Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

መሬት ያጣውን ነገር መልሰን የማንሞላ ከሆነ ያለውንም ጨርሶ ያጣል

0 577

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በመቶዎች የሚቆጠሩ ጐብኚዎች ለዓይን የሚስበውን የሽንኩርት ማሳ  በአድናቆት ይመለከታሉ፡፡ ለአርሶ አደሩ ታደሰ ይመር ግን ማሳው የጠበቁትን ያህል አልነበረም፡፡ እንዲያውም አንዳንድ በቀላሉ ሊስተካከሉ የሚገባቸው፣ ነገር ግን በቸልተኝነት የታለፉ ችግሮችን አስተውለዋል፡፡አቶ ታደሰ በደሴ አካባቢ በምትገኘው ለጋምቦ ወረዳ ገነቴ 08 ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ በአንድ የምርት ወቅት ከወጪ ቀሪ እስከ 150 ሺሕ ብር እንደሚያገኙ ይናገራሉ፡፡ የጐላ ችግር ሆኖ ዛሬ ለደረሱበት ደረጃ ከመድረስ ባይገታቸውም የኔ የሚሉትና የሚያለሙበት መሬት የላቸውም፡፡

መሬት ተከራይቶ ማልማት የጀመሩት ከዓመታት በፊት ነው፡፡ አንድ ሔክታር መሬት በዓመት 3 ሺሕ ብር ተከራይተው የተለያዩ የጓሮ አትክልቶችን ያለማሉ፡፡ ‹‹ያልቻሉ ናቸው የሚያከራዩኝ›› ሲሉ ከመሬቱ የሚያገኙት ጥቅምና የሚከራዩበት ዋጋ የሰማይና የምድር ያህል እንደሚለያይ ይናገራሉ፡፡በአራት ሔክታር መሬት ላይ እንደ ቃሪያ፣ ሽንኩርት፣ቲማቲም፣ ጐመን ያሉ የጓሮ አትክልቶችን ያለማሉ፡፡ ከችግኝ ጀምሮ ተገቢው እንክብካቤ ከተደረገ ጥሩ ምርት ማግኘት እንደሚቻል ያምናሉ፡፡ አሁን ላይ አንድ ሳጥን ቲማቲም ከ500 እስከ 600 ብር ድረስ ይሸጣሉ፡፡ ‹‹በጥሩ ሁኔታ ከተያዘ ከአንድ እግር ቲማቲም የምስራች ከሰጠበት እስከ ጠረጋ ባለው ጊዜ ሁለት ሳጥን መሰብሰብ ይቻላል፤›› ይላሉ፡፡ ይሁንና ብዙዎች በግንዛቤ ማነስ በዚህ መጠን አያገኙም፡፡

80 በመቶ የሚሆነው የአገሪቱ ሕዝብ በግብርና የሚተዳደር ነው፡፡ 46.3 በመቶ የሚሆነው የአገሪቱ ጠቅላላ ዓመታዊ ምርት፣ 83.9 በመቶ የሚሆነው አጠቃላይ የወጪ ንግድም ከዚሁ ከግብርናው ዘርፍ የሚገኝ እንደሆነም መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ድርቅ፣ የአፈር መሸርሸር፣ የደን መጨፍጨፍ፣ ከመጠን ያለፈ ግጦሽና የመሳሰሉት የአገሪቱ ግብርና የትም እንዳይደርስ ማነቆ ሆነው የቆዩ ችግሮች ናቸው፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች የመስኖ እርሻ እየተለመደ ቢሆንም ግብርናው በዝናብ ላይ የተመሠረተ መሆኑም ሌላው ችግር ነው፡፡

ለዚህም የዝናብ እጥረት በተከሰተባቸው ወቅቶች በአገሪቱ የተከሰቱትና ታሪክ የማይዘነጋቸው ድርቆችና ረሃብ ማሳያ ናቸው፡፡ የዝናብ እጥረት ሲከሰት ለወትሮው ለምለም የነበሩ ማሳዎች ባዷቸውን ይቀራሉ፡፡ ሚሊዮኖችን የሚመግበው አርሶ አደሩ የሚላስ የሚቀመስ አጥቶ በረሃብ ይሰቃያል፡፡በእነዚህ የድርቅ ወቅቶች የሚራቡት ሰዎች ብቻ አይደሉም፡፡ የሚግጡት ሳር፣ የሚጠጡት ውኃ ያጡ ከብቶችም እንደ ቅጠል ረግፈዋል፡፡ ማገገም እስኪያቅታቸው በአጥንታቸው ቀርተዋል፡፡ ለዚህም በ1977 ዓ.ም. ድርቅና በረሃብ ያለቁትን፤ ባለፈው ዓመት በነበረው ኤሊኖ የተራቡ ወገኖችም ምስክር ናቸው፡፡

በአሁኑ ወቅት አርሶ አደሩን በዝናብ ላይ ከተመሠረተው ግብርና ለማላቀቅ በተደረጉ ጥረቶች አንዳንድ መሻሻሎች መታየት ጀምረዋል፡፡ በተሠሩት ሥራዎች ባለፉት 15 ዓመታት ውስጥ የአገሪቱ አጠቃላይ ግብርና 8 በመቶ ዕድገት እያሳየ መምጣቱን፣ የአገሪቱ የሰብል ሽፋንም 12 ሚሊዮን ሔክታር መድረሱን፣ የአገሪቱ የግብርና ምርት መጠንም 270 ሚሊዮን ኩንታል መግባቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ 8ኛው አገር አቀፍ የአርሶና አርብቶ አደሮች በዓል ባሳለፍነው ሳምንት በአዳማ በተከበረበት ወቅት ገልጸዋል፡፡

ምንም እንኳን የአገሪቱን ግብርና ለማሻሻል በተደረገው ጥረት የማይናቅ ለውጥ ማስመዝገብ ቢቻልም፣ የባለድርሻዎችን ርብርብ የሚጠይቁ፣ የዘርፉን ዕድገት ወደኋላ እየጐተቱ ያሉ ችግሮች ይስተዋላሉ፡፡ በኢትዮጵያ ግብርና የአፈርን ለምነት ከማስጠበቅ ጀምሮ የተለያዩ ችግሮች መኖራቸው ይታወቃል፡፡መሬት የሚዘራበትን ተክል በተገቢው መጠን ማብቀል የሚችለው በውስጡ አስፈላጊ የሚባሉ ንጥረ ነገሮች ሲኖሩት ነው፡፡ በተደጋጋሚ ማረስ፣ ከአቅም በላይ የሆነ ግጦሽ፣ ማዕድናትን የሚይዘውን የአፈሩን ክፍል ከአገዳዎች ጋር ነቅሎ ማንሳትና የመሳሰሉት የአፈር ለምነትን የሚያሳጡ ነገሮች መሆናቸውን በእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር የአፈር ለምነት ማሻሻያ ፕሮጀክት መሪው አቶ ደረጀ ረጋሳ ይናገራሉ፡፡

‹‹መሬት ያጣውን ነገር መልሰን የማንሞላ ከሆነ ያለውንም ጨርሶ ያጣል›› የሚሉት አቶ ደረጀ፣ የአፈረን ለምነት ለመመለስ ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ ማዳበሪያዎች በጥቅም ላይ እንደሚውሉ ይናገራሉ፡፡ ተፈጥሯዊ ማዳበሪያዎች የሚባሉት እንደ ኮምፖስትና የእጽዋት ቅሪት ሲሆኑ፣ ሰው ሠራሽ የሚባሉት ደግሞ አርሶ አደሩ በስፋት የሚጠቀማቸው ዩሪያና ዳፕ በአሁኑ ወቅት ኤንፒኤስና ናይትሮጂን በሚባሉ ማዳበሪያዎች የተተኩ ናቸው፡፡በስፋት ጥቅም ላይ ከሚውሉት ማዳበሪያዎች አጠቃቀም ጋር በተያያዘም የተለያዩ ችግሮች ይስተዋላሉ፡፡ ዋናው የአንድ አካባቢ አፈር ምን ዓይነት ማዳበሪያ እንደሚፈልግ ጥናት አድርጐ ተገቢውን ማዳበሪያ ከመጠቀም ጋር ያለው የአሠራር ክፍተት ነው፡፡

በተለያዩ አካባቢዎች ያሉት አፈሮች ይዘት የተለያየ ነው፡፡ ለዚህም በዘፈቀደ ማዳበሪያ ከመጠቀም በፊት አፈሩን በላቦራቶሪ ማስመርመርና ምን ዓይነት ማዕድን እንደሚፈልግ ለይቶ ማወቅ ግድ ይላል፡፡ እንዲህ ያለው ዘመናዊ አሠራር በአሁኑ ወቅት ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል፡፡ ይሁንና ምን ያህሉ አርሶ አደሮች ይጠቀሙበታል የሚለው ጉዳይ አጠያያቂ ነው፡፡

የሚጠቀሙት የማዳበሪያ ዓይነትና መጠን እንደ መሬቱና እንደሚያለሙበት የምርት ዓይነት ይለያያል፡፡ አርሶ አደር እሸቱ በዳኔ ዝዋይ አቅራቢያ በሚገኘው ቆቃ አካባቢ ነዋሪ ናቸው፡፡ በአካባቢያቸው ለሚገኘው የማዳበሪያ መጋዘን ኃላፊ ናቸው፡፡ ‹‹በአንድ ወቅት ተከስቶ የነበረው የማዳበሪያ ችግር በአሁኑ ወቅት የለም፡፡ በቂ የሚባል አቅርቦትም አለ፡፡ የዋጋውን ጉዳይ ግን ምንም ማድረግ አይቻልም›› ይላሉ፡፡

አንድ ኩንታል ዳፕ 1,400 ብር ይሸጣል፡፡ አንድ ሔክታር ሽንኩርት ለማልማት ቢያንስ 4 ኩንታል ማዳበሪያ እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ፡፡ ይህ ግን ከዘርና ፀረ ተባይ ዋጋ አንጻር ሲታይ በጣም ቀላሉ ነው፡፡ጐመን፣ ቲማቲም፣ ቃሪያ፣ ሽንኩርት የመሳሰሉት አትክልቶች በተደጋጋሚ ጊዜ በተባይ ይጠቃሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ሽንኩርትን የሚያጠቁ ትሪፕስ፣ ፐርፕል ብሎጅ የተባሉ በሽታዎች አሉ፡፡ በ2005 ዓ.ም. በሱዳን በኩል እንደገባ የሚነገርለት ቱታ አፕስሉታ የሚባል ቲማቲምን የሚያጠቃ በሽታ አለ፡፡ በሽታው በአሁኑ ወቅት ላለው ዝቅተኛ የቲማቲም ምርት ምክንያት ነው፡፡ በእነዚህ አትክልቶች ላይ የሚከሰቱትን በሽታዎች መከላከያ ፀረ ነፍሳትና የፈንገስና የተለያዩ በሽታዎች መድኃኒቶች አሉ፡፡ ለምሳሌ ቱታአፕስሉታ ራዲያንት፣ አምብራጐና ከራጂን የሚባሉ ፀረ ተባዮች አሉ፡፡

የ45 ዓመቱ አርሶ አደር እሸቱ ከኃላፊነታቸው ጐን ለጐን ባላቸው 3 ሔክታር መሬት ላይ ሽንኩርትና ቲማቲም እንደሚያለሙ ይናገራሉ፡፡ ‹‹ፀረ ተባይ ለማግኘት ትልቅ ችግር አለ›› የሚሉት አርሶ አደሩ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የፀረ ተባይ ዋጋ የማይቀመስ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ከዚህ ቀደም በሊትር ከ50 እስከ 100 ብር ይሸጡ የነበሩ ፀረ ተባዮች 700 ብር እየተሸጡ ነው፡፡ ይህ ቀላል የሚባለው ለሽንኩርት ምርት የሚጠቀሙት የፀረ ተባይ ዋጋ ነው፡፡ በጣም የሚወደደው ለቲማቲም የሚጠቀሙት ፀረ ተባይ ሲሆን በሊትርም 5 ሺሕ ብር ነው፡፡

እሳቸው እንደሚሉት፣ 1 ሔክታር ሽንኩርት ለማልማት ከ30 ሺሕ እስከ 40 ሺሕ ብር ለፀረ ተባይ ግዥ ያወጣሉ፡፡ ለቲማቲም ደግሞ ከነጉልበት ሲታሰብ በሔክታር ከ100 ሺሕ ብር በላይ ይፈጃል፡፡ እንደዚህ ከፍተኛ ወጪ አውጥተው የሚሸምቷቸው መድኃኒቶች ሁልጊዜ ውጤታማ አይሆኑም፡፡ ፀረ ተባዩን አልፈው የሚከሰቱ በሽታዎች ያጋጥሟቸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በገበያ ላይ ለተከሰተው የቲማቲም ምርት አቅርቦት እጥረት ምክንያትም ይኸው መሆኑን አቶ እሸቱ ይናገራሉ፡፡ ‹‹ፀረ ተባዩ በሽታውን መቆጣጠር አልቻለም፡፡ ለምን እንደሆነ አልታወቀም›› በማለትም በውድ ዋጋ የገዙት ፀረ ተባይ የዘሩትን የቲማቲም ምርት ከተባይ ሳያተርፍላቸው ቀርቶ ለኪሳራ እንደዳረጋቸው ይናገራሉ፡፡

የመስኖ እርሻ ባለሙያው አቶ ዳዊት አሰግድ እንደሚሉት፣ ከፍተኛ የፀረ ተባይ እጥረት አለ፡፡ ከውጭ የሚገቡበት ዋጋም ውድ የሚባል ነው፡፡ ለገበሬው የሚደርሱት በዩኒየኖች በኩል ነው፡፡ ይሁንና አርሶ አደሩ በሚፈልገው መጠን እየቀረበለት አይደለም፡፡ ‹‹ለምሳሌ በኦሮሚያ በሎሜ ወረዳ ራዲያንትና ኮራጂን የሚባሉት ፀረ ተባዮች በሊትር እስከ 8 ሺሕ ብር እየተሸጡ ይገኛሉ፡፡ በማዳበሪያ አቅርቦት ድርጅት የሚሸጡበት ዋጋ ግን 2,900 ብር አካባቢ ነው›› በማለት እጥረት በመኖሩ ከመደበኛ ዋጋቸው በሦስት እጥፍ እየተሸጡ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

ይህ የፀረ ተባይ እጥረት ሰፋፊ እርሻ ላላቸው ባለሀብቶች ደግሞ ትልቅ ችግር እየሆነ ይገኛል፡፡ አቶ ደረጀ በርሄ፣ በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል በ400 ሔክታር መሬት ቦታ ላይ ሰሊጥ፣ አኩሪ አተር፣ በቆሎ፣ ቲማቲም፣ ሽንኩርት፣ ቃሪያና ጐመን ያመርታሉ፡፡ አጠቃላይ ካፒታላቸውም 24 ሚሊዮን ብር ደርሷል፡፡ በ8ኛው አገር አቀፍ የአርሶና አርብቶ አደሮች በዓል ላይም ሞዴል አርሶ አደር ሆነው ተሸልመዋል፡፡

ለሥራው ‹‹የተለያዩ ፀረ ተባዮችን ማግኘት አስቸጋሪ ነው፡፡ ትንሽ ግራም ኬሚካል 4 ሺሕ እና 5 ሺሕ ብር እየገዛን ነው፡፡ ብዙ ሔክታር መሬት ላይ ለመሥራት ወጪው እንዴት ይቻላል?›› ሲሉም ይጠይቃሉ፡፡‹‹ኬሚካሎቹ በነጋዴዎች እጅ ናቸው፡፡ ገበያው ላይ አርቴፊሻል እጥረት እንዲከሰት በማድረግ ዋጋው ጫፍ ሲነካ አውጥተው በውድ ዋጋ የሚሸጡም አሉ፡፡ አማራጭ ስለሌለን እነሱ ባሉበት ዋጋ እንገዛለን›› ይላሉ አቶ ደረጀ፡፡ ለተለያዩ ኬሚካሎች ግዢ በሔክታር ከ10 እስከ 15 ሺሕ ብር ያወጣሉ፡፡ የማዳበሪያ አቅርቦት ችግር እንዳለም ገልጸዋል፡፡ ወቅቱን የጠበቀ የማዳበሪያ አቅርቦት ባለመኖሩ ወደ ሌላ የአገሪቱ ክፍል ሄደው ማዳበሪያ ለመሸመት እንደሚገደዱም ተናግረዋል፡፡

በ8ኛው አገር አቀፍ የአርሶና አርብቶ አደሮች በዓል ዋዜማ ከአርሶ አደሮች ጋር በተደረገው ውይይት የበርካቶች ጥያቄ የነበረው የፀረ ተባይ ኬሚካሎች አቅርቦት ጉዳይ ነበር፡፡በፀረ ተባይ አጠቃቀም ረገድ ከፍተኛ የግንዛቤ ችግር መኖሩንም በዕለቱ የተገኙ ባለሙያዎች ተናግረዋል፡፡ ኬሚካሎች መቼና እንዴት መረጨት አለባቸው? ከሚለው ጀምሮ የተለያዩ ክፍተቶች መኖራቸው በውይይቱ ከተነሱ ጉዳዮች ይጠቅሳሉ፡፡ ለአንደኛው የተዘጋጀውን ኬሚካል ለሌላው የመጠቀም ሁኔታ አለ፡፡ ከዚህም ሌላ ተቀናጅቶና ተነጋግሮ በመሥራት ዙሪያም ችግር መኖሩ ተነግሯል፡፡

በዚህ ረገድ ኩታገጠም በሆኑ የእርሻ ማሳዎች ላይ ያለው ተናቦ የመሥራት ችግርም በምሳሌነት ተነስቷል፡፡ አንደኛው አርሶ አደር ኬሚካል በሚረጭበት ጊዜ ሌላኛው በአቅም ማነስ አልያም በሌላ ምክንያት ሳይረጭ ይቀራል፡፡ ይህም ታጥቦ ጭቃ እንዲሉ ተባዮች ኬሚካሉ ካልተረጨበት እርሻ ላይ ወደ ተረጨበት እንዲዛመቱ የሚያደርግ ነው፡፡

በገበያ ላይ ያሉት ኬሚካሎች የተላመዱ መሆናቸውን በመጥቀስ በሌላው ዓለም በጥቅም ላይ እየዋሉ ያሉ ሌሎች አዳዲስ ኬሚካሎች እንዲመጡ የጠየቁም አሉ፡፡ ምርት ከችግኝ ጀምሮ እስከ ምርት ደረጃ እስኪደርስ ወቅቱን ጠብቆ ፀረ ተባይ መረጨት ይኖርበታል፡፡ ይሁንና ከአንዳንድ አርሶ አደሮች በስተቀር አብዛኛዎቹ በዘፈቀደ እንደሚጠቀሙና እንደሚያባክኑ አቶ ዳዊት ተናግረዋል፡፡ በዕለቱ የጥራት ችግር ያለባቸው ፀረ ተባዮች ወደ አገሪቱ እየገቡ በነጋዴዎች እጅ እየተቸበቸቡ እንደሆነም ተነግሯል፡፡ ለዚህም የቁጥጥር መላላት የችግሩ መነሻ እንደሆነ፣ መንግሥትም ተገቢውን ትኩረት እንዲያደርግበት ከታዳሚዎች አስተያየት ተሰጥቷል፡፡

ፀረ ተባይ መጠቀም የመጨረሻው አማራጭ አለመሆኑን በመጥቀስ ሌሎች አማራጮችን መሞከር አስፈላጊ መሆኑን የሚናገሩም አሉ፡፡ እነዚህ ወገኖች ከዚህ ቀደም የነበሩ አርሶ አደሮች ይጠቀሙባቸው የነበሩትን አሠራሮች በማጐልበት ፀረ ተባይና ፀረ አረም ኬሚካሎችን ማስቀረት እንደሚቻል የሚያምኑ ናቸው፡፡ አርሶ አደሩ ከችግኝ ጀምሮ እስከ ምርት ድረስ የዘራውን በእጁ ማረም አለበት፡፡ ተባዮችን ለመከላከል ደግሞ ሰብል የማይነኩ ነገር ግን ተባዮቹን የሚመገቡ ተባዮችን በማሳ ውስጥ ማሰራጨት ዓይነተኛ መፍትሔ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ይህኛው ዘዴ በተለያዩ ቦታዎች ተሞክሮም ውጤታማ ሆኗል፡፡

ከዚህ ባለፈም የተባይ መምጫ አቅጣጫን ለይቶ ማወቅና መከላከልም አዋጭ እንደሆነ በውይይቱ የተገኙ ባለሙያዎች ተናግረዋል፡፡ በሌላ በኩልም ተገቢው ምርመራ ያልተደረገባቸው ዘሮች በተለያዩ አጋጣሚዎች ወደ አገሪቱ እየገቡ እንደሚገኙ፣ ይህም ለተባይና ለአረም በሽታ መስፋፋት አንዱ መንገድ እንደሆነና በዚህ ረገድ ያለው ቁጥጥር መጥበቅ እንዳለበት አስተያየታቸውን አንፀባርቀዋል፡፡

የፀረ ተባይ አጠቃቀም ችግር በአገሪቱ ጊዜ ያለፈባቸው ኬሚካሎች ከፍተኛ ክምችት እንዲኖር አድርጓል፡፡ እነዚህን ኬሚካሎች ለመግዛት ከፍተኛ ዋጋ የወጣ ሲሆን፣ ለማስወገድ የሚወጣው ደግሞ ከተገዛባቸው የበለጠ እንደሆነ ይነገራል፡፡ከዘር አቅርቦት ጋር በተያያዘ ያለውን ችግር ለመፍታትም የተለያዩ ዘሮች እዚሁ አገር ውስጥ የሚባዙበት ሁኔታ ቢመቻች በገበሬው ምርታማነት ላይ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው፣ መንግሥትም ትኩረት አድርጐበት እንዲሠራ ከባለሙያዎች ሐሳብ ቀርቧል፡፡

በዕለቱ የተገኙት የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር የእርሻና ሰብል ዳይሬክተሩ አቶ አብዱልሰመድ አብዶ፣ አርሶ አደሮች በተለያዩ ምክንያቶች በእኩል መጠን እያመረቱ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ ‹‹አንዱ በአንድ ሔክታር መሬት 90 ኩንታል ያመርታል ሌላው ደግሞ ከዚያ በታች ያመርታል፡፡ ይህንን ለማስተካከል በተደረገው ጥረት የተሳካው 22 በመቶ ብቻ ነው›› ብለዋል፡፡ ለዚህም የተለያዩ ምክንያቶች አሉ፡፡ ሰብሎች መዘራት በማይገባቸው ቦታዎች ሲዘሩ በሽታን የመከላከል አቅማቸው ይቀንሳል፡፡ ሌላም የተለያዩ የአሠራር ክፍተቶች በምርታማነት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ያሳድራሉ፡፡

ነገር ግን ባለው የግንዛቤ ችግር አለምንም ቅድመ ሁኔታ በዘፈቀደ የሚያርሱ አሉ፡፡ እንዲህ ባሉ ክፍተቶች የሚከሰቱ ችግሮችን ለመከላከል የሰብል በሽታ ከመድረሱ አስቀድሞ ክትትል ማድረግና በእንጭጩ መቅጨት የሚቻልበት ዕድል አለ፡፡ ችግሩ ከተከሰተ በኋላም በቀላሉ እንዴት ማጥፋት እንደሚቻል የሚያመለክቱ በዝርዝር የተቀመጡ አሠራሮች አሉ፡፡ ‹‹ነገር ግን ተግባራዊ ማድረግ ላይ ችግር አለ›› ብለዋል አቶ አብዱልሰመድ፡፡

የአገሪቱ የምርት መጠን እንዲያድግ ከግብርናው ዘርፍ ከፍተኛ ምርምር መደረግ አለበት የሚሉም አሉ፡፡ ‹‹ምርምር ካልተደረገ እንደ አባቶቻችን በግምት ነው የምንሠራው›› የሚሉት አርሶ አደሩ አቶ ደረጀ፣ ለምሳሌ አኩሪ አተር በሔክታር ከ15 እስከ 16 ኩንታል እንደሚወጣ፣ ነገር ግን ምርምር ተደርጐበት መሻሻል ቢችል የምርት መጠኑ በእጥፍ ሊያድግ እንደሚችል እምነታቸውን ይገልጻሉ፡፡

ሌላው የተለያዩ ለእርሻ የሚሆኑ ማሽነሪዎችን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ያሉትን ውጣ ውረዶች በተመለከተ የቀረበው ቅሬታ ነው፡፡ አንድ ማሽን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ከ6 ወር እስከ ዓመት እንደሚፈጅና ይህም ከአቅም በታች እንዲያመርቱ እንዳስገደዳቸው አርሶ አደሮቹ ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡ እንደ አቶ ታደሰ ያሉ አርሶ አደሮችም ባለው የመሠረተ ልማት ግንባታ ችግር ምክንያት ምርት ለገበያ ለማቅረብ እንደሚቸገሩ፣ ግማሽ ክፍያ ከፍለው የጭነት መኪና የሚያገኙበት ዕድል ቢመቻችላቸው መልካም እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy