Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

መግባባት ያልታየበት የኢህአዴግና የተቃዋሚ ፓርቲዎች ውይይት

0 365

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ኢህአዴግ በአገር አቀፍ ከሚገኙ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች እና ፓርቲዎቹ በሚኖራቸው የመወያያ አጀንዳዎች ላይ ለመደራደር የሚያስችላቸው ቅድመ ሁኔታዎች ላይ መወያየት ከጀመሩ ሁለት ወራት ተቆጥረዋል። ፓርቲዎቹ ድርድሩ በምን መንገድ መካሄድ እንዳለበት የየራሳቸውን ሃሳብ በጽሑፍ በማቅረብ ወደ አንድ አቋም ለመድረስም በተለያየ ጊዜ ውይይት አድርገዋል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፓርቲዎቹ የካቲት 30 ቀን 2009 ዓ.ም አድርገውት በነበረው ስብሰባ በይደር አቆይተውት የነበረውን «ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከኢህአዴግ ጋር በተናጠል ወይስ ፓርቲዎቹ በሚወክሏቸው ሰዎች ሃሳቦቻቸውን አቅርበው ውይይት ይደረግ በሚልና ፓርቲዎቹ ከኢህአዴግ ጋር የሚያደርጉት ድርድር በገለልተኛ ወይስ እራሳቸው ፓርቲዎቹ በየተራ ድርድሩን ይምሩት» በሚሉ ጉዳዮች ላይ ትናንት ውይይት ተደርጓል።

የመጀመሪያ አጀንዳ በሆነው ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከኢህአዴግ ጋር በተናጠል ወይስ ፓርቲዎቹ በሚወክሏቸው ሰዎች ሃሳቦቻቸውን አቅርበው ውይይት ይደረግ የሚለው ጉዳይ ላይ ሰፋ ያለ ክርክር በጧቱ መርሐግብር ተደርጓል። በአጀንዳው ላይ ከመድረክ ውጪ ሌሎቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እራሳቸውን ችለው በተናጠል ድርድር መደረግአለበት በሚል ስምምነት ላይ ደርሰዋል።

በዚህ አጀንዳ ላይ መድረክ የተለየ ሃሳብ አንፀባርቋል፣ ከኢህአዴግ ጋር የሚደረገውን ድርድር 21ዱን ፓርቲዎች ወክሎ መድረክ ቢመራው ጥሩ እንደሚሆን ሃሳብ ያቀረበ ሲሆን፣ ሃሳቡ በሌሎች ፓርቲዎች ተቀባይነት አላገኘም።
መድረክ «ከሌሎች ፓርቲዎች የተለየ አጀንዳ ስላለኝ ለብቻዬ ቅድሚያ ተሰጥቶኝ ከኢህአዴግ ጋር ድርድር ማድረግ እፈልጋለሁ» ብሏል።
ኢህአዴግ በበኩሉ ድርድሩ በተናጠልም ሆነ በቡድን ቢሆን የሃሳብ ልዩነት እንደሌለው አስቀምጦ፣ነገር ግን ውይይቱ በተናጠል የሚደረግ ከሆነ ተመሳሳይ አጀንዳ ላይ ሁሉም ፓርቲዎች በጋራ እንደሚደራደሩና የተለየ አጀንዳ ያለው ግን ለብቻው በስተመጨረሻ ድርድር ማድረግ እንደሚችል አስታውቋል።
መድረክ «አንገብጋቢና አጣዳፊ አጀንዳ ስላለኝ ከዋና ድርድሩ ጎን ለጎን ከእኔ ጋር ድርድር ሊደረግ ይገባል» በሚል ኢህአዴግ ባቀረበው ሃሳብ በተለይ «የግል አጀንዳ ያለው በስተመጨረሻ ድርድር ያደርጋል» የሚለውን ሃሳብ ሳይቀበለው ቀርቷል።
በዚህ አጀንዳ ላይ የነበረው ውይይት በተናጠል ይደረግ ወይም በጋራ ግልጽ ያለ መግባባት ላይ ሳይደረስ ወደ ሌላ አጀንዳ ታልፏል።
ከሰዓት በነበረው ውይይት ደግሞ «ፓርቲዎቹ ከኢህአዴግ ጋር የሚያደርጉት ድርድር በገለልተኛ ይመራ ወይስ እራሳቸው ፓርቲዎቹ በየተራ ድርድሩን ይምሩት» በሚለው አጀንዳ ላይ ውይይት ተደርጓል። በዚህ ሃሳብ ላይ አብዛኛው ተቃዋሚ ፓርቲ ድርድሩን ገለልተኛ የሆነ አካል ይምራው በሚል የተስማማ ሲሆን፣ ኢህአዴግ ግን ድርድሩን በየተራ በሁሉም ፓርቲዎች መመራት አለበት የሚል አቋም ይዟል።
ኢህአዴግም ድርድሩ ለአገር የሚበጁ ጉዳዮች ተመርጠው በጉዳዮቹ ላይም ሁሉም ፓርቲ ሃሳብ እየሰጠ መድረኩም በምርጫ በሚሰየሙ ሰዎች መመራት እንዳለበት አመልክቷል። ነገር ግን ሁሉም ፓርቲዎች የሚፈልጉትን ታዛቢ ማምጣት እንደሚችሉ አስቀምጧል። ያቀረበውም ሃሳብ የማይለወጥ መሆኑንም አስምሮበታል።
ኢህአዴግ ባቀረበው ሃሳብ ላይ የኢዴፓ ተወካይ እንዳሉት፣ ሃሳቡን ለመቀበልና ላለመቀበል ሁሉም ፓርቲዎች ከአባሎቻቸው ጋር ውይይት እንዲያደርጉ ዕድል እንዲሰጥ እንዲሁም ኢህአዴግ ሃሳቡን በድጋሚ የሚያይበት ነገር እንዲኖር ጠይቀዋል። ሰማያዊ ፓርቲ በበኩሉ ድርድሩን ገለልተኛ አካል የማይመራው ከሆነ እራሱን እንደሚያገል አቋሙን አሳውቋል። የተቀሩት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ግን በሃሳቡ ላይ ከአባሎቻቸው ጋር ውይይት አድርገው ለመምጣት ተስማምተዋል።
በኢህአዴግና በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል የሚደረገው ውይይት ለመጋቢት 20 ቀን 2009 ዓ.ም ኢህአዴግም ሆነ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በአጀንዳዎቹ ላይ የመጨረሻ የሚሏቸውን ሃሳቦች ይዘው ለመምጣት በቀጠሮ ተለያይተዋል። addiszemen

 

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy