍ የህገ-መንግሥት አስተምህሮ ላይ አለመሰራቱም ሌላኛው ማነቆ መሆኑ ተነስቷል።በጥናቱ ላይ መሻሻል ያሉባቸው የህግ ክፍተቶች መካተት እንዳለባቸውም ተሳታፊዎቹ አንስተዋል።

ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመገንባትና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ተጽዕኖ ፈጣሪ ሚዲያና ሕዝባዊ ምክር ቤቶችና ማኅበራት ተጠናክረው መሄድ እንደሚገባቸውም ተሳታፊዎች ገልጸዋል።

ህገ-መንግሥቱ ያስቀመጣቸውን ዝርዝር የሰብአዊ መብቶች፣ ሌሎችም መብቶች ላይ ግንዛቤ አለመኖር አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል ተብሏል።በውይይቱም የመንግሥት ከፍተኛ አመራሮች፣ ከክልል እስከ ፌዴራል የሕዝብ ምክር ቤቶች፣ ብዙኀን ማኅበራት፣ የመገናኛ ብዙኀን አመራሮች፣ የዴሞክራሲ ተቋማት እንዲሁም የሚመለከታቸው አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።ጥናቱ የተካሄደው በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በትግራይና በደቡብ ክልሎች እንዲሁም በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ሲሆን በአጠቃላይ 727 ሰዎች የጥናቱ ተሳታፊ መሆናቸው ታውቋል ምንጭ፦ ኢዜአ

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy