NEWS

መንግስት ያመቻቸውን የስራ እድል በአግባቡ በመጠቀም ሚሊየነር መሆን ይቻላል ወጣት ሞዴል አርሶ አደሮች

By Admin

March 14, 2017

መንግስት በመደበው ከፍተኛ በጀት የተመቻቸውን የስራ እድል በአግባቡ በመጠቀም ሚሊየነር መሆን እንደሚቻል በተግባር ያረጋገጡ ወጣት ሞዴል አርሶ አደሮች ተናገሩ፡፡ወጣት ዘውዱ ዓለሙ በስምንተኛው አገር አቀፍ የሞዴል አርሶአደሮች ፌስቲቫል ከጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ እጅ የሜዳሊያ ሽልማት ከተቀበሉ ሚሊዮነር ወጣት አርሶ አደሮች መካከል አንዱ ነው ።

እስከ 10ኛ ክፍል ድረስ ተምሮ ውጤት ስላልመጣለት ወደ ግብርና ስራ መሰማራቱን ገልጿል፡፡በአንድ በኩል የግብርና ስራውን ጎን ለጎን ደግሞ የእንስሳት እርባታውን አቀናጅቶ በማከናወን በአጭር ጊዜ ውስጥ  9 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ሀብት ማፍራት እንደቻለ ለኢዜአ በሰጠው አስተያየት ተናግሯል፡፡

ከሰሜን ሸዋ ዞን ቅንብቢት ወረዳ በስኬቱ ለአገር አቀፍ ሽልማት የበቃው ወጣት ዘውዱ 50 ለሚጠጉ ወገኖቹ የስራ እድል ፈጥሯል፡፡ወጣቶች ሀብት አፍርተው እሱ የደረሰበት ደረጃ ደርሰው የማየት ፍላጎት እንዳለው ያመለከተው ወጣት ዘውዱ ” ስራ በመፍጠርና  ጠንክሮ በመስራት ሀብት ማፍራት እንደሚቻል በተግባር አይቼዋለሁ፤ የእድሜ እኩዮቼም  እንደኔ እንዲሆኑ እመኛለሁ “ብሏል፡፡

ከባሌ ዞን ጊኒር ወረዳ 7 ሚሊዮን ብር ሀብት በማፍራቱ ተመልምሎ ለሽልማት የበቃው ወጣት አርሶ አደር ሰለሞን ደገፋ በበኩሉ በመስመር መዝራትን ጨምሮ የተለያዩ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በአግባቡ በመጠቀም ለስኬት መብቃቱን ተናግሯል ።

ከእርሻው ስራ በተጓዳኝ በከተማ የመኖሪያ ቤትና ሁለት መጋዘኖች ገንብቶ ወደ ንግድ መግባቱን ገልፆ “ወጣቶች መንግስት የሚፈጥርላቸውን የስራ እድል በአግባቡ ከተጠቀሙበት ስኬታማ መሆን እንደሚቻል ከእኛ ማረጋገጥ ይችላሉ” ብሏል ።” የወጣት ሞዴል አርሶ አደሮች ስኬት ማስፋት ከተቻለ በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ ወጣት ስራ ፈጣሪዎች ሲሸለሙ ማየት እንደምንችል እርግጠኛ ነኝ ” ብሏል፡፡

ከምስራቅ ሸዋ ዞን ዞን አዳሚ ቱሉ ወረዳ ተመልምሎ የሜዳሊያ ተሸላሚ የሆነው ወጣት አርሶ አደር ሹሚ ዱቤ  በበኩሉ  በግብርና ስራ የ8 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ባለሃብት መሆን እንደቻለ ተናግሯል፡፡”  የስራ እድል የፈጠረላቸው ከአስር የማያንሱ  ወጣቶች የስኬቴ ሚስጢር ናቸው ” በማለት ይገልፃቸዋል ።

ተምረው ቤት የተቀመጡ በርካታ ወጣቶች የስራ እድል ከተፈጠረላቸው ተአምር እንደሚሰሩ የሚገልፀው  ወጣት ሹሚ በአንድ በኩል መንግስት እድሉን ሊፈጥርላቸው በሌላ በኩል ደግሞ ወጣቶቹ እድሉን በአግባቡ ተጠቅመው ከልብ መስራት እንዳለባቸውም ጠቁሟል፡፡በተለይ የከርሰ ምድር ውሃን የሚጠቀሙና የመስኖ ልማትን የሚመርጡ ወጣቶች ጠንክረው ከሰሩ ስኬታማ እንደሚያደርጋቸውም ጠቁሟል።

መንግስት  ከፍተኛ በጀት በመመደብ ለይቶ ያመቻቸው  የስራ እድል በአግባቡ በመጠቀም ሚሊየነር መሆን እንደሚችል ወጣት ሞዴል አርሶ አደሮቹ የራሳቸውን የተግባር ውጤት በማመላከት ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝ ለሞዴል አርሶአደሮች ሽልማት በሰጡበት ወቅት  ባስተላለፉት መልእክት መንግስት በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሴቶችና ወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር እየተረባረበ መሆኑን ተናግረዋል ።በተለይም የወጣቶች ዘመናዊ የግብርና ልማት ተሳትፎ በአግባቡ ከተመራ የግብርናው ዘርፍ በማዘመን ታሪካዊ ተልእኮ የሚፈፅም እንደሚሆንም ገልፀዋል ።