Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

መምህራን በደመወዝ ስኬል ማስተካከያው ለምን አልተካተቱም?

0 1,109

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

መምህራን በደመወዝ ስኬል ማስተካከያው ለምን አልተካተቱም?  (ቶሎሳ ኡርጌሳ)

 የሀገራችን ፐብሊክ ሰርቪስ ሰራተኞች በሀገራችን እየተመዘገበ ካለው ፈጣንና ተከታታይ ዕድገት በየደረጃቸው ተጠቃሚ መሆን እንዳለባቸው የኢፌዴሪ መንግስት ያምናል። ከዚህ እምነቱ በመነጨም በተለያዩ ወቅቶች ለሰራተኞቹ የደመወዝ ማስተካከያዎችን አድርጓል። ይህም የፐብሊክ ሰርቪስ ሰራተኞች ከዕድገቱ ጋር ተያይዞ በሚፈጠሩ የኑሮ እመርታዎች እንዳይጎዱ ህገ ወጥ ነጋዴዎችን ለመቆጣጠር ከሚያደርጋቸው ጥረቶች  ባሻገር፤ አቅም በፈቀደ መጠን የደመወዝ ስኬል ማስተካከያ በማድረግ ጭምር በተለያዩ ጊዜያት በርካታ ተግባሮችን ሲያከናውን ቆይቷል።

ከእነዚህ ተግባሮች ውስጥ በዕውቀት የደረጁና ሀገር ተረካቢ ዜጎችን የማፍጠር ሙያዊ ሚናን እየተወጡ ለሚገኙት የሀገራችን መምህራን በተለያዩ ጊዜያት ያደረገው የደመወዝ ማስተካከያ ይጠቀሳል። ከቅርብ ጊዜው ማስተካከከያ ብንነሳ እንኳን፤ በሐምሌ 2008 ዓ.ም   ገደማ ለመምህራኑ ያደረገውን የደመወዝ ስኬል ማስተካከያ እናገኛለን። ሆኖም ስለ መምህራኑ የደመወዝ ስኬል ማስተካከያ ከመግለፄ በፊት ለግንዛቤ ይረዳ ዘንድ፤ በደመወዝ ጭማሪ፣ በኑሮ ውድነት ማካካሻና በደመወዝ ስኬል ማስተካከያ መካከል ያለውን ልዩነት ለመግለፅ እሞክራለሁ።

ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ወገኖች የተገኙ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፤ የደመወዝ ጭማሪ ማለት አንድ የፐብሊክ ሰርቪስ ሰራተኛ ከመደበኛ የውጤት ተኮር ምዘናው ውጤት ላይ ተመስርቶ ሰራተኛው ከተመደበበት የስራ ደረጃ የጣሪያ ደመወዝ ሳያልፍ የሚደረግ መደበኛ የእርከን ጭማሪ ነው። ይህም ሰራተኛው ከነበረበት የመነሻ ደመወዝ ወደ ቀጣዩ እርከን እንዲሸጋገር የሚደረግበት አሰራር ነው። የኑሮ ውድነት ማካካሻ ማለት ሰራተኛው በወቅታዊ የገበያ ሁኔታ እንዳይጎዳና የሚደርስበትን ጫና ለመቅረፍ የመንግስትን አቅም ባገናዘበ መልኩ የሚደረግ ማካካሻ ነው። የደመወዝ ስኬል ማስተካከያ ማለት ደግሞ፤ የመንግስትን የመክፈል አቅም ከግምት ውስጥ በማስገባት የፐብሊክ ሰርቪስ ሰራተኛውን ደመወዝን ከገበያው ጋር ለማቀራረብ የሚደረግ ማሻሻያ ነው። መረጃዎች እንደሚያስረዱት፤ ባለፉት አስር ዓመታት ውስጥ የደመወዝ ስኬል ማስተካከያና ማካካሻ በአማካይ ለሶስት ያህል ጊዜያት ተደርጓል። ይህም መንግስት በሰራተኛው ላይ ሊያጋጥሙ ከሚችሉ ወቅታዊ ሁኔታዎች ጋር በተያያዘ በተለያዩ ወቅቶች ማስተካካያዎችንና ማካካሻዎችን ማድረጉን ያስረዳሉ። በመሆኑም በተለያዩ ፅንፈኛ ሚዲያዎች እየተናፈሰ ያለው የመምህራን ደመወዝ ጉዳይ፤ የደመወዝ ስኬል ማስተካከያ እንጂ የደመወዝ ጭማሪ አለመሆኑን ነው።

ታዲያ ይህን እውነታ መሰረት በማድረግ ለመምህራኑ በያዝነው የበጀት ዓመት መጀመሪያ ላይ (በሐምሌ 2008 ዓ.ም) እና በጥር 2009 ዓ.ም የተደረገው የደመወዝ ስኬል ማስተካከያ እንጂ ጭማሪ ጭማሪ አይደለም—የደመወዝ ጭማሪ አንድ ሰራተኛ በተቀመጠው ውጤት ተኮር ምዘና መሰረት የሚከናወን ነውና። እናም በዚህ በኩል የጠራ ግንዛቤ ሊኖረን የሚገባ ይመስለኛል። ምክንያቱም በያዝነው የበጀት ዓመት መንግስት ለሰራተኞቹ የደመወዝ ስኬል ማስተካከያ እንጂ ምንም ዓይነት የደመወዝ ጭማሪ ባለማድረጉ ነው።

በያዝነው የበጀት ዓመት መጀመሪያ ላይ (ሐምሌ 2008 ዓ.ም) የደመወዝ ስኬል ማስተካከያ የተደረገላቸው የፐብሊክ ሰርቪስ ተቋማት ውስጥ፤ መምህራን፣ ዳኞች፣ ዐቃብያነ ህግ፣ የአካዳሚ ሠራተኞች እንዲሁም የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ቀዳሚዎቹ ናቸው። ለእነዚህ ተቋማት በየስድስት ወሩ ጭማሪ ማድረግ ስለማይቻል፤ በጥር ወር 2009 ዓ.ም በተደረገው የደመወዝ ስኬል ማስተካከያ ላይ እንዲካተቱ አልተደረገም። መምህራኑም በእነዚህ ተቋማት ውሰጥ የሚገኙ በመሆናቸው በማስተካከያው ውስጥ ሊካተቱ አልቻሉም። ሌላ ምንም ዓይነት ምክንያት የለውም። በቅርቡ የፐብሊክ ሰርቪስና የትምህርት ሚኒስቴር የስራ ኃላፊዎች በጋራ በሰጡት መግለጫ፤ በተለያዩ ወቅቶች ማስተካከያና ጭማሪ የተደረገላቸው 33 የመንግስት ተቋማት በማስተካከያው አልተካተቱም። ይህ ሁኔታም መንግስት ቀሪዎቹን በመንግስት በጀት የሚተዳደሩ ተቋማትን ከእነዚህ ተቋማት ጋር ለማመጣጠን የተደረገ በመሆኑ ፍትሐዊነቱ አጠያያቂ አይሆንም።

ለመምህራኑ የደመወዝ ስኬል ማስተካከያ ያልተደረገው ከዚህ መሰረታዊ ዕውነታ የመነጨ ብቻ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ የተረጋጋ የመማር ማስተማር ሂደት እንዳይኖር ተግተው የሚሰሩ እንዲሁም በዕውቀት የጎለበቱና የነገ ሀገር ተረካቢ ወጣቶች እንዳይኖራት የሚሹ አንዳንድ ፅንፈኛ ኃይሎች አዛኝ መሳይ ቅቤ አንጓች በመሆን ‘ለመምህራኑ ለምን ደመወዝ አልተጨመረም’ ሲሉ ይደመጣሉ። ይህ ፍላጎታቸውም ለመምህራኑ ከማሰብ የመነጨ አለመሆኑን የትኛውም ወገን የሚገነዘበው ይመስለኛል። ምክንያቱ የፅንፈኞቹ ዓላማ መምህራኑ የተሻለ ኑሮ እንዲኖሩ ከማሰብ በመነጨ ሳይሆን፣ ሀገራችን ውስጥ በእያንዳንዱ ጥቃቅን ጉዳዩች አለመግባባቶች ተፈጥረው ተራ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ካላቸው ቀቢፀ- ተስፋዊ ምኞት አኳያ ስለሚሰሩ ነው። ሆኖም ይህን ፍላጎታቸውን እዚህ ሀገር ውስጥ ሆነው መንግስት ለእነርሱ እያደረገ ያለውን ሁለንተናዊ ተግባር የሚያውቁትና በሚዛናዊ ሁኔታ ሃቁን የሚያገናዝቡት የሀገራችን መምህራን ይቀበሉታል ማለት የሚቻል አይመስለኝም።

እርግጥም የመምህራኑን የሰው ሃብትነ የመቅረፅ ከፍተኛ ኃላፊነት ከግምት ውስጥ በማስገባት ጥቅማ ጥቅማቸውን እያስከበረላቸው መሆኑን የሚገነዘቡ ይመስለኛል። ሌላው ቀርቶ በሐምሌ 2008 ዓ.ም የተደረገላቸው የደመወዝ ስኬል ማስተካከያ ከሌሎቹ የመንግስት ተቋማት ከፍተኛ ልዩነት ያለው መሆኑን ያውቃሉ። እርግጥም ጉዳዩ ለአንባቢዎቼ ይበልጥ ግልፅ ይሆን ዘንድ፤ በማሳያነት በስድስት የመምህራን የደመወዝ ስኬል አኳያ እንዲህ እንመለከተዋለን። በያዝነው የበጀት ዓመት መጀመሪያ ላይ ለመምህራኑ የደመወዝ ስኬል ማስተካከያ ከተደረገላቸው መምህራን ውስጥ የሰርተፍኬት መምህራን ጀማሪ መምህር ተጠቃሽ ናቸው። በዚህ ደረጃ የመምህሩ ደመወዝ ወደ 1 ሺህ 828 ብር ከፍ እንዲል ተደርጓል። በሌሎች ተመሳሳይ ተቋማት ጋር ያለው ክፍያ 1 ሺህ 370 ብር ነው—ይህም የስድስት እርከን ልዩነት ያለው ነው።

ሁለተኛው ማስተካከያ የተደረገላቸው ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ድረስ ያሉት ጀማሪ የዲፕሎማ መምህራን ናቸው። መምህራኑ በበጀት ዓመቱ ወደ 2 ሺህ 404 ብር እንዲያድጉ ተደርጓል። በዚህ ደረጃ በሌሎች ተቋማት ውስጥ ያለው ክፍያ 2 ሺህ 100 ብር ነው። ይህም መምህራኑ ማስተካከያ የሶስት እርከን ልዩነት ያለው መሆኑን ያሳያል። በሶስተኛ ደረጃም ከ9ኛ እስከ 10ኛ ክፍል ጀማሪ መምህር 3 ሺህ 137 ብር እንዲያገኝ ተደርጓል። ሆኖም የመጀመሪያ ዲግሪ በሌሎች ተቋማት ጀማሪ 2 ሺህ 748 ብር መሆኑ ይታወቃል። ይህም የሶስት እርከን ልዩነት አለው። የከፍተኛ መሪ መምህር 8 ሺህ 539 ደመወዝ በሌሎች ተቋማት ተማሳሳዩቹ መካከለኛ አመራሮች (ዳይሬክተር፣ የስራ ሂደት ባለቤት፣ ፅህፈት ቤት ኃላፊ… ወዘተ) የሚያገኙት ግን 7 ሺህ 647 ነው። ይህም ምን ያህል ልዩነት እንዳለው የሚያሳይ ነው።

በአራተኛ ደረጃም በመጀመሪያ ዲግሪ ቴክኒካል ድሮዊንግ መምህር 4 ሺህ 085 ብር እንዲሆን ተደርጓል። በሌሎች ተቋማት ግን ይህ ደረጃ 2 ሺህ 748 ብር ደመወዝ የሚከፈለው ነው። ይህ ልዩነትም የዘጠኝ እርከን ልዩነትን ያሳያል። እንዲሁም በተመሳሳይ ዘርፍ ከፍተኛ መምህር 10 ሺህ 567 ብር እንዲሆን ማስተካከያ የተደረገለት ሲሆን፤ በሌሎች ተቋማት ግን ክፍያው 7 ሺህ 647 ብር ነው። ይህም የዘጠኝ እርከን ልዩነት ያለው መሆኑን ያሳያል። በአምስተኛ ደረጃ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ በመጀመሪያ ዲግሪ በመምህርነት የተቀጠረ ግለሰብ 4 ሺህ 662 ብር እንዲያገኝ ተደርጓል። ይህ ደመወዝ በሌሎች የመንግሥት ተቋማት 2 ሺህ 748 ብር ነው። ልዩነቱም የ12 እርከን ነው። በዚሁ መስክ ከፍተኛ መሪ መምህር- III 11 ሺህ 720 ብር ደመወዝ እንዲያገኝ ሲደረግ፤ ደመወዙ በተመሳሳይ ደረጃ ላይ ባሉ ተቋማት ውስጥ ያሉ እንደ መካከለኛ አመራር (ዳይሬክተር፣ የስራ ሂደት ባለቤት፣ የፅህህፈት ቤት ኃላፊ… ወዘተ.) 7 ሺህ 647 ብር ያገኛሉ። ልዩነቱም ከአስር ይህ እርከን በላይ ነው።

በስድስተኛ ደረጃም መሰናዶ ትምህርት ቤት 2ኛ ዲግሪ ያለው ጀማሪ መምህርን ስንመለከት በአምናው ማስተካከያ 4 ሺህ 269 ብር እንዲያገኝ ተደርጓል። በአንፃሩ 2ኛ ዲግሪ ያለው ጀማሪ ሠራተኛ በሌሎች ተቋማት ውስጥ የሚያገኘስው 3 ሺህ 137 ብር ነው። ይህም የሰባት እርከን ልዩነትን ያሳያል። ከዚህ በተጨማሪ ከፍተኛ መሪ ርዕሰ መምህር በማስተካከያው 12 ሺህ 112 ብር እንዲያገኝ የተደረገ ሲሆን፤ በተመሳሳይ ደረጃ በሌሎች መንግሥት ተቋማት ውስጥ ያሉት መካከለኛ አመራሮች (ዳይሬክተር፣ የስራ ሂደት ባለቤት፣ የፅህፈት ቤት ኃላፊ… ወዘ.) የሚያገኙት ግን 7 ሺህ 647 ብር ነው። ልዩነቱም ከአስር እርከን በላይ መሆኑን ለመገንዘብ አያዳግትም።

እነዚህ ስድስት ማሳያዎች መንግስት ትውልድን በመቅረፅ ታላቅ ተልዕኮ ላላቸው መምህራን የሰጠውን ቀዳሚ ቦታ የሚያሳዩ ናቸው። በዚህም መንግስት የመምህራኑን የኑሮ ደረጃ አቅም በፈቀደ መጠን ለማገዝና መምህራኑም የተሰጣቸውን ኃላፊነት በትጋትና በሀገራዊ ስሜት መንፈስ እንዲያከናውኑ ያደርጋል። ከዚህ በተጨማሪ፤ መንግስት የመምህራኑን የቤት ችግር ለመቅረፍ አምስት ሺህ መምህራን በዕጣ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በኪራይ መልክ አስተላልፏል። አቅም በፈቀደ መጠንም የትራንስፖርት ችግራቸውን ለማቃለል ጥረት እየተደረገ ነው። ይህ ሁኔታም ወደፊት ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል። እርግጥ ይህ በመንግስት ለመምህራን የተሰጠው ትኩረት ተገቢና ትክክል መሆኑ የሚያጠያይቅ አይመስለኝም። ምክንያቱም ትውልድን የመቅረፅ ታላቅ ተልዕኮ የተረከቡት መምህራን በችግር ውስጥ ሆነው ተግባራቸውን መወጣት ስለሌለባቸው ነው።

በእኔ እምነት መምህራኑም ይህን የመንግስት ጥረት በማገዝ የሀገራቸውን ህዳሴ በማረጋገጥ ግንባር ቀደም ተዋናይ መሆን ይኖርባቸዋል። በተለይም ለኢትዮጵያ ህዳሴ የራሳቸውን አስተዋፅኦ ማበርከት የሚችሉ ብቁና ተወዳዳሪ ዜጎችን ለማፍራት ወሳኝ ሚናቸውን ማሳረፍ አለባቸው። አዲሲቷ ኢትዮጵያ በሁሉም ዜጋ የምትታነፅ በመሆኑ ሁሉም ዜጋ የበኩላቸውን ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸው አያጠያይቅም። ከዚህ አኳያ መምህራን  የሀገሪቱን ትውልድ የመቅረፅ ከፍተኛ ሀገራዊ ተልዕኮን የተረከቡ ዜጎች ስለሆኑ፤ ከምንጊዜውም በላይ በኢትዮጵያ ህዳሴው ጉዞ የሚያሳርፉትን አሻራ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ እምነቴ የፀና ነው።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy